/Ethiopia Nege News/:- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የታሰሩት ኤልያስ ገብሩና ዳንኤል ሽበሺ ክስ ሳይመሰረትባቸው ከስድስት ወራት በላይ በፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ። ኤልያስ ገብሩ፣አናኒያ ሶሪና የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አመራር ዳንኤል ሽበሺ ባለፈው ህዳር ወር በኮማንድ ፖስቱ ትፈለጋላችሁ በሚል ለእስራት መዳረጋቸው የሚታወስ ሲሆን አናኒያ ሶሪ ከአራት ወር እስራት በኋላ ክስ ሳይመሰረትበት በዋስ ተፈቷል።
ኤልያስ ገብሩ የሳይነስ ታማሚ ሲሆን በእስር ቤት ህመሙ እየበረታበት በመሄዱ ምክንያት ለተጨማሪ ህክምና የካቲት 12 ሆስፒታል ሪፈር ተፅፎለት ከ15 ቀን በፊት ወደ ሆስፒታሉ ያቀና ቢሆንም በቂ ህክምና እንዳላገኘ ከቅርብ ጓደኞች በተገኘ መረጃ ማወቅ ተችሏል።
ትናንት ዶይቼ ቬለ እንደዘገበው ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒሥትር ሀይለማርያም ደሳለኝ የአቤቱታ ደብዳቤ መፃፋቸውን ዘግቧል። የዶይቼ ቬለ ወኪል ያነጋገረው የተጠርጣሪዎቹን የስራ ባልደረባ፤ ጋዜጠኛ ኤልያስ እና አቶ ዳንኤል የጤና እክል እንደገጠማቸውና ተገቢውን የሕክምና ክትትልም አለማግኘታቸውን ተናግሯል።