ንቅናቄዓችን አርበኞች ግንቦት 7፣ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ከፍተኛ አስተዋጾ ሲያበረክት በቆየው ጓዳችን በአቶ ፈቃደ ሸዋቀና ያለጊዜው ከዚህ ዓለም በሞት መለየት የተሰማው ሀዘን ከፍተኛ ነው።
በንቅናቄያችን አሠራር የበርካታ አባላቶቻችን ማንነት ይፋ የማይደረግ በመሆኑ በግልጽ ባይነገርም አቶ ፈቃደ ሸዋቀና፣ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ንቅናቄው በውህደት እስከ ከሰመ ድረስ በተለያዩ የሥራ ቦታዎች ተመድቦ እየታገለ ሲያታግል ቆይቷል። በድርጅቶች ውህደት አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሲቋቋምም ቀድሞ በግንቦት 7 ሲያደረገው እንደነበረ ሁሉ በአርበኞች ግንቦት 7 የውጭ ዘርፍም ውስጥ እስከ ህይወቱ ፍፃሜ ድረስ የሚጠበቅበትን የአባልነት ግዴታ ሲወጣ ኖሯል።
አቶ ፈቃደ ሸዋቀና በመደበኛ ሙያው የታወቀና የተመሰከረለት የሳይንስና የምርምር ባለሙያ ነበር። ይህን ትምህርትና ልምድ የሰጡት እውቀት፤ በትዕግስት የማስተዋል፣ የማመዛዘን፣ በስሜት ሳይሆን በምክንያትና ማስረጃዎች የማመን፣ የአጭር ጊዜ ብቻ ሳይሆን የረዥም ጊዜ ጥቅምና ጉዳቶችን የማየት ክህሎቶቹ አርበኞች ግንቦት 7 ውስጥ ተግባራዊ አድርጎታል። የጥናትና ምርምር ኮሚቴ አባል በመሆን በትግል ስትራቴጂ፣ ታክቲክና ስልቶች ጥናቶች ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል፤ የሕዝብ ግኑኝነት ኮሚቴ አባል በመሆንም የሕዝብ ግኑኝነት ስትራቴጂዓችንን በመቅረጽና አቅጣጫ በማስያዝ አገልግሏል።
አቶ ፈቃደ ሸዋቀና የህወሓት አገዛዝ በኢትዮጵያ የመጨረሻው አምባገነን አገዛዝ እንዲሆን ሁለገብ የትግል ስልት እንደአማራጭ በመወሰድ ረገድ በተደረጉ የስትራቴጂ ውይይቶችና ክርክሮች በንቃት ተሳትፏል፤ ሁለገብ የትግል ስልት ማኅበራዊ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጥሯል።
ለአቶ ፈቃደ ሸዋቀና የህወሓት አገዛዝ መወገድ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ቢሆንም ከህወሓት በኋላ ስለምትኖረን ኢትዮጵያ ሲጨነቅና ሲጠበብ ኖሯል። በዚህም ምክንያት ከተለያዩ የአገራችን ማኅበረሰቦች ጋር ተቀራርቦ ለመነጋገር ያላሰለ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ኢትዮጵያችን የሁሉም ኢትዮጵያዊ አገር እንድትሆን ማኅበረሰቦችንና ቡድኖችን ለማቀራረብ ሌት ተቀን ብዙ ጥሯል።
አቶ ፈቃደ ሸዋቀና ለሕይወት አስጊ የሆነ የጤና እክል እንኳ ገጥሞት ከጀመረው ትግል ለማፈግፈግ ምክንያት ያላቀረበ፤ እስከ እድሜው ፍፃሜ የራሱን ህመም ውጦ የአገራችንና የኢትዮጵያ ሕዝብን ህመም የታመመ፤ ጽኑ፣ ብርቱ፣ ታጋሽ፣ አስተዋይና ብልህ ጓዳችን ነበር።
አርበኞች ግንቦት 7፣ በአቶ ፈቃደ ሸዋቀና ከዚህ ዓለም በሞት መለየት አንድ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የነበረው ታጋይ ጓዱን አጥቷል። የአቶ ፈቃደ ሸዋቀና ህልፈት ጉዳቱ ለቤተሰቦቹና የግል ወዳጆቹ ብቻ ሳይሆን ለአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች ከዚያም አልፎ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ ንቅናቄያችን ያምናል።
አርበኞች ግንቦት 7፣ በጓዳችን አቶ ፈቃደ ሸዋቀና ህልፈት መሪር ሀዘን ለደረሰባችሁ ሁሉ መጽናናትን እየተመኘ እሱ ለቆመላቸው ዓላማዎች በመቆም፤ የእሱን ህልሞች በማሳካት ዘላለማዊ ህይወት እንድናወርሰው ያሳስባል።
ዘላለማዊ ዝክር ለሰማዕቶቻችን በሙሉ!
አንድነት ኃይል ነው!