ሜይ 28 /2017 ምሽት አትላንታ ደምቃ ነበር። የኳስ ጎምቱዎች በአትላንታ ተሰባስበው በፍቅር ተናንቀዋል። በናፍቆት ተወዛውዘዋል። በአንድነት ስካር ጦዘዋል። በክብር ማማ ተሳቅለዋል።
አገራችን በ እግር ኳሱ መድረክ ዓለም ባያውቃትም፣ እንድትታወቅ የታተሩ ግን ብዙ ነበሩ። በሸራ ጫማ ልምምድ ከማድረግ ጀምሮ፣ በአንድ ኳስ ትልቅ ውድድር እስከማካሄድ ድረስ የለፉ ብዙ ነበሩ። አንዴ የተጠለዘ ኳስ ተይዞ እስኪመጣ ድረስ የደረቀ ሳር የለበሰ መሬት ላይ ቁጭ ብለው ረፍት የሚወስዱ፣ ኳሱ ተይዞ ሲመጣም ተነስተው የሚሮጡ ብዙ ነበሩ።
የግል ጸብ ቢኖራቸው እንኳን አገራቸውን በሚወክሉበት መድረክ ላይ ጸባቸውን “ላሽ በል” ብለው ለሰንደቅ ዓላማቸው ክብር እንደ ወታደር የተዋደቁ ብዙ ኳስ ተጫዋቾች ነበሩ። አንዳንዶቹ በህይወት የሉም፣ አንዳንዶቹ ደግሞ አሉ። ምናልባት ዛሬ ሮናልዶና ሜሲን የበለጠ ለማወቅ ተገፋፋን እንጂ፣ ሸዋንግዛው አጎናፍርና ካሳሁን ተካ፣ ሪኮ ጌራርዶ እና ሰለሞን ሽፈራው በጊዜያቸው ሮናልዶና ሜሲ ነበሩ።
እነዚህን የአገር ባለውለታዎችና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፊታውራሪዎች ለማክበር ነበር የአትላንታ እግር ኳስ ቡድን ከሰሜን አሜሪካ የቀድሞ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ማህበር ጋር በመሆን ይህን ድንቅ ምሽት ያዘጋጀው። በዚህ ሁኔታ ከ80 በላይ የቀድሞ የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ይገኛሉ ብሎ ማንም አልገመተም። ነገር ግን ሁሉም ከያለበት ቦታ ብቅ አለ።
ድሮ ድሮ ስማቸውን በሬዲዮ ስንሰማ፣ ሰለሞን ተሰማም ይሁን ደምሴ ዳምጤ “ይዞ ሄደ .. ወደፊት ገፋ፣ ጎል፣ ነቀነቀው “ እያሉ ልባችን ከፍና ዝቅ ሲያደርጉን የነበረው በነዚህ ተጫዋቾች ምክንያት ነበር። ከሩቅ በጥቁርና ነጭ ቲቪ፣ ከዚያ ካለፈ ምናልባት ሜዳ ውስጥ ከማዶ ስናያቸው የነበሩት ተጫዋቾች በሙሉ በአንድ አዳራሽ ተደርድረው ማየት ህልም ነበር።
ከመላው አሜሪካና አውስትራሊያ ጭምር ነበር የተሰባሰቡት። ማን ቀረ? በጥቂቱ እነዚህ ነበሩ። ሸዋንግዛው አጎናፍር፣ ሰለሞን ሽፈራው፣ ሪኮ ጌራርዶ፣ ሙሉጌታ ወልደየስ፣ ሙሉጌታ ከበደ፣ ዳኛቸው ደምሴ፣ ሙሉዓለም እጅጉ፣ ተካበ ዘውዴ፣ አፈወርቅ ጠናጋሻው፣ ዓለማየሁ ሃይለሥላሴ (ፊኛ)፣ ሰለሞን መኮንን (ሉቾ)፣ ዳዊት ሃይለዓብ፣ ጌቱ ከበደ፣ ካሳሁን ተካ፣ አቦነህ ማሞ፣ ንጉሴ አስፋው፣ አፈወርቅ ከበደ (ካቻ)፣ ዳንኤል ክፍሌ፣ ግርማ ከበደ፣ ዓይናለም ሞገስ፣ መንግስቱ ሁሴን፣ … እና ሌሎችም በርካቶች። [የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ባገኘንበትና ዳኛቸው ደምሴ የመጨረሻዋን ሪጎሬ ባገባበት ጨዋታ ከተሰለፉት 11 ተጫዋቾች 9ኙ እዚህ አዳራሽ ነበሩ]
በቡድን ደረጃም ከቀድሞዎቹ ትግል ፍሬ፣ ኤሌክትሪክ ፣ ኦሜድላ፣ ምድር ባቡር ወዘተ. የተጫወቱ ነበሩ። እነዚህ ተጫዋቾች እስከዛሬ ማንም የት እንዳሉ ሳያውቅ፣ እነሱም ርስ በርስ – በሆነ አጋጣሚ ካልሆነ በቀር ሳይገናኙ የቆዩ ነበሩ። አሁን ግን ከመገናኘትም አልፈው “ከሳህ ፣ ጠቆርክ፣ አምሮብሃል” እየተባባሉ ሶስት ቀን በአትላንታ ከትመው ቆይተዋል።
ከዚያም በላይ እያንዳንዳቸው ለአገራቸው በስፖርቱ ዘርፍ የከፈሉትን መስዋትነትና የዋሉትን ውለታ በመዘከር የሁሉም ስም እየተጠራ በጭብጨባና በ እልልታ፣ በቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” ሙዚቃም ታጅበው ወደ አዳራሹ እንዲገቡም ተደርጓል። ከዚያም በላይ ለአንጋፋዎቹ ልዩ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። ይህ ዝክር ለኢትዮጵያ ስፖርት ዓለም ትልቅ መነሳሳት ነው።
ቀድሞ መብራት ሃይል፣ ከዚያም ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የነበረው የአትላንታ ዘላለም ተሾመ ህይወቱ ካለፈ ወራቶች ተቆጥረዋል። ይህ ዝግጅት የሱ ህልም ነበር። ከመሞቱ በፊት “አደራ፣ የተራራቁትን አገናኙ፣ የተጣሉትን አስታርቁ፣ የተቸገሩትን ደግፉ” ብሎ ነበር የተናዘዘው። የአትላንታ ቡድንም ይህንን አደራ ይዞ ነበር ዝግጅቱን ያዘጋጀው።
በርግጥም ህብር ያለው ቀለም በአዳራሹ ታይቷል። ተገናኘተው የማያውቁ ተገናኝተዋል። ክብር የሚገባቸው ክብር አግኝተዋል። በመካከላቸው አጥር ሰርተው “አትየኝ፣ አላይህም” ሲባባሉ የነበሩ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠዋል። የስሜን አሜሪካው የስፖርት ፌዴሬሽን ሃላፊዎች፣ በኋላ ደግሞ ከዚህ ፌዴሬሽን ወጥተው “ኤሳ ዋን” የሚል ድርጅት የመሰረቱትም እዚሁ አዳራሽ ጎን ለጎን ተቀምጠዋል። “በህይወት ይኖር ይሆን?” የተባለላቸው ተጫዋቾች አምሮባቸው ብቅ ብለዋል።
ስፖርት ሁሉንም አንድ የሚያደርግ መሆኑን፣ ከፖሊቲካና ሃይማኖት፣ ከዘርና ከጎሳ በላይም እንደሆነ አሳይቷል። ስፖርተኛ እንደማንም ሰው የግሉ አቋም ሊኖረው ይችላል። በስፖርት ቤት ግን የሚያገናኘው አንድ ነገር ነው – ስፖርት። ስፖርት የተያያዘ፣ አንዱ በሌላው ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ነው። ዳኛቸው ደምሴ ያቺን ተአምረኛ ሪጎሬ ያገባው፣ ገብረመድህን ሃይሌ በጭንቅላቱ ጨርፎ መረብ ውስጥ ስለዶላት ነው፣ .. ገብረመድህን ሃይሌ ያንን ያደረግው፣ ሙሉ ዓለም አጅጉ ከኮርና አካባቢ አስተካክሎ ስለላከለት ነው፣ .. ሙሉ ዓለም ደግሞ ያቺን ጥሩ ኳስ የላካት፣ በባከነ ሰአት ተሯሩጦ ውጭ የነበረችውን ኳስ ባቀበለው “ኳስ አቀባይ” ምክንያት ነው። ኳስ አቀባዩ አንድ ሰከንድ ቢዘገይ ኖሮ ምናልባት ሰአቱ አልቆ ነበር። ሁሉም የሆነው ደግሞ በእግር ጣቱ ቆሞ “አይዟችሁ” እያለ በጮኸው ደጋፊ ምክንያት ነው።
ይህ ሁሉ ለመጨረሻው ውጤት ተያያዥ የሆነ ው ሕዝብ የአንድ ዕምነት፣ ፖሊቲካ አቋም ፣ ወይም ዘርና ጎሳ ተወካይ አይደለም። የህብር ውጤት እንጂ። ለዚህ ነው ይህ የአትላንታው ስብስብ የአንድነትና የፍቅር መሠረት የጣለው። እስቲ አስቡት ፣ ሰለሞን ሽፈራው በሚታወቅበት ቴስታው እንደ ስፕሪንግ ነጥሮና ከፍ ብሎ በግንባሩ የገጨው ኳስ ጎል ሲሆን፣ ያቀበለው መንግስቱ ወርቁ ነበር። ሁለቱ ግን በዚያን ቀን ጠዋት በአንድ ጉዳይ አንዱ አንዱን ከስ ሶ ፍርድ ቤት ነበሩ። ጠዋት ክስ ፣ ክሰአት ኳስ ሜዳ ፍቅር – ደስ አይልም? ሰለሞን ሽፈራው “እሱ ያቀበለኝን ኳስ ጫፉንም አልነካው” ብሎ “ሽል” ቢለው ኖሮ ማነበር የሚጎዳው?
ስፖርት ውስጥ ፣ ኳስ ውስጥ ፖሊቲካ ከገባ፣ ዘርና ጎሳ ከገባ፣ ኳስ ሳይሆን ኩስ ይሆናል። ኩስ ደግሞ ወይ ዳቦ ሆኖ አይበላ፣ ወይም ኩበት ሆኖ ዳቦ አይጋግር። ለመለያየቱ ብዙ ሜዳዎች አሉ፣ ለአንድነቱ ግን የስፖርት ሜዳ በቂ ነው።
ይህ መገናኘት እንደ እግዜር ፈቃድ በየሁለት ዓመቱ እንዲሆን ሃሳብ እንዳለ ተነግሯል። ዛሬ በህይወት ያገኘናቸውና አብረናቸው ፎቶ የተነሳናቸውን፣ የዛሬ ሁለት ዓመት ላናገኛቸው እንችላለን። እያለን እንከባበር፣ እያለን እንዘካከር። አትላንታ ታሪክ ሰርቷል።