ቴዲ አፍሮ እና የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር /በጥበቡ በለጠ/

ቴዲ አፍሮ እና የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር /በጥበቡ በለጠ/

/ሰኔ 9 ቀን 2009 ዓ.ም በሰንደቅ ጋዜጣ የታተመ/

ከሰሞኑ የኢትዮጵያዊያን ትልቅ መነጋገሪያ የሆነው የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ አልበም እና እሱን መሠረት አድርጐ የሚነሳው ውይይት፣ ክርክር፣ ምልልስ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉ ካሴት እና ሲዲ የሚሸጡ የመንገድ ላይ ነጋዴዎች እጃቸው ላይ ያሉትን ንብረቶች በሙሉ ቁጭ አድርገው የቴዲ አፍሮን ሲዲዎች መሸጥ ላይ ናቸው፡፡ ሌሎች ሲዲዎችን አትሽጡ የተባሉ ሁሉ ይመስላሉ፡፡ ቴዲ ይህን የሞተውን የሲዲ ገበያ እንዴት ፈነቃቅሎ መጣ? የሚለው ጉዳይ ብዙ የመወያያ አጀንዳ ይፈጥራል፡፡ የቴዲ የሲዲ ሽያጭ እንዴት ገኖ መጣ? ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?

ቴዎድሮስ ካሣሁን በየ አልበሞቹ ውስጥ ከሚታዩት ጉዳዮች አንዱ የታላላቅ ሰዎችን እና የነገስታትን ታሪክ መሠረት አድርጐ የሚሰራቸው ዘፈኖቹ ናቸው፡፡ ገና ከጅማሮው አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴን፣ አትሌት ቀነኒሳ በቀለን፣ አፄ ኃይለሥላሴን፣ ቦብ ማርሊን፣ አፄ ምኒልክን፣ እቴጌ ጣይቱን እና አሁን ደግሞ አፄ ቴዎድሮስን ይዞ መጣ፡፡ እነዚህ ዘዬዎች የቴዲ አፍሮ ልዩ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ ሰዎቹ በታሪክ ውስጥ ከፍ ብለው ሲጠሩ የኖሩ ናቸው፡፡ ቴዲ አፍሮ ደግሞ ከፍታውን የበለጠ ያጐላዋል፡፡

አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ በሩጫው ዓለም ግዙፍ ስብዕና ያላቸውና በወቅቱም ተወዳጅ ስለነበሩ፣ ቴዲ አፍሮ ትጋታቸውን ወደ ሙዚቃው ሲያመጣው ልዩ ትኩረት ተሰጠው፡፡ የእነሱ ስም እየተነሳ ሲዘፈን ይደነስ ነበር፡፡ ይጨፈር ነበር፡፡ በየክለቡ “ቀነኒሳ አንበሳ” እየተባለ ሲጨፈርበት ትዝ ይለኛል፡፡
በዘመነ ደርግ ከመንበረ ስልጣናቸው ተነስተው የታሰሩት እና በግፍ የተገደሉት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ከፍ በማድረግ ትልቅ ታሪክ ሰርተዋል፡፡ ነገር ግን ታሪካቸው እንዳይነገር እና ትውልድም እንዳያውቃቸው ሲባል ደርግ ስብዕናቸውን አጠልሽቶ ያቀርበው ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተዳፍኖ የኖረውን ታሪካቸውን መዘዝ አድርጐ ቴዎድሮስ ካሣሁን “ግርማዊነትዎ…” እያለ ሲመጣ ሁሉም ነገር ተለወጠ፡፡ አገር ጨፈረበት፡፡ ተደሰተበት፡፡

የአድዋ ጀግኖቹን እነ አፄ ምኒልክን እና እቴጌ ጣይቱንም በክሊፕ አስደግፎ ብዙ ገንዘብ አውጥቶበት አዜመላቸው፡፡ የአድዋ ጀግኖችን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፡፡

አሁን ደግሞ አፄ ቴዎድሮስ ዘንድ መጣ፡፡ በርግጥ የቴዲ ስሙ ራሱ ከአፄ ቴዎድሮስ የተወረሰ ነው፡፡ የአባቱ ስም ካሣሁን ሲሆን፤ የአፄ ቴዎድሮስ እናታቸው ያወጡላቸው ስም “ካሣ” ነው፡፡ ስለዚህ ቴዲ አፍሮ እና አፄ ቴዎድሮስ በስም የመወራረስ ሁኔታ ይታይባቸዋል፡፡

ዛሬ እንደውም ላነሳሳ የፈለኩት የአፄ ቴዎድሮስን ጉዳይ ነው፡፡ ቴዎድሮስ በታሪክ ውስጥ፣ ቴዎድሮስ በፀሐፊያን፣ በደራሲያን፣ በአጠቃላይ በኪነ-ጥበብ ሰዎች ውስጥ ምን ዓይነት ሰብዕና አላቸው የሚለውን ጉዳይ ማንሳት ፈለኩ፡፡ አቤት የፍላጐቴ ብዛት? ደግሞ ሌላ መጣብኝ፡፡ ቴዲ አፍሮ ሲዘፍን እንዲህ የሚል ግጥም አለ፡-

አምጡ ቆርጣችሁ ከሹሩባው ላይ
እንዳንለያይ፤ ኪዳን እንሰር
ይላል፡፡
ቴዲ የአፄ ቴዎድሮስን ፀጉር አምጡልኝ ሲል ተምሳሌት /Symbolism/ ነው፡፡ እውነተኛውን የቴዎድሮስን ፀጉር እንድናመጣለት አይደለም፡፡ የዘፈኑን ሀሳብ ለማጐልመስ የተጠቀመበት ገለፃ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ያ የአፄ ቴዎድሮስ ገለፃ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ያ የአፄ ቴዎድሮስ ሹሩባ የት ነው ያለው? አብሯቸው ተቀብሯል? እመሬት ውስጥ ነው ወይስ ሌላ ቦታ?
የአፄ ቴዎድሮስ ሹሩባ፣ የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር ዛሬም አለ፡፡ ከሰውነት ገላቸው ላይ በምድር ላይ የቀረው ፀጉራቸው ብቻ ነው፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ ትንሽ ላጫውታችሁ፡፡

አፄ ቴዎድሮስ ሰኞ ሚያዚያ 7 ቀን 1860 ዓ.ም መቅደላ ላይ ራሳቸውን ከሰው በኋላ የእንግሊዝ ወታደሮች ደረሱ፡፡ ሲያዩዋቸው ሰውነታቸውና ልብሳቸው በደም ተጨማልቋል፡፡ ሊያምኑ አልቻሉም፡፡ አላማቸው ቴዎድሮስን መማረክ ነበር፡፡ ቃል-ኪዳናቸውም ቴዎድሮስን መያዝ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ መይሳው በሰው እጅ አልወድቅም ብለው ሽጉጣቸውን ጠጥተዋል፡፡ የእንግሊዝ የጦር መኮንንኖች በሸቁ፡፡ የማይገባ ድርጊት ፈፀሙ፡፡ አስከሬናቸው ላይ ግፍ ሰሩ፡፡ ይህም ከሙት ገላቸው ላይ የለበሱትን ልብስ እየቀደዱ ተከፋፈሉት፡፡ የቴዎድሮስ ደም የነካውን ልብስ ለማግኘት እየቦጫጨቁ ተቀራመቱት፡፡ የቴዎድሮስ አስከሬን ራቁቱን ቀረ፡፡ ይህንን ትዕይንት በጦርነቱ ወቅት የእንግሊዝ የጂኦግራፊ ባለሙያ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ የመጣውና በኋላም ታሪክ ፀሐፊ የሆነው Clements Markham የተባለው ሰው ፅፎታል፡፡ ከዚሁ ጋር ሌላ እጅግ አሳዛኝ ድርጊት ተፈፅሟል፡፡ የእንግሊዝ ወታደሮች የአፄ ቴዎድሮስን ሹሩባ ፀጉር አናታቸውን ገሽልጠው ወስደዋል፡፡ ይህ የአፄ ቴዎድሮስ ሹሩባ በአሁኑ ወቅት London National Army Museum ተብሎ በሚጠራው ተቋም ውስጥ ይገኛል፡፡ እናም የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር በለንደን ከተማ ውስጥ ይገኛል፡፡

ከእርሳቸው ሞት በኋላ እንግሊዞች ኢትዮጵያን ሙልጭ አድርገው ዘርፈው ሄደዋል፡፡ ይህን ዘረፋ በተመለከተ ከዚህ ቀደም አንድ ዶክመንተሪ ፊልም ሠርቼ ነበር፡፡ ከዚሁ ፊልም ውስጥ የተወሰኑትን አጠር አድርጌ ላቅርብላችሁ፡፡

*** *** ***

“ፋይናንሻል ታይምስ” የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ በአንድ ወቅት ሲዘግብ ዐፄ ቴዎድሮስ ከመቅደላ አምባ ላይ ከሞቱ በኋላ ከስፍራው ተወስደው ወደ ለንደን የመጡት የኢትዮጵያ የብራና ጽሁፎች ብቻ በገንዘብ ቢተመኑ ሁለት ቢሊዮን ፓውንድ ያወጣሉ ብሎ ፅፏል፡፡ አስቡት እንግዲህ፡፡ ብራናዎቹ ብቻ ናቸው ሁለት ቢሊዮን ፓውንድ የሚያወጡት፡፡

የዐፄ ቴዎድሮስ ልጅ የሆነው የልዑል ዓለማየሁ ታሪክም እንዲሁ አሳዛኝ ነው፡፡ ልዑል ዓለማየሁ ገና የስድስት ዓመት ህፃን ሳለ አባቱ ራሳቸውን በሽጉጥ አጠፉ፡፡ ከዚያ በፊት የእናቱ የእቴጌ ጥሩወርቅ አባት (አያቱ) ደጃች ውቤ ሞተዋል፡፡ እናቱም አጐቶቻቸውን ደጃዝማች ንጉሴ እና ደጃዝማች ተሰማን አጥቷል፡፡ አለማየሁ ዙሪያውን የተከበበው በቴዎድሮስ ጠላቶች ነው፡፡ እንግሊዞቹ ዓለማየሁ እና እናቱ እቴጌ ጥሩወርቅን ይዘው ወደ ለንደን መጓዝ ጀመሩ፡፡ እቴጌ ጥሩወርቅ መንገድ ላይ ታመሙ፡፡ ግንቦት 15 ቀን 1860 ዓ.ም አረፉ፡፡ ከዚያም በጀነራል ናፒር ትዕዛዝ ሬሳቸው ወደ ሸለቆት ስላሴ ቤተ-ክርስትያን እናታቸውና ዘመድ አዝማድ እየተላቀሰ መቀበራቸውን በዓይኑ ያየው እንግሊዛዊው ክሌመንትስ ማርክሃም A History of the Abyssinian Expedition በተባለው መጽሐፉ ውስጥ ገልጾታል፡፡ እናም ልዑል ዓለማየሁ ገና በስድስት ዓመቱ ይህን ሁሉ ቤተሰቡን አጣ፡፡ የእናቱ እናት አያቱ በእቴጌ ጥሩወርቅ ቀብር ወቅት ለንግስት ቪክቶሪያ የፃፉት ደብዳቤ ምን እንደሚል ታውቃላችሁ? እንዲህ ይላል፤ “በስመ አብ … ከወይዘሮ ላቂያዬ፤ የእቴጌ ጥሩወርቅ እናት፡፡ የደጃዝማች ዓለማየሁ አያት የተላከ፡፡ ይድረስ ለእንግሊዝ ንግስት፡፡ አንባቢው እጅ ይንሳልኝ፡፡ መድሃኒያለም ጤና ይስጥልኝ፤ መንግስትዎን ያስፋ፡፡ ጠላትዎን ያጥፋ፡፡ ሦሰት ደጃዝማቾችን (ባለቤቴን ደጃች ውቤን፣ የእህቴ ልጆች ደጃች ንጉሴንና ደጃች ተሰማን አጣሁ)፡፡ አራተኛ ልጄ እቴጌ ጥሩወርቅ ሞተውብኝ የቀረኝ ደጃዝማች ዓለማየሁ ብቻ ነው፡፡ አደራዎን ይጠብቁልኝ፡፡ እግዚአብሔር አባቱንና እናቱን ቢነሳው እርስዎን ሰጥቶታል፡፡ እኔም ካላየሁት ከሞቱት ቁጥር ነኝ፡፡ እርሰዎን እናቴ ይላል እንጂ እኔን እናቴ አይለኝም፡፡ አላሳደግሁትምና፡፡ እርሰዎ ያሳድጉት ስለ እግዚአብሔር ብለው” የሚል የመማፀኛ ደብዳቤ ፅፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ ልዑል ዓለማየሁ እንግሊዝ ከሄደ ከ12 ዓመት በኋላ በ1879 ዓ.ም ብቸኝነት እንደተሰማው ህይወቱ አለፈች፡፡ የልዑል ዓለማየሁ አፅሙ፣ አልባሳቶቹ፣ ጌጣጌጦቹ ሁሉ ለንደን ውስጥ ዛሬም አሉ፡፡

ለምሳሌ ካፒቴን ሆዚየር የተባለው የእንግሊዝ ተዋጊ እና ፀሐፊ ሲገልፅ፣ መቅደላ መላ ዙሪያዋን በእሣት መጋየቷን ገልጿል፡፡ የቴዎድሮስ ቤተ-መንግስት፣ መድሃኒያለም ቤተ-ክርስትያን እና መንደሩ ሁሉ ጋየ፡፡ እንደርሱ አገላለፅ ወደ ሦስት ሺ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ ጭሱ ሰማይ ላይ ትልቅ ደመና ሰርቶ እንደነበርም ያወሳል፡፡ ይሄ ሁሉ ተደርጐም ነው ቅርሶቹ የተዘፉት፡፡

የመቅደላ ቅርሶች የተሰበሰቡት በአፄ ቴዎድሮስ ነው፡፡ አፄው መቅደላን የኢትዮጵያ መዲና አደርጋለሁ ብለው እጅግ ግዙፍ የሆነ ሙዚየም እየከፈቱ ነበር፡፡ ለዚህም ሙዚየም ትልቅነት እንዲያገለግላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ቅርሶች ከያሉበት ሰብስበው መቅደላ ሙዚየም ውስጥ አከማችተዋቸው ነበር፡፡ እንግዲህ ይህ አጋጣሚ ነው ለእንግሊዞች ዘረፋ ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው፡፡

በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ የመቅደላ ቅርሶች ለቁጥር የሚያታክቱ ስለነበሩ የእንግሊዝ ወታደሮች እንዲከፋፈሏቸው ሁለት ቀን ሙሉ ጨረታ ተደረገ፡፡ እ.ኤ.አ ሚያዚያ 20 እና 21 ቀን 1868 ዓ.ም ላይ ማለት ነው፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ የሦስት ሺ ዓመታት የታሪክና የማንነት አንጡራ ሀብቶችን መቅደላ ላይ ተቀራመቷቸው፡፡ ለምሳሌ በጦርነቱ ወቅት ከብሪትሽ ሙዚየም ውስጥ አንድ ሠራተኛ የነበረው የቅርስ ባለሙያና የአርኪዮሎጂ ባለሙያ ተብሎ ከጦሩ ጋር መጥቶ ነበር፡፡ እናም ይህ ሰው በሁለቱ ቀናት ውስጥ ብቻ በጨረታ አሸንፎ የገዛቸው የኢትዮጵያ ድንቅ ብራናዎች በቁጥር 350 እንደነበሩ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ፅፈውታል፡፡ እነዚህ ብራናዎች ዛሬ ለንደን ብሪትሽ ሙዚየም ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ያልመጣ ባለሙያ የለም፡፡ ይህ የሙዚየም ባለሙያ የሆነው ሪቻርድ ሆልመስ በፃፈው ማስታወሻ እንደሚገልፀው፤ ዐፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ከገደሉ በኋላ የእንግሊዝ ባንዲራ መቅደላ ላይ ከአስር ደቂቃ በላይ አልተውለበለበም ይላል፡፡ ምክንያቱም ወደተከማቹት እጅግ ብርቅ እና ድንቅ የቅርሶች ዘረፋ መገባቱን ይናገራል፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው ቀን ላይ 61bs የሚመዝን ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተሰራ የጳጳስ አክሊል መውሰዱን ጽፏል፡፡ ከዚህ ሌላ ግዝፈታቸው በአንድ ሰው ሸክም የማይቻሉ ብራናዎች ሁሉ እንደተወሰዱም ገልጿል፡፡ እነዚህ ቅርሶች አብዛኛዎቹ አሁንም ለንደን ውስጥ አሉ፡፡ ስድስት እጅግ አስገራሚ ቅርሶች በመባል የሚታወቁ ብራናዎች ደግሞ ዊንድሶር ተብሎ የሚታወቀው ህንፃ ውስጥ በለንደን ሮያል ላይብረሪ ውስጥ አሉ፡፡ ሁለት መቶ ሌሎች እጅግ ውድ የሚባሉ የኢትዮጵያ ብራናዎች ደግሞ Bodleian ላይብረሪ ማለትም ለኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ፣ ለካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ላይብረሪ እና ማንችስተር ውስጥ ላለው ለጆን ራይላንድ ላይብረሪ ተከፋፍለዋል፡፡ ያከፋፈለው ደግሞ የጦርነቱ መሪ የነበረው ጀነራል ናፒር ነው፡፡

ጄነራል ናፒር ከጦርነቱ በኋላ ለጉብኝት በሄደባቸው ሀገሮች ሁሉ ለልዩ ልዩ ተቋማት የሚያቀርበው ገፀ-በረከት የኢትዮጵያን ታላላቅ ቅርሶች ነበር፡፡ ለምሳሌ ቬና ኦስትሪያ ውስጥ ለሚገኘው ሮያል ላይብረሪ የኢትዮጵያን ብራናዎች አበርክቷል፡፡ ለጀርመኑ ቄሳር ሁለት ታላላቅ ብራናዎችን እና ለፓሪሱ Biblioltheque National ተብሎ ለሚታወቀው ተቋም እጅግ ውድ የሚባሉ ብራናዎችን አበርክቷል፡፡

“እጅግ ውድ ብራናዎች” የሚባሉት ምን ዓይነት ናቸው?
አንደኛ የተፃፉበት የዘመን ርዝማኔ ነው፡፡ ሁለተኛ በውስጣቸው የያዙት ሃሳብ እና ቁም ነገር ነው፡፡ ሦስተኛ የተፃፉበት ማቴሪያል ነው፡፡ አራተኛ በየትኛውም አለም ላይ አለመኖራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የብራናው ቀለም በወርቅ የተፃፈ፣ ወርቅ እየነጠረ ወርቅን እንደ ቀለም እየተጠቀሙ የእግዚአብሔርን እና የማርያምን ስም በወርቅ እየፃፉ ያስቀመጡ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ደራሲዎች ነበሩ፡፡ የእነርሱ ስራዎች ናቸው እጅግ ውድ የሚባሉት፡፡

በጣም ብዙ ንብረቶች ናቸው የተወሰዱት
ለቁጥር ያታክታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ንብረቶች የተጫኑት በ15 ዝሆኖች፣ በ200 በቅሎዎች ነበር’ኮ፡፡ አንድ ነገር ልንገርህ፡፡ ኢትዮጵያ ውሰጥ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ውስጥ ፅላት እጅግ የተከበረ እና የሃይማኖቱም መገለጫ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ የማንነት መገለጫ የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ፅላት በመቅደላው ጦርነት ተዘርፎ የሄደው በቁጥር በርካታ ናቸው፡፡ ተመዝግበው የተቀመጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን አስር ፅላቶች ለንደን ውስጥ አሉ፡፡ ተዘርፈው የተወሰዱ ናቸው’ኮ! ፅላት ቤተ-መቅደስ ውስጥ እንጂ ሙዚየም ውሰጥ አይቀመጥም፡፡ ዘረፋው ይህን ያህል አዋርዶናል! ከነዚህም ሌላ በከበሩ ማዕድናት የተሰሩ መስቀሎች፣ ፀና ፅሎች፣ ከበሮዎች ልዩ ልዩ የቤተ-ክርስቲያን መገልገያዎች፣ በወርቅ የተሰሩ ትልልቅ ቁሳቁሶች ሁሉ ቀድሞ South Kensington ሙዚየም ተብሎ በሚጠራው አሁን ግን Victoria and Albert ሙዚየም በሚባለው ተቋም ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አንዳንድ የአፄ ቴዎድሮስ የግል ንብረቶች ደግሞ Museum Of Mankind ተብሎ በሚጠራው ተቋም ውስጥ አሉ፡፡

እነዚህን የሀገሪቱን ቅርሶች ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት እንዴት ነው?
ለብዙ ዘመናት ጥረት ተደርጓል፡፡ ግን እስከ አሁን ድረስ ይህን ያህል የሚነገርለት ጠንካራ ጥረት የለም፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአፄ ቴዎድሮስ በኋላ የነገሱት አፄ ዮሐንስ እ.ኤ.አ በኦገስት 10 1872 ዓ.ም ለንግስት ቪክቶሪያ ክብረ-ነገስት የተባለው ብራና እንዲመለስላቸው ደብዳቤ ፅፈው ነበር፡፡ በኋላ ኰፒው ተልኰላቸዋል፡፡ የቅርስ መመለስን ስናነሳ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡

አንዲት ሌዲ ሚዩክስ /Lady Meux/ የምትባል እንግሊዛዊት ነበረች፡፡ የእንግሊዝ ወታደሮች የኢትዮጵያን ቅርስ ዘርፈው ሲመጡ እየገዛቻቸው በግሏ ቅርስ የሰበሰበች ናት፡፡ በኋላም የቅርሶቹን ምንነት የሚያስረዳ ጽሁፍ አቅርባለች፡፡ የፅሁፉን መግለጫ የፃፈላት ደግሞ በጦርነቱ ተሳተፊ የነበረው ሰር ኤርነስት ዊል በጅ (Sir Ernest Willis Budge) የሚባል ሰው ነው፡፡ ታዲያ በአንድ ወቅት ማለትም እ.ኤ.አ በ1902 ዓ.ም የዐፄ ምኒልክ ቀኝ እጅ የነበሩት ራስ መኰንን (የጃንሆይ አባት) እንግሊዝን ሊጐበኙ ወደ ለንደን ይመጣሉ፡፡ እናም የሌዲ ሚዩክስን የኢትዮጵያን ቅርሶች ያያሉ፡፡ በጣም ተገረሙ፤ ተደነቁ፡፡ በሀገሬ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እንዲህ የሚያምሩ እና የሚደንቁ ቅርሶች የሉም፡፡ ወደ ሀገሬ ስመለስ ለዐፄ ምኒልክ ነግሬያቸው ገዝተናቸውም ቢሆን እንወስዳቸዋለን አሉ፡፡ ከዚያም ግንኙነቱ በረታ፡፡ ሴትየዋም በመጨረሻ ቅርሶቹ ወደ ሀገራቸው መመለስ አለባቸው ብላ እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 1910 ዓ.ም ወሰነች፡፡ እንግሊዝ ታመሰች፡፡ ነገር ግን ሌዲ ሚዩክስ ዲሴምበር 20 ቀን 1910 ድንገት ሞተች፡፡ የቅርሶቹ መመለስም በዚህ ምክንያት ተቋረጠ፡፡ ዘ ታይምስ የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ እ.ኤ.አ ፌብሩዋሪ ሰባት 1911 ዓ.ም ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፡-
“Many Persons interested in Oriental Christianity will view with regret the decision of lady Meux to send her Valuable once and for all out of the country” ይህ አባባል የሚያስረዳው አብዛኛው እንግሊዛዊ ቅርሶቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ሌዲ ሚዩክስ መወሰኗ ልክ እንዳልነበር እና የሚያስቆጭም እንደነበር ነው፡፡ ግን ምን ያደርጋል እሷም አፄ ምኒልክም ራስ መኰንንም ተከታትለው ሞቱ፡፡

ከነምኒልክ በኋላስ?
ወደ ስልጣን የመጡት ንግስት ዘውዲቱ እና አፄ ኃይለስላሴ ናቸው፡፡ ዐፄ ኃይለስላሴ ገና አልጋ ወራሽ እያሉ እ.ኤ.አ በ1924 ዓ.ም ለንደንን ጐብኝተው ነበር፡፡ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያም ሲመጡ የቴዎድሮስን የጭንቅላት አክሊል ከቪክቶሪያ እና ከአልበርት ሙዚየም አምጥተው ለንግስት ዘውዲቱ አስረክበዋል፡፡ በኋላም ንግስት ኤልሳቤጥ እ.ኤ.አ በ1965 ዓ.ም ኢትዮጵያን ሊጐበኙ ሲመጡ የአፄ ቴዎድሮስን ባርኔጣ እና ማሕተም ይዘው መጥተው ነበር፡፡ የደርግ ዘመን ደግሞ ከምዕራቡ ዓለም ጋር እሳትና ጭድ ሆነ፡፡ በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ በተለይም በስመ ጥሩው የታሪክ ሊቅ በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የሚመራ “አፍሮሜት” የሚባል የመቅደላ ቅርስ አስመላሽ ቡድን ተቋቁሞ ብዙ ሰርቷል፡፡ ለምሳሌ የአፄ ቴዎድሮስን የአንገት ክታብ አስመልሷል፡፡ ጋሻቸውንም አስመልሷል፡፡ ነገር ግን እነ ሪቻርድ ፓንክረስት እድሜ እየተጫጫናቸው ሲሄዱ ይህንን ትልቅ ኃላፊነት የሚረከብ ትኩስ ኃይል በመጥፋቱ ታላቁ አላማቸው ተቀዛቅዟል፡፡
ቴዲ አፍሮ ሆይ፤ የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር፣ ሹሩባ እንግሊዝ ውስጥ ነው፡፡ ስለ ታላላቅ ቅርሶችም ታቀነቅናለህ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

LEAVE A REPLY