‹‹አማራ በመሆኔ ዘሬን እንዳልተካ ተደርጌያለሁ….በጣም ብዙ በደል በማንነቴ ብቻ ደርሶብኛል…›› መቶ አለቃ ጌታቸው /ለፍርድ/
/Ethiopia Nege NEWS//፦ በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን መዝገብ 16 ሰዎች በፌደራል አቃቤ ህግ “በሽብር“ መከሰሳቸው የሚታወቅ ሲሆን ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ከ16ቱ ተከሳሾች መካከል 6ቱ በነፃ ሲሰናበቱ ቀሪዎቹ ደግሞ ጥፋተኛ ተብለዋል።
ከአማራ ክልል ጥቅምት 2007ዓ.ም በያሉበት የተያዙት “በባህርዳርና ጎንደር አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ለአርበኞች ግንቦት ሰባት ለተባለ የሽብር ድርጅት የሀገሪቱን መረጃ በመስጠትና አባላትን መልምሎ ወደ ኤርትራ በመላክ” የሚል ክስ የተመሰረተባቸው እነ መቶ አለቃ ጌታቸው፤ ለሁለት ዓመታት ያህል ከከሳሽ አቃቤ ህግ ጋር ሲከራከሩ ቆይተዋል።
ዛሬ የተሰየመው 19ኛ ወንጀል ችሎት ልደታ ምድብ የሚከተሉትን ተከሳሾት ነፃ በማለት በአስቸኳይ ማረሚያ ቤቱ እንዲለቃቸው ትዕዛዝ አስተላልፏል።
1ኛ/ ተከሳሽ መቶ አለቃ ጌታቸው
4ኛ/ አወቀ ሞኝሆዴ
5ኛ ዘሪሁን በሬ
6ኛ ወርቅየ ምስጋናውና
7ኛ አማረ መስፍን
8ኛ) ተስፋየ ታሪኩ
10ኛ ተፈሪ ፋንታሁን
13ኛ እንግዳው ቃኘውና
15ኛ አግባው ሰጠኝ
በነፃ የተሰናበቱ ሲሆን
ጥፋተኛ ባላቸው ሰባት ተከሳሾች ላይ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠትም ለሰኔ 16 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። ጥፋተኛ የተባሉት ተከሳሾች፦
2ኛ ተከሳሽ በላይነህ ሲሳይ
3ኛ ተከሳሽ አለባቸው ማሞ
9ኛ ተከሳሽ ቢሆነኝ አለነ እናዲሁም
11ኛ ፈረጀ ሙሉ
12ኛ አትርሳው አስቻለው
14ኛ አንጋው ተገኘ
16ኛ ተከሳሾች አባይ ዘውዱ ናቸው።
ተከሳሾቹ በማዕከላዊ የወንጀል ምርመራና በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በነበሩበት ወቅት የደረሰባቸውን የመብት ረገጣ በተደጋጋቢ ለፍ/ቤት ለማስረዳት የሞከሩ ቢሆንም ፍ/ቤቱ በወቅቱ ትኩረት አለመስጠቱን ሒደቱን የተከታተሉ ታዛቢዎች ይገልፃሉ።
አንደኛ ተከሳሽ የሆነው መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን ‹‹አማራ በመሆኔ ዘሬን እንዳልተካ ተደርጌያለሁ….በጣም ብዙ በደል በማንነቴ ብቻ ደርሶብኛል…›› ሲል ፍርድ ቤቱ ሳያስጨርሰው እንዳቋረጠው መገለፁን ለአብነት ማንሳት ይቻላል።
የሰማያዊ ምክር ቤት አባል 15ኛ ተከሳሽ አቶ አግባው ሰጠኝ ከቂሊንጦ ማ/ቤት የእሳት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ሌላ ክስ እንደተመሰረተበት ይታወቃል።
በሌላ ዜና ይኸው ችሎት በእነ ጉርሜሳ አያና ለ7ኛ ጊዜ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ለሰኔ 15/2009 ሰጥቷል።