መነገር ያለበት ቁጥር 11
እኔ ምን አገባኝ – የምትሉት ሃረግ
እሱ ነው ያረዳት – ሃገሬን እንደ በግ
የምትለው ግጥም – ልጽፍ አሰብኩና
ምንአገባኝ ብዬ – ቁጭ አልኩ እንደገና
ኑረዲን ኢሳ
እነሆ እኛም “እነዚህ ሰዎች” እያልን፣ እየተማረርን አንዳንዴ ከሕዋ እንደ መጡ ሰዎች እየተመለከትናቸው፣ ሲደላን አብረናቸው ለመስራት ስንሞክር፣ ሲከፋን ትግሉን ጥለን እየሸሸን ስናማ ፣ ስንቀማጠል በውጭ ሃገር በድረገጽ፣ በፌስቡክ፣ በቲዊተር ትግሉን እኛ ነን የምንመራው ስንል፣ ሲሰለቸን እጃችንን አጥፈን እየተቀመጥን፣ እነርሱን መታገል ሳንችል ስንቀር ከራሳችን እየታገልን ስንከፋፈል፣ ስንፈራ አጠገባችን ያለው ጠላት አድርግን ስንወጋ፣ ሃገራችንን ቀስ በቀስ ሲፈራርሷት አብረን እያፈረስን ሦስተኛው ዓሥርተ ዓመታት ዋዜማ ላይ ደርሰናል። ዛሬማ ብለን ብለን የወያኔን የዘር ፖለቲካ እኛው በመድገም አሳፋሪ ዜጋዎች ሆነን እንገኛለን።
በዚህ ውጣ ውረድ በበዛበት ትግል ውስጥ መለስ ብለን ወደ ኋላ ስንመለከት ከነ ሙሉ ድክመቱ ሀገራችን እስካሁን እንደ ሃገር እንድትቆም የቻለችው ታመነም ተካደም በአንድነት ኃይሉ ብዙ መሰዋትነት መሆኑን እንገነዘበዋለን ። እንደ ወያኔም ሆነ የወያኔ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ዘረኞች ቢሆንማ ኖሮ ኢትዮጵያ ፈርሳ እንደ ሶቬየት ሕብረት ፣ እንደ ዩጎዝላቢያ ፣ ለታሪክ ብቻ ቀርታ ነበር ።
የአንድነት ኃይል ስንል ፖለቲከኞችን ብቻ የሚጠቃልል የሚመስላቸው ጥቂት አይደሉም። የአንድነት ኃይል እንደኔ የዘር ፖለቲካ ወደፊት ሊያመጣ የሚችለውን የእርስ በርስ እልቂት ተገንዝቦ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር እንድትቀጥል የሚሠራውን(የሚያምነውንም ጭምር) ሁሉ ነው። በተለይ በዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያዊነት በማጉላት የስነ ጥበብ ሰዎች ያደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽዎ የሚረሳ አይደለም።
ዛሬ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት መናገር፣ መሟገት ብዙ ችግር ያለበት ውስብስብ ጉዳይ ሆኖ ይስተዋላል። ለኢትዮጵያ መቆም በሁለት ስለታማ ጎራዴ መሐል የቆመ ተስፋ ይማስላል። እነዚህ ሁለት ስለታማ የአንድነት ጠላቶች በአንጻራዊ ዓይን ሲታዩ ልዩነት ያላቸው ይምሰሉ እንጂ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆናቸው አሁን አሁን ይፋ እየወጣ መጥቷል። ወያኔና ከወያኔ በተቃራኒ የቆሙ በሚመስሉ ነገር ግን የወያኔ የዘር ፖለቲካ ድርብ አልባሽ ሆነው በቆሙ አስመሳይ ተቃዋሚዎች ስውር ደባ ሳቢያ፣ በአንድነት ኃይሉ ላይ የደረሰበት የተቀነባበረ ሴራ የሐገር ፍቅሩ ቡድን (የአንድነት ኃይል) ወደ መዳከምና መፈራረስ እየገፋው እንደሆነ ይስተዋላል። የአንድነት ኃይሉ እነዚህ ድርብ ጠላቶቹ በሚፈጸሙበት ገደብ የለሽ ግድያ፣ እስር ፣ ድብደባ፣ ወከባና አፈና፣ ስድብ፣ ውርደትና ስደት ዛሬ ተዳክሞ ይገኛል።
የአንድነት ኃይሎችም በተለይም ምሁራኑ፣ በቦዘኔ የዘር ፖለቲከኞችና በለየላቸው ወያኔዎች በሚደርስባቸው መረን የለሽ ጋጠ ወጥ ስብዕናን የሚዋርድ ዘለፋና ስድብ ምክንያት “እኔ ምን አገባኝ” በማለት ትግሉን እንዲሸሹ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል። ደፍረው ታሪክን ያስተማሩ ምን እንደሚደርስባቸው በቅርብ ያየነው ነው። (አስረጅ – ፕሮፌሰር ሃይሌ ላሬቦ ላይ የደረሰው ስድብና ውርደት ማስታወስ በቂ ነው።)
የአንደነት ኃይሉ ይህንን የተቀነባበረ የጸረ ኢትዮጵያ ሴራ በመፍራት ትግልን ትቶ ማፈግፈግና ምን ያገባኛል ብሎ መቀመጥ ከታሪክ አለመማር ነው የሚሆነው። በደርግ ዘመን ቀበሌዎች እንደተቋቋሙ ምሁራን በቀበሌዎች በመመረጥ ለሃገር ለመስራት ተነስተው ነበር ። ነገር ግን በተፈጠረው ሁኔታ ምሁራን ሲሸሹ ቦታውን ቦዘኔ አብዮት ጥበቃዎች በመያዛቸውም በየቀበሌው የተደረገው ጭፍጨፋ ትምህር ሊሰጥ በተገባ ነበር ። ዛሬ የአንድነት ኃይሉ በደረሰበት እጥፍ ድርብ እርብርቦሽ ሳቢያ ወደ ኋላ በማፈግፈጉ ሃላፊነት የጎደላቸው በእኔ አባባል የጎሣ መሣፍንቶች ተተክተዋል። ይህ ደግሞ የሚመጣውን መገመት ከተሳነን ከታሪክ የማንማር ነን ማለት ነው ።
የጸረ ዘረኝነት ትግሉ እያደር ከድጡ ወደ ማጡ እየገባ እንደሆነ ያደባባይ ሚስጥር ነው። በፀረ አንድነት ክፍሎች በሚደረግበት ሃይለኛ ግፊትና ተጽዕኖ ብቻ ሳይሆን ከራሱም በውስጡ ከሚነሳ የወንበር ሽኩቻ ጭምር ራሱን በራሱ አዳክሞታል። ዜጎች ድርጅቶችን ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ በማለት በየስብሰባው ሲጠይቁ ቆይተዋል። አሁንም ከመጠየቅ አላባሩም። ሆኖም ግን የድርጅት መሪዎች ከመተባበር ይልቅ መሰባበርን ምርጫቸው ያደረጉ ሆነው ይታያሉ። በአሁኑ ወቅት ከአንጋፋ ድርጅቶች እስከ አዳዲሶቹ ከስም በስተቀር በተግባር አይታዩም ። ትግሉን የመምራት አቅም ተስኗቸው ቦታውን ለአዳዲሶቹ መሳፍንቶች ቀስ በቀስ እየለቀቁ ነው ።በአንድነት ጎራ ያሉ ድርጅቶችም ይሁን ምሁራን ቦታውን ለአዳዲስ መሳፍንቶች በዘመኑ አጠራር አክቲቪስቶች ለሚባሉ ለቀው ጥግ ጥግ ይዘው መታዘብን መርጠዋል።
እነዚህ የጎሳ አክቲቪስቶች ራሳቸውን በአማራጭ ሃይልነት መድበው ወያኔን ለመተካት ተስፈኞች ሆነው በመጠባበቅ ላይ ናቸው። በሌላ በኩል ወያኔ ቀባሪ ያጣ በቁም የሙት መንፈስ ሆኖ በነውጥ ማዕበል እየተወዛወዘ ነው። ከገባበት አዘቅት ለመውጫ መላ የዘየደ መስሎት የሕዝብን ጥያቄ ባግባቡ እንደመመለስ ፈንታ በጊዜያዊ አስቸኳይ አዋጅ ጠፍንጎ አስሮ እንዳሻው ዜጎችን ማጎሳቆልና ማሰቃየትን መርጧል።
ባለፈው ጊዜ ጉዞ ወደ ዘመነ መሣፍንፍት በሚል ርዕስ ጽፌ ነበር ። ያኔ እንደ ዛሬው መሣፍንቶቹ ሁሉ ጎልተው ባልታዩበት ወቅት ስለነበር ምናልባት ትንቢታዊ መልዕክት ይመስል ነበር ። ብዙዎችም መሳፍንቶቹ የት አሉ? ብለው የጠየቁ አሉ ። እንደ ድሮው ዘመን ደጅአዝማች፣ ቀኝአዝማች፣… ወዘተ አይባሉ እንጂ የሚመጥናቸው የዘመኑ መጠሪያ ስም ይዘው በመገናኛ ዘዴዎች ( ፌስ ቡክ ፣ ቲውተር ፣ ድረገጽ ) ውስጥ ሕዝብን ( በተለይ ወጣቱን ) ሲያምሱት ይታያሉ። ሁሉም እንደየ ባህሪያቸው የየራሳቸው አንጋች ሎሌና ተከታይ አላቸው ። እነዚህ የዘር ፖለቲካ የፈለፈላቸው አጉራ ዘለል መሣፍንቶች ባመዛኙ “አክቲቪስት” የሚል መጠሪያቸው ሆኗል። የአማራ አክቲቪስት፣ የኦሮሞ አክትቪስት ፣ የጎጃም አክቲቪስት ፣ የጎንደር አክቲቪስት፣ የአፋር ፣ የሶማሌ …ወዘተ። እነዚህ አክቲቪስቶች (የዘመኑ መሳፍንቶች) የራሳቸው የሆኑ ደጋፊዎችና ጀሌዎች በውጭም፣ በውስጥም ሃገር አሏቸው። እነዚህ ጀሌዎች በፌስ ቡክ ፎሎወርስ (followers) ይባላሉ። እንደ ደጋፊዎቻቸው ብዛትና ዓይነት የአክቲቪስቶቹ ትልቅነት ፣ የፖለቲካ ተንታኝነት ፣ በየመድረኩ የመጋበዝ፣ ቃለ መጠይቅ የመስጠት እናም የነዋይ ጉዳይም ጭምር ይወሰናል። ይህንን ለመታዘብ የፈለገ ወደ ፌስ ቡክ ብቅ ማለት ብቻ ይበቃዋል። የሚያጸይፍ ስድብ፣ ሕዝብን የሚከፋፈሉ ንግግሮች ፣ ስብዕናን የሚያጎድፉና በተለይም የዜጎችን ማንነት የሚያዋርዱ ጽሁፎች ማንበብ የተለመደ ሆኗል። በተለይ ወጣቱ ከፌስ ቡክ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ በእነዚህ ዘመናይ መሣፍንቶች በቀላሉ ይጠመዳል፣ ይከፋፈላል፣ ይሰዳደባል። ጎበዝ ይህ ትኩረት ተሰጥቶበት ከወዲሁ ሊቆምና ልንቆጣጣረው የሚገባው አፍራሽ ፀረ ኢትዮጵያ ተግባር ነው። አለበለዚያ ግን ለወያኔና የኢትዮጵያን አንድነት ለማይፈልጉ ክፍሎች እንዳሻቸው መፈንጫና ለጥፋት ተልእኳቸው ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ ማገልገሉን ይቀጥላል።
ዛሬ ተደራጅቶ መታገል ጊዜው “ያለፈበት” ተብሎ በመታመኑ ማንም ከማንም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ራሱን አጣምሮ መገኘት ሞኝነት መስሎ ይታያል። በዚህ ዘመን አክቲቪስት ሆኖ መገኘት ከብዙ ውጣ ውረድ ያድናል፣ ከተጠያቂነት ያስመልጣል፣ በነዋይ ያበለፅጋል፣ በቶሎ ለመታወቅ አቋራጭ መንገድ ነው። አክቲቪስት ለመሆን ብዙ ድካም አይጠይቅም ። በቀላል ሊገኝ የሚቻል ሹመት ነው ። ጥሩ ምላስ ካለ በቂ ነው። የታወቀ ድርጅት ወይም የታወቀ ግለሰብ መስደብ፣ ወይም በሃገር ወሳኝ አጀንዳ ላይ ገብቶ መፈትፈት ራሱን ችሎ አክቲቪስት ያሰኛል። ጠንክሮ ለተሳደበ ወይም ሕዝብን ለከፋፈለለ እስከ የአፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ተንታኝነት ሊደርስም ይችላል። ኧረ ከዛም በላይ ሳያስኬድ ይቀራል ብላችሁ ነው?
እነዚህ አክቲቪስቶች ልብ ብሎ ላስተዋላቸው ለሃገራችን ችግርና መፍትሄ የሚሰጡት ትንተና የሚገርም ነው። ባመዛኙ ሲፈተሽ ወያኔ እየከፈላችው ሃገርን የሚከፋፍልና የእርስ በእርስ ጦርነት የሚጭር የቱሪናፋ ወሬ ሆኖ እናገኘዋለን። ግን ደግሞ ዘርን የተመረኮዘ ስለሆነ ብዙዎችን ያማልላል። ሌሎችን እንደ ጠላት እንዲመለከቱ ያደርጋል።በተለይ በአሁኑ ወቅት ሕዝብን ማስተማር የሚችሉ ምሁራን ከትግሉ በመሸሻቸው ምክንያት በየፌስቡኩ ፣ በየድረ ገጹ የሚበተነውን መርዝ ለመመርመርና ወጣቱን ለማስተማር፣ ተንኮሉን ለአዳዲስ ወጣቶችን ለማስረዳት የሚችል ተቆርቋሪና ደፍሮ የወጣ የልሂቃን ወገን የለም። አንዳንዶች እንኳን ቢሞክሩም ከላይ እንደጠቀስኩት ስብዕናን የሚነካ አዋራጅ ስድብ ይደርስባቸዋል። ጎበዝ እስከመቼ ነው ይህንን እያየን ዝም የምንለው ? ሃገራችን እስከምትፈርስ ? የእርስ በእርስ ጦርነት እስከሚነሳ ?
“ባለጌና ዋንጫ ከወደ አፉ ሰፊ ነው” እንዲሉ፣ ለአብነት ያህል አንድ የኦሮሞ አክቲቪስት ሰሞኑን ብዙዎቻችንን በእሱ አስተሳሰብ ሃገር አልባ አድርጎናል ። ይህ የዘመኑ “ሊቅ” አማራ በአማራ አክቲቪስቶች ሥር በመሰባሰቡ ምክንያት ኢትዮጵያ የሚሉ የአንድነት ሃይሎች ወይም ድርጅቶች በሙሉ ሃገር የሌላቸው (ሆም ለስ)ፖለቲከኞች (homeless politicians) ሆነዋል ብሎ ከኢትዮጵያ ፈንቅሎ ጥሎናል። በዚህ ብቻ አላበቃም የዚህ ዘረኛ አባባል በሌሎች ዘረኞች የአማራ አክቲቪስት ነን የሚሉም ጭምር ተደንቋል። የእከከልኝ ልከክልህ ፖለቲካ ይመስላል።
በሃምሌ የሚያብድ በሰኔ ጨርቁን ከፍ ከፍ ያደርጋል” እንዲሉ ሌላው የአማራ አክቲቪስ ነኝ ባይ ደግሞ የኢሕአፓ አባላት የነበራችሁ በሙሉ ኢሕአፓ በደርግ ዘመን ፀረ አማራ ስለሆነ ዛሬ ወያኔን የመቃወም መብት የላችሁም ብሎ ብዙዎችን ከትግሉ እንዲወጡ ሲስብክ ተደምጧል። ለነገሩ ግለሰቡ በቅርቡ ትግሉን በወያኔ ትዕዛዝ የተቀላቀለ ነው የሚመስለው። መረጃ ብሎ ከወያኔ የሰበሰበውን ወረቀት ሲበትን እንደነበር ብዙዎቻችን የታዘብነው ነው። ይኸው አክቲቪስት ሲከፋው የጎጃም ነጻ አውጪ አክቲቪስት፣ ሲደላው የአማራው አክቲቪስት ሆኖ ይገኛል። ወያኔ ቤት ገባ ወጣ ማለቱ እንዳለ ሆኖ። ይህ አክቲቪስት ስለ ሃገራችን የእስልምና ሃይማኖት የጻፈውን ላነበበ ምን ያህል የወያኔ ተልዕኮ እንዳለው መረዳት ከቶ አያዳግትም። የሃይማኖትም ይሁን የዘር ፖለቲካ ተነስቶ የእርስ በእርስ ጦርነት ቢከፈት ምን ቸግሮት? ዓላማው እንደ ሌሎቹ ሁሉ ወያኔ አለያም ሌሎች ወያኔን መሰል ብረት ለበስ ፀረ- አንድነት ሃይሎች የሰጡትን ተልዕኮ ማሟላት ነው። ለእሱ የትም ፍጭው ንዋዩን አምጭው ነው መፈክሩ።
ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰቆቃ ያራዘመው አክቲቪስ በለንደኑ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ጉባዔ ላይ “ኢትዮጵያን እናፈራርሳታለን” በማለት ጮቤ ሲረግጥ የነበረው አክቲቪስት ነው ። የኦሮሞ ሕዝብ እየተገደለ ባለበት ወቅት ሁሉም ዜጎች ከኦሮሞ ሕዝብ ጎን በመቆም ወያኔን ባጣደፉበት ሰዓት ለወያኔ ታላቅ ጥቅም ያስገኘ አክቲቪስት መሆኑን ከቶ መዘንጋት አያሻም። ከወያኔ የተሰጠው ተልዕኮ መሆኑን የሚጠራጠር ካለ ህሊናውን የሳተ ብቻ ነው። የአትላንታው የኦሮሞ አክቲቪስቶች ጉባኤም ቢሆን የኦሮሞን ሕዝብ በሦስት ከፋፍሎ ከመሄድ ባሻገር አንዳች ያስገኘው ጥቅም የለም ።
ስለ አክቲቪስቶች መጻፍ ከተጀመረ ብዙ መጻፋችን አይቀርም። መለስ ብለን ስለ ጎንደር አክቲቪስቶች ብናወራ ደግሞ ወያኔ ቤት መለስ ቀለስ ባዬች ሁሉ ተመልሰው በጎንደር አክቲቪስትነት ሰም ትግሉ ሲቀላቀሉ አስተውለናል። ከወያኔ ጋር ሲሰሩ የከረሙ ሁሉ ዛሬ በጎንደሬ ስም ወደ ጎንደር ሕብረት ለመጠጋት መሞከራቸው ብቻ ሳይሆን “ከኔ ወዲያ ፉጨት አፍን ማሞጭሞጥ ነው” ሲሉ ይስተዋላሉ። መለኪያው ጎንደሬነት እስከሆነ ድረስ ማንም ሊከለክላቸው አይችልም። የጎንደር ሕብረትም ለዚም ምንም መከላከያ ያዘጋጀም አይመስልም።
ጥያቄው የአክቲቪስቶች ብዛት ይህችን ሃገር ከወያኔ መንጋጋ ያላቅቃታል ወይ ? ነው።
ይህ የአክቲቪስቶች ብዛት የወያኔን እድሜ ማራዘሚያ ወይም በሃገር ውስጥ ለእርስ በርስ ጦርነት በር ከፋች ብቻ ሊሆን ነው የሚችለው ። እኔ በበኩሌ ሃላፊነት ከሚሰማቸው የፖለቲካ ድርጅት በተናጠል መረን በተለቀቁ አክቲቪስቶች በሚደረግ አጉራ ዘለል ትግል ነጻነት ይገኛል ብዬ አላምንም ። ምንም እንኳን መፈክሩን ቀይረን አክቲቪስቶች ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ ብንልም እንኳን አክቲቪስት ተብዮዎቹ መተባባር ቀርቶ የያዙትንም አቋም ረዥም ርቀት ይዘው መጓዝ ተስኗቸው ከርሞ ጥጃ ሲሆኑ እየተስተዋለ ነው ። ዛሬ በኢትዮጵያ አንድነት ስም ዋይ! ዋይ! ሲሉ ይውሉና ነገ ደግሞ በዛው በለመደ አፋቸው ጉድ አማራ! ጉድ! ጉድ! ይላሉ። እንዲሁ ሌላ ጊዜ ደግሞ አኒ ባዴ! ባዴ! ኦሮሞን! ሲሉ ይገኛሉ ። ዛሬ የደገፉትን የፖለቲካ ድርጅት በማግስቱ አፈር ከድሜ ሲያገቡት ይታያሉ ። ዛሬ የያዙትን አቋም ነገ በሌላ ርዕስ በሌላ አጀንዳ እንደ ሸሚዝ ይቀይሩታል። ትላንት ኢትዮጵያዊ በሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የነበሩ ዛሬ ተከልስው የዘር ድርጅት አንጋችና አዝማች መሆን እንዴት ቀላል እንደሆነ ትልቅ ማሳያ ናቸው። … አፈርንባቸው እንጅ በእጅጉ!
እኛ ሁሌም እኛ ነን። አዲስ ሲመጣ ብዙ ነገር እንጠብቃለን፣ የነፈሰው አየር ይዞን ይነጉዳል፣ ከረፈደ መባነን ልማዳችን ነው። የጠመጠመ ሁሉ የሚቀድስ፣ የጮኸ ሁሉ የሚነክስ ይመስለናል። አዲስ የሆነ ሁሉ የሚያማልለን፣ በጥቅሉ አዲስ የሆኑ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ይመስለናል ። ድጋፋችንን ገንዘባችንን ሳይቀር እንገፈግፋለን ። ሲሳደቡ አብረን እንሳደባለን ፣ ሲሰደቡ ቀድመን እናለቅሳለን፣ ስድባቸውንና ዘለፋቸውን ተሽቀዳድመን እንደ አማኑኤል ጸበል እንረጫለን፣ እንዲያውም ለስድባቸው መልስ ይሰጣቸው ብለን እንጨቃጨቃለን ። ለመሆኑ ለማነው መልስ የሚሰጠው ? ለወያኔዉ አንጋች ? ለዘር ፖለቲካ አቀንቃኝ?
ለመሆኑ ለእነዚህ የወያኔን ተልዕኮ ለሚያራምዱ ዘረኞች መልስ መስጠትና አተካሮ መግጠም ያስፈልጋልን? ነው ጥያቄው ። በዚህ ጊዜ ማጥፋትን አጀንዳውን ለመቀየር በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ መጠመድ አስፈላጊ አይደለም ። አሁን ግን ትግሉ፣ ትንቅንቁን ከወያኔ ቀይሮ ወደ እርስ በርስ በእርስ ንትርክ መቀየር ለወያኔ ከመቆም አይተናነስም።
ይህ ሊያከትም የሚገባው ሃገርን የማፈራረስ ተግባር ነው ። ትላንት የኢትዮጵያ አንድነት የሚለው የአንድነት ጥያቄውን ትቶ በዘር ድርጅት ሲደራጅ፣ ከራሱ ዘር በቀር ለሌሎች ለተበደሉ ኢትዮጵያውያን መቆም አይቻለውም። አበቃ። ምን በቃላት ቢያሳምሩት ምን በንግግር ቢሽቆጠቁጡት የማይሆን ነገር ነው።
ጎበዝ ኢትዮጵያን የሚሉ ምሁራንንና የሥነ ጥበብ ሰዎችን ማዋረድ ፣ መስደብ ዝም እንዲሉ ማድረግን ሁላችንም በአንድነት ቆመን መታገል አለብን። እውነተኛ ታሪክን ለሚያስተምሩ ታላቅ ክብር ልንሰጥ ይገባል። ለእነዚህ ለአንድነት ለቆሙ ምሁራን የሬዲዮና የድረገጽ መድረክ ማዘጋጀታቸንን ትተን ለከፋፋይ አክትቪስቶችና ጥራዝ ነጠቅ የታሪክ “ምሁራን” የምናሸረግድ ከሆነ ይህቺን ሃገር በቅርብ እናጣታለን ። በተለይ ኢሳት ከዚህ ብዙ ሊማር ይገባዋል። ስለ ሃገር አንድነት የሚዘፍኑ አርቲስቶችን ማክበር ካልጀመርን ሆዳም አቀንቃኞች ቦታውን ይሞሉታል። ወያኔ ደርሶ የሚመለስውን አንቱ ብለን ካሞካሸንና ለረጅም ዘመናት ቆርጠው ወያኔን የታገሉትን ካዋረድን ይህቺን ሃገር እናጣታለን ። የአንድነት ኃይል የሆኑ ድርጅቶችን ካፈረስን ዘረኛ አክቲቪስቶች ቦታውን ይቀራመጡታል። በስልጣን ጥም ድርጅቶችን የምንከፋፍል ከሆነ ሃገራችንን እናጣታለን።
ጎበዝ የሃገራችን የወደፊት ዕጣ በእኛ እጅ ወድቋል ። ሃገሪቷም አስጊ ሁኔታ ላይ ነች። በንዋይ የሰከሩ ወያኔዎች ይህችን ሃገር ሊመሯት እንደማይችሉ የተረጋገጠ ነው። ዛሬ እኔ ምን አገባኝ የሚለው አባባል ያለ ጥርጥር ሃገር ያሳጣናል ። ለሠራነው ብቻ ሳይሆን ላልሰራነውም በታሪክ መጠየቃችን አይቀርምና መለስ ብለን ሃገራችን ከገባችበት አደጋ ለማታደግ ያለማመንታት መታገል አለብን።
ሰለ ሃገራችን በጎ የሚያስብ ሁሉ በሰላም ይክረም !
08/05/2017