የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ለማስከበር” እያሉ በነፃ አሳልፎ መስጠት አለ እንዴ? /ስዩም ተሾመ/

የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ለማስከበር” እያሉ በነፃ አሳልፎ መስጠት አለ እንዴ? /ስዩም ተሾመ/

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ አራት ግዜ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል “እምብርት ላይ የምትገኝ በመሆኗ” ይላል። የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 (5) ግን አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል “መሃል” የሚገኝ መሆኑን የሚጠቅሰው “ሁለቱን በሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች” ሊኖሩ እንደሚችሉና በዚህም የክልሉ ልዩ ጥቅም ሊጠበቅለት ስለሚገባ ነው። የሕገ-መንግስቱ ድንጋጌ ታሳቢ ያደረገው አዲስ አበባ የክልሉ “እምብርት” በመሆኗ ላይ አይደለም።

በ54ሺህ ሄክታር መሬት ላይ፤ ከ3 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች፣ የክልልና የፌደራል መንግስት ተቋማት፣ እንዲሁም የአህጉራዊና ዓለም-አቀፋዊ ድርጅቶችና ሰራተኞች በውስጧ ይዛ አስፈላጊውን አገልግሎት እና የተፈጥሮ ሃብት (Natural Resource) አቅርቦት ሊኖራት እንደማይችል ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህቺ ከተማ በኦሮሚያ ክልል ሸዋ፥ ባሌ ወይም ወለጋ፣ በአማራ ክልል ጎጃም፥ ጎንደር ወይም ሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወላይታ፥ ሲዳማ ወይም ሃድያ፥… ወዘተ፣ በየትኛውም የሀገራችን አከባቢ ብትገኝ በዙሪያዌ ካለው ክልል ጋር በአገልግሎት አቅርቦትና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ረገድ የጥቅም ትስስር ይኖራታል።

አንቀፅ 49(5) በዋናነት ታሳቢ ያደረገው ነገር የፌደራሉ ዋና ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሃል የምትገኝ ስለሆነ በመካከላቸው የጥቅም ትስስር ሊኖር እንደሚችል ነው። በተለይ በ54ሺህ ሄክታር ይዞታ ያላት አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ የሚያስፈልጋትን አገልግሎት እና የተፈጥሮ ሃብት በራሷ አሟልታ ማቅረብ አትችልም። ስለዚህ፣ የአዲስ አበባ ከተማ በራሷ በቂ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ስለሌላት እና በኦሮሚያ መሃል የምትገኝ እንደመሆኗ መጠን እነዚህን አገልግሎቶች እና የተፈጥሮ ሃብቶች ከክልሉ ታገኛለች። በመሆኑም፣ በሁለቱ መካከል በአገልግሎት አቅርቦት እና በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ረገድ የጥቅም ትስስር ይኖራል። ይህን ታሳቢ በማድረግ “የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና በመሳሰሉት ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል” በማለት ይደነግጋል።

በመሰረቱ፣ ከአገለግሎት አቅርቦትና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል ያለው ግንኙነት በዋናነት በስነ-ምጣኔ (Economics) መርህ ላይ የተመሰረተ ነው። ከተማዋ እያደገ የሚሄድ የአገልግሎትና የተፈጥሮ ሃብት ፍላጎት (demand) አላት፣ የኦሮሚያ ክልል ደግሞ አቅርቦት (Supply) አለው። ከተቆረቆረችበት ግዜ አንስቶ ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል አዲስ አበባ የሚያስፈልጋትን ለመጠጥ ውሃ፣ ለመኖሪያ ቤት፥ ለአገልግሎት መስጫ ተቋማት እና ለመሰረተ-ልማት ግንባታዎች የሚያስፈልጋትን የተፈጥሮ ሃብቶች ያለ በቂ ክፍያና ካሣ ስታገኝ ኖራለች። የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ይህን የተዛባ ግንኙነት መቀየር አለበት በሚል እሳቤ የተደነገገ ነው። ስለዚህ፣ ከተማዋ የተጠቀሱትን አገልግሎቶችና ጥሬ ሃብቶች ያለ በቂ ክፍያ ወይም በነፃ እያገኘች መቀጠል የለባትም።

ከላይ በተጠቀሰው የስነ-ምጣኔ ትስስር ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ የአገልግሎትና የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ (service and natural resource consumer) ስትሆን የኦሮሚያ ክልል ደግሞ አቅራቢ (supplier) ነው። ስለዚህ፣ የኦሮሚያ ክልል ከአገልግሎት አቅርቦትና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሊከበርለት የሚገባው ልዩ ጥቅም “ለከተማዋ ለሚያቀርበው አገልግሎትና የተፈጥሮ ሃብት ተገቢ ዋጋ (reasonable price) ሊከፈለው ይገባል” የሚለው ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ስለሚኖረው ኢኮኖሚያዊ አገለግሎት ልዩ ጥቅምን በተመለከተ የመሬት አቅርቦት፣ የውሃ አገልግሎት አቅርቦት፣ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች የማስወገድ አገለግሎት፣ እንዲሁም የገበያ ማእከላት አቅርቦትና አርሶ አደሩ ለልማት ተነሺ ሲሆን በቂ ካሣ የማግኘትና በዘላቂነት የማቋቋም አገልግሎት፣…ወዘተ” በማለት ይዘረዝራል።

በእርግጥ እያንዳንዱ የአዲስ አበባ ነዋሪ ለንፁህ ውሃ አገልግሎት በፍጆታው ልክ ይከፍላል። ይህ ውሃ ከአዲስ አበባ ከርሰ-ምድር የወጣ ወይም ከሰማይ የዘነበ ሳይሆን ከኦሮሚያ ክልል የተገኘ የተፈጥሮ ሀብት ነው። ከላይ በተገለፀው የስነ-ምጣኔ መርህ መሰረት፣ አዲስ አበባ ከተማ ከኦሮሚያ ከርሰ-ምድር ለምታገኘው ለእያንዳንዷ ሊትር ውሃ ተገቢውን ክፍያ መክፈል አለባት። የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሻ አገልግሎት ድርጅት ንፁህ የመጠጥ ውሃን ከኦሮሚያ ከርሰ-ምድር በነፃ እየቀዳ ለአዲስ አበባ ነዋሪ እየሸጠ ገቢውን ለብቻው ይሰበስባል። ለምሳሌ የዛሬ አራት አመት የመስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት አቅርቦቱን ለማሻሻል በየአመቱ ከ2ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ይመድባል።

የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ለማስከበር በሚል በወጣው አዋጅ መሰረት የክልሉ ጥቅም “የውሃ ጉድጓዱ በሚቆፈርበት እና የውሃ መስመሩ አቋርጠው በሚያልፍባቸው ከተሞችኛ አና ቀበሌዎች የመጠጥ ዉሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ” ብቻ እንደሆነ ተጠቅሷል። ለሁለትና ሶስት ቀበሌ ነዋሪዎች የውሃ ቧንቧ በመዘርጋት ብዙ ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በነፃ እየቀዳህ ለሦስት ሚሊዮን ተጠቃሚ መሸጥና በቢሊዮን የሚቆጠር ብር መሰብሰብ የሚቻለው በየትኛው ዓለም ነው? ድንቄም ልዩ ጥቅም ማስከበር!

ሌላው የኦሮሚያ ክልል በከተማው ስለሚኖረው የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና የአካባቢ ጥበቃ ልዩ ጥቅም፤ “ከከተማው መሠረተ-ልማት አቅርቦት፣ ከመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ከደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር የተያያዘ በተፈጥሮ ሃብት ላይና በአየርና ውሃ ላይ የሚደርስ ብክለት እንዳይኖር የሚያደርግና ይህንን መብት የማስጠበቅ” እንደሆነ ይጠቅሳል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የክልሉ ልዩ ጥቅም እንደሆነ ከተጠቀሱት ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

“ለአዲስ አበባ ከተማ ልማት የግንባታ ማእድናት ማግኛ ሥፈራዎች የአየር ብክለት እንዳያስከትሉ እና ለደን ልማት ወይም ለሌሎች ልማቶች መዋል እንዲችሉ እንዲያገግሙ አንደሚደረጉ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማከሚያና ማስወገጃ ቦታዎች እንዲሁም መልሶ መጠቀሚያ ስፈራዎች አስተዳደሩና ክልሉ በጋራ ባጠኗቸው ቦታዎችና ሳይንሳዊ መስፈርቶችን ባሟሉ ሁኔታዎች እንዲተዳደሩ አንደሚደረጉ፣…”

ለአዲስ አበባ ልማት የግንባታ ማዕድናት ማግኛ ስፍራዎች ከሚወጣ የአየር ብክለት ሆነ የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ከሚደርሱ የአካባቢ ብክለትና ጉዳት የመጠበቅ መብት በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 92 ላይ “የአከባቢ ደህንነት ጥበቃ አላማዎች” በሚል በግልፅ ተቀምጧል።የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) የሚደነግገው የኦሮሚያ ክልል “ልዩ ጥቅም” እንዲጠበቅለት ነው። የኦሮሚያ ክልል ለአዲስ አበባ ከተማ ልማት የሚያስፈልጉ የግንባታ ማዕድናት እያቀረበ ትርፉ የአየር ብክለትና የደን ውድመት የሚሆንበት ምክንያት ምንድነው? ብክለትና ጉዳቱን መከላከል በሕገ-መንግስቱ መሰረት የተጣለ ግዴታ ነው። “ልዩ ጥቅም” ማለት ደግሞ “የክልሉ መንግስት ከእነዚህ ማዕድናት አቅርቦት ተገቢ የሆነ ዋጋ ሊከፈለው ይገባል” የሚል ነው።

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ እንደ አዲስ የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታዎች “አስተዳደሩና ክልሉ በጋራ ባጠኗቸው ቦታዎችና ሳይንሳዊ መስፈርቶችን ባሟሉ ሁኔታዎች እንዲተዳደሩ ይደረጋል” መባሉ በጣም ያስቃል። ምክንያቱም፣ የሰንዳፋ ዘመናዊ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃም ቢሆን በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ምሁራን እና በሌሎች ተቋማት ተጠንቶና የቦታ መረጣ ተደርጎለት….ለወደፊት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ እኮ ነበር። የአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ በማስወገድ በየአመቱ ከ3 ሚሊዮን ብር በለይ የአገልግሎት ክፍያ ይሰበስባል። ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ወስዶ ከጣለው ደረቅ ቆሻሻ ደግሞ የኤሌክትሪካ ኃይል በማመንጨት ተጠቃሚ ይሆናል። በእርግጥ፣ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ለመወሰን በወጣው አዋጅ መሰረት፣  “ቆሻሻ ለአዲስ አበባ ሃብት፣ ለኦሮሚያ ግማት ሆኖ ይቀጥላል። ይህ ረቂቅ አዋጅ በአዲስ አበባ ዙሪያ ላለው የኦሮሞ ሕዝብ ምን የተለየ ነገር ይዞ መጣ?

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ አመፅና ተቃውሞ የተነሳበት ምክንያት ምንድነው? “በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሞ አርሶ-አዶሮች በኢንቨስትመንት እና በመሰረተ-ልማት ግንባታ ሰበብ ያለ በቂ ካሣ እና የመልሶ-ማቋቋሚያ ድጋፍ ተፈናቀሉ። በዚህ ምክንያት በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ-አዶሮች ከነቤተሰቦቻቸው በድህነት አረንቋ ውስጥ እየተዘፈቁ ነው። እንደ ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ ከመሬታቸው ያለ መፈናቀል መብታቸው ይከበር…” የሚል ነበር። በአመፅና ተቃውሞ ግንባር ቀድም ከነበሩት አከባቢዎች ውስጥ የተውሰኑት ለመጥቀስ ያህል አምቦ፥ ወሊሶ፥ አለምገና፥ ቡራዩ፥ …. ተቃውሞው የነበረው በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነበር። በረቂቅ አዋጁ ቅድሚያ የተሰጣቸው ግን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሞ አርሶ አዶሮች ሳይሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ “ውስጥ” ለሚገኙ አርሶ አደሮች ነው፡-

“በከተማው ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት የኖረው የኦሮሞ አርሶ አደር ቁጥሩ ቀላለ ባልሆነ ሁኔታ በልማት ምክንያት ተነሺ ነበር፡፡ አሁንም ለልማቱ ተፈላጊ እስከሆነ ድረስ በማሳመን ይህንኑ መፈፀም የሚገባን ይሆናል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ይህ ተነሺ አርሶ-አደር ቢያንስ ቢያንስ ከቀድሞ ኑሮ የተሻለ ሁኔታ ሊፈጠርለት ይገባል፡፡ በልማቱ ማስፋፋት ምክንያት ተጎጂ ሊሆን በጭራሽ አይገባም፡፡ በዚህ መሠረት ለወደፊቱ በቂ ካሣና በዘላቂነት የሚቋቋምበት ሁኔታ እንዲመቻችለት፣ ከዚህ በፊት የተሠራውም ሥራ ተፈትሾ ጉድለቶች እንዲስተካከሉ፣ እነዚህን ሥራዎች የሚያስተባብር የሚመራና የሚያስፈጽም ጽ/ቤት እንዲደራጅ በአዋጁ እንዲካተት ተደርጓል፡፡”

በመሰረተ-ልማት ግንባታና በኢንቨስትመንት ምክንያት በብዛት ከመሬቱ እየተፈናቀ ያለው በአለምገና፣ ቡራዩ፣ ገላን፥ ሰንዳፋ፥ …ወዘተ ያለ አርሶ-አደር ወይስ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለ አርሶ-አደር? ብሶትና ምሬት ፈንቅሎት ለሞት፥ ለእስርና አካል ጉዳት የተዳረገው የቱ ነው? ላለፉት ሶስት አመታት ለታየው አመፅ አለመረጋጋት ዋና ምክንያት የነበረው በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች መፈናቀልን አስመልክቶ በረቂቅ አዋጁ የቀረበው የመፍትሄ ሃሳብ “የከተማ አስተዳደሩ ምርቶቻቸውን የሚሸጡባቸውን የገበያ ቦታ በማዘጋጀት በራሱ ወጭ የግብይት ማዕከላትን እንዲያቋቁምላቸው የሚል ነው።

በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኘው አርሶ አደር በልማት ስም ከእርሻ መሬቱ ያለ በቂ ክፍያ እየተፈናቀለ ባለበት ወቅት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት “ለክልሉ ለተለያዩ መንግሥታዊ ሥራዎች እና ሕዝባዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንጻዎች የሚሠሩበትን መሬት ከሊዝ ነጻ” ይፈቀድልኝ ብሎ ይጠይቃል። በሺህዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች በከፈሉት መስዕዋት በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኖሩ የክልሉ መንግሥት ሠራተኛ የኮንደሚኒዬም ቤት ሲጠይቁበት ማየት ያሳፍራል። ኧረ ለመሆኑ፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ አይደለችም እንዴ? ዋና ከተማ ከሆነች ደግሞ የከተማ መስተዳደሩ የፌደራል መንግስትን በሚያስተናግድበት አግባብ የኦሮሚያ መንግስት የማስተናገድ አለበት። የኦሮሚያ ክልል በራሱ ዋና ከተማ ውስጥ ከሊዝ ነፃ መሬት ይሰጠኝ ብሎ የሚጠይቅበት ምክንያት ምንድነው? በአዲስ አበባ ላይ የፌደራሉ መንግስት ከኦሮሚያ መንግስት ምን የተለየ መብት ሊኖረው ይችላል?

LEAVE A REPLY