/እዚህ ጽሁፍ ዉስጥ ያለዉ ሀሳብ በሙሉ የኔ የግሌ፥የኔና የኔ ብቻ ነዉ/
“አንድ መቶ ሃምሳ መንገደኞችን ይዞ ከለንደን ወደ ቻይና ሲጓዝ የነበረ ቦይንግ 720 የመንገደኞች ማመላለሻ አዉሮፕላን መሬት ላይ ወድቆ ተከሰከሰ . . . . በህይወት የተረፈ መንገደኛ እንደሌለ ከአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የደረሰን ዜና ያስረዳል”… የኢትዮጵያ ሬዲዮ እንዲህ አይነት ዜና እያሰማኝ ነዉ ያደኩት። “በህይወት የተረፈ መንገደኛ የለም” የሚለዉ ዜና ዛሬም ድረስ የጉዞ ነገር ሲነሳ ያስፈራኛል። አደራ ቦቅቧቃ እንዳትሉኝ! “Phobia” እንጂ ፍርሀት የለብኝም። ፍርሃትና “Phobia” ደግሞ ለየብቻ ናቸዉ፥ ሰዉ ሞት ፈርቶ ወደ ሞት አይሄድም። እንግዲህ ይታያችሁ ይህ “Phobia” በተለይ “ፍላይት ፎቢያ” የሚሉት ነገር ነዉ “አዉስትራሊያ ትሄዳለህ” የሚባል ዜና ሲነገረኝ ከብዙ ወገኖቼ ጋር የሚያገናኘኝ መልካም ዜና እንደ መርዶ የከበደኝ። እግዚአብሄር ይመስገን በሠላም ደርሼ በሠላም ተመልሻለሁ! የአዉሮፕላን ጉዞና ፍርሀቱ ግን ሸገር ገብቼ እፎይ እስክል ድረስ ይቀጥላል . . . . ከዚያ በኋላማ ቢመጣስ ሸገር ላይ ሆኖ ማን ይፈራል?
ከአስመራ ኦሺኒያ ደርሼ እስክመለስ 18 ግዜ አዉሮፕላን ቀያይርያለሁ፥ በሰባት አገሮች ዉስጥ በ12 የተለያዩ አዉሮፕላን ማረፊያዎች ዉስጥ አልፍያለሁ፥ ወደ ሰባ ሰአታት አካባቢ አየር ላይ ቆይቻለሁ። የበረራዉን ነገር በተለይ ርዝመቱን ግን አታንሱብኝ! ተኝቼ ስነቃ ሰማይ ላይ ነኝ፥አሁንም ተኝቼ ስነቃ እዚያዉ ሰማይ ላይ ነኝ። አንድ ሰአት፥ አራት ሰአት፥ ስድስት ሰአት፥ አስር ሰአት… ረጂም ሰአት ሰማይ፥ ሰማይ፥ ሰማይ ብቻ! አንጋጥጬ ወደላይ ሳይ የሚታየኝ ሰማያዊ ቀለም ነዉ። “በስመአብ” ብዬ ሳጎነብስም የሚታየኝ ያዉ ሰማያዊ ቀለም ነዉ። ሰማዩ ሰማያዊ ዉኋዉም የሰማዩን ቀለም ተዉሶ ሰማያዊ ነዉ። ደሞኮ የፍርሃት ነገር ሆኖ ነዉ አንጂ ሰዉ በሁለት ግዙፍ ሰማያዊ አካላት መካከል እየበረረ ይፈላሰፋል እንጂ እንዴት ይፈራል! ወይ ፍርሃት . . . . ፍርሃት መጥፎ ነገር ነዉ። ሰዉ ሲፈራ የሚወደዉን ነገር ይጠላል፥ ሰዉ ሲፈራ የናቀዉንና ያዋረደዉን ያከብራል፥ ሰዉ ሲፈራ ረግጦ ለሚገዛዉ ይሰግዳል . . . . ሰዉ ሲፈራ ነጻነቱን የቀማዉን ጎንበስ ብሎ ያገለግላል . . . . ሰዉ ሲፈራ ህይወቱን ተቀምቶ ኑሮ ይናፍቀዋል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ነጻ ሆነን የራሳችንን ኑሮ ለመኖር እኔም ተዝናንቼ ለመብረር ማድረግ ያለብን አንድ ነገር ቢኖር ፍርሃን ማስወገድ ብቻ ነዉ። የሚገርማችሁ “ካሁን በኋላ መፍራት ያለብን ፍርሃትን ብቻ ነዉ” የሚለዉ የፕሬዚደንት ሩዝቨልት አባባል ምድር ላይ ሆኜ ምንም አይመስለኝም ነበር። የአባባሉ ትርጉም በትክክል የገባኝና ሰዉየዉን ያደነቅኳቸዉ በሁለት ሰማያዊ አካላት መካከል ስበር ነዉ።
የአዉሮፕላኑ አብራሪ ሆስተሶቹን ሲንጋፖር ልናርፍ ነዉና ቦታ ቦታችሁን ያዙ ብሎ ሲናገር… ያ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተማሪ እያለሁ የማዉቀዉ የብርቲሽ “አክሰንት” እንቅልፌን ቀማኝ። ከ13 ሰአት በረራ በኋላ ሲንጋፖር ስደርስ አዉስትራሊያ የደረስኩ መስሎኝ ደስ አለኝ። አለመድረሴን ያወቅኩት “ትራንዚት” መንገደኞች በዚህ በኩል እለፉ ተብሎ ሲነገር ነዉ። ይታያችሁ 13 ሰአት በርሬ የመጀመሪያ ስብሰባዬን የማደርግበት ከተማ ለመድረስ ገና የ11 ሰአት በረራ ይጠብቀኛል። ምን ልሁን? እንዴት ልሁን? ዝም ብዬ እንዳልቀመጥ ከ13 ሰአት በላይ የተቀመጥኩበት መቀመጫዬ ደንዝዞ የኔ መሆኑን እረስቼዋለሁ። ፈታ ልበል ብዬ ከመቀመጫዬ ብድግ ስል እግሬ ሰዉነቴን መሸከም አቅቶት ተመልሼ መቀመጫዉ ላይ ዘጭ አልኩ። የጀርባዬን ነገርማ ተዉት አገግሞ ስታገኙት እሱ እራሱ ይነግራችኋል።
ስድኒ አዉሮፕላን ማረፊያ የአንድ ሰአት ተኩል ቆይታ ካደረኩ በኋላ ጉዞ ወደ ኦክላንድ ኒዉዚላንድ ሆነ። ኦክላንድ የኒዉዚላንድ ትልቁ ከተማ ነዉ፥ ኒውዚላንድ ዉስጥ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ያሉትም እዚሁ ኦክላንድ ዉስጥ ነዉ። ኦክላንድ አዉሮፕላን ማረፊያ ስደርስ ከዚህ ቀደም መልካቸዉን ላይ ቀርቶ ስማቸዉን እንኳን ሰምቼ የማላዉቅ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉልኝ አቀባበል በቅርቡ አቦይ ስብሐት የፈጠራ ታሪክ ነዉ እንጂ “ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት” ብሎ ነገር የለም ብለዉ የተናገሩት ንግግር ሰዉዬዉ እንደ ብረት የዛጉና ጭንቅላታቸዉም እንደ አባባ ጎርፉ ቮልስዋገን የወላለቀ መሆኑን አረጋገጠልኝ።
የአዳራሹ ዉጭና ዉስጥ በአረንጓዴ፥ ቢጫ፥ ቀይ ቀለም ደምቋል። ወደ አዳራሹ ስገባ ከፊት ሆነዉ የሚመሩኝና ከኋላዬ የሚከተሉኝ ወጣቶች የያዙትም የለበሱትም የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ነዉ። ብቻ ምን ልበላችሁ ሀሙስ ማርች 23 ከኦክላንድ አዉሮፕላን ጣቢያ ስወጣ ጀምሮ የተከተለኝ የኦክላንዶች ፍቅርና መስተንግዶ እሁድ ማርች ሃያ አምስት ስብሰባዉ አዳራሽ ዉስጥ ተከትሎኝ ገባ። የዕለቱ የስብሰባ መሪ . . . . . ስሜን ጠርቶ ወደ መናገሪያዉ ቦታ ሲጋብዘኝ አዳራሹ ዉስጥ ይሰማ የነበረዉ ጭብጨባና ሆታ በአንድ በኩል አዳራሹ ዉስጥ ያለዉ ህዝብ ወክዬዉ ለቆምኩት ድርጅትና ለኔ ያለዉን ክብር ይገልጻልና ክብርና ኩራት ተሰማኝ፥ በሌላ በኩል ግን እኔም ንቅናቄዬም የተሸከምነዉ ህዝባዊ አደራ ትዝ ሲለኝ… እንወጣዉ ይሆን የሚል ሀሳብ ሰዉነቴን ካላይ ታች ወረረዉና ለግዜዉም ቢሆን አደራዉ ከበደኝ። እመኑኝ የተሸከምኩትን ህዝባዊ አደራ እኔ ባልወጣዉ በኔ ላይ ተረማምዶ የሚመጣዉ ትዉልድ ይወጣዋል እንጂ እቺ የአዋቂዎች አገር አለማወቃቸዉን በማያዉቁ አላዋቂዎች እየተገዛች አትኖርም!
ኒዉዚላንድ 4 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባት ትንሽ አገር ናት፥ ሩቅ አገር ናት፥ ዳር አገር ናት። ከኒዉዚላንድ በኋላ ወደ መጡበት መመለስ ነዉ እንጂ ሌላ አገር የለም። ኢትዮጵያዊያን በብዛት ከማይኖሩባቸዉ አገሮች ዉስጥ አንዷ ኒዉዚላንድ ናት። የኒዉዚላንድ ኢትዮጵያዊያን ግን ያገር መዉደድ መለኪያዉ ብዛት ሳይሆን ጽናት፥ ቁጥር ሳይሆን ፍቅር መሆኑን በተግባር አሳዩኝ። የኒዉዚላንድ አበሾችና እዚያዉ ኦሺኒያ አካባቢ የሚገኝ አንድ ወፍ ይመሳሰሉብኛል። ይህን የምላችሁን ወፍ “Zoo” ዉስጥ ሲጮህ ሰምቼዉ አጠገቡ ሌላ ትልቅ ወፍ መፈለግ ጀመርኩ – ምክንያቱም ያንን የመሰለ ወዲህ ማዶ ሆኖ ወዲያ ማዶ የሚሰማ ድምጽ ከዚያ ትንሽ ወፍ አፍ የሚወጣ አይመስልም። ኒዉዚላንዶችም አገርን ለማዳን ለሚደረገዉ የጋራ ትግል ያደረጉት አስተዋጽኦ ከነሱ የወጣ አይመስልም! . . . . ስለኒዉዚላንዶች ብዙ ማለት ይቻላል . . . . ለግዜዉ “ኪያ ኦራ” ብያቸዉ ልሰናበት።
አዉስትራሊያ ዙሪያዋን በዉኋ የታጠረች አገር ናት፥ ሲድኒ፥ ሜልቦርን፥ ብርስበርን፥ፐርዝና አደላይድን የመሳሰሉ ብዙ ህዝብ የሚኖርባቸዉ ትልልቆቹ የአዉስትራሊያ ከተማዎች የሚገኙት ጥግ ጥጉን የአትላንቲክ፥ የህንድና የሠላማዊ ዉቂያኖስን ዳርቻ ተከትለዉ ነዉ። አዉስትራሊያ ውስጥ የመጀመሪያዉን ስብሰባዬን ያካሄድኩት ፐርዝ የሚባል ከተማ ዉስጥ ነዉ። ፐርዝ የምዕራባዊዉ አዉስትራሊያ ግዛት ዋና ከተማ ናት። እንደ አዉሮፓ ዘመን አቆጣጠር በ1829 ዓም እንግሊዛዊዉ ካፕቴን ጀምስ ስተርሊንግ እንደመሰረታት የሚነገርላት ፐርዝ አዉስትራሊያ ዉስጥ ካሉት ትልልቅ ከተማዎች አራተኛዋ ናት። የፐርዝ ዉበቷ ዉሃዎቿ ናቸዉ። በዉቅያኖስና በወንዞች የተከበበችዉ ፐርዝ ፈጣሪ ታይቶ በማይጠገብ የተፈጥሮ ዉበት ያደላት ቆንጅዬ ከተማ ናት። ፐርዝ ዉስጥ የሚገኘዉ ወንዝ በአገሬዉ በአቦርጂኖች ቋንቋ “ደርባርል የሪጋን” በሚል መጠሪያ ስም ነበር የሚታወቀዉ፥ ዕድሜ ለእንግሊዝ ወራሪዎች ዛሬ የሚታወቀዉ “ስዋን ወንዝ” በሚል መጠሪያ ነዉ። ይህ ፐርዝን ግራና ቀኝ እየገላመጠና ከምስራቅ ወደ ምዕራብ እየፈሰሰ ህንድ ዉቅያኖስ ዉስጥ የሚገባዉ ወንዝ የፐርዝ ከተማ የዉበት ምንጭ ነዉ።
ቅዳሜ ማርች 25 ቀን ኦክላንድ ዉስጥ መደበኛና የቤት ዉስጥ ስብሰባዬን ጨርሼ ማታ አልጋ ላይ የወጣሁት በነጋታው አዉሮፕላን ጣቢያ ለመሄድ አምስት ሰአት ሲቀረኝ ነው። ከኦክላንድ-ኒዉዚላንድ ፐርዝ-አዉስትራሊያ በአዉሮፕላን የሰባት ሰአት መንገድ ነዉ። ፐርዝ ስብሰባ አዳራሽ የገባሁት ከአዉሮፕላን ጣቢያ ወጥቼ ለምሳ የሁለት ሰአት ቆይታ ካደረኩ በኋላ ቢሆንም የፐርዞች መስተንግዶ ብርታት ሆኖኝ ድካም የሚባል ነገር ሰዉነቴ ዉስጥ አልነበረም። ፐርዝ፥ ብርስበርን፥ሜልቦርን፥ አደላይድና ሲድኒ አዉሮፕላን ጣቢያ ስደርስና በየከተማዎቹ በቆየሁባቸዉ ቀኖች የኦዚ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉልኝ አቀባበል ትዝታዉ አሥመራ ድረስ ተከትሎኝ ገብቶ ዛሬም ደክሞኝ ሳዛጋ ፊቴ ላይ እየመጣ ድቅን የሚለዉ የኦዚዎች ፍቅርና ፈገግታ ነዉ እንጂ ያ የምወደዉ ቡና አይደለም። ኦዚዎች በልቼ የጠገብኩ አይመስላቸዉም፥ ጠጥቼም የምረካ አይመስላቸዉም። ሁሉም ሲያገኙኝ ብላ፥ ጠጣ ተጫወት ብቻ ነበር የሚሉኝ። የኦዝዎች ግብዣ እንዳፍላ ፍቅር አሁንም አሁንም ነዉ። ኦዚዎች ሰዉ እንኳን ርቋቸዉ ሄዶ አብሯቸዉ እያለም ይናፍቃሉ። አሁንማ ስተኛ “ፐርዞች” ስነቃ “ሜልቦርኖች”፥ እራት ላይ “ስድኒዎች” ምሳ ላይ “አደላይዶች” ቁርስ ላይ “ብርስበርኖች” ሆነዋል በምናቤ እየመጡ በርታ፥ አይዞህ፥ አለንልህ እያሉ የሚያበረታቱኝ! ብቻ ምን አለፋችሁ እዚህ በረሃ ዉስጥ ሁሉም ነገሬ ኦዚ . . .ኦዚ . . . ኦዚ ብቻ ሆኗል። ኦዚዎችች በሉ እንግዲህ አገራችሁ ሩቅ ቢሆንም ፍቅራችሁ፥ትህትናችሁና ቸርነታችሁ ከልጓም ይስባልና ያንን ሩቅ መንገድ ተስቤም ተጎትቼም እንደገና መድፈሬ አይቀርም!
አዉስትራሊያ ዉስጥ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ጋር የመጀመሪያዉን ስብሰባ ያደረኩት ፐርዝ ዉስጥ ነዉ፥ ኦሺኒያ ዉስጥ ያለዉን ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ትኩሳት በመጠኑም ቢሆን መለካት የቻልኩትም እዚሁ ፐርዝ ዉስጥ ነዉ። አዉስትራሊያ ዉስጥ ከፐርዝ በተጨማሪ ብርስበርን፥ ሜልቦርን፥ አደላይድና ሲድኒ ዉስጥ ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ጋር በቅርብ ተገናኝቼ መወያየት ችያለሁ። ፐርዝ ዉስጥ መለስ ዜናዊን “ሰንደቅ አላማ ጨርቅ ነዉ” ስትል ምን ማለትህ ነዉ ብሎ የጠየቀዉን ጋዜጠኛና የህወሓትን ትክክለኛ ምንነትና ማንነት ፍርጥርጥ አድርጎ ለኢትዮጵያ ህዝብ የተናገረዉን ገብረመድህን አርአያን አግኝቼ ከሌላ ከየትም ቦታ ማግኘት የማልችላቸዉን ብዙ መረጃዎች ከእነዚህ ሁለት ወገኖቼ ማግኘት ችያለሁ። ገብረመድህን አርአያ ከህወሓት የቀድሞ ታጋዮች ዉስጥ ህወሓት የፈጸማቸዉን ወንጀሎችና ባጠቃላይ የህወሓትን ስዉር አላማ ምንም ሳይደብቅ የተናገረ ብቸኛ ሰዉ በመሆኑ ለዚህ ኢትዮጵያዊ ያለኝ ክብርና አድናቆት ከፍተኛ ነዉ።
ሜልቦርን ዉስጥ ህወሓትን ከሰላሳ አመት በላይ የታገሉና ዛሬ ዕድሜያችዉ በሰባዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኝ አዛዉንት ቤት ሄጄ ከሳቸዉና ከሌሎች መሰል ጓደኞቻቸዉ ጋር ለሰአታት ተወያይተናል። እነዚህ አባቶቻቸዉ ከጣሊያን ወራሪዎች ጋር የተዋደቁና እነሱም ለኢትዮጵያ አንድነት ዋጋ የከፈሉ ጀግኖች አደራ ያሉኝ ቃልና ባጠቃላይ ኦሺኒያ ዉስጥ አጠገቤ መጥተዉ ያናገሩኝ ሴቶች፥ ወንዶች፥ ወጣቶችና አዛዉንት ኢትዮጵያዊያዊያን ዕምባ እየተናነቃቸዉ . . . . “ኤፍሬም” አደራ እያሉ ያዋዩኝ ሀሳብ ተመሳሳይ ነዉ። የሁሉም ጭንቀት ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ አንድነት ነዉ። የኦዚ ኢትዮጵያዊያን ማንነታቸዉን በኢትዮጵያዊነት ዉስጥ የሚያዩ አስተዋይና አርቆ አሳቢ ሰዎች እንጂ የዘዉግና የክልል እስረኞች አይደሉም።
ኦዚዎችና ኒዉዚላንዶች ያስተማሩኝ አንድ ትልቅ ትምህርት ቢኖር . . . . ከኢትዮጵያዊነት ዉጭ ወያኔን እንደማናሸንፍና በኢትዮጵያዊነት ስም ተሰልፈን ደግሞ በፍጹም እንደማንሸነፍ ነዉ። ይህ አባባል ኦሺኒያ ዉስጥ ዘርና ቋንቋ ሳይለይ የወንዱም፥ የሴቱም፥ የወጣቱም የሽማግሌዉም ኢትዮጵያዊ ሙሉ እምነትና ፍላጎት የተሞላበት አባባል ነዉ። አዉስትራሊያ ዉስጥ የሚኖሩ ዕድሜያችዉ በሰባዎቹ መጨረሻና በሰማኒያዎቹ መጀመሪያ የሚገኝ ኢትዮጵያዊያን አባቶቼም የነገሩኝ እነሱ ከአባቶቻቸዉ ተረክበዉ ለኔ ትዉልድ ያስተላለፏትን ኢትዮጵያ የኔ ትዉልድ ለልጅ ልጆቹ ማስተላለፍ የሚችለዉ እራሱን እንደ ኢትዮጵያዊ ሲመለከት ብቻ እንደሆነ ነዉ። ሜልቦርን ዉስጥ መኖሪያ ቤታቸዉ ድረስ ሄጄ ያናገርኳቸዉ አባት ዛሬም ድረስ ትዝ ይሉኛል። እኚህ አባት እንዲህ ብለዉ ነበር ያጫወቱኝ . . . ልጄ የ“ቴዎድሮስ ዘር ነኝ” እያለ የሚሰብከዉን ዉሸታም ሁሉ አደራ እንዳታምነዉ፥ ቴዎድሮስ አንድነትን እንጂ ልዩነትን አልሰበከም . . . . . እዉነታቸውን ነዉ! አጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መሳፍንትን ዘግተዉ ዘመነ አንድነትን ጀመሩ እንጂ እንደዛሬዎቹ የሳቸዉ ልጆች ነን ባዮች ቋንቋና ዘርን አልሰበኩም። አንድ ኢትዮጵያዊ የ“ቴዎድሮስ ልጅ” ነኝ ለማለት ቋራ፥ ጎንደር ወይም አማራ ክልል መወለድ የለበትም። ኢትዮጵያዊ የትም ይወለድ የት አንድነትን እስከሰበከ ድረስ የቴዎድሮስ ልጅ ነዉ። የቴዎድሮስ ትልቅነትና አዋቂነት ይዞት የተነሳዉ ራዕይ ነዉ እንጂ የተወለደበት ቦታ አይደለም።
ቀኑ ቅዳሜ ሚያዚያ ዘጠኝ ቦታዉ አደላይድ አዉስትራሊያ ነዉ። አደላይድ ብዙ አበሾች የማይታዩባት የደቡባዊዉ አዉስትራሊያ ግዛት ዋና ከተማ ናት። ከአራት ሰአት በላይ የፈጀዉ ስብሰባ አልቆ ከመቀመጫዬ ልነሳ ስል አንድ ምርኩዝ የያዙ አዛዉንት መድረኩ ላይ ወጥተዉ አጠገቤ ተቀመጡና ታሪካቸዉን ያጫዉቱኝ ጀመር። የታሪካቸዉ ርዝመትና የገድላቸዉ ብዛት ትንሽነቴን በትልቅነታቸዉ ዉስጥ አሳየኝና “ምን ሰራሁ” ብዬ እራሴን መጠየቅ ጀመርኩ። መልሴ “ምንም” ሲሆንብኝ በራሴ አፈርኩ። ሰዉዬዉ የህወሓትን ወራሪ ጦር ወልቃይት ዉስጥ ከአስራ አምስት አመት በላይ የተዋጉ ጀግና ናቸዉ። ዕድሜ ተጫጭኗቸዉ ሰዉነታቸዉ ደክሟል፥ መንፈሳቸዉና ህወሓትን የማሸነፍ ፍላጎታቸዉ ግን እንደብረት የጠነከረ ነዉ። ስለ ወልቃይት ሲናገሩ ከአፋቸዉ ከሚወጣዉ ቃል ይልቅ የሚንቀጠቀጠዉ ጉንጫቸዉ ህወሓት ወልቃይት ዉስጥ የሚፈጽመዉን የዘር ማጽዳት ወንጀል በጉልህ ይናገራል። አንዳንዶቹ ወንጀሎች እንኳን በኛ በሰዎች ባህል በአራዊትም ባህል ጸያፍ ናቸዉና አልደግማቸዉም። እኚህ ባለብዙ ታሪክ ኢትዮጵያዊ ህወሓት በ1972 ዓም ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይትን ከጎንደር ቆርጦ ትግራይ ላይ ሲቀጥል “እምቢ አሻፈረኝ” ብለዉ ህወሓትን ለብዙ አመታት የታገሉ ሰዉ ናቸዉ። እኚህ ቆራጥ ወልቃይቴ የህወሓትን ወራሪ ጦር ለመፋለም “ዱር ቤቴ” ከማለታቸዉ በፊት ከብዙ የህወሓት ካድሬዎች ጋር ተገናኝተዉ በወልቃይት ጠገዴ ማንነት ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል። አንድ የወያኔ ካድሬ እኚህ በህይወታቸዉ የቆረጡ ሰዉ ወልቃይት ጠገዴ የማነዉ በሚለዉ ጥያቄ ላይ ያላቸዉን የማያወላዉል አቋም ከተመለከተ በኋላ እንዲህ ብሎ ነበር ያስፈራራቸዉ . . . . “በወልቃይት ትግራይነት የማያምን ሁሉ ቀኑ ይጨልምበታል፥ የወልቃይትን ትግራይነት የሚቀበል ግን ጨለማዉ ይበራለታል”። ህወሓቶች ሁለት ቀን መኪና ስለነዱ ሂሊኮፕተር ካላበረርን የሚሉ ቂሎች ናቸዉና አባባሉ አልገረመኝም፥ ደሞም ነገሩ “ቀን የሰጠዉ ቂል ድንጋይ የሰብራል” ነዉና የካድሬዉ ድፍረትም አልገረመኝም። እኔን የገረመኝ እነዚህ ቀን ማጨለም፥ ጨለማዉን ማብራትና “ተራራ ማንቀጥቀጥ” የሚችሉ ሰዎች ለምን እነሱ እራሳቸዉ ድፍን ሃያ ስድስት አመት ከኖሩበት ድቅድቅ ጨለማ ዉስጥ መዉጣት እንዳቃታቸዉ ነዉ . . . . ወይስ ጨለማዉን ይወዱታል?
እኛ ኢትዮጵያዊያን አዉስትራሊያ እንሁን አሜሪካ፥ አዉሮፓ እንሁን ወይም አፍሪካ በየተሰበሰብንበት ቦታ ሁሉ “ኢትዮጵያ አገራችን” የምትለዉ ስንኝ መዝሙራችንም፥ ዘፈናችንም፥ መተከዣችንም መዝናኛችንም ናት . . . አዎ! ኢትዮጵያዊያን አገር በመዉደድ አንታማም። አገር መዉደድ ሲባል ግን የምንወደዉ የግድ የተወለድንበትን ቦታ ብቻ መሆን የለበትም፥ ተራራዉን፥ ወንዙንና ጫካዉን ብቻም መሆን የለበትም። አንድ ኢትዮጵያዊ አገሬን አወዳለሁ ሲል በዚህ ትልቅ አባባል ዉስጥ በፍትሃዊነትና በሚዛናዊነት ላይ የተመሰረተ የህይወት መርህ ሊኖረዉ ይገባል። አገሬን እወዳለሁ ማለት ለዚህ በፍትሃዊነትና በሚዛናዊነት ላይ ለተመሰረተ መርህ ታማኝ ሆኖ መኖር ማለት ነዉ። እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደዚህ አይነት ጠንካራ መርህ እንዲኖረን የግድ አማራ ሆነን፥ ትግሬ ሆነን ወይም ኦሮሞ ሆነን ወዘተ መፈጠር የለብንም። ኢትዮጵያ የምትባል አገር ዉስጥ ሰዉ ሆነን መፈጠር ብቻ ነዉ ያለብን። ዛሬ እንዲህ አይነቶቹ ትላልቅ የኢትዮጵያዊነት እሴቶች ተረስተዉ በአንዳንድ የፖለቲካ መድረኮች ላይ በአገር መዉደድ ስም ብሄረተኝነት እየተሰበከ ነዉ። ይህ አደገኛ ስብከት አገራችን የምትገኝበትን ሁኔታ በሚገባ ካለመረዳት፥ ከግድ የለሽነት፥ ለራስ ጥቅም ከመቆምና አገር ወዳድነትንና ብሄረተኛነትን ለያይቶ ካለማየት የሚመጣ በግዜ ካልታከሙት የማይድን በሽታ ነዉ። በአገር ወዳድነትና በብሄረተኛነት መካከል የሰማይንና የምድርን ያክል ትልቅ ልዩነት አለ። አገር ወዳዶች ሰዎችን ለያይተዉ የሚያዩበት የዘር መነጽር የላቸዉም፥ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከቱት እንደወገናቸዉ ነዉ። ብሄረተኞች ግን ከነሱ ብሄር ዉጭ የሆነዉን ዜጋ ሁሉ እንደራሳቸዉ አድርገዉ አይመለከቱም። ለአገር ወዳዶች የሁሉም ነገር መነሻና መድረሻ አገርና ዜግነት ነዉ፥ለብሄረተኞች ግን የሁሉም ነገር መነሻና መድረሻ የነሱ ብሄር ብቻ ነዉ። ስለዚህ ብሄረተኞች ከአፋቸዉ የሚወጣዉ ቃል ሁሉ “እነሱና እኛ” ሲሆን አገር ወዳዶች ግን ንግግራቸዉ የሚጀምረዉ “እኛ” በሚል ሁሉን አቀፍ ቃል ነዉ። ዛሬ እያንዳንዳችን የፈለገዉን ያክል ጠንካራ የብሄር ድርጅት ቢኖረንም ህወሓትን በተናጠል ገጥመን ማሸነፍ አንችልም፥ ምክንያቱም በብሄር የተደራጁ ሀይሎች ሁሉ እንደ ጠላት አድርገዉ የሚመለከቱት ህወሓትን ብቻ ሳይሆን ከራሳቸዉ ዉጭ ያለውን ብሄር ሁሉ ነዉ። ስለዚህ እርስ በርስ እየተዋጋን ህወሓትን እናሸንፋለን ማለት ዘበት ነዉ።
ከቅርብ ግዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረኮች ላይ መሰማት የጀመረ አንድ እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ ስብከት አለ . . . . እሱም የ“አማራዉ አማራ ሆኖ መደራጀት የአማራንም የኢትዮጵያንም ነፃነት ያፋጥናል” የሚለዉ ምንም አይነት መሠረት የሌለዉ ስብከት ነዉ። የዚህ ስብከት መሰረተ ቢስነት የሚጀምረዉ ከሰባኪዎቹ ማንነት ነዉ። የዚህ ስብከት ሰባኪዎች ከጥቂት አመታት በፊት አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ከኦነግ ጋር ዉይይት ሲጀምሩ “በዘር ከተደራጀ ድርጅት ጋር ዉይይት እንዴት ተብሎ” እያሉ ዉይይቱን ይኮንኑ የነበሩና ባጠቃላይ በዘር መደራጀት ኃጢያት ነዉ እያሉ የሚራገሙ ግለሰቦች ነበሩ። እነዚህ ግለሰቦች ከላይ ከሰማይ ተቀብተዉ የተላኩ የዘመናችን ነቢያት ካልሆኑ በቀር የኦሮሞን በዘር መደራጀት ኃጢያት የነሱን በዘር መደራጀት ፅድቅ የሚያደርገዉ ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም። ማንም ተደራጀ ማን የዘር ፓለቲካና በዘር መደራጀት የአንድን አገር ፖለቲካ የአልጋ ቁራኛ የሚያደርግ መርዝ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ አንድ ብሄር በተናጠል የሚወስዳቸዉ እርምጃዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃነት ሊያራዝመዉ ወይም ሊያሳጥረዉ ይችላል፥ ከዚህ በተረፈ ግን ማንም ብሄር በራሱ ወይም ብቻዉን የኢትዮጵያ ነፃነት ዋስትና መሆን አይችልም። የኢትዮጵያ ነፃነት ዋስትና የኢትዮጵያ ህዝብ ነዉ። ነፃ ከወጣን እንደ ህዝብና እንደ አገር ነዉ ነፃ የምንወጣዉ፥ እየተረገጥን ከተገዛንም እንደ ህዝብና እንደ አገር ነዉ የምንረገጠው። ከዚህ እዉነት ዉጭ አማራዉ በዘር ተደራጅቶ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን በተለየ መንገድ የኢትዮጵያ ጠባቂ ይሆናል የሚለዉ አባባል እራስን አግዝፎ ወይም ሌሎችን አሳንሶ ከማየት የሚመጣ የአዕምሮ በሽታ ነዉ። ያንተን ጉዳይ “እኔ አዉቅልሃለሁ” የሚባልበት ዘመን አክትሟል። የአማራዉ በዘር መደራጀት የሚጠቅም ከሆነ የሚጠቅመዉ ይህንን አላማ የሚያራምዱትን ጥቅት የፖለቲካ ልህቃን ብቻ ነዉ። እዉነቱን እንናገር ከተባለ የአማራዉ በዘር መደራጀት በአንድ በኩል ህወሓት ከተቃዋሚዉ ጎራ የሚፈልገዉ ትልቁ ስጦታ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የአማራዉ በዘር መደራጀት ኢትዮጵያ ከተጋረጡባት አደጋዎች ሁሉ ትልቁ ነዉ። ለዚህም ይመስለኛል የአማራዉን በዘር መደራጀት ከማንም በላይ አብዝቶ የሚኮንነዉ አማራዉ እራሱ የሆነዉ። ለመሆኑ በአማራዉ በዘር መደራጀት ኢትዮጵያ ተጎድታ አማራ የሚጠቀምበት ሁኔታ አለ? መልሱን አማራዉ በዘር መደራጀት አለበት ብለዉ ለተነሱ ጥቂቶች እተዋለሁ።
ከዘረኛዉ የህወሓት አገዛዝ ነፃ ለመዉጣት ብቸኛዉ መንገድ እንደ ህወሓት በዘር መደራጀት ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ሆኖ በጋራ መታገል ብቻ ነዉ። ተበታትነን በየራሳችን እስካፍንጫችን ታጥቀን ህወሓትን ብንገጥመዉ አንድ በአንድ ከማለቅ ዉጭ ሌላ የምንፈይደዉ ምንም ፈይዳ የለም። አንዳችን በሌላዉ ላይ ተጭነን በምንፈጥረዉ ግዜያዊ ህብረት ህወሓትን ብናሸንፍ እንኳን አምባገነኖች ከመሆን የሚያቆመን ምንም ነገር የለም። ስለዚህ ህወሓትን ለማሸነፍና ኢትዮጵያ ዉስጥ ሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት የሚያስፈልገን ኢትዮጵያዊ ሆነን መደራጀት ብቻ ነዉ። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዘሩ ከተደራጀ አንደኛ- ለኢትዮጵያዊነት ጥብቅና የሚቆም አይኖርም፥ ሁለተኛ- በዘር መደራጀት ያራርቀናል እንጂ አያቀራርበንም፥ ሦስተኛ- እኛ በዘር ተከፋፍለን ህወሓትን በተካነበት የዘር ዉጊያ ገጥመን አናሸንፈዉም። ስለዚህ ህወሓትን ለማሸነፍና ኢትዮጵያ ዉስጥ ሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት እኛ የኢትዮጵያ ልጆች የሚያስፈልገን በኢትዮጵያዊ ዜግነት ላይ የተመሰረተ ህብረትና አንድነት ብቻ ነዉ።“ኢትዮጵያዊነት” የምንለዉ እንዲህ አይነቱን ህብረትና አንድነት ነው . . . . ኢትዮጵያዊነት ያሸንፋል ስንልም እንደዚህ አይነቱ በጋራ ተስማምተን የፈጠርነዉ ህብረትና አንድነት ነዉ የሚያሸንፈዉ።
ህወሓትን የምንዋጋዉ በመርህ ደርጃ ተስማምተን ከሆነና መርሆዎቻችን ፍትህ፥ ነፃነት፥ እኩልነትና ዲሞክራሲ ከሆኑ እነዚህ መርሆዎች የዘር፥ የጎሳ፥ የቋንቋና የሀይማኖት አጥሮችን ሁሉ ዘልለዉ የሰዉን ዘር ሁሉ የሚያቅፉ መርሆዎች ናቸዉና ህወሓትን ተዋግቶ ለማሸነፍም ሆነ ከህወሓት በኋላ የምትመጣዉን አዲስቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት መደራጀት ያለብን በዘርና በቋንቋ ዙሪያ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ብቻ ነዉ። አንዳንድ ግዜ በአመለካከታችንና በአስተሳሰባችን ልንለያይ እንችላልን፥ ይህ የሃሳብ ልዩነት እንጂ የሚያጣላንና በመካከላችን አጥር የሚፈጥር ልዩነት አይደለም፥ እንዲያዉም እንዲህ አይነቱ ልዩነት ሊኖር የሚገባዉ የዕድገት መሠረት የሆነ ልዩነት ነዉ። በእንደዚህ አይነት ልዩነቶች ላይ የተመሰረቱ ዉይይቶችና ክርክሮች ለራሳችንና ለአገራችን የምንወስናቸዉ ዉሳኔዎች ሁሉ በእውቀትና በመረጃ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ የሚረዱን መሳሪያዎቻችን ናቸዉ እንጂ የሚለያዩን አጥሮች አይደሉም። እንደ ኢትዮጵያዊያን በአገራችን ትላልቅ ጥቅሞች ላይ መለያየት የለብንም፥ በዋና ዋና የወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይም መከፋፈል የለብንም። ይህ ማለት ግን ሀሳባችን፥ አመለካከታችን፥ እምነታችንና ከራሳችን ዉጭ ስላለዉ አለም ያለን እይታ ተመሳሳይ ይሁን ማለት አይደለም።
ኢትዮጵያ ጎሳ፥ ብሄር ወይም ዘውግ አይደለችም። ኢትዮጵያ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ህዝቦች ባጋጣሚ ተገናኝተዉ የሰሯት የብሄር ብሄረሰቦች ተራ ስብስብም አይደለችም። ኢትዮጵያ በተለያየ ዘመን ታሪክ አቆራኝቷቸዉ ለረጂም አመታት አብረዉ የኖሩ በባህል፥ በታሪክ፥ በፖለቲካና በማህበራዊ እሴቶች የተሳሰሩ ህዝቦች ጎን ለጎን የሚኖሩባት አገር ናት። ከዚህ በተጨማሪ “ኢትዮጵያ” አሁን ከሚኖርበት የድህነት፥ የረሃብ፥ የፍትህና የነፃነት አልባ ኑሮ ተላቅቆ ፍትህና ነፃነት ወደ ሰፈነበት የዕድገትና ብልፅግና ኑሮ ለመሸጋገር ከፍተኛ ጉጉትና ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሞት የሽረት ትግል በማካሄድ ላይ ያለ ህዝብ የሚኖርባት ትልቅ አገር ናት። ይህ ለረጂም አመታት አብሮ የኖረ ህዝብ በአንድ በኩል የአገሩ አንድነት ተከብሮ እንዲቀጥል ይፈልጋል፥ በሌላ በኩል ደግሞ በአገሩ ዉስጥ መብቱና ነፃነቱ ተከብሮ በእኩልነት መኖር ይፈልጋል። የኢትዮጵያ ህዝብ እነዚህ የጋራ የሆኑ አገራዊ ፍላጎቶቹን ለማሟላት ከህወሓት ጋር በሚያደርገዉ መራራ ትግል እራሱን እንደ አንድ ህዝብ ነዉ የሚመለከተዉ እንጂ አዳዲሶቹ የዳያስፖራ ነቢያት እንደሚነግሩን እራሱን በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ የዛሬ መቶና መቶ ሃምሳ አመት አባቶቹ በህብረት ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን አሳፍረዉ እንደመለሱ ሁሉ እሱም ዛሬ የህወሓትን ስርአት ደምስሶ አዲስቷን ኢትዮጵያ የሚገነባው በህብረትና በአንድነት ነዉ። የኢትዮጵያ አንድነት ተከብሮ የኖረዉ የብዙ ጀግኖች የደምና የህይወት መስዋዕትነት ተከፍሎበት ነዉ፥ ዛሬም የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሓቶች በአገሩ አንድነት ላይ ያሴሩትን ሴራ በጣጥሶ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያረጋግጠዉ ደሙን አፍስሶና አጥንቱን ከስክሶ ነዉ። ለኢትዮጵያ አንድነት መከበር የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ አባቶቻችን ታሪካ የተጻፈዉ የ“አማራ”፥ “ኦሮሞ”፥ “ሲዳማ”፥ “ወላይታ” ወዘተ ጀግኖች ታሪክ ተብሎ ሳይሆን የ”ኢትዮጵያ” ጀግኖች ታሪክ ተብሎ ነዉ። ይህ ታሪካችንንና እኛነታችንን “ኢትዮጵያዊ” ብሎ የመጥራቱ ልማድና ባህል አሁንም ለዘለአለሙም ይቀጥላል እንጂ አይቆምም።
ዛሬ ተወልደን ያደግንባት አገራችን ኢትዮጵያ የማናዉቃት አገር ሆናለች። ባህላችን ከመረሳቱ የተነሳ ባህል ያለን ሰዎች አንመስልም። ማህበራዊ እሴቶቻችን ከመዉደማቸዉ የተነሳ ነጋዴዎቻችን በርበሬና ቀይ አፈር ቀላቅለዉ መሸጥ ጀምረዋል። የመሪዎቻችን አዋቂነትና ትልቅነት የሚለካዉ በሚናገሩት የዉሸት አይነትና መጠን ሆኗል። የሀይማኖት መሪዎቻችን ተበዳዮች በዳዮችን ይቅርታ እንዲጠይቁ ማግባባት ዋና ስራቸዉ ሆኗል። ሽማግሌዎቻችን ህሊናቸዉን ሽጠዉ የነብሰ ገዳዮች ተላላኪ ሆነዋል። አንድነታችን ከመላላቱ የተነሳ ጎረቤቶቻችን ንቀዉናል። በድሮዋ ኢትዮጵያ ከድንበር ማዶ ሆነዉ ሲያዩን ጎንበስ ብለዉ እጅ ነስተዉን የሚሄዱ ጎረቤቶቻችን ዛሬ እንዳሻቸዉ ድንበር ጥሰዉ እየመጡ ዜጎቻችንን ከመግደል አልፈዉ ሴቶችና ህጻናትን አፍነዉ ሲወስዱ “ማነህ አንተ” የሚላቸዉ ጠፍቶ በሠላም ወደ መጡብት ይመለሳሉ። ኢትዮጵያ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስትና ቋሚ የመከላከያ ሰራዊት ኖሯት በኖረችባቸዉ አመታት ዉስጥ የታጠቁ የባዕድ አገር ወታደሮች ድንበር ጥሰዉ ገብተዉ ዜጎቿን ሊገድሉ ቀርቶ አጸፋዉ ምን ሊሆን እንደሚችል በሚገባ ስለሚያዉቁ እንደዚህ አይነት አይን ያወጣ ድፍረት ሀሳባቸዉ ዉስጥ ገብቶም አያዉቅም። ዛሬ ግን ሱማሌና ደቡብ ሱዳን ዉስጥ በሠላም ማስከበር ስም የሚሞተዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የራሱ ወገኖች በባዕዳን ሲገደሉ ቆሞ ተመልካች ሆኗል። ድሮ ጦርነት ሲባል የምናዉቀዉ ከዉጭ ከመጣ ወራሪ ሀይል ጋር ነበር፥ ዛሬ ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ ክልልና ክልል ተዋጉ ተብሎ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይዘገባል። የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ከቆሻሻ ክምር ዉስጥ ምግብ እያወጣ የሚበላዉ ምስኪን ወገናችን የቆሻሻ ክምር ተንዶ ይገድለዋል። ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ የህወሓት ስርአት ደጋፊዎች “ገና ሺ አመት እንገዛችኋለን” እያሉ ይዝቱብናል፥ ጠ/ሚንስትራችን “ስፌድ አምጡና ወርቅ ዝገኑ” እያሉ ያሾፉብናል፥ መሪዎቻችን የኢትዮጵያዊነታችን ምልክት የሆነዉን እንግዳ ተቀባይነታችንን የ“ቁጩ ታሪክ” ነዉ እያሉ ይዘባበቱብናል፥ ካድሬዎቻችን “ግድግዳ ግፉ” እያሉ ለኛ ያላቸዉን ንቀት ሳይደብቁ በግልጽ ይነግሩናል። የሚገርመዉ ይህ ሁሉ ንቀት፥ በደል፥ ዘበት፥ ጥላቻና ዉርደት በየቀኑ የሚደርስብን እኛ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ የፍጹም ባርነት ኑሮ ለመዉጣት ከምናደርገዉ ትግል ይልቅ አንዳችን ሌላዉን ጠልፈን ለመጣል የምናደርገዉ ትግል ይበልጣል። ዛሬማ ጭራሽ ብሶብን ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚጮኸዉን አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ “ውግዝ ከመ አሪዮስ” ማለት ጀምረናል። እግዚአብሄር ይቅር ይበለን!
ኦዚ እያለሁ አንድ ወጣት አግኝቼ . . . . አሜሪካንን የመሰለ ኑሮ ትተህ በረሃ ዉስጥ መሬት ላይ ተኝቶ ማደሩን እንዴት ቻልከዉ? ደሞስ ሰዉ እንዴት አይኑ እያየ ህይወትን ሸሽቶ ሞት ቤት ይሄዳል ብሎ ጠየቀኝ። እኔና አንተ ለህይወት ያለን ትርጉም ይለያያል አልኩት። እንዴት? ብሎ ጠየቀኝ። ለምን እንደምኖር በቂ ምክንያት ከሌለኝ መሞት እመርጣለሁ፥ በረሃ የገባሁት ግን ሞት ፍለጋ ሳይሆን ህይወት ፍለጋ ነዉ አልኩት። አልገባኝም አለ። ለመሞት ፈቃደኛ ካልሆንክ በህይወት መኖር አትችልም አልኩት። ኧረ አሁንም አልገባኝም አለ። ኢትዮጵያን ከልቤ እወዳታለሁ እሷም ትወደኛለች፥ በሷ መወደዴ ለኔ ጥንካሬዬ ነዉ፥ እኔ እሷን መወደዴ ደግሞ ድፍረቴ ነዉ። ዛሬ እቺ የምትወደኝና የምወዳት አገሬ ኢትዮጵያ ከማይወዷትና ከማትወዳቸዉ ሰዎች ጋር የጉልቤ ትዳር መስርታ የስቃይ ኑሮ እየኖረች ነዉ። ይህ የኢትዮጵያ የስቃይ ኑሮ ድፍረቴንም ጥንካሬዬንም ወሰደብኝና የመኖር ምክንያት አጣሁ። በረሃ የገባሁት ይህንን ዘረኞች የቀሙኝን የመኖር ምክንያት ለማስመለስ ነው አልኩት። ምንድነዉ የምታስመልሰዉ አለኝ? . . . . ኢትዮጵያን፥ ጥንካሬዬንና ድፍረቴን አልኩት! ለጥቂት ደቂቃዎች እኔም እሱም ዝምታዉን መረጥንና ያለንበት ቦታ ሰዉ የሌለበት ይመስል ጭጭ እርጭ አለ። ቀና ብሎ ሲያየኝ ከሁለት አይኞቹ ዕምባ ሲፈስ አየሁና ወዳጠገቤ ሳብ አድርጌዉ አይዞህ አልኩት። ምንም ሳይናገር ጠጋ ብሎ በሁለት እጁ አቀፈኝ። የወጣትነት ጥንካሬዉና የዋህነቱ ባቀፈኝ እጆቹ በኩል ሰዉነቴ ዉስጥ ዘልቆ ሲገባ ተሰማኝ። የማወቅ ጉጉቱ ደስ አለኝ፥ ያገር ልጅነቱ ተመቸኝ፥ ወጣት ሁሉ እንደሱ አለመሆኑ ግን ትንሽም ቢሆን ቅር አለኝ። እጆቹን ከትከሻዬ ላይ ሳያነሳ ወደ ጆሮዬ ጠጋ አለና . . . . . ጋሼ ኤፍሬም ብሎ ጠራኝ። አቤት አልኩት። “ያንተ ጥንካሬ ኢትዮጵያ የኔ ጥንካሬ አንተ ነህ” አለኝ። የሁለታችንም ጥንካሬ ኢትዮጵያ ናት አልኩት። አንገቱን ቀና ሲያደርግ አይኖቻችን ገጠሙ . . . . . ምን ላድርግ ጋሼ ኤፍሬም ብሎ ጠየቀኝ . . . . . ለምን እንደምትኖር ታዉቃለህ ብዬ ጥያቄዉን በጥያቄ መለስኩለት። አላዉቅም አለኝ። በል ሳትዉል ሳታድር ለምን እንደምትኖር እወቅ አልኩት . . . . እሺ ብሎ ተለየኝ።
እርግጠኛ ነኝ ይህ ወጣት ካሁን በኋላ ብንገናኝ ለምን እንደሚኖር ይነግረኛል። ዛሬ የብዙዎቻችን ችግር ለምን እንደምንኖር አለማወቃችን ነዉ . . . ብናዉቅ ኖሮ ህወሓትን ያክል ትልቅ ጠላት አስቀምጠን እርስ በርስ አንባላም ነበር። ለምን እንደምንኖር ብናዉቅ የተወለድንባትን ምድር ከቀሙን ወንጀለኞች ጋር እጅና ጓንት አንሆንም ነበር። ለምን እንደምንኖር ብናዉቅ የምንታገላቸዉን ሰዎች “እሰይ” የሚያሰኝ ስራ አንሰራም ነበር።ለምን እንደምንኖር ብናዉቅ ጠላትና ወዳጅ፥ ፍቅርና ጥላቻ፥ ያገር ፍቅርና የንዋይ ፍቅር ፥ ኢትዮጵያዊነትና ብሄረተኛነት ተቀላቅለዉብን አድራሻ እንደጠፋዉ ተላላኪ እዚህም እዚያም አንዘልም ነበር። ህወሓቶች ለምን እንደሚኖሩ ስለሚያዉቁ ነዉ እኛን ገድለዉ እነሱ የሚኖሩት። እኛ ግን ለምን እንደምንኖር ስለማናዉቅ እየሞትን እናኖራቸዋለን። አንባቢ ሆይ! ያንተን/ያንቺን አላዉቅም እኔና ኦዚዎች ግን ያንን የህወሓት ካድሬዎች ግፉ ያሉንን ግድግዳ ገፍተን እነሱም ግድግዳዉም የሚገፉ መሆናቸዉን በተግባር እናሳያቸዋለን አንጂ እኛ ሞተን እነሱ ኖረዉ፥ እኛ ሰግደን እነሱ አሰግደውንማ አንኖርም . . . . . ሞኝና መሃይም እንኳን ሰግደህለት ብታብድለትም የበለጠ ያሳብድሃል እንጂ አይተዉህም! አይደል ኦዚዎች?
ቸር ይግጠመን ኤፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር