የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባኤ በሲያትል የአቋም መግለጫ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባኤ በሲያትል የአቋም መግለጫ

ይህ በአይነቱ የመጀመሪያ በሆነውና አሜሪካ ውስጥ በዋሽንግተን ስቴት ሲያትል ከተማ ግንቦት 19 እና 20 2009 ዓ.ም. በተካሄደው የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ጉባኤ ላይ ከመላው ዓለም የመጡ ከ20 በላይ ታዋቂ ምሁራን፣የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ሲቪክ ማህበራት መሪዎች፣እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል። በሲያትል እና ዙሪያዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአካል ተገኝተው በጉባኤው የተሳተፉ ሲሆን በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ በመላው ዓለም የሚገኙ ወገኖቻችን ደግሞ በኢሳትና በሌሎች የመገናኛ አውታሮች ውይይቱን ተከታትለዋል።

በሲያትል የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባኤ ተሳታፊውች የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታዎች ገምግመንና በሀገራችን ብሄራዊ አንድነት፣ የጋራ ራዕይና ሀገራዊ አጀንዳችን ላይ ሰፊ ውይይት አካሄደን የሚከተለዉን ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ ዛሬ ግንቦት 20 2009 ዓ.ም. አውጥተናል፡፡

1. በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ እንቢተኝነት ተከትሎ በንጹሃን ዜጎች ላይ በወያኔ ልዩ ጦር ኃይል የተወሰዱትንና እየተወሰዱ ያሉትን እጅግ ዘግናኝ አረመኔያዊ ጭፍጨፋዎችንና አፈናዎችን አምርረን እናወግዛለን፤ ይህንን ግፍ የፈጸሙ አካላት በሙሉ በሕግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ያላሰለሰ ጥረት ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡

2. ወያኔ/ኢህአዴግ ለተለየ አመለካከት ቦታ የማይሰጥ፤ በሰላማዊ መንገድ ተደራጅተውና አማራጭ ፖሊሲዎች ይዘው የሚታገሉ ኃይሎችን በፀረ ሕዝብነት የሚፈርጅ፤ ለዜጎች መብት መከበር ፍፁም ደንታ የሌለው አምባገነናዊ ስርአትን የሚከተል ስለሆነ በየጊዜው በዜግነታቸዉ ሊኖራቸው የሚገባውን መብት በሰላማዊ መንገድ ስለጠየቁ ብቻ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና አባላት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ጋዜጠኞች በየእስርቤቱ እንዲማቅቁ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት በየቦታው ታስረው የሚገኙ የህሊና እስረኞች ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ አጥብቀን እንጠይቃለን፤ ለተግባራዊነቱም በፅናት ለመታገል ቃል እንገባለን፡፡

3. ሀገራችን ኢትዮጵያ የረጅም ታሪክና የስብጥረ-ሕዝብ ባለፀጋ ነች፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የማንነታችን መግለጫ የሆኑት ብሄር፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት ሳይለያዩን ተጋብተን፣ ተዋልደን፣ ተከባብረን እና በፍቅር በደግም ሆነ በክፉ ግዜ አገራዊ አንድነታችንን ጠብቀን ኖረናል፡፡

ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝብን ከህዝብ ለመነጠል፤ ተዋልደውና ተባብረው ለዘመናት የኖሩትን የሀገሪቱ ህዝቦች ለማቃቃር የሚሰሩ ኃይሎች ተደጋግመው እያታዩ ነው። ከነዚህ ኃይሎች ደግሞ ዋነኛው ሀገሪቱን በብሔርና በሀይማኖት በመከፋፈልና እርስ በርስ በማጋጨት የስልጣን ዕድሜውን እያራዘመ ያለው ወያኔ/ኢህአዴግ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሀገር ወዳድ ግለሰቦች፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ካለፈው የፖለቲካ ታሪካችን ተምረን፤ ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችን ላይ አተኩረን ይህን የተጋረጠብንን ብሄራዊ የመበታተን አደጋ ለመቀልበስ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንነሳ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

4. በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት መሠርቱ ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት በወያኔ/ኢህአዴግ ሲፈጸሙ የነበሩ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች፣ አስተዳደራዊ በድሎች፣ አምባገነናዊ የኃይል እርምጃዎችና ሌሎች ብሶቶች ተጠራቅመው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በአንድ ጊዜ መፈንዳታቸው ነው። በአሁኑ ወቅት የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶች፣አድሎና የፍትህ መዛባት፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የዜጎች በገፍ ሥራ ማጣትና መሰደድ የሀገራችን ተጨባጭ መገለጫዎች ናቸው። ስለሆነም ወያኔ/ኢህአዴግን ከስልጣን በማስወገድ ሥር-ነቀል የስርአት ለውጥ ማምጣት አማርጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብሎ የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ካለው ሕዝባችን ጎን መቆማችንን እናረጋግጣለን። እኛም የበኩላችንን ለመወጣት ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ለመተባበር ቃል እንገባለን፡፡

5. ወያኔ/ኢህአዴግ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ለተቀሰቀሱ ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ፍላጎት እንደሌለው በግልጽ አሳይቷል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ የዜጎችን የመሰብሰብ፣ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ እና ሰላማዊ ሰልፍ እና ተቃውሞ የማድረግ መብታቸውን ከመገደቡም በላይ የመከላከያ ሰራዊቱን አሰማርቶ ዜጎችን ያስገድላል፣ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎችን በጅምላ በማጎሪያ ጣቢያዎች በማጎርና በማሰቃየት ህዝባዊ ተቃውሞዎችን መጨፍለቅን መርጧል፡፡ ይህ የወያኔ/ኢህአዴግ አምባገነናዊ ባሕሪይ በሀገራችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደገኛ ሁኔታ በጥሞና የገመገመን ሲሆን ከዚህ አደገኛ ባሕሪው በአስቸኳይ ታርሞ በአሁኑ ወቅት ዘግቶ የሚገኘውን የሰላማዊ መፍትሔ በር በአስቸኳይ እንዲከፍትና ለእውነተኛ ውይይትና ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ዝግጁ እንዲሆን አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

6. ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት ከልምድ የተማርነው ትልቅ ቁምነገር ቢኖር ካልተባበርን በስተቀር ዘረኛውና አምባገነኑን ወያኔ/ኢህአዴግን በተበታተነ ኃይል አስወግዶ ህዝብን የስልጣን ባለቤት ማድረግ እንደማይቻል ነው። በቅርቡ ወያኔ/ኢህአዴግን ብርክ ያስያዘውና በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የተካሄደው መጠነ ሰፊ ህዝባዊ እንቢተኛነትን የበለጠ ለማጠናከርና ለትግሉ የተማከለ የፖለቲካ አመራር መስጠት ያልተቻለው ጠንካራ የተቃዋሚ ኃይሎች ህብረት ባለመኖሩ ነው ብለን እናምናለን።ይህ ደግሞ ሁላችንንም የታሪክ ተጠያቂ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ስለሆነም ተቃዋሚ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በሚያግባቧቸው ዓላማዎች ሥር በመሰባሰብ አንድ ጠንካራ ሀገር-አቀፍ የተቃዋሚ ኃይሎች ህብረት እንዲፈጥሩ፣ የተባበረ ትግል እንዲያደርጉና ለሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር መሠረት እንዲጥሉ ቆመንለታል በሚሉት ህዝብ ስም እንጠይቃለን። ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ በዚህ ጉባኤ የተገኘን ሁሉ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን።

7. በሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለቱ ዋነኛ ሃይማኖቶች ማለትም ክርስትናና እስልምና ለረጅም ዘመናት ሳይነጣጠሉ በሀገራችን አንድነትና በሕዝባችን ነፃነት ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ለመቋቋም፤ የሀገራችንና የሕዝባችንን አንድነትና ነፃነት ሳያደፈር እንዲቆይ ለማድረግ ያደረጉት ተጋድሎና የከፈሉት መስዋእትነት እጅግ ጉልህ መሆኑን በተደረገው ውይይት አጽንኦት ተሰጥቶታል። ወደፊትም ስለፍቅር፣ ሰላምና ተቻችሎ አብሮ ስለመኖር ከመምከር ባሻገር የሀገር አንድነት የሚጠበቀውና ዘላቂ ሠላም ማግኘት የሚቻለው ፍትህና ማህበራዊ መረጋጋት በሰፈነበት የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ መኖር ሲቻል መሆኑን የሃይማኖት ተቋማት ለተከታዮቻቸው ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲያስተምሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

8. ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት ከሆኑት ዓበይት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የፕሬስ ነፃነት ቢሆንም በሀገራችን ኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን በነፃነት ሊሰሩ የሚችሉበት ሁኔታ ፈፅሞ የለም። በተለይ የወያኔ/ኢህአዴግ የፀረ ሽብር አዋጅ ፀድቆ ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ የግል ፕሬሶች ሚና እጅግ ከመገደቡም ባለፈ ሚዲያዎቹ በግዳጅ ከኢንዱስትሪው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡የመንግስት ሚዲያዎችም በሳንሱር ሰንሰለት ተሸምቅቀው ከአንድ ፓርቲ ፕሮፓጋንዳና አስተምህሮ በስተቀር ነፃ አስተሳሰቦች አይስተናገዱባቸውም። በዚህም የተነሳ ህዝቡ አማራጭ መረጃዎችን የሚያገኝባቸው ዕድሎች ሙሉ በሙሉ ተዳፍነዋል ማለት ይቻላል። የሚዲያ ነፃነት የሚረጋገጠው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑን አምነን በቅድሚያ የህዝቡንና የሚዲያውን ነፃነት አፋኝ የሆነውን አምባገነን ሥርዓት አጥብቀን ለመታገል ቃል እንገባለን፡፡

9. ጉባኤው የጋራ ራዕያችን እና ሀገራዊ አጀንዳችን ምን መሆን ይገባዋል በሚለው ጥያቄ ላይ በሰፊው ከመከረ በኋላ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ዋና ዋና የጋራ ዓላማዎች አሰባሳቢ ናቸው ብሎ ያምናል፤ ስለሆነም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያለው ወገናችን በነዚህ ዓላማዎች ዙሪያ ተሰባስቦ ሀገሩን ኢትዮጵያን እንዲያድን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

ሀ. የጋራ ራዕያችን ብሄራዊ አንድነቷ የተጠበቀ፣ ሰላም የሰፈነባትና የበለጸገች አንዲት ኢትዮጵያን ማየት ነው።
ለ. የአጭር ጊዜ ትልማችን ሀገራችን በአጭር የሽግግር ሂደት አልፋ በሕዝብ ነፃ ምርጫ ላይ ወደ ተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ መንግሥታዊ ሥርዓት እንድትሸጋገር ማስቻል ሲሆን

ሐ. የረጅም ጊዜ ግባችን ደግሞ ለሁላችንም የምትመች፣ ሰብአዊ መብቶች የሚከበሩባት፣እውነተኛ እኩልነት፣ ፍትህና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባትና ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት ሀገር እንድትኖረን ማድረግ ነው።

10. በመጨረሻም ከላይ በተራ ቁጥር 9(ለ)ላይ የተጠቀሰውን የሽግግር ሂደት ሊመራ የሚችል፤ ሁሉን አሳታፊ የሆነ ብሔራዊ ምክርቤት በአጭር ጊዜ ለመመሥረት የሚያስችል ጥናት የሚያደርግ፤ ከሌሎች ተመሳሳይ ጥረት ከሚያደርጉ ወገኖች ጋር በቅንጅት የሚሰራና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባኤ ቀጣይነት ባለው መልኩ በየዓመቱ በተለያዩ ከተሞች እንዲደረግ የሚያስተባብር ቀጥሎ የተዘረዘሩት አስራ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ መስርተናል።

1. ፕ/ር ጌታቸው በጋሻው
2. ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ
3. ዶ/ር አረጋዊ በርሄ
4. ዶ/ር በያን አሶባ
5. አቶ ኦባንግ ሜቶ
6. ፕ/ር ተድላ ወልደዮሀንስ
7. አቶ አበበ ገላው
8. ወ/ሮ መታሰቢያ ሙሉጌታ
9. ወ/ሮ ንግስት ሰልፉ
10. ወ/ት ርዕዮት ዓለሙ
11. ወጣት ሀብታሙ አብዲ
12. ወጣት ነጻነት ስመኝ
13. ወጣት እሸቱ ሆማ ከኖ
14. ወጣት እንዳልካቸው ጫላ
15. መምህር ልዑለቃል አካሉ
16. አቶ መንሱር ኑሩ
17. ዶ/ር አሸናፊ ጐሳዬ
ይህ ታሪካዊ ጉባኤ የተዘጋጀው በሲያትል ከተማ የሚኖሩ ሀገር ወዳዶችና በሲያትል የኢትዮዽያውያን ሕዝባዊ ፎረም በጋራ በመሆን ነው። ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሰውተው ይህን ሀገራዊ ፋይዳ ያለውንና ወቅታዊ የሆነውን ጉባኤ እጅግ የተሳካ እንዲሆን የተሳተፉትን ሁሉ ከልብ እናመሰግናለን።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባኤ ተሳታፊውች
ግንቦት 20 2009 ዓ.ም.
ሲያትል – አሜርካ

LEAVE A REPLY