በባህር ዳር የሚገኙ ሆቴሎች የመፀዳጃ ቤት ቆሻሻ ጣና ሐይቅንና አባይ ወንዝን እየበከሉ...

በባህር ዳር የሚገኙ ሆቴሎች የመፀዳጃ ቤት ቆሻሻ ጣና ሐይቅንና አባይ ወንዝን እየበከሉ ነው

/Ethiopia Nege News/:- በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ሆቴሎች የመፀዳጃ ቤት ቆሻሻን ከፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ ጋር በማገናኘት ጣና ሐይቅንና አባይ ወንዝን እየበከሉ መሆኑን የክልሉ ዋና ኦዲተር አረጋግጫለሁ አለ።

በሪፖርቱም በባህር ዳር ከተማ የመፀዳጃ አገልግሎቶች አለመሟላትና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር መኖሩ ተረጋግጧል።
ፓፒረስ፣ ሆምላንድ፣ ባህር ዳር እና አቫንቶ ሆቴሎች የቆሻሻ ማፋሰሻቸውን ከጎርፍ ቦይ ጋር በማገናኘት ወደ ጣና እንዲገባ ማድረጋቸውን የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ለክልሉ ም/ቤት ሪፖርት ማድረጉን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ዘገባ ያመለክታል።

የባህር ዳር ከተማ ጤና መምሪያ ባካሄደው ቅኝት

  • ፓፒረስ ሆቴል ሴፍቲ ታንክ ቢኖረውም አስመጠጥን የሚሉትና ያላቸው የደረሰኝ ወረቀት የማይገናኝ መሆኑ፤
  •  ድብ አንበሳ ሆቴል የቆሻሻ ውሃ ውጋጁን በቀጥታ ወደ ጣና እንዲፈስ ማድረጉን፤
  •  ግራንድ ሆቴል የቆሻሻ ዉሃ መጠራቀሚያ ቢያሰራም ስራ ላይ አለመዋሉና
  •  ጣና ሆቴል ቆሻሻው በቀጥታ ወደ ጣና እንደሚገባ ማድረጉን በተደረገው ቅኝት ተረጋግጧል ተብሏል።

በባህርዳር ከተማ እንዲሁም በጣና ሁሪያ የሚገኙ ሆቴሎች የመፀዳጃ ቤታቸውን ያስመጠጡበትን ደረሰኝ አንዲያቀርቡል ሲጠየቁ ማቅረብ አለመቻላቸውም ተጠቅሷል።በመሆኑም ሆቴሎች የመጸዳጃ ቤቶችን ፍሳሽ በቀጥታ ወደ ጣናና አባይ ወንዝ በመልቀቅ ጉዳት እያደረሱ እንደሆነ ተነግሯል።

ከ50 ሽህ ሄክታር በላይ ሐይቁ በአረም ቢሸፈንም መንግስት ትኩረት ሊሰጠው አለመቻሉን ተከትሎ በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች፣ወጣቶችና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ሐይቁን ለመታደግ የሚመሰገን ጥረት በማድረግ ላይ ቢሆኑም ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ይህ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ጉዳዩ ለሚመለከተው ሁሉ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ናቸው። በክልሉ የሚገኙ ዩንቨርሲቲዎችም ገንዘብ በመለገስና በአረሙ ላይ ምርምር እያደረጉ እንደሆነም ታውቋል።

“የጣና ሀይቅ የአሳ ሃብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ በመምጣቱ እና ለገበያ የሚመጥን ዓሳ ከሐይቁ ማግኘት ባለመቻሉ ዓሳ ከተከዜ ወንዝ ሰው ሰራሽ ግድብ እየመጣ በባህር ዳር ከተማ ለገበያ እየቀረበ ነው።” የሚለው ዜና ትናንት ከተሰማ በሗላ በመንግስት ላይ የሰላ ትችት እየተሰነዘረ ይገኛል።

LEAVE A REPLY