በተቋረጠው የሱሉልታና መቀሌ ከተማ የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ውሳኔ ተሰጠ

በተቋረጠው የሱሉልታና መቀሌ ከተማ የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ውሳኔ ተሰጠ

/Ethiopia Nege News/:- በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 28ኛ ሳምንት ጨዋታ ረቡዕ ሰኔ 21 ቀን 2009 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በሱሉልታ ከተማና መቀሌ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ ከእረፍት መልስ መቋረጡ ይታወቃል።

57ኛው ደቂቃ ላይ መቀለ የግብ ክልል ውስጥ የሱሉልታው አጥቂ ቶሎሳ ንጉሴ ጥፋት ተሰርቶብኛል በማለት ቢወድቅም የዕለቱ ዳኛ “ሆን” ብለህ ነው የወደቅከው በማለት ቢጫ ካርድ ሰጥተውት ጨዋታው ቀጥሎ መቀሌ ከተማ አንድ ጎል አስቆጠረ።

በዳኛው ውሳኔ ደስተኛ ያልነበሩት ሱሉልታዎች ዳኛውን በመክበብ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ባለበት ሰአት አምበሉ ቶሎሳ ንጉሴን ጨዋታውን እንዳልመራ አውከኸኛል በማለት በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጣ። ለጥቂት ደቂቃዎች ከተቋረጠ በኋላ የቀጠለው ጨዋታ 69ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ክስተት ተፈጠረ፡፡ የመቀሌው ተጨዋች የግብ ክልል ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደ ጎል ቢሞክረውም ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታኮ ይወጣል፡፡ ሆኖም የእለቱ ዳኛ ኳሱን ሲመታው ጥፋት ተሰርቶበታል በሚል የፍፁም ቅጣት ምት ሰጡ፡፡ በዳኛው ውሳኔ ሱሉልታዎች እጅግ ተበሳጩ። ጨዋታውም 69ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ ተቋረጠ።

በሶስት ቀን ውስጥ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሱሉልታ ከተማን ጨዋታውን አቋርጠው በመውጣታቸው በማለት የ50ሺህ ብር ቅጣትና ለተጋጣሚው መቀሌ ከተማ ፎርፌ (3 ነጥብ እና 3 ጎል) እንዲሰጥ ሲወሰን በእለቱ ጨዋታውን በመሩት ዳኛ ላይ ደግሞ የአንድ ዓመት እገዳ መጣሉ ታውቋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ግንቦት ወር በባህር ዳርና መቀሌ ከተማ መካከል በመካሄድ ላይ በነበረ ጨዋታ የመቀሌ ከተማ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ቢገቡም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በመቀሌ ከተማ ላይ የሰጠው ውሳኔ የገንዘብ ቅጣትና ደጋፊዎቻቸውን አስልጥነው ለፌዴሬሽኑ ሪፖርት እንዲያደርጉ ነበር።

የመቀሌ ከተማ በውድድር ዓመቱ 17 የፍጹም ቅጣት ምት መሰጠቱ ብዙዎችን አስገርሟል።ከትግራይ ክልል ተወካይ ባለመኖሩ ምክንያት የህወሓት ባለስልጣናት መቀሌ ከተማ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ወደ ፕሪሜር ሊጉ እንዲያድግ በፌዴሬሽኑ በኩል ቀጭን ትዕዛዝ መተላለፉን ለስፖርቱ ቅርብ የሆኑ አካላት መረጃ አለን ማለታቸው ታወቋል።

LEAVE A REPLY