መጽሐፉን ለማተም የሚደፍር ማተሚያ ቤት በድፍን ኢትዮጵያ ጠፍቷል
ዋዜማ ራዲዮ:- “ዘጭ እንቦጭ” የተሰኘ ርዕስ እንዳለው የተነገረና በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የተጻፈው ባለ ሦስት መቶ ገጽ አዲስ መጽሐፍ አታሚ ማጣቱን ለደራሲው ቅርብ የሆኑ ግለሰቦች ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት መጽሐፉን ለማሳተም በከተማዋ የሚገኙ በርካታ ማተሚያ ቤቶች እንደተንከራተቱ የገለጹት ለፕሮፌሰሩ ቅርብ የኾኑ ምንጮች ኾኖም አታሚዎች ገና የደራሲውን ስም ሲመለከቱ ድንጋጤ ዉስጥ እንደሚዘፈቁ ተናግረዋል፡፡
‹‹አንዳንዶች ‹‹እባካችሁ ችግር ዉስጥ አትንከተቱን፣ ሠርተን እንኑርበት›› ይሉናል፤ “የከፈልነውን ቀብድ መልሰው የሚሰጡንም አሉ›› ትላለች ረቂቁን በማሳተም ረገድ ጥረት እያደረጉ ካሉ ወጣቶች አንዷ ስለሁኔታው ተጠይቃ ስታብራራ፡፡፡፡
ማተሚያ ቤቶች በበኩላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ፡፡ ከኮማንድ ፖስት ሴክሬቴሪያት “የይታተምላቸው” የድጋፍ ደብዳቤ ካመጣችሁ እናትምላችኋለን የሚሉ የማተሚያ ቤት ኃላፊዎች እንዳጋጠሟትም ይህቺው ወጣት ተናግራለች፡፡
50ሺህ ኮፒዎችን ለማተም ዝግጅት ተደርጎ በሰኔ ወር መጀመርያ አንባቢ እጅ እንደሚደርስ ታሳቢ ተደርጎ የነበረው ይህ የፕሮፌሰር መስፍን አዲስ መጽሐፍ ዋና ይዘት ምን እንደሆነ ለደራሲው ቅርበት ያላቸው ወገኖች ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ኾኖም ወቅታዊውን የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ላይ መውደቅ የሚዳስስ ክፍል እንዳለው ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ ፕሮፌሰር መስፍን አገቱኒ፣ የክህደት ቁልቁለት፣ መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ እና አዳፍኔ የተሰኙ አወዛጋቢና ሰፊ መነጋገሪያ መሆን የቻሉ መጻሕፍትን ለአንባቢ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
ፕሮፌስር መስፍን ለረጅም ዘመናት በአደባባይ ተሟጋችነት የሚታወቁ በሀገር ጉዳይ “ያጋባኛል” የሚሉ በዚህ አቋማቸውም ወህኒ እስከመውረድ የደረሱ ምሁር ናቸው።