“የዐቃቤ ሕግ ያለህ!” የሚል ርእስ ይዤ፤ ይህን መጣጥፍ ለማቅረብ ምርኩዝም፣ መግፍኤም የኾነኝ፤ በቅርቡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለፓርላማው ያቀረበው፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የ2007 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ግኝት ሪፖርት ነው፡፡
ከኹሉ አስቀድሜ፤ እነኚኽ የኦዲት መሥሪያ ቤቱ ባለሞያዎች፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በተመለከተ እና በሌሎችም ተመሳሳይ የሒሳብ ኦዲት ግኝት ጉዳዮች ላይ ላሳዩት ትጋት እና ቆራጥነት እንደ አንድ ዜጋ፣ የበኩሌን አክብሮት ላቀርብላቸው እፈልጋለኹ።
ይህ ጽሑፌ በሦስት መደብ የተከፈለ ይዘት ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያው፦ ስለ ዩኒቨርሲቲው የሥልጣን ሥርዓተ ወግ እና መዋቅር፤ ኹለተኛው፦ የኦዲት ሪፖርቱን ሐቲት እና ያለውን አንድምታ፤ ሦስተኛው፦ የዩኒቨርሲቲው የንዋይ አስተዳደራዊ – ሥርዓት – አልባነት እና የሙስና መገለጫዎቹ፤ በሚል የተሰናዳ ነው፡፡
ሥልጣን እና ሥርዓት በዩኒቨርሲቲው ቅጽር፤
ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጽር እና የሥልጣን ሥርዓተ ወግ ሐተታ፣ በቀጥታ ከመግባታችን በፊት፣ የዩኒቨርሲቲውን አካላዊ መልክእ እና ከፖለቲካ ሥርዓቱ ጋራ ያለውን መመሳሰል ማየት በእጅጉ የተገባ ይኾናል፡፡ የምልከታ መነጽራችንንም፥ ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እውቁ ፈላስፋ ሚሼል ፉኮ ተውሰን፣ እርሱ የተነተናቸውን፣ የአውሮፓ የፖለቲካ ሥልጣን ሥርዓተ ወጎች፣ የሐተታችን ምሕዋር አድርገን እናሔዳለን፡፡
ፉኮ ካቀረበው ትንታኔ እንደምንረዳው፥ ዘውዳዊ ሥርዓት ባለበት አገር፣ የፖለቲካ ኃይልንና ሥልጣንን ጠቅልሎ የያዘው፣ እንደ ሉዓላዊነቱ ራሱ ንጉሡ ነበር፡፡ ከፍጹማዊ የዘውድ አገዛዝ መወገድ በኋላ፣ የፖለቲካ ኃይል ከአንድ ግለሰብ እጅ ወጥቶ ወደ ብዙ ማዕከላት ተሠራጭቷል፡፡ ይኹን እንጂ፣ ከአንድ ሉዓላዊ ሰው የወጣው መንግሥታዊ ሥልጣን፣ እንደ ሊብራል አስተምህሮ፣ በቀጥታ ወደ ዜጎች ወርዶ ሕዝቡ ሉዓላዊነትን የተጎናጸፈበት ሳይኾን፣ ወደተለያዩ የሥርዓቱ ንኡሳን ተቋማት የወረደበትን ሒደት የሚያሳይ ነው፡፡ በመኾኑም እነዚኽ የሥርዓቱ ንኡሳን ተቋማት፣ ከዋናው ማዕከላዊ መንግሥቱ የሥልጣን ተቋዳሾች ናቸው። በዚኽ ሥርዓተ ወግ፣ ሥልጣን፣ አንድ ቦታ ብቻ የተከማቸ ሳይኾን፤ ከተለያየ ቦታ የሚነሣ ነው። በመኾኑም የዜጎች መብት የሚወሰነው፣ ከአንድ ማዕከል በሚነሣ የኃይል ሚዛን ብቻ ሳይኾን፣ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ወቅት በምናገኛቸው ተቋማት ነው፡፡
የፖለቲካ ሥልጣን ተቋዳሽ ኾነው፣ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ከሚያጋጥሙን ተቋማት መካከል፦ እንደ ቀበሌ፤ ወረዳ አስተዳደሮች፤ የከተማ ማዘጋጃ ቤት፤ የፍትሕ ተቋማት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት… ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ ፉኮ አስተሳሰብ፣ የአንድን አገር ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ለመረዳት፣ የኹሉንም ተቋማት ኹኔታ በመመርመር አንድ አገራዊ ገጽታ ለማቅረብ ከመሞከር ይልቅ፣ የአንድ ውስን ተቋም ሥርዓትን ብቻ ለይቶ መመልከት፣ አጠቃላይ የአገሪቷን ሥርዓት ለመረዳት እንደሚያስችል ያሳየናል፡፡
በውቅያኖስ ውስጥ የሚገኘውን ንጥረ ነገር ለማወቅ፣ ከውቅያኖሱ ጥቂት የውኃ ናሙና ብቻ በመውሰድ በላብራቶሪ እንደምንመረምር ኹሉ፣ እኛም አንድን ተቋም፣ ማለትም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን እንደ ማሳያ በመውሰድ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የተስፋፋውን ሙስና ወደሚያሳየን ተጨባጭ ኹኔታ ለመድረስ እንሞክራለን፡፡
በመጨረሻም ፉኮ፣ “ሕዝብ ሉዓላዊ ነው” የሚለውን አስተምህሮ፣ በእውነታ ሚዛን እንደ ሞገተ ኹሉ፤ እኔም፣ ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ ሉዓላዊ ሥልጣን መፍረስ በኋላ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በተፈራረቁ ሥርዓቶች፣ ሕዝብ ሉዓላዊነትን ተረክቧል፤ የሚል እምነት የለኝም፡፡
ሽግግር፡- ከቤተ መንግሥት ወደ ዩኒቨርሲቲ፤
የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ቀድሞ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥት በነበረበት መልክኡ፣ በሦስት መካናተ ክበብ የተዋቀረ እንደ ነበር፣ በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ አጫውተውኛል። ይኸውም፣ የመጀመሪያው ደረጃ፥ ንጉሠ ነገሥቱ፣ ልዑላንና ልዕልታት በአጠቃላይም ንጉሣውያን ቤተሰቦችን ብቻ የያዘ፤ ኹለተኛው መካነ ክበብ፥ መሳፍንቱንና መኳንንቱን የያዘ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የሚገኘው የቤተ መንግሥቱ መዋቅር ደግሞ፣ በተለያየ ደረጃ ያሉ የመንግሥቱን አገልጋዮች እና የቤተ መንግሥቱን ባለሟሎች የያዘ ነበር፡፡ በዚኽ መልኩ በሦስት ደረጃ የተከፋፈለው ቤተ ንጉሥ፦ የትእምርታዊነት፣ የዓላማና የተግባር መደባዊ ማዕርግን የሚያንጸባርቅ ቅጽር አለው፤ የቅጽሩም አሻራ ዛሬ ድረስ ይታያል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ሺፈራው ገለጻ፣ ይህ ዓይነቱ የቤተ ንጉሥ ማዕርጋዊ አወቃቀር፣ ከቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊ የሕንፃ ሥሪት የተወረሰ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን፥ “ምቋመ ካህን ወምእመን፤ ምቋመ ነገሥት ወንግሥታት” ተብለው የተለዩ፥ መቅደስ፣ ቅድስት እና ቅኔ ማሕሌት እንዳሉ ኹሉ፣ በቤተ መንግሥቱም ከላይ ያየናቸው ሦስት “ምቋመ ሹማምንት” በባህል ተናበው እናገኛቸዋለን፡፡
በተጨማሪም፣ ቤተ መንግሥቱ ምንጊዜም ንጉሠ ነገሥቱ መርጦ በሾመው ልዩ ኃይል ይጠበቃል። ይህም በየዘመኑ የተለያየ መልክ፣ አደረጃጀት እና ስያሜ ሊይዝ ይችላል፡፡ ለምሳሌ፡- በመካከለኛው ዘመን “ቊርባን” የተሰኘ ልዩ ኃይል፣ በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት “መሀል ሠፋሪ”፣ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ደግሞ፣ “የክብር ዘበኛ” በሚል ስያሜ ተደራጅተው ቤተ መንግሥቱን ይጠብቁ ነበር፡፡
የአኹኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኃይልና የሥልጣን አወቃቀር ስንመለከት፣ ልክ እንደ ቀድሞው የቤተ መንግሥት አወቃቀር ኹሉ፣ በሦስት ደረጃ የተከፈለ ነው፡፡ በአንደኛ ደረጃ፡- የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት፣ የቦርድ ሰብሳቢውና አባላቱ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲኹም በተለያዩ ፋኩልቲዎች ባላቸው የፖለቲካ ቅቡልነት የተመረጡ ዲኖች ናቸው፤ በኹለተኛ ደረጃ ያለው የአወቃቀር ዕርከን ራሱን በኹለት ይከፍላል፡- የመጀመሪያው፥ ከተለያዩ ክልሎች በብሔር ማንነታቸው ተመርጠው የተሾሙ ባላባታዊ ካድሬዎችና “የፓርላማ ተመራጭ” በሚል ሰበብ የሚገቡ የኢሕአዴግ የፖለቲካ አቀንቃኞች ሲኾኑ፣ ኹለተኛው ክፍል ደግሞ፤ የኢሕአዴግን ፕሮግራሞች እና ፖሊሲዎች ምሁራዊ ልባስ ለመስጠት የተሰለፉ ምሁራን ናቸው። እነዚኽም፤ በቤተ መንግሥቱ አግብኦተ ግብር ወቅት እየተነሡ፣ ንጉሡን፥ “አልቦ እምቅድሜከ ወአልቦ እምድኅሬከ” (ከአንተ በፊት እንዳንተ ያለ አልነበረም፤ ከአንተም በኋላ እንዳንተ ያለ አይመጣም) እያሉ በማሕሌተ ገንቦ እና በመወድስ ቅኔ የውዳሴ አምኃ እንደሚያዘንቡበት ያለ ፈሊጥ ይዘው፣ ለሥርዓቱ ያደሩ ምሁራንን የሚያሳይ አሰላለፍ ነው፡፡ እነኚህ ምሁራን፣ ለሥርዓቱ ቅቡልነት ለማስገኘት በየብዙኃን መገናኛው እየቀረቡ እንደ ማስረዳታቸውና ለሥርዓቱ ሌት ተቀን እንደ መድከማቸው፣ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር፥ በሹመት፣ በንዋይ፣ በቁሳዊና በትምህርት ማዕርግ ከፍ ከፍ የሚያደርጋቸው መምህራንን የሚይዝ መዋቅር ነው፡፡
በሦስተኛው የዩኒቨርሲቲው የሥርዓት መዋቅር ውስጥ የምናገኛቸው፡- በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች፥ በሞያቸው፣ በዕውቀታቸውና በምርምር ውጤቶቻቸው እያስተማሩና እየተመራመሩ ያሉ ዓይነተኞቹ መምህራን የሚገኙበት የመዋቅር ዕርከን ነው፡፡
ከዚኽ ሐቲት እንደምንረዳው፣ አንድ ሥርዓት ተቀየረ ወይም ወደቀ ሲባል፣ መገለጫ ወጎቹንና ስያሜውን ኹሉ ለጊዜው ያጣ፤ ወግ ሥርዓቱ ኹሉ የፈረሰ ቢመስልም፣ የኋላ ኋላ ግን፣ የታሪክ ምሁራን “የታሪክ ክትያ” እንደሚሉት፣ መገለጫ መልኩን ቀይሮ፣ ስምና ግብሩን ሌላ አስመስሎ መከሠቱ አይቀርም፡፡
ከላይ ባቀረብነው የቤተ መንግሥቱ እና የዩኒቨርሲቲው ወግ ውስጥ፣ የገጽታና የግብር መወራረስ እንዳለ ያሳያል፤ ሽግግሩም፥ ከጥንቱ “የዘር” መሳፍንታዊ አሰላለፍ ወደ አዲሱ “የብሔር” መሳፍንታዊ አሰላለፍ የመቀየር ሒደት ብቻ እንደኾነ በግልጽ እንረዳለን፡፡
የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት፤
የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር፥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የ2007 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ግኝት ሪፖርትን አስመልክቶ፣ ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ ለፓርላማ አንድ ሰነድ አቅርቦ ነበር፡፡ የሰነዱ ይዘት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኮሌጆች “የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲትን” ዋና ትኩረቱ ያደረገ ሲኾን፣ ይህን ተከትሎ፣ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የከፍተኛ ትምህርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ በዩኒቨርሲቲው የሦስት ቀናት የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
የኦዲቱን ግኝት ይዘት ለመፈተሽና የሪፖርቱን መሠረታዊ ጭብጥ በውል ለመረዳት፣ ኹለት የሒሳብ አያያዝ እና የኦዲት ባለሞያዎች ሞያዊ ገለጻ እንዲያደርጉልኝ ጠይቄ ነበር፡፡ እነርሱም ከኦዲት ግኝቱ የጨበጡትን ግንዛቤ፣ በተለያዩ ቀናት በአካል እየተገናኘን ካስረዱኝ በኋላ፣ ሐሳባቸውን ጠቅለል ባለ ማስታወሻ ጽፈው ሰጥተውኛል፡፡ በዚኽ ክፍል ሐቲት ውስጥ የተካተቱት የኦዲት ፅንሰ ሐሳባዊ ትንተናዎችና ከሪፖርቱ የተጠቀሱ አስረጂዎችና ማብራሪያዎች፣ በእነዚኽ ባለሞያዎች ምልከታ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡
የሪፖርቱ ቁልፍና መሠረታዊ መጠይቃዊ መነሻ፣ በመግቢያው ላይ እንደሚከተለው ይነበባል፤ ‹‹አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውስጥ ገቢውን የሚያስተዳድርበትና ከመንግሥት በጀት በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመደብለትን በጀት፣ ለበጀት ማዕከላቱ የሚደለድልበት፣ አፈጻጸሙን የሚከታተልበት፣ ዓመታዊ ሒሳቡን እየዘጋ የሚያሳውቅበት እና ለኦዲት የሒሳብ መግለጫዎችን፣ ሪፖርቶችንና መዛግብትን ከነደጋፊ ማስረጃዎች ለማቅረብ የሚችልበት ሥርዓት ለምን መዘርጋት አልተቻለም?›› ሲል ይጠይቃል፡፡
ይህም ማለት እንግዲኽ፣ ዩኒቨርሲቲው፣ በወል የሚታወቅ የፋይናንስ ሥርዓት ወይም ሕግ እና ደንብ፣ እንዲኹም የፋይናንስ እንቅስቃሴውን የሚከታተልበት የቁጥጥር ‘ራዳር’ የሌለው መኾኑን ያመለክታል፡፡ ይህ ጥሰት፣ መሠረታዊ የኾኑትን የኦዲት አሠራር መርኆዎች ስላልተከተለ ለምርመራ ሥራው አመቺ አልነበረም፡፡ በመኾኑም፣ ዩኒቨርሲቲው የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት እንደሌለው ያረጋግጥልናል፡፡ ይህ ኹኔታ፣ በአንድ ወቅት ባሕሩ ቀኜ፥ ‹‹ያዝ እጇን፣ ዝጋ ደጇን፣ ሳም ጉንጯን›› ብሎ ያዜመውን ያስታውሰኛል፡፡
በዚኽ ሰበብም፣ ከቁጥጥር ሥርዓት አለመኖር ጋራ ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸው የሚከተሉት የአሠራር ሕጸጾች እንደተገኙበት ሪፖርቱ ያስረዳል፤ ሀ) ተአማኒነት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አለመኖር፤ ለ) የፋይናንስ አሠራሩ፥ ሕግ፣ ደንብና ፖሊሲ የተከተለ አለመኾን፤ ሐ) የሒሳብና የንብረት አስተዳደር የሥራ ድርሻ ክፍፍል ጉድለት፤ መ) ለክፍያ በአግባቡ የተሰነደ የወጪና የገቢ መረጃ አለመቅረብ፤ ሠ) ዕቅዱንና የዕቅዱን አፈጻጸም የሚገመግም የበላይ አካል አለመኖር ናቸው፡፡
የዩኒቨርሲቲውን የፋይናንስ ሥርዓት ጥሰት በምናይበት ጊዜ፥ በሪፖርቱ ውስጥ በዋናነት ተጥሰዋል ተብለው የተዘረዘሩትን ሰፊ ጉዳዮች፣ ከሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት መሠረታዊ መርኆዎች አንጻር፣ በአምስት ማሕቀፎች ዘርዝሮ ማቅረብ ይቻላል፡፡
1/ የበጀት ሪፖርት ማቅረቢያ ሥፍረ ጊዜ፤
በሒሳብና መዝገብ አያያዝ ሞያ፣ እንደ “ሀሁ” ከሚቆጠር መርሕ እንደምንረዳው፣ ማንኛውም በበጀት የሚተዳደር ተቋም ሕጋዊና ትክክለኛ የፋይናንስ ሪፖርት ሊኖረው ይገባል፡፡ የፋይናንስ ሪፖርት የሚያቀርበው ግን፣ ተቋሙ ወይም ድርጅቱ በመረጠው ጊዜ ሳይኾን፣ የአካውንቲንግ መርሕ በሚያዝዘው ዓመታዊ ሥፍረ ጊዜ እና አስቀድሞ በተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስንመጣ፣ ይህን የበጀት ሪፖርት ማቅረቢያ ወቅትን የመጠበቅ፣ ወይም የበጀት ሪፖርት ማቅረቢያ ሥፍረ ጊዜ መርሕን የጣሰ እንደኾነ ከዋና ኦዲተሩ ሪፖርት መረዳት እንችላለን፡፡ ይህን የሕግ ጥሰት አስመልክቶ፣ የኦዲት ኮሚቴው በሪፖርቱ ከገለጻቸው ጉዳዮች መካከል፡-
3.1. በ2006 የተሟላ የሒሳብ ሪፖርት ለኦዲተር ለማቅረብ ለምን አልተቻለም? በ2007 መክፈቻ ሒሳብ፣ መመልከት የሚገባቸው በ2006 የዞሩ ቋሚ ሒሳቦችስ ለምን አልተመዘገቡም?
3.2. ሰኔ 30 ቀን 2007፣ ቀሪው ሒሳብ ፈሰስ ተደርጎ ባዶ መኾን የነበረበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባንክ ሒሳብ ቁጥር 14087395956 ለ/ኢ/ት ሚ/ር ፈሰስ ሳይደረግ ለምን ብር 1,176,894.39 ተገኘበት?
8.2. የኢንስቲትዩቱ የባንክ ሒሳብ ቁጥር 1000002264211 (ማለትም የውስጥ ገቢ አካውንት) ለምን በየወሩ የባንክ ሒሳብ ማስታረቂያ አይሠራለትም? የገቢ ሒሳብ ዝርዝር የለምና በዚኹ ሒሳብ ቁጥር ሰኔ 30 ላይ ብር 8,228,420.30 የሚታየው ቀሪ ሒሳብ ትክክል ስለ መኾኑ ለኦዲተሩ ለምን ማረጋገጥ አልተቻለም?”
8.3. በ2006 በጀት ዓመት የዞሩ ቋሚ ሒሳቦች (ተከፋይ፤ የተጣራ ሀብት ወዘተ.) ለ2007 በጀት ዓመት መክፈቻ ኾነው ለምን አልተመዘገቡም? የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የእነዚኽ፦ የሒሳብ ሪፖርት ለኦዲተር አለመቅረብ፤ ከተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የዞሩ ቋሚ ሒሳቦች አለመመዝገብ፤ ቀሪ ሒሳብ ፈሰስ አድርጎ የባንክ ሒሳቡን ባዶ ያለማድረግ ችግር፤ የዕቃ ግዢ በተያዘ በጀት ዓመት መገዛቱን የሚያረጋግጥ የክፍያ ወቅቱን የሚያሳውቅ ሰነድ አለማቅረብ፤ እንዲኹም የውስጥ ገቢ እና የፕሮጀክት ገንዘብ አለመታወቅ…፤ ዩኒቨርሲቲው የሒሳብ አያያዝ መሠረታዊ መርሖን እንደ ጣሰ የሚያረጋግጥ ግዙፍ የእውነታ ማሳያ ነው፡፡
2/ ተጨባጭ የማረጋገጫ ሰነድ አቅርቦት መርሕ፤
ከዋና ዋናዎቹ የሒሳብ አያያዝ መርሖዎች አንዱ የኾነው፣ “ተጨባጭ የማረጋገጫ/ደጋፊ ሰነድ አቅርቦት መርሕ”፦ እያንዳንዱ በፋይናንስ ሪፖርት ላይ የሚቀርቡ የሒሳብ እንቅስቃሴ ውጤቶች በበቂ ማስረጃ ወይም በሒሳብ አስረጂ ሰነዶች የተደገፉ እና የተመሳከሩ መኾን ይገባቸዋል፤ ይላል፡፡ እነዚኽም ሰነዶች አሳማኝ እና በቂ መኾን አለባቸው፡፡ ይህ መሠረታዊ መርሖ፣ ለእያንዳንዱ የሒሳብ አያያዝ እጅግ ወሳኝ ኾኖ ሳለ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግን ይህን በሚጥስ መልኩ የሚከተሉትን ጥፋቶች ፈጽሞ እንደ ተገኘ፣ ከሪፖርቱ ለናሙና ያኽል ከወሰድነው ማስረጃ መገንዘብ ይቻላል፡፡
3.3. ከርቀት ትምህርት የተገኘ ገቢን ለሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቲ አካላት በሒሳብ ርእስ 4008 ዝውውር መደረግ ሲገባው፣ በናሙና ኦዲት በተደረገው ብቻ ያለአግባብ የወጪ ማስረጃ ሳይኖር በድምሩ ብር 24,535,222.80 በወጪ ሒሳብ ተመዝግቦ ሪፖርት ተደርጓልና እንዴት ሊኾን ቻለ? ወይም ምን ማለት ነው? በዚኽ የናሙና ኦዲት መነሻ የተቀሩትን ዝውውሮች ፈትሻችኹ ምን አረጋገጣችኹ?
3.11. በድምሩ ብር 1,000,378.50 ሲከፈል መቅረብ ያለበት የእጅ በእጅ ሽያጭ ደረሰኝ በዱቤ ሒሳብ ተወራርዶ ተገኝቷልና፣ ለምን እንዲያ ሊኾን ቻለ? አልፎ አልፎም ቢኾን በተቋማችኹ የተለመደ አሠራር ላለመኾኑ ምን ማስረጃ አለ?
3.16. ክፍያዎች በገቢው የሒሳብ አርእስት ተመዝግበው ሪፖርት ለመደረጋቸው፤ ኦዲት ሲደረግም የተለያዩ የግንባታ የቅድመ ክፍያዎች በድምሩ ብር 8,521,076.04 በተሰብሳቢ ሒሳብ መያዝ ሲገባው በወጪ ሒሳብ ተይዘዋል፡፡ ይህ የሒሳብ አመዘጋገብ ችግር ለምን ተፈጠረ? አኹንስ ተስተካክሏል ወይ?
3.21. በዩኒቨርሲቲው የተጠቃለለ ሒሳብ ሪፖርት ላይ በጥሬ ገንዘብ እንዳለ የተመለከተው ብር 266,844.43፣ በሰኔ 30 ቀን 2007 በተደረገው የጥሬ ገንዘብ ቆጠራ ስላልተገኘ በተጠቃለለው ሒሳብ ሪፖርቱ የተመለከተው ብር 266,844.43 ጥሬ ገንዘብ በብልጫ ታይቷል፡፡ ለምን በብልጫ ታየ? አኹንስ ለችግሩ የማስተካከያ ርምጃ ተወስዷል ወይ?
4/ ሕጋዊ፣ ምክንያታዊ እና ፍትሐዊ የሒሳብ መርሖዎች፤
በተቋሙ ውስጥ የሚገኙ ማንኛውም የሒሳብ እንቅስቃሴዎች፣ የፋይናንስ ሕጉን የተከተሉና ምክንያታዊ እንዲኹም ፍትሐዊ መኾን አለባቸው። ከማስረጃ ውጪ፥ ደመወዝ፣ አበል፣ የትርፍ ሰዓት ሥራ ክፍያ ተከፍሏል፤ ተወዳዳሪ ያልቀረበበት ጨረታ ማካሔድና ያለውድድር ለፈለጉት ኩባንያ ኮንትራት መስጠት፤ አሳማኝ ምክንያት ሳይቀርብ፣ በጨረታውም አነስተኛ ግምት ያቀረበውን ትተው፣ ከፍተኛ ግምት ያቀረበውን መርጠው የጨረታ ኮንትራት መስጠታቸው፤ የጨረታ ውሳኔዎች ያለጨረታ አማካሪ ባለሞያዎች ይኹንታ እንዲወሰን መደረጉና ሌሎችም፣ የዚኽን መርሕ በዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ መጣስ ያመለክታል፡፡
ማስረጃ፡-
3.5. በሐምሌ እስከ ግንቦት 2007 ብር 2,075,620.34 የተለያዩ አበል ክፍያዎች ተብሎ ያለአግባብ ለሠራተኞች መከፈሉን የደመወዝ ሒሳብ ኦዲት ሲደረግ ተረጋግጧል፡፡ ለምን ያለአግባብ ክፍያ እንደተፈጸመና ለመመለሱም ቢገለጽ?
3.7. በግዢ ጨረታ ሕግ መሠረት በውስን ጨረታ ግዢ፣ አምስት ተወዳዳሪዎች ሳይቀርቡ ለአንድ ዓመት በሚቆይ የውል ስምምነት የጥበቃ አገልግሎትን ከአንድ ሓላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ለሦስት ኮሌጆች ከነተጨማሪ ዕሴት ታክሱ በድምር በብር 7,377,945.72 ገዝታችኋል፡፡ ከሕግ ውጪ ለምን ተፈጸመ? መጠየቅ ያለባቸው ተጠይቀዋል ወይ?
3.8. ያለጨረታ ውድድር በድምር ብር 1,190,803.16 ከዩኒቨርሲቲው ሓላፊነቱ የተወሰነ የግል ኢንተርፕራይዝ የኅትመት አገልግሎትና በድምሩ ብር 7,879,095.18 የማማከር አገልግሎትን በቀጥታ ግዢ ከኮንስትራክሽንና ዲዛይን አገልግሎት ማኅበር ግዢዎችን ፈጽማችኋል፡፡ ለምን ከሕግ ውጪ ግዢዎችን ፈጸማችኹ?
3.17. የመንግሥት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የድንገተኛ ሕክምና ሕንፃን ለማስገንባት በጠየቃችኹት ልዩ ፈቃድ መሠረት በድርድር፣ ቢቻል ለመሐንዲስ የዋጋው ግምት ሳይበልጥ …. የውሉ የገንዘብ መጠን የግዢ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲው ከፈቀደው የጭማሪ ጣሪያ ይቅርና የአማካሪ መሐንዲሱ ካቀረበው የ15% ጭማሪ ምክረ ሐሳብም በብር 50,991,857.19 ይበልጣል። በማን ፈቃድ፣ በየትኛው ሕግ፣ በማን ሥልጣንና ለምን በሚመለከተው ያልተፈቀደውን ወሰናችኹ? የመንግሥት የግዢ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ይኹንታ ለእናንተ ትርጉም ከሌለው፣ መጀመሪያውንስ ለምን ፈቃዱን ጠየቃችኹ? ሕጋዊ ሥልጣን እንዳለው አውቃችኹ ፈቃድ ከጠየቃችኹ ደግሞ ለምን ፈቃዱን እንደ ሕጋዊ ጥብቅ መመሪያ አላከበራችኹም?
6.6. በበጀት ለመፈቀዱ ማስረጃ ሳይኖር ለምን ከውስጥ ገቢ ብር 50,624,321.75 ወጪ ተደረገ?
4/ የተጣማሪነት መርሕ
በአንድ ተቋም ሒሳባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚታዩ ገቢዎችና ወጪዎች፣ በተጣመረ የሰነድ ማመሳከሪያ መቅረብ አለባቸው፤ ማለትም፣ አንድ ወቅታዊ የሒሳብ ገቢ እውነተኛነቱ የሚረጋገጠው፣ የወጡትን ወጪዎች በወቅቱ ከተገኘ ገቢ ጋራ ማጣመር ሲቻል ነው፡፡ ይህ መርሕ የተጣሰባቸው፣ በዩኒቨርሲቲው የተገኙ ስሕተቶችን፣ ሪፖርቱ እንደሚከተለው ይጠይቃል፡፡
ማስረጃ፡-
3.10. በ2006 በጀት ዓመት ገቢ ለኾነ ዕቃ ዓመቱንና ወቅቱን አልፎ በ2007 በጀት ዓመት ብር 2,365,757.60 ክፍያ ፈጽማችኋልና፣ በወቅቱ ለመክፈል ለምን ተሳናችኹ? በሕጉ መሠረት ክፍያ አለመፈጸሙ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል መገንዘብ አልተቻለም ነበርን? ይብራራ?
3.20. በበጀት ዓመቱ የሒሳብ ምዝገባ እና ሪፖርት የሌለ፣ ነገር ግን፣ ገንዘብ የተጠየቀበት መኾኑን የተገለጸና በችሮታ ጊዜ እስከ ሐምሌ 30 መከፈል ሲኖርበትም ከችሮታው ጊዜ በኋላ የተከፈለ የብር 39,393,465.69 ሒሳብ በኦዲቱ ተረጋግጧል። ይህ እንዴት ሊኾን ቻለ? በ2007 በጀት የሒሳብ ምዝገባ እና ሪፖርት የሌለ፣ እንዲኹ ከችሮታ ጊዜ በኋላ ለምን ተከፈለ?
5/ የሒሳብ ገቢ አመዘጋገብ ስምምነት መርሕ፤
ከመደበኛ እንቅስቃሴዎች የሚገኙት ገቢዎች፣ እንዲኹም መደበኛ ካልኾኑ ወይም ከአስተዳደራዊ እንቅስቃሴዎች የሚሰበሰቡት ገቢዎች፣ በሒሳብ ሪፖርቱ ውስጥ በተናጠል መቅረብ አለባቸው። በዚኽ መርሕ መሠረት፣ የዩኒቨርሲቲው አሠራር ሲፈተሽ፤ መደበኛውና አስተዳደራዊው የሒሳብ እንቅስቃሴ ተምታቷል፣ የውስጥና የውጭ ገቢ ተምታቷል፣ የቋሚ ንብረት እና የአላቂ ንብረት አመዘጋገብ ተምታቷል፡፡
ማስረጃ፡-
8.5. ከመደበኛ ተማሪዎች የተሰበሰበ የመደበኛ ሥራዎች ገቢን ለምን ወደ መደበኛ ሒሳብ በማስገባት ፈንታ ወደ ኢንስቲትዩቱ ገቢ ሒሳብ አካውንት ታስገባላችኹ?
9.2 ከውስጥ ገቢ የሚሰበሰብ ሒሳብ በገቢ ሒሳብ ተመዝግቦ ሪፖርት መደረግ ሲገባው፣ ብር 17,336,592.20 እንደ ቋሚ ሒሳብ ተደርጎ በተጣራ ሀብት ሪፖርት የተደረገ መኾኑንና ከዚኽ ውስጥ ብር 4,488,676.46 ከ2006 በጀት ዓመት የዞረ እጥረት ተብሎ መተላለፉን የኦዲት ግኝቱ ያሳያል፤ ለምን ተፈጠረ?
ወደ ጽሑፌ መደምደሚያ ከመድረሴ በፊት፣ ሦስት ትዝብቶችን አስቀምጬ ማለፍ እፈልጋለኹ። የመጀመሪያው፡- ከላይ በኦዲት ሪፖርቱ በግልጽ እንደታየው፣ ዩኒቨርሲቲው ሥርዓት አልባ ቢኾንም፤ የዩኒቨርስቲውን ጸጥታ እና ደኅንነት በሚመለከት ግን፣ ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት ያለው ግቢ እንደኾነ ግልጽ ነው፡፡
ኹለተኛው ትዝብቴ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፥ በፋኩልቲ ደረጃ፣ በፋይናንስ ማኔጅመንት እና አካውንቲንግ፤ በማኔጅመንት እና ኦዲቲንግ በማስተማር ተማሪዎችን ያስመርቃል፡፡ በመኾኑም፣ ከዩኒቨርሲቲው ይጠበቅ የነበረው፣ ሳይንሳዊና የተሻለ የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋትና ለሌላው ተቋም አርኣያ መኾን ነበር፤ ነገር ግን፣ ዩኒቨርሲቲው ለራሱ ተግባራዊ ባላደረገው የፋይናንስ አያያዝ እና ቁጥጥር ሥርዓ
ተማሪዎችን ማስመረቁ፣ የመስኩ ዕውቀት ስለሌለው ሳይኾን፣ ይኹነኝ ብሎ የቁጥጥር ሥርዓቱን ለማዳከምና ለማጥፋት እንደኾነ ግልጽ ነው፡፡ “ያዝ እጇን፤ ዝጋ ደጇን፤…” አይደል ዘፈኑስ የሚለው፡፡
ሦስተኛው ትዝብቴ፤ በአቶ ካሳ ተክለ ብርሃን ሰብሳቢነት የሚመራው ቦርድ፣ ይህ ኹሉ የፋይናንስ መርሕና አሠራር ጥሰት ሲፈጸም፣ ምን ዓይነት ሚና እንደነበረው ነው፡፡ በዚኽ ረገድ፣ ሪፖርቱም በተ.ቁ (2.8) በግልጽ እንዳሰፈረው፥ “የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአስተዳደር ቦርድ፣ የዩኒቨርስቲው የፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ጉዳዮችን የሚያይበትና አመራር የሚሰጥበት ሥርዓት ለመኖሩና እየተገበረ ለመኾኑ፣ የ2007 የኦዲት ሪፖርት ላይም የተወያየበት ለመኾኑ ግልጽ ይደረግልን?” ሲል ጠይቋል፡፡ እኔም በዚኽ ጽሑፌ፣ ምላሽ የምሻበት ጥያቄ ነው፡፡
ማጠቃለያ
በርከት ያሉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በአፍሪቃ ምድር፣ ሙስና ከገንዘብ ምዝበራ በላይ፦ በብሔር፣ በዘመድ እና በፖለቲካ ሽርክና ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ሙስና፥ አግባብ የለሽ ሹመትን፣ አድልዎንና ምስጋናን ያለችሎታና ያለአቅም የሚያስገኝ እኵይነት ነው፡፡
በዩኒቨርሲቲው የሰፈነውን፥ ሕገ ወጥነት፣ ወገንተኝነትና ፖሊቲካዊ ሽርክና ለመረዳት ያኽል ብቻ፣ የዛሬ ኹለት ዓመት ገደማ፣ በፕሬዝዳንት አድማሱ የተፈጸመውን ድርጊት በምሳሌነት እናንሣ።
የሕግ ትምህርት ቤት አስተማሪ ለመቅጠር እንደሚፈልግ ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ በማስታወቂያው መሠረት፣ አንድ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር ለመቀጠር ያመለክታል፡፡ መምህሩ፣ የሕግ ትምህርት ክፍሉ ያወጣውን መስፈርት ማሟላት ባለመቻሉ ማመልከቻው ውድቅ ይኾናል። ይህ በእንዲኽ እንዳለ፤ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ፣ በምክትል ፕሬዝዳንቱ በኩል ደብዳቤ ጽፈው፣ የተባለው ሰው፣ “በሕግ ትምህርት ቤቱ መቀጠሩን እንድታውቁት” ሲሉ ለትምህርት ክፍሉ ላኩ፤ ቅጥሩም ተከናወነ፡፡
ይብሱኑ፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ፣ “የሕግ ትምህርት ቤቱ ዲን ኾኖ ውድድሩን አሸንፏል” በሚል፣ ማንም ባልተወዳደረበት ኹኔታ ዳግመኛ ደብዳቤ ጽፈው፣ ይህንኑ ግለሰብ ከሕግና ደንብ ውጪ “ዲን ኾኗል” ብለው ሾሙት፡፡ አበው፥ አጠረ ቢሉት በርከክ አለ፤ የሚሉትን ዓይነት መኾኑ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ለሙስና መንሰራፋት ኹለት ኹነኛ ምክንያቶችን በማቅረብ ጽሑፌን ላጠቃልል፡፡
የሕግ የበላይነት መሻር፡-
የሰው ልጅ የፖለቲካ ነጻነትን ለመጎናጸፍ ሥልጣንን ይገድባል፤ እንደ ልጓም እንዲያገለግለውም፣ ሕግንና ደንብን እንደ መሣሪያ ይጠቀማል፡፡ በመኾኑም፣ የፖለቲካ ነጻነት፣ ከሕግ የበላይነት ይመነጫል፡፡
ለፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ ግን፣ ሕግ ማለት፣ ፍትሕን የተመረኮዘ ደንብ እና ሥርዓት ሳይኾን፣ የገዢውን ሥርዓት ያስደሰተ ኹሉ ነው፡፡ በዚኽ አተያያቸው፣ መንግሥትን አለመታዘዝ ማለት፣ ሕግን እንዳለመታዘዝ አድርገው በመውሰድ፣ የሕግን ምሕዋር ለቀው በፖለቲካ ምሕዋር ውስጥ ይቀዝፋሉ፡፡ ይህም፣ የጥንት ግሪካውያን፣ “ሕግ ማለት ብዙኃኑን የሚያስደስት ኹሉ ነው፤” ብለው ዳጥ ውስጥ እንደገቡት መኾኑ ነው፡፡
በተጨማሪም፣ የሕግ የበላይነት ሲባል፣ ከሰዎች አስተዳደር ወደ ሕግ አስተዳደር መዘዋወር ማለት ነው፡፡ ፋይናንሱ ላይ እንደታየው፣ ፕሬዝዳንት አድማሱን የሚመራው፣ የዩኒቨርሲቲው የንዋይ አስተዳደራዊ ሥርዓት፣ በሕግ መመራቱ ቀርቶ፣ በምትኩ፣ በሹመኞች ፈቃድና ፍላጎት ብቻ የሚመራ አስተዳደር ሰፍኖበታል፡፡ ይህም አካሔድ፣ የሕግን ሥርዓት በእጅጉ ይጥስና፣ ለምዝበራ የተመቸና በሹመኞች ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዲገነግን ሰበብ ኾኗል፡፡
በግለሰብ እና በማኅበረሰብ ጥቅም መካከል ያለ መገዳደር፤
የግለሰብ ጥቅም፣ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ ጥቅም የሚገዳደር ኾኖ መገኘቱ፣ ሌላው ኹነኛ የሙስናው ገጽታ ነው፡፡ ችግሩን ለመሻገር፣ የማኅበረሰብ ጥቅም ላይ የተመረኮዘ አካሔድ ሊኖር ይገባል፡፡
የግል ጥቅምን በማኅበረሰብ ጥቅም ላይ መጫን ሲባል፣ በፕሬዝዳንት አድማሱ ድርጊት እንደታየው፣ ማንኛውም ምሁር ከምርምር ጋራ የተያያዘ ሥራ ለመሥራት፣ ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ከሚያገኘው ገቢ “ኮሚሽን” እንዲከፍል የሚደረግበትን አሠራር በመዘርጋታቸው ላይ የተንጸባረቀ ነው፡፡ ይህም በሌላ ቋንቋ፣ “ምሁራዊ ጭሰኝነት” ብለን ልንገልጸው እንችላለን፡፡ የሚያስገርመው ነገር፣ “መሬት ላራሹ” በሚል የሀገር ህልውና ጉዳይ ታላቅ ንቅናቄ በተነሣበት ግቢ፣ ዛሬ እንደገና የጭሰኝነት ሥርዓት በሌላ መልክ መተከሉ ነው፡፡
ሪፖርቱ ካቀረባቸው ጥያቄዎች ስንነሣ፤ “ያለአግባብ ክፍያ፣ ያለአግባብ ንብረት ግዢ፣ ሕገ ወጥ ጨረታ፣ ገቢ እና ወጪ በወጉ አለመመዝገብ፣ አለ የተባለ ገንዘብ አለመገኘት፣ የውስጥ እና የውጪ ኦዲት ሪፖርት አለማቅረብ፣ ከበጀት ውጪ ያልተፈቀደ ገንዘብ ማውጣት፣ የገቢ ምክንያት አለመግለጽ፣ የተቀባይ ደረሰኝ አለመኖር፣ የሒሳብ ማስታረቂያ አለማዘጋጀት፣ ለተቀበሉት ገንዘብ ሕጋዊ ደረሰኝ አለማቅረብ” የመሳሰሉት ጉዳዮች ታይተዋል፡፡ እነኚኽ ኹሉ ተደማምረው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ላይ፣ የ720.1 ሚሊዮን ብር ያልተወራረደ ሒሳብ መገኘቱን፣ ለፓርላማው ሪፖርት ያቀረቡት ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ ገልጸዋል፡፡
በዚኽም ጽሑፍ ያረጋግጥነው የዩኒቨርሲቲው ሥርዓት አልበኝነት፣ ቀደም ብለን ለመግለጽ እንደሞከርነው፣ ሥርዓት ለመግባት ባለመፈለግ “ይኹነኝ ተብሎ” የተፈጠረ ነው፡፡ የማኅበረሰብ ጥቅም፣ ለጥቂት አማሳኞች ጥቅም መሥዋዕት ኾኖ በመቅረቡም የተፈጠረ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የታየው የሥርዓት ተፋልሶ፣ ከዚኽም በላይ ብዙ ሊባልለት የሚቻል ቢኾንም፤ ለጊዜው “ይቆየን” ብለን፤ በዋናው ኦዲተር የቀረበውን፣ የዩኒቨርሲቲውን ያልተወራረደ የሒሳብ ሪፖርት በማስረጃነት ይዞ፣ ጩኽታችንን የሚያስተጋባልን ዐቃቤ ሕግ እንዲሠየምልን የምንጠይቅበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ደርሰናልና፣ እስከ “ጽርሐ አርያም” በሚሰማ ጩኸት፤ “የዐቃቤ ሕግ ያለህ!!!” እንላለን፡፡