/ዳንኤል መስፍን/
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቀጣዩ ወር የአመቱን የመጀመርያ የነጥብ ጨዋታ ያደርጋል፡፡ አዲሱ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለም 29 ተጫዋቾችን መርጠዋል፡፡ አሰልጣኙ በስብስባቸው አንጋፋው አጥቂ አዳነ ግርማን ለማካተት ጥሪ ለተጫዋቹ አቅርበውለት እንደነበረም ተሰምቷል፡፡
በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን የሰጠው አዳነ ግርማ አሰልጣኝ አሸናፊ ጥሪ አቅርበውለት እንደነበር ገልጿል፡፡ ” በርግጥ አሁን ያለኝ ወቅታዊ አቋም የሚያጫውተኝ ቢሆንም በዚህ ሶስት አመት ውስጥ ራሴን ከብሔራዊ ቡድን አግልያለሁ። ከብሔራዊ ቡድን ካገለልኩ ጀምሮ ብዙ አሰልጣኞች እንድመለስ ጠይቀውኛል ፤ አሁንም አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እንድጫወት ጠይቆኛል፡፡ በዚህም አመሰግነዋለው። እንደሚታወቀው ለሀገሬ ከ10 አመት በላይ አቅሜ በቻለ ነገር ሁሉ አገልግያለው፡፡ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ። አሁን ክለቤ ላይ ትኩረት ማድረግ ስለምፈልግ እንጂ አቅሜ ሳይችል ቀርቶ አይደለም ራሴን ከብሔራዊ ቡድን ያገለልኩት። ” ሲል አዳነ ተናግሯል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ የአሰልጣኙ ምርጫ ላይ በሰጠው አስተያየት የአሸናፊን ምርጫ እንደሚያከብር ጠቁሟል፡፡ ” አሰልጣኙ የራሱ አካሄድ አለው፡፡ በብዛት በቡድናቸው ውስጥ ጥሩ የሚንቀሳቀሱ ሀገር ውስጥ አሉ የሚባሉ ተጨዋቾች ተመርጠዋል። ሆኖም መጠራት እየተገባቸው ያልተመረጡ አሉ፡፡ የአሰልጣኙን ስራ የማከብር ቢሆንም ወደ ፊት እያየ ይጨምራል ብዬ አስባለው። አሁን ለራሱ አጨዋወት ታክቲክ ይመጥናሉ ብሎ ያመነበትን መርጧል፡፡ እንግዲህ ስራውን ለእርሱ መተው ነው። በዚህ አጋጣሚ መልካም እድል እመኝለታለሁ።
አዳነ ግርማ በ2006 ራሱን ከብሔራዊ ቡድኑ ካገለለ ወዲህ ዋልያዎቹ 3 አሰልጣኞችን ቀያይረዋል፡፡ ደጉ ደበበ እና አይናለም ኃይለም የአዳነን ፈለግ ተከትለው ራሳቸውን ከብሔራዊ ቡድን አግልለዋል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ፣ የአለም ዋንጫ ማጣርያ እና የቻን ውድድሮች ላይ ተሳትፋም መልካም ውጤቶችን አላስመዘገበችም፡፡ አዳነም ባገለለባቸው አመታት ያለው ብሔራዊ ቡድን አለመረጋጋት እንደሚታይበት ያምናል፡፡
” ብሔራዊ ቡድኑ ብዙ አሰልጣኝ ነው የተፈራረቀበት፡፡ እኔ እንደ ብሔራዊ ቡድን ሳስበው በሌላው አለም አንድ አሰልጣኝ ሁለት አመት እና ከዛ በላይ ጊዜ ይሰጠዋል። እኛ ሀገር የስድስት ወር እና የአንድ አመት ውል እየሰጠህ እንዴት ነው የሚሆነው? ይህ አይነት አሰራር ሊቀር ይገባል፡፡ ኢትዮጵያም የሌሎች ሀገሮችን ተመኩሮ መውሰድ አለባት እላለው። ” ሲል በብሄራዊ ቡድኑ ዙርያ ያለውን ሀሳብ ቋጭቷል፡፡
በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ አሳሳቢ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የሆነው የተጫዋቾችን ክብር የሚነካ ዘለፋ ነው፡፡ ዘንድሮ በተለያዩ ተጫዋቾች ላይ ይህ ተግባር ተፈፅሞ በክለቦች ላይ ቅጣቶች መጣሉም የሚታወስ ነው፡፡ ከጉዳዩ ሰለባዎች አንዱ የሆነው አዳነ ግርማ ይህ ተግባር ሊወገድ እንደሚገባ ተናግሮ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር የነበረውን ቆይታ ቋጭቷል፡፡
” እንደ ደጋፊ ሳስበው ስታድየም የሚመጡት ሊዝናኑ እና የሚወዱት ቡድናቸውን ሊደግፉ እንጂ የተቃራኒን ቡድን እና ተጨዋች ለመሳደብ አይደለም። እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ቡድንህን እና ቡድንህን ብቻ ደግፈህ መውጣት ነው ያለብህ። ይህን መልዕክት የማስተላልፈው ለዚህ ቡድን ለዛ ብዬ አይደለም ፤ ለሁለም ቡድን ደጋፊዎች ነው። ቡድናቸውን ደግፈው ቡድናቸው ተዝናንተው በሚመዘገበው ውጤት ቢያሸንፍም ተደስተው ቢሸነፍም ተከፍተው ቡድናቸው ላይ መስተካከል ያለበትን ነገር አግባብ ባለው መንገድ ተናግሮ መሄድ ነው እንጂ የተቃራኒ ቡድን ተጨዋች መስደብ ተገቢ አይደለም። አሁን የስፖርት ቤተሰቡ ወደ ሜዳ መምጣቱ ትልቅ ነገር ነው። ይህን ህዝብ በስታድየም ለማስቀረት አላስፈላጊ ነገሮችን መቅረፍ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ “
/ሶከር ኢትዮጵያ/