ራስ አሉላ አባ ነጋ የኢትዮጵያ ጀግና!! /ያሬድ ሹመቴ/

ራስ አሉላ አባ ነጋ የኢትዮጵያ ጀግና!! /ያሬድ ሹመቴ/

በዘመነ አብዮቱ (ደርግ) በትግራይ ክፍለ ሀገር ፣ ዓድዋ አውራጃ ፣ አባ ገሪማ ገዳም ከወትሮው የዝምታ እና የመናንያት የተመስጦ ቀናት ውጪ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብና የጦር ሰራዊት ገዳሙ ተርመስምሷል። የገዳሙ መናንያንም በከፍተኛ የድግስ ዝግጅት ተጠምደዋል።

በቦታው በአካል ከነበሩ ሰዎች መሀል የልጅነት ትዝታቸውን የማይረሱት አንድ ጎልማሳ ሰው ይህንን ትዝታቸውን ይተርካሉ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ጦር ጀግና ራስ አሉላ አባነጋ አጽማቸው ካረፈበት ጥንታዊው የአባ ገሪማ ገዳም የመታሰቢያ ሀውልታቸው ሊመረቅ ነው – ይህ ሁሉ ሽር ጉድ። የዓድዋው ተወላጅ ጎልማሳው ሰው በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በሞቀ መንፈስ ይተርካሉ።

በርካታ በሬዎች ለድግሱ ተጥለዋል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ተማሪዎችና በርካታ እንግዶች ስፍር ቁጥር የሌለውን የድግስ ዝግጅት ሊታደሙ በየዳሱ ተሰይመዋል። እንደ ተራኪያችን አገላለጽ እንዲህ አይነት ብዛት ያለው ህዝብ ለድግስ ተሰብስቦ በህወታቸው አይተው አያውቁም።

ከተራራማው የአባ ገሪማ ገዳም ዙሪያ ያሉ ጉብታዎች በሙሉ በአብዮቱ ዘመን ወታደሮች ተከቦ ጥበቃው ተጠናክሯል። በአባቶች መንፈሳዊ ዝማሬ፣ በህዝቡ ደግሞ ጀግናን በሚያወድስ የድል ፉከራ እና ሽለላ ገዳሙ የጥምቀት ያህል ደምቋል።

አሁን ህዝቡ በሙሉ ከተጣሉት ግዙፍ የመመገቢያ ዳሶች እየወጣ እንግዳውን ሊቀበል ተዘጋጅቷል። በርካታ ሰዎችም የእግዳውን ማንነት እየገመቱ በመንሾካሸክ ያወጋሉ። በርካቶች ያልተጠራጠሩት እንግዳ ኮሎኔል ፍስሀ ደስታ ነበሩ። ኮሎኔሉ በዓድዋ ንግስት ሳባ ትምህርት ቤት የተማሩ የአካባቢው ተወላጅ እንደመሆናቸው መጠን ይህንን የጀግና ሃውልት ከሳቸው ያነሰ መሪ መጥቶ አይመርቀውም እያሉ ይወራረዳሉ።

ራስ አሉላ ኢትዮጵያ ሀገራችንን ከወራሪ ለመመከት ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉ ታላቅ ጀግና ናቸው። ከአፄ ዮሐንስ ጋር በተለያዩ የጦር አውድማዎች ዘምተው ኢትዮጵያን ከጠላት የታደጉ ሰው ናቸው። ከአፄ ዮሐንስ ህልፈት በኋላም ከዳግማዊ አፄ ምንሊክ ጋር በመሰለፍ ዳግም ኢትዮጵያን ከወራሪ ለመመከት ከፍተኛ ጀብዱ የፈፀሙ የሀገር ባለውለታ ናቸው። በተለይም በሶሎዳ ተራራ ጀርባ በመመሸግ የየካቲት 23 እለት የመጨረሻውን ውጊያ በማሪያም ሸዊቶ ግንባር ተዋግተው የጄኔራል ዳቦርሜዳን ጦር የደመሰሱ ሰው ናቸው።

ራስ አሉላ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት አንድም ወራሪን በመመከት አንድም ኢትዮጵያን ላስተዳደሩ መሪዎች ለአፄ ዮሐንስ እና አፄ ምኒልክ በፍፁም ታማኝነት ኢትዮጵያን ብቻ በማስቀደም የተሰለፉ ትልቅ ድልድይ ናቸው።

የኚህን ሰው መታሰቢያ ኃውልት ከሞታቸው 80 አመታት በኃላ ለማቆም የተዘጋጀው ታላቁ መሰናድዖ የክብር እንግዳው ሲመጡ ሊመረቅ ሁሉ ነገር አልቆ ደቂቃዎች ቀርተዋል።

የዓድዋ ሰማይ አጉረምራሚ ድምጽ ባላቸው የጦር አውሮፕላኖች ደመቀ። በመሀልም አንዲት ነፋሪት (ሔሊኮፍተር) ዝቅ ብላ የመሬቱን አቧራ እያላወሰች ወረደች። አቧራው መሬት እስኪይዝ እልልታውና ጭብጨባው ጭፈራውና ሆታው የእንግዳውን ማንነት ይበልጥ አጓጊ አደረጉት።

የነፋሪቷ እርግብግቢት በርዶ እንደቆመ ጓድ መንግስቱ ኃይለ ማርያም ከሌሎች ከፍተኛ ባለ ስልጣኖቻቸው ጋር ከሄሊኮፍተሯ ወረዱ። ብዙዎች ያልገመቱት በመሆኑ እልልታውና ሆታው ደመቀ። እጃቸውን አንዴ ለህዝባዊ ሰላምታ እያውለበለቡ አንዴ ደግሞ ለወታደራዊ ሰላምታ አየሩን እየቀዘፉ አቀባበሉን በደስታ ካስተዋሉ በኋላ። በፍጥነት እየተራመዱ ወደ ክብር ቦታቸው አመሩ።

የተለያዩ ትርዒቶች እና ንግግሮች ከቀረቡ በኋላ ሀውልቱ በጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም ተመርቆ የክብር መጎናፀፊያው ተከፈተ።

“የጀግና ሰው ክብሩ፣
ዳር ድንበሩ”

ሲሉም ወታደሮች አዜሙ፣ ህዝቡም (በትግርኛ ፉከራ) “ቱታ ቱታ…” እያለ ጀግናውን አሞገሰ ካህናቱም ስለኢትዮጵያ ክብር ዝማሬውን ከቅኔው አሳምረው አቀረቡት።

ከተራኪያችን በተጨማሪ በቦታው የነበሩት አንድ መነኩሴ እንዳጫወቱኝ ጓድ መንግስቱ ግሩም ንግግር አደረጉ። ቃል በቃ ባያስታውሱም “ጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ ለሀገራቸው ነፃነት ለከፈሉት ዋጋ” ያላቸውን ክብር ገለፁ።

ሽማግሌው መነኩሴ ቀጥለው እንዲህ አሉኝ፣
“በህይወቴ ሙሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛቱ የዚያን እለት የመጣው ይመስለኛል” ሲሉ ትዝታቸውን ነግረውኛል።

የእለቱ መርኃ ግብር ተፈጽሞ ህዝቡም ተሸኝቶ ጓድ መንግስቱ እና ባለስልጣኖቹ ተሰናብተው ካለቀ በኋላ የገዳሙ መነኮሳት የድግሱን ግሳንግስ ፈጣጥመው ወደ ጥሞና ወደ ቀደመ ፀጥታቸው ተመለሱ። ደስታ እና እርካታቸውን እያጣጣሙ ወደ የማረፊያቸው ገቡ።

“ይህ ከሆነ በኋላ…” ይላሉ መነኩሴው “ይህ ከሆነ በኋላ የወያኔ ታጋዮች በሌሊት መጡ። እኛ አልሰማንም። ጠዋት ያየነው ግን አስደነገጠን። በጓድ መንግስቱ የተመረቀው የራስ አሉላ ኃውልት ፍርስርሱ ወጥቷል። ብዙዎቻችን አለቀስን። ለምን እንዲህ ይደረጋል ስንልም ጮህን!”

“በኋላ ላይ የታጋዮቹ መሪዎች ጉዳዩን ኮንነው ልክ አይደለም አሉና መልሰው ሀውልቱን ለመጠገን ከቀናት በኋላ በድብቅ መጡ። የተወሰነ ለማስተካከል ቢሞክሩም ለምልክትነት ካልሆነ በቀር እንደቀድሞው መሆን ሳይችል ቀረ”
ወዲያውኑ ከመጣው የመንግስት ለውጥ በኋላ ታላቁ የራስ አሉላ ሀውልት ለአመታት የሚያስታውሰው አጥቶ እንደ ማንኛውም ሰው ምልክቱ ብቻ በሊሾ የተከደነ መቃብር ሆኖ ቆየ። በቅርቡም ከአንድ አመት በፊት አቶ ዳዊት ገ/እግዚአብሔር በተባሉ ግለሰብ ለወንዶችም ለሴቶችም ምቹ በሆነ የገዳሙ ቅጥር ግዚ ውስጥ በጉዞ ዓድዋ ተጓዦች አማካኝነት ውብ የሆነ ኃውልት አቆሙላቸው። የመቃብራቸውም ቦታ በድጋሚ በእምነ በረድ ታንፆ ታደሰ።

ራስ አሉላ አባ ነጋ የኢትዮጵያ ታላቅ የጦር መሪ ብዙ የውጭ ሰዎች ደግሞ የመጀመሪያው የአፍሪካ ጄኔራል ሲሉ ይጠሯቸዋል።

እኚህ ሰው ለኢትዮጵያዊነት በከፈሉት ዋጋ ምክንያት ኢትዮጵያዊያን ሁል ግዜም እያከበርን እያወደስናቸው እንኖራለን። ከግዜያት በኋላ በመጣ የጠበበ የዘር በሽታ ታላቁን የኢትዮጵያ ጀግና አውርደን የመንደር ተሟጋች ስናደርጋቸው ይስተዋላል።

በጀግኖቻችን ማንነት ዙሪያ ከዘንድሮው አመለካከት ይልቅ ጓድ መንግስቱ ምን ያህል ኢትዮጵያዊ እንደነበሩ እታዘባለሁ።

ከኢትዮጵያዊነት አንውረድ። ታሪካዊ ጀግኖቻችን እኛን አንድ የሚያደርጉ ድልድዮች እንጂ የልዩነት አጥሮች አይደሉም!!

ክብር ለታላቁ ራስ አሉላ እንግዳ (አባ ነጋ)
ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!

LEAVE A REPLY