የወልቃይት ጠገዴ ትግል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ትግል ነው – ክፍል ሁለት /ዶ/ር አክሎግ...

የወልቃይት ጠገዴ ትግል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ትግል ነው – ክፍል ሁለት /ዶ/ር አክሎግ ቢራራ/

የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት ምሽት

ለችግሩ መፍትሄ አለ ወይንስ የለም?

በጎንደሬውና በሌላው የአማራ ብሄር ላይ የሚካሄደውን በህወሓቶች የተቀነባበረ እልቂት አግባብ ባለው መልክ አገናዝቦ መፍትሄ ለመሻት የሚቻለው የችግሩን መንስኤ በማወቅ ነው። መንስኤው ህወሓት የአማራውን ሕዝብ “የትግራይ ሕዝብ መደበኛ ጠላት ነው” ብሎ የትግራይን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ሌላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማሳመን መሞክሩ ነው። ሌላው ይህን እቅድ ስኬታማ ለማድረግ በማሰብ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ በቋንቋና በብሄር ከፋፍሎ ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲጋጭ ለህወሓት አመቻች የበላይነት ሁኔታዎችን መፍጠሩ ነው። የዚህ ውጤት የመሬት ነጠቃ፤ የሚዘገንን ጭፍጨፋ፤ አግላይነትና የሰብአዊ መብቶች ገፈፋን ይጨምራል። ባለፉት 26 የህወሓት/ኢህአዴግ ዓመታት፤ የዚህን መከራ አንበሳ ክፍል የተሸከመው ጎንደሬውና ሌላው የአማራ ሕዝብ ነው።

በመሬት ላይ ሲታይ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተቃዋሚ ታስሮ የመሰቃየት እድሉ ከፍ ያለ ነው፤ በተለይ የአማራውና የኦሮሞው ሕዝብ። በቃሊቲና በመአከላዊ እስር ቤቶች የሚሰቃየው ወልቃይቴና ሌላ ጎንደሬ  ብዙ ነው። ወያኔዎች ጡንቻችንን ቅመሱት በሚል እብሪት፤ እነዚህንና ሌሎችን የፖለቲካ እስረኞች ከግድግዳ ጋር አጣብቀው ያሰቃያሉ። ከጩኸት ውጭ ማንም የውጭ ኃይል አልደረሰላቸውም። ልጨምረው የምፈልገው አስኳል ጉዳይ ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ልኡል ሃሳን ተቋሙ በኦሮምያና በአማራ ክልሎች የተፈጸመው የመንግሥት ጭካኔና እልቂት በድርጅቱ ራፖርተሮች “መመርመር አለበት” ያሉት የአቋም ውሳኔ ነው። የህወሓት/ኢህአዴግ ገዢዎች ይህን ሃሳብ እንደማይቀበሉ መገመት አለብን። የተቀነባበረ ጫና ማድረግም ግዴታችን ነው።በየትኛውም ኢትዮጵያ ቢኖር፤ የአማራው ሕዝብ ቤቱም ሆኖ ሰላምና እርጋታ አግኝቶ አያውቅም። መሬቱን ተነጥቆ ይሰደባል። ሰብአዊ መብቱን ተገፎ ይገረፋል፤ በገፍ እንዲሰወርና እንዲሰደድ ይገደዳል። ተስፋ የሚሰጡ የአማራ ብሄር ወጣትና ሌሎች መሪዎች ወያኔ በፈጠራቸው “የሲዖል እስር ቤቶች” ይሰቃያሉ (Torture)። ሃብታሙ አያሌው የዚህ ግፍ ምስክር ነው። ህወሓቶች የኢትዮጵያን ሕዝብ ባጀት እየተጠቀሙ “ከእኛ በላይ የተደራጀና የታጠቀ ኃይል የለም” ይሉናል። ሌላውን ሕዝብ አግልለው ለጥቂት የትግራይ ተወላጆች በህልማቸው ለማሰብ የማይችሉትን ገቢ፤ ኃብትና ንብረት አበርክተዋቸዋል። ለዚህ የኢኮኖሚና የተፈጥሮ ኃብት የበላይነት ዋና ምሳሌ EFFORT ተብሎ የሚጠራው የህወሓት ቤተሰቦች የግል ድርጅትና ኃብት ነው። ይህ ብዙ ቢሊየን ዶላር ካፒታል ያካበተ ተቋም ኃብቱን እንዴትና ከማን እንደሰበሰበ ብዙ ዘገባዎችና መረጃዎች ስላሉ አልፈዋለሁ።

በመረጃ ፈጠራ የሰለጠነው ህወሓት ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት እጥፍ አሃዝ እድገት አሳይታለች ብሎናል። በዚህ አንደነቅ። የመረጃ ማጭበርበር የህወሓት ስልት ነው። እንደ ዓለም ባንክ፤ አይ ኤም ኤፍ፤ የአውሮፓ የጋራ ማህበር ያሉ ድርጅቶች የሚጠቀሙት ይኼን የተሳሳተ መረጃ) ነው።  እርዳታው ማንን ለመጥቀም? ብለን ብንጠይቅ፤ የሚደግፉትንና አገልጋያቸው የሆነውን ቡድን፤ ራሳቸውንና ለእነሱ የሚሰሩ አማካሪዎችን ለመጥቀም ነው። ያለዚህ ድጋፍ ህወሓት ቀፎ ነው፤ ደፋርም አይደለም፤ አስቸኳይ አዋጅ አያውጅም ነበር።

እርዳታንና የዲፕሎማቲክ ድጋፍን በሚመለለከት፤ ለጋስና አበዳሪ ድርጅቶች ተሳስተዋል። የኢትዮጵያን ሕዝብ በድለዋል ለማለት እደፍራለሁ። አንድ ምሳሌ ላቅርብ። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተዛባ ገቢ፤ ኃብትና ኑሮ በግልጽ ይታያል። ባላቸው በጥቂት የህወሓት አባላት፤ የትግራይ ተወላጆች፤ ደጋፊዎቻቸውና በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ያለው የገቢና የኑሮ ልዩነት ለኢትዮጵያ አደጋዎችን ፈጥሯል። አብዛኛው የእድገት ውጤት፤ የተፈጥሮ ኃብት እና የኢትዮጵያ ዘመናዊ ኢኮኖሚ በህወሓቶች፤ በምርጥ ትግሬዎችና በታማኝ ግለሰቦች ቁጥጥር ስር ነው ተማርኳል። ፖለቲካውና ኢኮኖሚው በሕግ የበላይነት አይሰራም። ስለዚህ ድህነት ሊጠፋ አይችልም።  እርጋታ አይኖርም።

ጎንደሬዎችና ሌሎች ለኢትዮጵያ ዘላቂነት ተቆርቋሪዎች የሆንን ሁሉ ማሰብ ያለብን የትላንቱንና የዛሬውን የሚዘገንን ሁኔታ ብቻ አይደለም። ነገ ምን ምን መረጃዎች፤ ምን አይነት ሰንዶች፤ ምን ምስክሮች ይዘን ታግለን ሌሎች እንዲታገሉበትና እንዲፋረዱበት እናደርጋለን የሚለውም ወሳኝ ነው። ህወሓት ዘላለማዊ አይደለም፤ ይወድቃል!!

የአጼ ቴዎድሮስ ዘላቂ ትምኅርት

ተቆርቋሪዎች የሆንን ሁሉ ቃል ኪዳን መግባት አለብን። የኢትዮጵያ ሕዝብ በባርነት ልኑር ብሎ ለህወሓት/ኢህአዴግ ቃል ኪዳን አልገባም” ለማለት እንድፈር!!  እኔን ጎንደሬው ያስተማረኝ ይህ ቆራጥና ደፋር ሕዝብ ለኢትዮጵያዊነት፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂነትና ሉዐላዊነት፤ አገር ወዳዱ ቴዲ አፍሮ እንዳሳሰበን፤ “ዋልታና ማገር” መሆኑን ነው። “ጎንደር ጎንደር የቴዎድሮስ አገር፤ የኢትዮጱያ አንድነት ዋልታና ማገር” እያለ ሲቀሰቅሰን” ማሰብ የሚኖርብን ኢትዮጵያ የሁላችንም መሆኗን ነው። ጎንደሬው በህወሓት ላይ ትግል የሚያካሂደው ማንነቱን ተቀብሎ፤ መብቱን አስከብሮ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ተባብሮ የኢትዮጵያን ዘላቂነት ለማስከበር ነው። በጎንደርና በሌሎች አካባቢዎች ህወሓቶችና አባሮቻቸው የፈጠሩት ሳይታሰብ ሊቀጣጠል የሚችል እሳትና ጭድ ሊጠፋ የሚችለው መሰረታዊ ችግሮች ሲፈቱ ብቻ ነው። ህወሓት ይህን ችግር ሊፈታው አይችልም። በእኔ እምነት፤ ሕዝብ ከተነሳ ምንም ኃይል እንደማያቆመው ባለፈው ዓመት አስመስክሯል። የእኛ ቃል ኪዳን ለሕዝቡ አጋርና  የለውጥ አምባሳደር መሆን ብቻ ነው። ልድገመው!!

በተጨማሪ፤ የሚከተሉትን የፖሊሲ አቅጣጫዎች ብናስብባቸውና ብንደጋገፍባቸው ታሪካዊ ግዴታችን የመወጣት እድላችን ከፍ ይላል የሚል እምነት አለኝ።

  1. ዛሬ በጎንደር ሕዝብ ላይ ወያኔ የሚፈጽመው ግፍ፤ ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ለተከታታይ ትውልድ የማይረሳ ወንጀል ነው። የታሪክ ጠባሳ ነው!!! ለመብቱ የታገለውና ወደፊትም የሚታገለው ሕዝብ ራሱን፤ ልጆቹንና ንብረቱን መስዋእት የሚያደርግበት ዋና ምክንያት የመሬት ነጠቃው፤ የሰብአዊ መብቶች አፈናውና እልቂቱ የህልውና ጥያቄ ስለሆነ ነው። ለወንጀሉ በሃላፊነት መጠየቅ ያለባቸው ህወሓቶችና ተባባሪዎቻችው ናቸው።
  2. ህወሓት የጎንደሬውንና የሌላውን አንጡራ መሬት ነጥቆ ከራሱ ከታላቋ ትግራይ ክልል ጋር ሲያቀላቅል በነዋሪዎቹ ላይ ወንጀል ፈጸመባቸው ብቻ ሳይሆን ነዋሪዎቹ እንዲደኸዩ፤ እንዲሰደዱ፤ እንዲሰቃዩ፤ ስንኩልና መካን እንዲሆኑ፤ መሪና ተከታታይ ትውልድ እንዳይኖራቸው፤ እንዲሞቱ አደረገ ማለት ነው። ይህ በዓለም ሕግ Crime Against Humanity ይባላል።

ይህን መከራ እንደምንወጣው አምናለሁ። ወሳኙ በአካባቢው የሚኖረው፤ የሚሰቃየው ሕዝብና የሚያደርገው የተቀነባበረ ትግል ነው። የጎንደሬውን ችግር በቅርብ የሚያውቀው ጎንደሬው ነው። በልዩ ልዩ ምክንያትና በድብቅ “የወያኔ መሳይ” ተልእኮ” አትደራጅ የሚል ጎንደሬ፤ ሌላ አማራና ኢትዮጵያዊ በመሬት ላይ የሚካሄደውን ግፍ አያውቀውም። አንድ ገበሬ፤ ቤቱንና ቤተሰቡን ትቶ “ራሴን መስዋእት አደርጋለሁ!! የኮሎኔል ደመቀ ትግልና መስዋእትነት የራሴ ነው!! ራሴን ከወያኔ መንጋጋ ነጻ ካላወጣሁ አገሬ ኢትዮጵያም ትፈርሳለች!! እኔም እንድጠፋ፤ አገሬም እንድትፈርስ አልፈቅድም” እያለ ሲነሳ አትደራጅ፤ ለመብትህ አትታገል የማለት የሞራል ብቃት የለንም። ልድገመው!!

ግዴታችን ምን እንርዳህ? እንዴት እንተባበርና እንዴት አብረን አቅማችን እናጠናክር? የሚል ነው። መከፋፈሉን ወያኔ እያደረገልን ነው!! ህወሓት “አንተ ቅማንት ነህ!! አንተ ቤተ ኢስራኤል ነህ!! አነተ አገው ነህ!! እያለ ይሰብካል፤ ይከፋፍለናል። ጎንደሬዎች በአብዛኛው አማራዎች ናቸው። አንድ ዓላማና አንድ ተልእኮ ነው የሚጠራቸው። ዋናው ስራቸው ራሳቸውን ከወያኔ አሰቃቂ ግፍና እልቂት ማዳን ነው!! ጎንደሬው ሆነ ሌላው የአማራ ሕዝብ የወላድ መካን አይደለም ማለት ግዴታው ነው። የሕዝቡ ጥሪ፤ የወላድ መካን፤ ሥስታምና ፈሪ ተተክቷል የሚል አይደለም!! የጀግናው፤ “የቋራው አንበሳ” የአጼ ቴዎድሮስ አደራ ይኼው ነው፤ ቃልንና ማተብን ማክበር ነው፤ መተባበር ነው!!

  1. ዛሬ የጎንደሬውና የሌላው የአማራ ሕዝብ ራሱን ከስደት፤ ከእልቂትና ከውርደት ለመከላከል የሚያደርገውን “የአልሞት ባይ ተጋዳይነት” ትግል አደንቃለሁ። ለኢትዮጵያ ዘላቂነት፤ ነጻነትና ሉዐላዊነት ምሰሶ ለሆነው ለጎንደርና ለሌላው የአማራ ሕዝብ ማንም ሲሟገትለት፤ ማንም እርዳታ ሲለግሰው፤ የዲፕሎማቲክ እውቅና ሲሰጠው አላየሁም። አንዱ ተቀዳሚ ስራችን የተቀነባበረና ዘላቂነት ያለው የዲፕሎማሲ ስራ ነው።

ይሕ ታላቅ ሕዝብ ለራሱ ህልውና በራሱና ከአብራኩ በወጡ በልጆቹ አቅምና በራሱ መሪዎች የመንፈስ ቆራጥነት መታገል ግዴታው ሆኗል። የተከፈለው ዋጋ ተከፍሎ፤ የጎንደርና ሌላው የአማራ ሕዝብ ከወያኔ/ህወሓት የሚወርድበትን የመሳሪያ ጥቃትና እልቂት፤ የተቀናጀ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ተባብሮና ተማምሎ ይወጣዋል የሚል እምነት ይኑረን። የጎንደሬው ትግል ከአማራው ትግል አይለይም። ከኦሮሞው ትግል ጋር ቀጥታ የሆነ ግንኙነት አለው። የአማራው ትግል ከሌላው፤ ለምሳሌ፤ ከአፋሩ፤ ከአኟኩ፤ ከወላይታው፤ ከጉራጌው ወዘተ በኢትዮጵያዊነቱ ከሚያምነው ሕዝብ ትግል አይለይም።

  1. ከሌሎቻችን የሚጠበቀው ታሪካዊ ግዴታ በማንኛው ዘርፍ የአቅማችን ድጋፍ ማበርከት ነው። ይህን ካደረግን ጎንደሬውና ሌላው ሕዝብ ማሸነፉ አይቀርም። ካሸነፈ ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ያድናታል የሚል የማያወላውል እምነት አለኝ። የወልቃይት ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ነው የምልበት ለዚህ ነው። የኦሮሞው ወጣት ትውልድ ህወሓት ለሱዳን መንግሥት ያበረከተውን ሰፊ ለም መሬት አውግዞ “የድንበሩ ባለቤት” የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጅ ህወሓት አለመሆኑን አስምሮበታል። ይህን መልእክት አንርሳው።
  2. ዛሬ አገራችን የገጠማት ክፍተት ግልጽ ነው። ኢትዮጵያንና መላውን ሕዝቧን መአከል ያደረገ፤ ጠንካራና ዘላቂነት የሚያሳይ ሕብረ-ብሄር የፖለቲካ ድርጅት የለም። በተከታታይ ህወሓት ህብረ-ብሄር የፖለቲካ ድርጅት እንዳይመሰረት አድርጓል። መሪዎች እንዳይኖፕሩ አድርጓል። ጠንካራ ህብረ ብሄር የፖለቲካ ድርጅትና አመራር ቢኖር ኖሮ ህወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ በባርነት መልክ አይገዛም ነበር። ይህ ክፍተት በኢትዮጵያዊነቱ ለሚያምነው ለአማራው ሕዝብ መጠቂያው ሆኗል። በእኔ ግምት የአማራው ሕዝብ የሚታገለው ስልጣን ለመያዝ ሳይሆን መብቱን ለማስከበር፤ ራሱን አደራጅቶ፤ ራሱን ከእልቂት አድኖ ከሌሎች አገር ወዳዶች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ለማደን ነው። የወቅቱ ጥሪ ዲሞክራሲወይንም እድገት  አይደለም። አገርን ከመፈራረስና ሕዝብን ከእርስ በርስ እልቂት ማዳን ነው።

ዲሞክራሲና እድገት ያለ አገር ስኬታማ ሊሆኑ አይችሉም።

  1. የወልቃይትጠገዴ፤ የጠለምት፤ የሰቲት ሁመራ፤ የዋልድባ፤ የራያ፤ የመተከልና የሌሎች የአማራ ሕዝብ የሚኖርባቸው መሬቶች ነጠቃና የትግራይ ተስፋፊነት ጉዳይ የነዋሪዎቹ ችግር ብቻ አለመሆኑን በማያሻማ ደረጃ አቅርቤዋለሁ። የጎንደር ሕዝብ ከአማራው ሕዝብ የተለየ ህይወት የለውም። የጎንደር ሆነ ሌላው የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ሌላ ዓለም አያውቅም። የወልቃይት ጉዳይ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ መሆኑን እንድንቀበል አሳስቤአለሁ።

በተመሳሳይ፤ የጎንደር ሕዝብ ትግል የመላው ኢትዮጵያ  ሕዝብ ትግል ነው።  ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንዲያስብበት የምመኘው፤ የጎንደር የነፍስ አድን ጥሪ የብሄራዊ ጥሪ እንጅ የጎጣዊ ጥሪ አለመሆኑን ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይህን መርህ ተቀብሎ ከጎንደሬውና ከሌላው የአማራ ታጋይ ሕዝብ ጋር እንዲተባበር በአደራ መልክ እጠይቃለሁ።አንፍራ!! የአማራውና የኦሮሞው ሕዝብ ለኢትዮጵያና ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ምሰሶዎች ናቸው። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የጎንደርን ትግል እንደ ራሱ ትግል መቁጠር አለበት የሚል እምነቴ ጠንካራ ነው። እደግመዋለሁ!!

  1. ከሁሉም አቅጣጫ ቅንነትና የፖለቲካ ፈቃደኛነት ካለ መፍትሄም አለ። በመጀመሪያ ወሳኙ ጉዳይ የአካባቢው ተቆርቋሪዎችና ሌሎች፤ መሬታቸው የተነጠቁት የሚጠይቋቸውን ማስተናገድና እንዲተባበሩ ግፊት ማድረግ ግዴታችን ነው። የመሬት ነጠቃውና የትግራይ ተስፋፊነት በዘላቂነት ሲታይ ለትግራይም ሕዝብ ሆነ መሬታቸው ለተነጠቀው ጎንደሬዎችና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን አደገኛ ነው። በመጀመሪያ የሚጎዱት ከቀያቸው የተባረሩት ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ጉዳቱ ከዚህ ላይ አያቆምም። የትግራይን ሕዝብ ወደባሰ ሁኔታ ያሸጋግራል። ጉዳዩ የህልውና ነው የምለው ለዚህ ነው።
  2. የተነጠቁት መሬቶች የትግራይ አካል ሆነው አያውቁም። የወልቃይትጠገዴን፤ የጠለምትን፤ የሰቲትሁመራን፤ የዋልድባንና የራያን ጉዳይ ሳጤነው የመጀመሪያው የሚያዋጣው አማራጭ፤ መሬታቸው ከተነጠቁትና ከትግራይ ሕዝብ ቅንነት፤ ተአማኔነት፤ ተቀባይነት ያላቸው መንፈሳዊና ሌሎች አባቶች፤ ምሁራንና ሌሎች ሁለቱም ሕዝቦች የሚቀበሏቸውን ግለሰቦች ጠቁሞ፤ እነዚህ ተገናኝተው የወንድማማችነት፤ እህትማማችነትና ዘላቂነት ያለው መፍትሄ ቢያቀርቡ ነው። ይህ አማራጭ ዘላቂነት ይኖረዋል። ሕዝብ ለሕዝብ የሚደረግ ውይይትና መፍትሄ ከማንኛውም አማራጭ በበለጠ ይመረጣል። ሆኖም፤ ከጥቂት የትግራይ ተወላጆች ውጭ፤ ህወሓቶችና ደጋፊዎቻቸው ይኼን አማራጭ የሚፈልጉት አይመሰለኝም።
  3. የእኔ ምርምርና ጥናት ያሳየው፤ በታሪክ፤ በሕዝብ ስርጭት፤ በባህል፤ በልምድ፤ በሕዝብ ትሥስርና ግንኙነት፤ በጅኦግራፊ፤ በአስተዳደር፤ ከህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት በፊት በነበሩት ተከታታይ መንግሥታት እውቅና መስፈርቶች፤ ወልቃይትጠገዴ፤ ሰቲት ሁመራ፤ ጠለምት፤ ዋልድባና አካባቢ፤መተከል፤ ራያና ሌሎች በህወሓት የተነጠቁ መሬቶች የትግራይ ክልል አካል ሆነው አያውቁም። የመሬት ነጠቃና ወደ ትግራይ ማጠቃለሉ የህወሓት የፖለቲካ ውሳኔ እንጅ በታሪክ የተደገፈ አይለም። የቤጌምድር/ጎንድርና የትግራይ ወሰን ወይንም ዳር ድንበር ተከዜ መሆኑን በማያሻማ መረጃ አሳይቻለሁ። የመጀመሪያው የህወሓት ውሳኔ መሆን ያለበት ይህን ድንበር መቀብልና የተነጠቁትን መሬቶች ለቤጌምድር/ጎንደር ሕዝብ መመለስ ነው። ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያዊነት ዜግነትን እንደ መለያው የተቀበለው ነዋሪው ሕዝብ ወገኖቹን “ከመሬታችን ውጡ” እንደማይል እገምታለሁ። ለምሳሌ፤ እኔ ጎንደር ከተማ በኖርኩበት ወቅት አብዛኛውን ዘመናዊ ኢኮኖሚ የያዙት የትግራይና የኤርትራ ተወላጆች ነበሩ። ጎንደሬው አይገባችሁም ያለበት ጊዜ እንዳልነበረ የአይን ምስክር ነኝ።
  4. ከወሎና ከጎጃም የተነጠቁ መሬቶች ለእነዚህ ክፍለ ሃገሮችና ሕዝቦች መመለስ አለባቸው። ዘላቂ ሰላም፤ እድገት እና ብሄራዊ አንድነት ሊመሰረቱ የሚችሉት የነዋሪዎች ሰብአዊ መብቶች፤ ፍትህና የሕግ የበላይነት፤ መሰረታዊ ነጻነት፤ በሕግ ፊት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መብትና እኩልነት ሲከበሩ ብቻ ነው። ይህ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መብት የሚከበርባት ኢትዮጵያ ከተመሰረተች፤ ማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የመኖር፤ የግል ኃብት የመያዝ፤ የመምረጥና የመመረጥ መብቱ የተከበረ ይሆናል። የትግራይ ተወላጅ በመሆን ብቻ የተለየ መብትና ባለቤትነት ሊኖር አይችልም። የአንዲት እናት አገር ልጆች ከሆንን የእያንዳንዳችን መብት መከበር አለበት። ይህን መሰረታዊ መርህ የጣሰው ህወሓት ነው።
  5. ህወሓቶች ማንኛውም ኢትዮጵዊ፤ የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ፤ በየትኛውም ኢትዮጵያ የመኖር፤ የግል ኃብት የመያዝ፤ የመምረጥ፤ የመመረጥ መብቱ/መብቷ መከበር አለበት የሚለውን ኢትዮጱያዊነት አይቀበሉም። በተመሳሳይ፤ የአማራው ሕዝብ በኦሮምያ፤ በደቡብ፤ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ፤ በጋምቤላ፤ በሃረርና በሌሎች ቦታዎች የመኖር መብቱ መከበር አለበት የሚለውን አያምኑም።

በእኔ ጥናትና እምነት፤ ይህን የዜግነት መብት ከተቀበልን፤ የትግራይ ሕዝብ አሁን እንደሚታየው በየትኛውም ኢትዮጵያ የመኖር፤ የተፈጥሮም ሆነ ሌላ ኃብት የመያዝ፤ የመምረጥና የመመረጥ መብቱ በሕግ የሚከበርበት ሁኔታ ይፈጠራል። ሰላም ሊኖር የሚችለው፤ ማንኛውም ብሄር የሌላውን ብሄርና የብሄር አባል በዜግነቱ ወይንም በኢትዮጵያዊነቱ መብቱን ሲቀበልና ሲያከብር ብቻ ነው። አንድ ብሄር የበላይ እና ሌላው የበታች ወይንም “የእንጀራ ልጅ” ሆኖ የሚሰቃይበት ክፍለ ዘመን አልፏል።

  1. የኢትዮጵያዊ የዜግነት መብት ሊከበር የሚችለው አንድ አገር፤ አንድ ሕዝብ የሚለው መሰረታዊ መርህ ሕገ-መንሥታዊ ድንጋጌ ሲያገኝ ነው። እውነተኛ ዲሞክራሲ ያስፈልጋል የምልበት ዋና ምክንያት ለዚህ ነው። ይህ መርህ የስርዓት ለውጥን ይጠይቃል። የስርዓት ለውጥ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ነው። ላሰምርበት የምፈልገው መልእክት አለኝ። በጎንደሬው መቃብር ላይ አዲስ ስርዓት ሊመሰረት አይችልም። ማንኛውም በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የሚያምን ዜጋ የትግሉና የመስዋእት ክፍያው ተሳታፊ መሆን አለበት!! ሁሉም ኢትዮጵያዊ መስዋእት መክፈል አለበት። እደግመዋለሁ!!
  2. ህወሓቶች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን ማርከው፤ ዘመናዊ ኢኮኖሚውንና የተፈጥሮ ኃብትንም ማርከውታል። ይህ የበላይነት ለህወሓት ከሕዝባዊ አመጽ ውጭ ማንም ሊወዳደረው የማይችል ድርጅታዊ አቅም አበርክቶታል። ህወሓት የሚወክለው “አናሳ” ብሄርን ነው ቢባልም ብቃቱና ኃይሉ 104 ሚሊየን ሕዝብን ለመቆጣጠርና ለመግዛት “አስችሎኛል” ወደሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ወስዶታል። ይህ ሁኔታ የሚያስታውሰኝ ጥቂት የአውሮፓ መንግሥታትና ቅኝ ገዢዎችን–እንግሊዞችን፤ ፖርቱጊሶችን፤ ስፓኒሾችን፤ ፈረንሳዮችን፤ ደቾችንና ሌሎችን ነው። እነዚህ አውሮፓዊያን 87 በመቶ የሚሆነውን የሶስተኛውን ዓለም ሕዝብ በበላይነት እንዲገዙት ያስቻላቸው የኢንዱስትሪ ልማትና የመሳሪያ ኃይል ነው። ቅኝ ገዢዎች ዘላለማዊ እንዳልሆኑ ታሪክ ይመሰክራል። ህወሓትም ዘላለማዊ አይደለም። የህወሓትና የፈጠራቸው የብሄር ድርጅቶች መሪዎች ድምዳሜ የተሳሳተ መሆኑን የኦሮሞውና የአማራው ሕዝብ እምቢተኛነት አሳይቷል። የህወሓቶች ጥንካሬ የራሱ አፈ ታሪክ (Myth) መሆኑን በዚህ ጽሁፍ አሳይቻለሁ። ከአሁን በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱን ለአፈ ታሪከኞች ብዢታ፤ ለአፈና፤ ለእልቂት፤ ለስቃይና ለውርደት አጋልጦ ይሰጣል ብየ አልገምትም።
  3. በአፈ ታሪከኞቹ በህወሓቶች የተካሄደው የመሬት ነጠቃንም ሆነ ሌላ ስርዓት ወለድ ተግዳሮቶችን ለማስወገድ ከተፈለገ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሰረታዊውን የፖለቲካ ችግር ለማስወገድ የስርዓት ለውጥ ያስፈልገዋል። ይህ ተግዳሮት የሚጠይቀው ሕዝባዊ አመጽን ይሆናል። ይህም መተባበርን ይጠይቃል። ተቀናቃኝ ወይንም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊያስቡበት የሚገባቸው መሰረታዊ ሃሳብ በመከፋፈላቸውና የህወሓቶች ሰለባ በመሆናቸው፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ለመሆን አለመቻላቸውን ነው። በኢትዮጵያዘላቂነትና በኢትዮጵያዊነት መስፈርት ላይ የጋራ ዓላማ እስከሌላቸው ድረስ ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ አማራጭ ለማቅረብ አይችሉም። ይህ እንዳለ ሆኖ ሕዝቡ እንደገና ተባብሮና ደፍሮ ከተነሳ (መነሳቱ አይቀርም የሚል እምነት አለኝ) ስርዓቱን ይገለብጠዋል።

ከዚያስ ምን? የሚለው ሌላ ትንተና ያስፈልገዋል!!

  1. የህወሓት የመሬት ነጠቃና የትግራይ ተስፋፊነት ለብዙ ዓመታት የታሰበበት፤ በእቅድ የተሰራ፤ ዘላቂነት እንዲሆን በአዲስ ሰፋሪዎችና በጦር መሳሪያ ኃይል የተደገፈ ነው። ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ ቃል ኪዳን የገባበት ስለሆነ በሕገ መንግሥቱ መርህና በድርድር የሚፈታ አይመስለኝም። ሕዝቡ ይኼን በሚገባ ያውቀዋል። በጎንድርና በሌሎች የአማራ ክልል ተብሎ በሚጠራው እየተስፋፋ የሄደው ትግል አይቆምም። ሌሎች ኢትዮጵያዊያን የትግሉን አድማስ የማስፋት ግዴታ አለባቸው። ምክንያቱም በጎንደሬው ላይ የደረሰው በእነሱም ላይ ይደርስባቸዋል ወይንም ደርሶባቸዋል። ማመን ያለባቸው አስኳል ጉዳይ አንድ ነው። የህወሓቶች የመሳሪያ ኃይል ይገድላል እንጅ አያሸንፍም።
  2. ጎንደሬውና ሌላው ችግሩን ሊወጣው የሚችለው በመተባበር፤ አቅምን በማጠናከርና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን እንዲተባበሩት ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ነው። በመጀመሪያ መተባበር ያለበት መሬቱ የተነጠቀው የአማራው ሕዝብ ሲሆን፤ አጋርና አምባሳደር መሆን ያለበት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። ጎንደሬውና የኦሮሞው ወጣቶች እንዳሳሰቡን፤ የወልቃይት-ጠገዴና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ብሄራዊ ችግሮች ናቸው።
  3. ህወሓትና ደጋፊዎቹ ሰላምንና እርጋታን ከፈለጉ የቤጌምድር/ጎንደርና የትግራይ ድንበር ተከዜ መሆኑን መቀበል አለባቸው። ለሱዳን የሰጡትን መሬት መሳብ አለባቸው። በሕዝቡ ላይ የሚያካሂዱትን ጭካኔና እልቂት ማቆም አለባቸው።
  4. እኔን ያሳሰበኝ ጎንደሬው አይደለም። ጎንደሬው ራሱን ለመከላከል የማንንም የሰው ኃይል ድጋፍ አይፈልግም። ጎንደሬው ቆርጦ ከተነሳ በኋላ የሚያቆመው ኃይል አይኖርም። ጎንደሬው የሚፈልገው መፈላለግን፤ መተባበርን፤ አብሮ ለአንድ ብሄራዊ ዓላማ መቆምንና ኢትዮጵያን ከመፈራረስ አደጋ መታደግን ነው!! ይህ እምነትና እሴት ፈረንጆች እንደሚሉት ”DNA”ውእና መለያው ነው። ይህን ስል እልቂቱ አያሳስበኝም ማለት አይደለም። ያሳስበኛል።

በተጨማሪ ያሳሰበኝ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት እናምናለን የሚሉ ስብስቦችና ግለሰቦች የወልቃይትን ጉዳይ ችላ ማለታቸው ነው። ይህ አቋም ተቀባይነት የለውም። ጎንደሬው “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” ብሎ ከተነሳ ሌላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ትግራዩንም ጨምሮ “የወልቃይት” ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ነው” የሚልበት ጊዜ አሁን ነው። መፍትሄው ኢትዮጵያዊነት እንጅ “ትግራዊነት” ወይንም “ህወሓታዊነት” ወይንም ሌላ ጠባብ ብሄርተኝነት አይደለም።

በመጨረሻ እኔ የምመኛቸውን ስኬታማ ሊሆኑ የሚችሉ ዓላማዎች ላቅርብ፤

አንድ፤ እኛ እርስ በርስ የምናደርገውን የፌስቡክና ሌላ የቃላትና የፕሮፓጋንዳ ጦርነት እናቁም፤ መሪዎች እናውጣ!! ጠባብ ብሄርተኛውን ህወሓት እያወገዝን እኛም ጠባብ ብሄርተኛ ወይንም የብሄር ትምክህተኛ እንዳንሆን እንጠንቀቅ!!

ሁለት፤ ገንቢ ሃሳቦችን እያቀረብን ለታጋዩ የጎንደር ሕዝብ የምናደርገውን ድጋፍ ተከታታይ እናድርገው!!

ሁለት፤ እያንዳንዳችን የወልቃይትን እውነተኛ ታሪክ ለልጅ ልጆቻችንና ለወዳጆቻችን እናስተምር!!

እሶስት፤ እኛ በራሳችን መደራጀትና አቅም ግንባታ እንመን፤ የራሳችን መንነትና ኢትዮጵያዊነታችን ተቀብለንና አክብረን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ለመተባበር ከቆረጥን ሕዝባዊው ትግል ያሸንፋል!! ወልቃይት ጠገዴ ወደ ጎንደር/ቤጌምድር ይመለሳል!!

አራት፤ ከሌሎች ጋር በመተባበር የዲፖሎማሲ ስራዎችን በዘላቂነትና በቆራጥነት እንስራ!!

አምስት፤ በህወሓቶች ላይ የኢኮኖሚ እገባን በሚመለከት በሚደረገው ዘመቻ ጎንደሬዎች ያልተቆጠበ ትብብር እንዲያደርጉ እንቀስቅስ!!

በትእግስት ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ።

ታሪካዊዋ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!!

April 29, 2017

LEAVE A REPLY