ክፍል ሁለት
የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ህጋዊና መልስ የሚሻ ጉዳይ ነው ክፍል ሁለት የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ስለ ኦሮሞ ህዝብ ታሪካዊ አመጣጥ፣ አሁን ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለማሳየትና አሉ የሚባሉት ችግሮችም በቀጣይ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ የሚፈቱበትን ግላዊ አስተያየት ለመስጠት እንጂ ከማንኛውም ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ ወገናዊነትን ለማሳየት አሊያም አንደኛውን ወገን ሂስ ለመስጠት የተዘጋጀ ጽሁፍ አይደለም።
የዚህ ጽሁፍ አቅራቢም የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባልም ደጋፊም አይደለችም። እንደ ሁሉም ቋንቋ ኦሮምኛም የራሱ የሆነ የዲያሌክቲስን ህግ የተከተለ ሂደት አለው። ማንኛውም ቋንቋ ዘላለማዊነት (eternity) የለውም። የሰው ልጅ ከተፈጠረና ቋንቋ መጠቀም ከጀመረበት ዘመን አንስቶ በርካታ ቋንቋዎች ተወልደዋል፣ አድገዋል፣ አርጅተዋል ከዚያም ሞተዋል። ለሰው ልጅ ቋንቋ ከመግባቢያነት በላይ የማንነትና የልዩነት ምንጭ ተደርጎ መወሰዱ በራሱ ለጊዜው ተቀባይነት የሌለው ሃሳብ ቢሆንም ምንጩ አርቆ ካለማየት (short sighteedness) ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።
የሰው ልጅ ባህሪያዊ እኔነት (ego) ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ አንደኛውን ቡድን ወደራሱ ለመሳብ ሲል ብቻ አንዴ በቋንቋ፣ አንዴ በቆዳው ቀለም፣ አንዴ በመደብ፣ አንዴ በጾታ፣ አንዴ በሚያመሳስል ባህሪይ (መጥፎም ቢሆን) ወዘተርፈ እየተቧደነ በተፈጥሮ የሌለ (non-existent) ህሊናዊ ስዕል በመፍጠር የራሱን ሰላምና ዕረፍት አውኮ የሌሎችንም በማወክ በንደዚህ ዓይነቱ መቧደን የማያምኑትም ጭምር ሳይወዱ ወደዚህኛው ፈሊጥ እንዲገቡና ያ ትክክለኛ ዕምነታቸውን መልሰው መላልሰው እንዲጠራጠሩት በማድረግ ተፈጥሮ የሰጠችንን የማወቅና ህሊናን በነጻነት የማሰራት ስጦታ ችላ ብለን በቀን ተቀን እንካ ስላንትያህ እንድንጠመድ አድርጎናል። አሁን አዲስ ፍልስምና በማምጣት ስለ አዲስ ፍልስምናው ለመወያየት ሳይሆን ባለውና ምድራችን በመትከተለው ዘመናዊው አስተሳሰብ ተመስርተን የኦሮሞ ህዝብ ዙሪያ በተጨባጫዊነት (objectivism) ላይ ተመስርተን እንወያይ። የኦሮሞ ህዝብ ባብዛኛው እንደሁሉም ሰላም ወዳድ ህዝብ በሰላም መኖር፣ በሰላም ልጆቹን ማሳደግና ለቁም ነገር ደርሰው ማየት ነው የሚመኘው።
ማንም ህዝብ እንደ ህዝብ ከዚህ የተለየ አመለካከት ሊኖረው ይችላል ብሎ ለማሰብ ከባድ ነው። የህልውና ጥያቄ በበርካታ አካላዊና ስነልቦናዊ መስፈርቶች ላይ እየተቀመጠ ሲሰላ ደግሞ እንደየትርጓሜው የተለያየ ስዕል ይሰጠውና መኖር ብቻውን ምንም ትርጉም የለውም፣ መኖር እነዚህንና የመሳሰሉት መስፈርቶች አሟልቶ ሲገኝ ነው ሙሉ የሚሆነው የሚል ትንታኔን ያስከትላል። አንድ ሰው በህይወት ለመኖር እነዛ መሰረታዊ ፍላጎቶችች (basic needs) የሚባሉት ማግኘት ይኖርበታል፡ ከነክብሩና ከነስነልቦናዊ ዕርካታው ጋር እንዲኖር ግን ሰው በርካታ ተጨማሪ ነገሮች ያስፈልጉታል። በምግብ፣ በልብስና በመጠለያ ብቻ የሚገኝ የተሟላ ስብዕና የለም። የሰው ልጅ መሰረታዊ መለኪያ የሆነው የማህበራዊ እንሰሳነቱ መገለጫ አንዱ ግንኙነት (communication) ነው።
በዚህ ኮሙዩኒኬሽን ጥልቀት ውስጥ ሃሳብን በነጻነትና ካለምንም ችግር ማቅረብና መደመጥ መቻል ነው። በዘመናዊ አገላለጽ ዲሞክራሲ ነው። ይህ ሰፊ ቃል በውስጡ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብት፣ የመደራጀትና የማደራጀት መብት፣ በህግ ፊት እኩል ሆኖ የመታየት መብት፣ የመደገፍና የመቃወም መብት፣ በመቃወም ምክንያት ሰለባ ያለመሆን ጥበቃ (protection) የማግኘት ወዘተ መብቶችን ያካትታል፡ ዲሞክራሲ በፍትህ የበላይነት የሚጠበቅ በመሆኑ። ከሰው መፈጠር ጋር አብረው የተፈጠሩ ቅዱስ ሃሳቦች የሰው ልጅ በመደብ መከፋፈል ሲጀምር የሁሉም መብት መሆናቸው እየቀረ የጥቂት ባለሃይሎች (dominant groups) ልዩ መብት (exclusive right) እየሆነ መጣ። በዚህ ምድራችንን የተፈጥሮ ህጎችን በመጣስ የከፋፈላት ሂደት ሰለባ ሳይሆኑ ጥቂት ህዝቦች ያንን ተፈጥሮአዊና ጥንታዊ (primitive) የአኗኗር ዘይቤ በዘመናዊ አኳሃን አሻሽለው ግን መሰረታዊ ህግጋቶችን ሳይቀይሩ በልዩ ባህሪይ የቀጠሉ ህዝቦችም ነበሩ።
ከነዚህ አስደናቂ ህዝቦች አንዱ የኦሮሞ ህዝብ ነው። የስልተ ምርት ለውጥና የመደብ መኖር በስርዓቱ ተቀብሎ መሰረታዊ የሆነውና የማይገሰሰውን የዲሞክራሲ ስርዓትን በከፍተኛ ጥበቃ አቆይቶ ሃብትና ዘር ለስልጣንና ለሹመት እንደማያበቃ በስነ ቃል ከትውልድ ትውልድ በተላለፈው የገዳ ስርዓት አማካኝነት ይዞት ለዘመናት ተጉዟል።
ጎረቤት ታውኮ በሰላም ለመኖር እንደማይቻል ሁሉ ባገራችን በየአውራጃውና በየክፍለሃገሩ በተፈጠሩ ቱጃሮችና ተስፋፊ ወራሪዎች አማካኝነት ወረራና ሁከት ተዛመተ። ከነስሙም ዘመነ መሳፍንት የሚባል ሰፊ የጊዜ ሰሌዳ ተፈጠረ። በዚህ ጊዜ ሌሎች በርካታ የራሳቸውን ባህላዊና ማህበራዊ እሴት ለመጠበቅ እየፈለጉ ካቅማቸው በላይ በሆነ ሁኔታ ሰለባ እንደሆኑት ህዝቦች ሁሉ የኦሮሞ ህዝብም ሰለባ ሆነ።
የጊዜ ሃያልነት ያንን የበደል ዘመን ወደ ታሪክ እየቀየረው መጥቶ ህዝቡ እነዛ ጥቂት በዳዮቹን ሳይሆን ተበዳዮች የሆኑት ሚሊዮኖችን በማየት በተፈጠረው ስርዓት ውስጥ እራሱን ትክክል (normalize) አድርጎ ለዘመናት አብሮ ኖሯል። ከበርካታ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ጋርም ተጋብቶና ተዋልዶ ብቸኛ (pure) ነገድ ከመሆን ወጥቶ ድብልቅ (hybrid) ሆኗል።
ለዚህም ነው አሁን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እራሳቸውን ከአንድ ብሄር በላይ ውስጥ ተወላጅ ሆነው ለመገኘት የሚገደዱት። ይህ አንድ ጎሳ ስልጣን ላይ ሲወጣ እሱን የመምሰል ባህሪያዊ ነገር ትተን አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ህዝቦች የትውልድ ሃረጋቸው ሲመዘዝ በአምስትና ከዚያም በላይ በሆኑ ጎሳዎች ውስጥ ተወልደው የሚገኙበት ጊዜ ብዙ ነው። የኦሮሞ ህዝብ በማንኛውም ምክንያት ወደ ክልሉ ይሂዱ ብቻ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ድብልቅ ዘር ያላቸው ህዝቦች እራሳቸውን እንደ ኦሮሞ ቢገልጹም የዘር ሃረጋቸ ሲመዘዝ ግን ወደ አራቱም የሃገሪቱ አቅጣጫ ይሄዳል።
ይህ ዕውነት በርካታው የኦሮሞ ህዝብ ያውቃል። የአብዛኛው የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄም በሃገራችን ከሌሎች ህዝቦች ጋር ለመኖር ከተፈለገ የኛን ማንነት በሌሎች ማንነት እንድንቀይር መገደድ የለብንም የሚል ነው። ከዚያም ባሻገር ማንም እራሱን ይምሰል፣ እራሱንም ከፍ ያድርግ፡ እራሱ ከፍ የሚያደርገው ታዲያ ሌሎችን ዝቅ በማድረግ መሆን የለበትም በማለትም ያሳስባል። ያንዱ ቁንጅና አንደኛውን ፉንጋ በማድረግ የሚገለጽ ከሆነ አደገኛ ነው። ከዚያ ጎን ለጎንም ደግሞ አንዳንድ ስሜታዊ ሰዎችም የሌሎች ከፍ ማለትና እኔ ትልቅ ነኝ ብሎ ማቅራራት እነሱን ያሳነሳቸው መስሎ ስለሚታያቸው ብቻ ተቃራኒ ድርጊት ሲሰሩ ይታያሉ።
እነዚህ ቀጥታዊና (direct) ትርጉማዊ (implied) ስሜቶች ላይ የተመሰረቱ አስተሳሰቦች እስከተስተካከሉ ድረስ የኦሮሞ ህዝብ የመገንጠልን ጥያቄ እንደ ሁነኛ መንገድ እንደማይከተለው የሁሉም ሰው ልብ ያውቀዋል። በመጀመሪያ የኦሮሞ ህዝብ ስለ አንድነት ጥቅም በደንብ የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ ከአንድነት ሌላ አማራጭ ወስዶ ወደማያባራ የርስ በርስ ዕልቂት እንዲገባ አይፈልግም። የስነልቦናዊ ዘይቤው፣ የቋንቋና የባህል መስፈርቶች ሁሉ በአማካይ መለኪያ ተሟልተው ቢገኙም እንኳ ኦሮሚያ ክልል ካለበት ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ አንጻር ለብቻ መሆን እጅግ አዳጋች አሊያም የማይሞከር አቅጣጫ ነው። የሰከነ አዕምሮ ያለው ብዙው የኦሮሞ ህዝብ ሃገሪቱ የምታስገኘውን ጸጋ አብሮ መካፈልና በራሱ ማንነት ላይ እርሱ ብቻ ወሳኝ የሚሆንባት ጠንካራና ሁሉም በውዴታ የሚቀበላት ኢትዮጵያ እንድትመሰረት ይፈልጋል።
ይህ የመላው ዓለም ችግር የሆነ የጎሳና የዘር አስተሳሰብ የዕድገት ደረጃው ሲጨርስ የዲያሌክቲክስን ህግ ተከትሎ ወደ መቀመቅ የሚወርድ ዘመን አመጣሽ ወረርሺኝ መሆኑ ቢታወቅም በሚሰራበት ወቅት ታዲያ ኋላ በጸጸትና በይቅርታ የማይጠገን ሰፊ ክፍተት ፈጥሮ ሊያልፍ እንደሚችል ለመገመት አዳጋች አይሆንም። በአንድ ወቅት ይሰሩ የነበሩ አስተሳሰቦች ከዓለም መለወጥና ከሰው ልጅ አስተሳሰብ አድማስ መስፋት ጋር እየተለወጡ መሄዳቸው የግድ ነው። አሁን ያለው የኦሮሞ ህዝብ ልከኛ አቤቱታ (Genuine inquiry) ምንድነው ካልን ደግሞ ከመላምትና ከሃሳባዊ ትንተና ወጥተን በተጨባጭ ነገሮች ላይ ለመወያየት እንችላለን። ባሁኑ ሰዓት እንደ ሁሉም የሃገራችን ህዝቦች የኦሮሞ ህዝብም የስራ አጥነት፣ የድህነትና የመሰረታዊ መብት መነፈጎች ያጋጥሙታል። እነዚህ ለሰው ልጅ ሙሉዕነት (completness) የሚያስፈልጉ ነገሮች ባልተሟሉባቸው ሃገሮች ሁሉ ከሰላማዊ ሰልፍ አለፍ ወዳሉ ግጭቶችና አመጾች የሚገቡበት ሁኔታ ሰፈጠርም አይተናል። እነዚህ ህዝባዊ ነውጦች በጣም ብዙ ታምራት ሲያደርጉም ታይተዋል።
ባሁኑ ሰዓት ባገራችን ያለው መንግስት በራሱ ፍልስፍና ተጠምዶ ለሃገራችን ህዝቦች ይበጃል ያለውን አመለካከት ወደ ተግባር ለመተርጎም ሲፍጨረጨር እናያለን። በርካታ ሊካዱ የማይችሉና ለመካድ መሞከር በራሱ ትዝብት ላይ የሚጥል የልማት ተግባሮችም ተከናውነዋል። ከዚህ ልማትና ብልጽግና ጎን ለጎን ደግሞ ብዙ ሙስና አድልዎና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተከናውነዋል፡ አሁንም በመከናወን ላይ ናቸው። የፖለቲካ ችግሮች የሰላ የፖለቲካ ትግል በማከናወን መፍታት መልካም ዘዴ ሆኖ ሳለ በነዚህ የጎሳና የብሄርተኝነት አመለካከቶች ካባ ስር ተደብቆ ስለሚመጣ በአንድ ሳይንሳዊ መንገድ ብቻ ለማከም የሚያስቸግር ግራ የተጋባ የሃገር አቅጣጫ እስኪመስል ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ሲከሰት እናያለን። የብሄርና የጎሳ ጉዳይ ከሚገባቸው በላይ ተራገቡ እንጂ የኖሩና የሚቀጥሉ ማህበራዊ ችግሮች ናቸው ከሚሉት ጎን ለጎን የዚህ ሁሉ ጣጣ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሃላፊ ነው የሚሉ ጭፍኖችም ሞልተዋል። በመጀመሪያ ከስድሳ ዓመት በፊት የተነሳው የተቀጣጠለው የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ጥያቄን ያነገበ ትግል መንሴው መደባዊ ሳይሆን ብሄራዊ ጭቆና ነበር።
አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከስድሳ ዓመት በፊት አልነበረም። የትግራዮች የትግል አቅጣጫም መሰረቱ ብሄራዊ ጭቆናና አድልዎ ለመፍታት እንደነበር ነው የሚታወቀው። ይህ የነበረን ኣያለ የብሄራዊ ማንነት ጥያቄ ለመፍታት የአንድ ወገን ፖለቲካዊ ጥረት ብቻውን ፋይዳ የለውም።
ፖለቲካዊ ችግሮች እንደ ተላላፊ ህመም (communicable disease) በአንድ ዓይነት መንሴና በተወሰነ አቅጣጫ ወደ ማህበረሰቡ ቢገቡም ከሌሎች የቆዩ ችግሮች ጋር ግንባር በመፍጠር ህመሞቹ በተፈጥሮ ሊያስከትሉት ከሚገባ ስሜትና ጉዳት በላይ ሲገኑ ይታያሉ። እነዚህ የብሄራዊ ማንነት ጥያቄዎችም ራሳቸውን ችለው ሳይሆን በማህበረሰቡ ስር ከሰደዱ (chronic) አመለካከቶችና ባህላዊ ኣንዲሁም ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች ጋር ተሰባጥረው ትርጉማቸውን የሳቱ እስኪመስሉ ድረስ መልካም ባልሆኑ ሰዎች ዘንዳም መጠቀሚያ ሆነው ሃገርን ሲያውኩና ልማትን ሲያደናቅፉ ይታያሉ።
የኦሮሞ ህዝብ ኣንደ ሁሉም ህዝብ የራሱ የሆኑ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ስነልቦናዊ ወዘተ እሴቶች አሉ። የአንድ ህዝብ ዕውቀትና የህሊና የመገራት ባህሪይም በራሱ ከነዚህ አስተሳሰቦችና ውርስ (aquired) ዕውቀቶች ጋር ባያሌው ስለሚነካኩ አስተሳሰቦች በብቻቸው ሊቆሙና ራሳቸውን ችለው ጥያቄና መልስ ሊሆኑ አይችሉም። በሌላ አገላለጽ ስናየው የሰው ልጅ አረዳድ እንደ ሰዉ የአቀባበል ደረጃና የስነልቦና ዝግጅት የሚለያይ እንጂ ተመሳሳይነት (uniformity) እንደሌላቸው ነው። አንድን ነገር ለመረዳት የተቀባዩ (receiver) ህሊና ቅድመ ስሪትና ዝግጅት የሚሻ በመሆኑ ህዝብን ወደ ተመሳሳይ አቅጣጫ ለማምጣት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው። በምድር ላይ ህዝብን አሳምኖ እንደ መምራት ከባድ ችሎታን የሚፈታተን ምንም ዓይነት ክስተት ሊኖር አይችልም። ህዝብ እንደ ህዝብ ሲነቃ፣ ሲደራጅና ሲታጠቅ ብቻ እንጂ ብዛት ስላለውና በደፈናው የህዝብ ፎርማሊቲ ስላሟላ ብቻ ታሪክ ሊሰራ አይችልም።
እንደ አጠቃላይ አረዳድ (consensus) “ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ ነው” የሚል የቆየና የተለመደ አባባል ቢኖርም በተጨባጭ ያልነቃ ያልተደራጀና ያልታጠቀ (በስነ ልቦና ያልተዘጋጀ) ህዝብ ታሪክ ሰርቶ አያውቅም፡ ወደፊትም ሊሰራ ይችላል ተብሎ አይጠበቅም። በተለያዩ ህዝቦች ላይ የሚደርሱ በደሎች በብዛታቸው መጠን ሊመከቱና በእንጭጩ ሊቀሩ የማይችሉበት ዋነኛው ምክንያትም ይኸው የብዛት ትርጉም በሌሎች መስፈርቶች ላይ የተመሰረት መሆን ነው። አሁን ባገራችን የሚታየውና በዳያስፖራው ዘንዳ እየተራገበ ሃገሪቱ በሰፊው ህዝብ አመለካከት ሳይሆን በግለሰቦችና ቡድኖች መልካም ፈቃድ ንጹህ አየር የምትተነፍስ የሚያስመስል አኪያሄድ በራሱ የዚህ ጽንሰ ሃሳብ ውጤት ነው። የገለሰቦች ሚና የማይናቅ መሆኑ በብዙ ታሪካዊ ምዕራፎች ላይ ታይቷል። አሁን ግለሰቦችና ቡድኖች የኦሮሞ ሰፊ ህዝብ ያልጠየቀውንና ያላሰበውን የግድ ያንተ አመለካከት ይሄ ነው በሚል ተከታታይ ውትወታ (brain storming method) እራሱን እንዲጠራጠር ለማድረግ ሙከራቸውን ቀጥለዋል። የኦሮሞ ህዝብ ከማንም ህዝብ ባላነሰ አልያም ላቅ ባለ ለአንድነትና ለህብረት ከፍተኛ ከበሬታ ያለውና የነዚህ ግለሰቦችን ህልምና የስልጣን ጥማት ለማርካት ሲልም ለነሱ አቴቴ (bloody marry) የሚገብረው ትርፍ ደምና ህይወት የለውም።
በታሪክና በዝና የሚኩራራባቸው ሳይሆን ከጉያው ሳይርቁ ታሪክ የሚሰሩና ዘራቸውን በሰላም የሚያስቀጥሉ ክልጆች እንዲኖሩት ነው የሚመኘው። ምክንያቱም አሁን በፊት ሳይነቃና ሳይደራጅ የደረሰበትን በደል ደግሞ ለመቀበል፡ የሚችለበት ምንም ዓይነት ቦታ (ground) የለምና። የኦሮሞ ህዝብ አሁን ነቅቷል፣ ተደራጅቷል፣ የስነ ልቦና ዝግጅቱም በቂና እራሱን ከማንኛውም ጥቃት የሚያስጠብቅ ደረጃ ላይ ለማድረስ ብዙ መከራ ማለፍ የማይፈልግበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ነው። ለዚህም ነው ጥያቄዎቹን በየፊናው በማቅረብ መንግስት ሳያማክረው ያወጣቸውን እንደ አዲስ አበባ ማስተር ፕላን ያሉትን ሌሎች ነገሮችም ለማስቆም የቻለው።
ይህ እመርታ ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት የማይቻል አልያም የማይሞከር እንደነበር ሁሉም ያውቀዋል። የሰው ልብ ጉጉና ችኩል ቢሆንም የታሪክ የለውጥ ሂደት (evolution) ግን አዝጋሚ በመሆኑ ይኸው በሃምሳ ዓመት ለውጦች እየታዩ መጡ። አሁን ኦሮሞ መሆን የሚያኮራና በራስ ስምም ሆነ በራስ ቋንቋ መገለጽ ምንም የማያሳፍር ሆኗል። ገዢ መደቦች አንድን ህዝብ ረግጠው ለመያዝ የሚጠቀሙበት ዋነኛ መንገድ በተጨቋኙ ህዝብ ላይ የስነልቦና ጦርነት በመክፈት እሱን የሚመለከቱ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች እንዲቀጭጩ ማድረግ ነው። ቅኝ ገዢዎችም እንደዚሁ የጠሉት ህዝብ ያለውን ሳይሆን የጎደለውን፣ መላካሙን ሳይሆን ጉድለቱን ደጋግመው በመንገርና በማስነገር አንሶ እንዲታይና በማንነቱ እንዲያፍር ያደርጋሉ። ይህ ባህሪኦያዊ ነው። ከመቶ ዘመናት በላይ በኦሮሞና በሌሎች ብሄሮች ላይ የደረሰው ትቃትም ይኸው ነበር። እነዚህ አደገኛ ቀስቶች ተሰባብረው ወደ ጥልቁ ስለተጣሉ አሁን በነሱ ዙሪያ መስራት ትርፉ ድካም ይሆናል። ቢሆንም ታዲያ እነዚህ ሸካራ የታሪክ ምዕራፎች የተዉኣቸው በርካታ ሊታረሙ የሚገባቸው አስተሳሰቦችና ጠባሳዎች አሁንም አሉ። እነሱ በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ መመከትና መወገድ አለባቸው፡ ይህንን ለማድረግ ጊዜውም መድረኩ ተመቻችቷል።
ይህ ከሆነ ታዲያ የኦሮሞ ህዝብ ለምን የመበደል ድምጾችን እስከዛሬ ድረስ ያሰማል የሚል መልካም ጠያቂ መነሳቱ የግድ ነው። ዓባይ ጎርፉ ቢቆምም ከስር በየስርቻው የሚንዠቀዠቁ በርካታ ምንጮች መኖራቸው የግድ ነው። ጎርፉን እንጂ እርጥበቱ ፈጽሞ ለማጥፋት ዓባይ ከቦታው መነሳት አለበት ማለት ነው። የዚህ መልካም ያልሆነ አስተሳሰብ ሰለባዎች የሆንን ሰዎች በህይወት እስካለንና እናም ይህንን ርክሰት ያቀበልናቸው ልጆች ካሳደግን ይህ ክፋት ረዥም ዕድሜ ሊያገኝ ይችላል። ይህንን መጥፎ አስተሳሰብ የያዙ ጥቂትም ቢሆኑ በሆነ ታሪካዊ አጋጣሚ ስልጣን ላይ ሲወጡ ደግሞ ያ አውሬነታቸው በታክስ ከፋይ ወጪ ተግባር ላይ ለማዋል ሲጥሩ ያኔ የኦሮሞ ህዝብ እምቢ ይላል። ይህ ተገቢ (legitmate) አኪያሄድ ነው። ይህ ሂደት ደግሞ ገና ብዙ ይቆያል፡ የኦሮሞን ህዝብ ለትጥቅ አልያም ሰላማዊ ላልሆነ ትግል የመጋበዝ ሃይል ግን የለውም ወደፊትም እንደዚህ ያለ ስጋት ሊመጣ አይችልም። የኦሮሞ ህዝብ የትግል አቅጣጫ በማይሆኑ ሰዎች እጅ ሲገባ ግን እራሱንም ጭምር ወደሚጎዳና ወደማይተገበር ስልት አስገብተው ወደማያባራ ኪሳራ ሊያስገቡት ይሞክራሉ።
ሰላም እንሰንብት
ቀጣዩን በክፍል ሶስት ይመልከቱ
yordanosbtola@gmail.com