የጌትሽ ማሞን ‘ተቀበል’ የተሰኘ የዘፈን ክሊፕ ልቤ እስኪጠፋ የወደድኩት ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው’ንኳ ሳላውቅ ነበር። ‘እንከባበር’ (ተቀበል ቁጥር ፪) የተባለውን የዘፈን ክሊፕ ስመለከት ግን የመጀመሪያውም ትርጉም ተገለጠልኝ።
እንዴት አንድ ዘፈን እንዲህ ሰሙም፣ ወርቁም፣ ዜማውም አዙዋሚውም፣ ክሊፑም፣ ሁሉም ይጣፍጣል?
ጌትሽ ማሞ ክሊፑን ያሠራው አዝማሪ ቤት ውስጥ ነው (ለዚህ የክሊፑ አዘጋጆችም ምስጋና ይገባቸዋል)። እንዲያውም ‘እንከባበር’ የሚለው ክሊፑ የሚጀምረው በትውፊታዊው የአማራ ልማድ መሠረት ባልና ሚስቱ ሽማግሌዎች ፊት ለእርቅ ሲቀርቡ ነው። ዜማው እና አንዳንድ ግጥሞቹ የሕዝብ ቢሆኑም በጥሩ ሁኔታ ተቀነባብሮ ለጆሮ እንዲጥም ተደግሶ ቀርቧል።
‘ወርቁን ሰሙ ውስጥ የመቅበር’ ባሕል
“አዝማሪ ምን አለ?” የሚለው ቃል የቀድሞ ነገሥታቶቻችን የሕዝቡን ብሶት የሚያደምጡበት እንደነበር ብዙ ግዜ ሰምተናል። አንድ የሕዝብ ትግል በሰለ የሚባለው አርቲስቶች ሲያቀነቅኑለት እንደነበር ከዚህ በፊት፣ ያለፈው ዓመትን ሕዝባዊ አመፅ ተከትለው የወጡ ዘፈኖችን አጣቅሼ ጽፌ ነበር። አሁን ደግሞ የጌትሽ ዘፈኖችን ሳደምጥ ያስታወስኩትን ታሪክ ለመንደርደሪያነት ላስታውስ።
በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ግዜ፣ ጣልያን ሕዝቡን ያሳምፁብኛል በሚል ፍራቻ አዝማሪዎች ስለአገር እንዳይዘፍኑ አግዶ ነበር። ይህንን ማዕቀብ ለማለፍ አዝማሪዎቻችን ለፍቅረኞቻቸው እያስመሰሉ ለአገራቸው ይዘፍኑ ነበር።
“አመፅ የሚቀሰቅሱ” በሚል ሰበብ ዘፈን በስልክ ቀፎ ይዞ መገኘት በአዋጅ በተከለከለበት በዚህ “የፋሺስት መሳይ” ግዜ፣ ጌትሽ ማሞ የመንግሥትና ሕዝብን ግንኙነትን በትዳር መስሎት፣ ብሶታችንን በአዝማሪ ስልት አቀንቅኖታል። “አዝማሪ ምናለ?” ማለት የኛ ድርሻ አይደለም።
የመንግሥትና ሕዝብ ትዳር
(በጌትሽ ዜማ ውስጥ)
ሁሉን ነገር ግልጽ የሚያደርጉልን፣ ‘እንከባበር’ በሚለው ዜማው የሚገኙት እነዚህ ስንኞች ናቸው፣
«እቴ ያንቺ ነገር፥ ሳስበው ይገርመኛል፣
የሰው ሚስት አግብቼ፣ የምኖር ይመስለኛል።»
እንግዲህ ይህ አባባሉ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለሕዝቡ ባዳ መሆናቸውን ለመንገር ያሰበ እንደሆነ መገመት ቀላል ነው። እዚያው ዘፈን ላይ ባለሥልጣናቱ ሀብት እዚህ እያፈሩ ወደውጭ የሚያሸሹ መሆናቸውን ሲናገር እንዲህ እያለ ነው፦ «አንቺ ግፍ አትፈሪም፥ እኔ ቤት ሆነሽ፣ ዳንቴል ትሠሪያለሽ፥ ለዚያኛው ቤትሽ።»
የገዢዎቻችንን ከነሱ አገዛዝ ውጪ አገሪቷ “ትተራመሳለች” እያሉ ማስፈራራት የሚያጣጥለው የሚከተለውን በመቀኘት ነው፦
«የቤቱ ምሰሦ ጣሪያው፣ ግድግዳው፣
በአንቺ ብቻ አይደለም፥ ፀንቶ ያየሽው፣
የልብሽን ዙፋን፣ መንበር ባልታደል፣
እኔ አላንስም ለቤቱ – እንከባበር።» ይህን ሲል ክሊፑ ላይ ያለችው ሚስቱ ሽምግልና ረግጣ ትሔዳለች። ገዢዎቻችን በፖለቲካ ፀብ ውስጥ ሽምግልና ሲላክባቸው በ:ዳይ ሆነው ሳለ “ይቅርታ ጠይቁኝ” ባይ መሆናቸው ታዋቂ ገድላቸው ነው። ጌትሽ ከተቀባዮቹ ጋር «አይይይ እንግዲህ፣ እንከባበር» እያለ ትከሻ በሚንጠው ዜማ ማስገምገሙን ይቀጥላል።
የአምናው አገር አንቀጥቅጥ አመፅ “ገዢዎቻችንን አሰናበተ” ሲባል ተቀልብሶ መልሰው የተደላደሉ በመምሰላቸው ያለውን ፀፀት ሲገልጽልን ይመስለኛል፣ እንዲህ ይላል፦
«መሔድሽ ነው ብዬ፥ ጫፍ ደርሰሽ ተመለስሽ፣
ተለያየን ብዬ ጫፍ ደርሰሽ ተመለስሽ፣
‘ሚገርመው አታፍሪም ትነካኪኛለሽ።»
‘ተቀበል’ ላይ፣ የዛሬ ገዢዎቻችን በትግል ወቅት ነበራቸው የሚባለው “ደግነት” ሥልጣን ሲይዙ መጥፋቱን ለመጠቆም በሚመስል መልኩ ደግሞ እንዲህ እያለ ይጠይቃል፦
«ከማድጋ ውኃ ቀድተሽ በጣሳው፥
መስጠት ታውቂ ነበር፥ ለተጠማ ሰው፣
ምነው ታዲያ ዛሬ፥ ሲደርስ የልብሽ፣
ሁሉን ለኔ-ለኔ፣ ለኔ ማለትሽ?»
እዚያው ላይ፣
«አንቺ እጅሽ ሰፊ ነው፥ የለ ‘ሚጎልሽ፣
ለኔ ሕልም እንጀራ ወግ እየጋገርሽ።» በማለት “የልማታዊ መንግሥታችን” ማባበያ ላይ ‘ተነቃቅተናል’ የሚል መልዕክት ያስተላልፋል።
የፌዴራሉ ሹማምንትን በክልል መንግሥታት ራስን የማስተዳደር ጉዳይ ጣልቃ መግባትን እያሸሞረ በሚመስል መልኩ ደግሞ እንዲህ ይላል፦
«አንቺም አባወራ፣ እኔም አባወራ
ግራ ገባው ቤቱ በ‘ማ እንደሚጠራ»
‘እንከባበር’ ላይ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ቤተዘመዳዊነት (nepotism) ሲያወግዝ እንዲህ እያለ ነው፦
«አንቺን ተመርኩዘው፥ ጊዜን ቢታደሉ
አለቃ ሆኑብኝ፥ ዘመዶችሽ ሁሉ።»