የፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር የመረጧቸው አጀንዳዎች ይፋ ሆኑ

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር የመረጧቸው አጀንዳዎች ይፋ ሆኑ

/ETHIOPIA Nege News/:- ምንም ለውጥ አያመጣም የተባለለትና ህወሃት ኢህአዴግ ከወራት በፊት አንዴ ውይይት በሌላ ጊዜ ደግሞ ድርድር በማለት በራሱ ልክ ጠፍጥፎ የፈጠራቸው ፓርቲዎችን ጨምሮ ከሰላማዊ ተቃዋሚዎች ጋር ድርድር እንቀመጥ ብሎ ጥሪ ሲያስተላልፍ ወራቶች ቢይልፉም አንኳር አንኳር የሆኑ ነጥቦችን ተዘለው ለድርድር የተስማሙበት ሰነድ ይፋ ሆኗል፡፡

በድርድሩ አገዛዙ ከገባበት አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣት ሲል ቢያንስ በግፍ የታሰሩትን “የህሊና እስረኞች”ን ይፈታል የሚል ግምት ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በሚያሳዝን ሁኔታ ለአጀንዳነት እንኳን ሳይበቃ መቅረቱ ስርዓቱ ምን ያህል በደመነፍስ ውስጥ እንዳለ የበለጠ ያሳያል ተብሏል።

ፓርቲዎቹ የቀረቱን የድርድር አጀንዳዎች ለመምረጥ ዛሬ ስብሰባ የነበራቸው ሲሆን አጠቃላይ የድርድር አጀንዳዎች ይፋ ሆነዋል።

ፓርቲዎቹ ዛሬ ባካሄዱት 13ኛ ዙር ውይይት በይደር ባቆዩዋቸው ረቂቅ የድርድር አጀንዳዎች ላይ ሀሳብ ከተለዋወጡ በኋላ ለድርድር የሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ ተስማምተዋል።

በዚህም መሰረት የምርጫ ህጎች እና ተያያዝ ጉዳዮች በድርድር አጀንዳነት ከጸደቁት መካከል አንዱ ነው።

በዚህ አጀንዳ ስርም፦

• የፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብ

• የ1999 ዓ.ም የምርጫ ህግ

• የ2002 ዓ.ም የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ይበኙበታል።

አዋጆች እና ተያያዝ ህጎች የሚለው አብይ የድርድር አጀንዳም በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድርድር ሊካሄድበት ፀድቋል።

በዚህ አብይ አጀንዳ ስርም፦

• የፀረ ሽብር ህግ

• የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነት ህግ

• የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ማደራጃ አዋጅ

• የታክስ አዋጅ

• የመሬት ሊዝ አዋጅ እና የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ ሁኔታ በንኡስ የድርድር አጀንዳነት ፀድቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፦

• የዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ ተቋማት አደረጃጃት

• ዜጎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ የመስራት መብት

• የክልል መንግስታት ህጎች

• ወቅታዊ እና ኢኮኖሚ ወለድ የህዝብ ጥያቄዎች

• በሄራዊ መግባባት

• የፍትህ ተቋማት አደረጃጀት እና አፈጻጸም አዋጆችም በፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር የፀደቁ አጀንዳዎች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባቀረቡት ሀሳብ መነሻነት ኢህአዴግ በፀረ ሽብር ህግ እና በመገናኛ ብዙሃንና መረጃ ነጻነት አዋጅ እንዲሁም በፓርቲዎች

ምዝገባ አፈጻጸም ላይ ከህግ ውጭ በቁጥጥር ስር የዋሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር እና አባላት ካሉ በአዋጆቹ ላይ በሚደረግ ድርድር ሊቀርብ ይችላል ብለዋል።

ውድቅ የተደረጉ የድርድር ረቂቅ አጀንዳዎች

1.የህገ መንግስት ማሻሻያ

ኢህአዴግ በህገ መንግስቱ ማሻሻያ እንዲረግባቸው በተጠየቁ ሶስት አንቀጾች ማተልም አንቀጽ 39፣ አንቀጽ 46 እና አንቀጽ 72 አልደራደርም ሲል አቋሙን አሳውቋል።

2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ ለድርድር የቀረበው ረቂቅ አጀንዳም ኢህአዴግ ሀገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆና ስለአዋጁ መደራደር በማለቱ ውድቅ ተደርጓል።

3 የመሬት ስሪት ፖሊሲ

የመሬት ስሪት ፖሊሲን በተመለከተ ለድርድር የቀረበው ረቂቅ አጀንዳ “የመሬት ስሪት የኢህአዴግ ልዩ ፖሊሲ በመሆኑ መሬት የህዝብ እና የመንግስት ነው የሚለው አቋም ለድርድር አይቀርብም በማለቱ” ውድቅ ተደርጓል።

4. የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የድንበር ወሰን

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የድንበር ወሰን በፓርቲዎች ድርድር ሳይሆን በሀገራት መንግስታት መካከል የሚከናወን በመሆኑ ለድርድር የቀረበው ረቂቅ አጀንዳ ውድቅ ተደርጓል።

5. የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች

“የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች አሉ” ተብሎ በፓርቲዎች የቀረበው ረቂቅ የድርድር አጀንዳ ላይ “የህግ እንጂ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኛ የለም” የሚል ሀሳብ ከኢህአዴግ በመቅረቡ አጀንዳው ለድርድር አልበቃም።

ከዚህ በተጨማሪም ኢህአዴግ “አልደራደርበትም ያለው ረቂቅ አጀንዳ፤ ህጋዊ እና ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ በውጭ ሀገር ሆነው እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፖለቲካ ሀይሎ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሳተፉ” የሚለውን ነው።

ይህንን አጀንዳ ያቀረቡት አምስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አጀንዳው ለድርድር አለመቅረብ ላይ ተስማምተዋል።

በመጨረሻም ፓርቲዎቹ ለድርድር የመረጧቸው አጀንዳዎች ቅደም ተከተል፣ የድርድር ጊዜ ሰሌዳ እና የድርድር መጀመሪያ እና መጨረሻ ጊዜ በአደራዳሪ ኮሚቴው ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ በመስማማት የዛሬው ውይይታቸውን አጠናቀዋል።

LEAVE A REPLY