ቪኦኤ ሰሞኑን በሐረር ከተማ ስለሚገኙ ተማሪዎች ልብ የሚነካ ታሪክ አስደምጦናል። ታሪኩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ሰብስቦ እና በአንድ ቤት ውስጥ አድርጎ ለማኖር እና ለማስተማር እየጣረ ስለሚገኝ ወጣት የሚያትት ነው። ወጣቱ ተስፋ አለባቸው ይባላል። ተስፋ ከሰዎች እያሰባሰበ ኪራይ በሚከፍልበት ቤት ውስጥ 40 የጎዳና ልጆችን ለማስተዳደር እያታገለ ነው። ተጣጥሮ ትምሕርት ያስጀመራቸው እና በአሁኑ ሰዓት በተለያየ የትምሕርት እርከን ላይ የሚገኙት እኒህ ልጆች አኗኗራቸው አሳዛኝ ነው። ከትምሕርት ቤት መልስ ዕድለኛ ከሆኑ የሚቀርብላቸው ምግብ ከሆቴል ቤቶች የተሰበሰበ ትርፍራፊ ነው። ከእርዛት የሚታደግ ልብስ፣ ከእንቅፋት የሚያድን ጫማ፥ ለእነሱ ከስንት አንድ የሚገኝ ዕድል ነው፡፡
እንዲያም ቢሆን ብዙዎቹ መንፈሰ ጠንካራ እና የዜግነት ድጋፍ ካልተለያቸው ትልቅ ቦታ የሚያደርስ ተሰጥኦ እና ብቃት ያላቸው ናቸው። በዓመታት ውስጥ ያለፉበት አበሳ በስነልቦናቸው ላይ ጫና ማምጣቱን ተጋፍጠው የሁለተኛ ደረጃቸውን በከፍተኛ ውጤት ያጀቡ፣ በስፖርት እና መሰል ተሰጥኦዎች ትልቅ ተስፋ ያላቸው ፣ በትንሽ ድጋፍ ትልቅ ማማ ላይ የሚደርሱ አይነት ናቸው፡፡
‹‹ልጆቹ የተረጂነት ስሜት እንዲይዙ አልፈልግም›› የሚለው የእነዚህ ልጆች አሰባሳቢ እና ደጋፊ ተስፋ አለባቸው ለበጎ አድራጎት ስራው ቋሚ ገቢ የሚያስገኝ ዕቅድ በራዲዮ ጣቢያው ላይ አጋርቷል፡፡ የመጀመሪያው ዕቅድ በተከራየው ቤት ውስጥ እንጀራ እያገገረ ለሆቴሎች በማቅረብ እንዲሁም የልብስ አጠባ አገልግሎት ለአካባቢው ነዋሪዎች በመስጠት የሚገኘውን ገቢ ልጆቹ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን የሚያሟሉበት ለማድረግ ነው፡፡ እነዚህን ሥራዎች ለመስራት ሚያስችሉ ዕቃዎች መግዣ በትንሹ 100ሺ ብር ($4500) ያስፈልጋል። እንዲሁም ልጆቹን ቢያንስ ሥራውን እስኪጀምሩ ድረስ እቤት ውስጥ አብስለው እንዲመገቡ የስድስት ወር ብናዋጣላቸው በወር ለአንድ ልጅ $20፣ በአጠቃላይ ለ40 ህጻናት የ6 ወር ወጪ $4800 ይሆናል። በአጠቃላይ በድምሩ ($9300) ይሆናል። እኛ ለዚህ ገንዘብ የበኩላችንን ጠጠር ብንወረውር ተማሪዎቹን በብዙ እንረዳቸዋለን።
ስለሆነም ውድ ኢትዮጵያዊያን! የሚበሉት የረባ ነገር ባይኖርም፥ ትልቅ የሚያልሙትን፣ የሚለብሱት የሚረባ ባይኖራቸውም፥ ተስፋ የደረቡትን እኒህን ህጻናት እና ታዳጊዎች፣ ታሪካቸውን እንቀይር ዘንድ የተቻላችሁን ድጋፍ ታደርጉ ዘንድ ወደ እናንተ አምጥተናል። በምንታወቅበት የመረዳዳት ብሂል የቻልነውን በመለገስ ካሉበት ችግር እንድንታደጋቸው ይሁን፡፡
ለዚህ አካውንት የሚሰጡት ማናቸውም መጠን ያለው የገንዘብ ድጋፍ የ40 ህጻናት እና ታደጊዎችን ነገ የሚያፈካ ነውና ከልብ እናመሰግናለን፡፡ ስለ ደግነታችሁ እና መልካምነታችሁ ክብር አለን-በድጋሚ እናመሰግናለን፡፡
ይህ አካውንት በአንድ ሰው ይከፈት እንጂ ያስተባበርነው ግን ፕሮግራሙን ሰምተን አላስችል ያለን ሰባት ሰዎች በጋራ ሆነን ነው።