‹‹ምራቃቸውን ተፍተውብኛል፣ ጺሜን እየነጩ አሰቃይተውኛል›› ፍቅረማርያም አስማማው

‹‹ምራቃቸውን ተፍተውብኛል፣ ጺሜን እየነጩ አሰቃይተውኛል›› ፍቅረማርያም አስማማው

/Ethiopia Human Rights Project/

ስም፡- ፍቅረማርያም አስማማ

ዕድሜ፡- 32

አድራሻ፡- አዲስ አበባ ከተማ

አሁን በእስር የምገኝበት ቦታ፡- ቂሊንጦ እስር ቤት

ለእስር የተዳረግሁበት ምክንያት፡- በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረሃል የሚል ነው፡፡

በይፋ የተመሰረተብኝ የክስ አይነት፡- መጀመሪያ የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁን አንቀጽ 7(1) በመተላለፍ ኤርትራ የሚገኘውን የግንቦት ሰባት ወታደራዊ ክንፍ ልትቀላቀል ነበር የሚል ሲሆን በዚህ ክስ የአራት አመት እስር ቅጣት ተወስኖብኛል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ በነሐሴ 2008 ዓ.ም ቂሊንጦ እስር ቤትን አቃጥላችኋል በሚል የሽብር ክስ ከቀረበባች እስረኞች መካከል አንዱ አድርገው ከሰውኝ በእስር ላይ እገኛለሁ፡፡

በእስር በምገኝበት ወቅት የሚከተሉት የመብት ጥሰቶች ተፈጽመውብኛል፡፡

ሀ. ማዕከላዊ ወንጅል ምርመራ እያለሁ

1. ቀዝቃዛ ክፍል ታስሬያለሁ፡፡

2. ጠያቂ ተከልክየ ቆይቻለሁ፡፡

3. ስድብና ዛቻ ደርሶብኛል፡፡

ለ. በቂሊንጦ ቃጠሎ ምክንያት ሸዋሮቢት ለምርመራ በተወሰድሁባቸው ጊዜያት

1. ሲቪል በለበሱና ማንነታችን ባልገለጹልኝ መርማሪዎች ከፍተኛ ድብደባ በተከታታይ ቀናት ደርሶብኛል፡፡

2. የፊጥኝ በማሰር ገልብጠው ውስጥ እግሬን በአጠና ዱላ ደብድበውኛል፡፡

3. ሁለቱን የእጅ አውራ ጣቶቼን በሲባጎ አስረው አሰቃይተውኛል፡፡

4. እጅና እግሬን አራርቀው በመወጠር ሰቅለው አሰቃይተውኛል፡፡

5. ስድብና ዛቻ፣ እንዲሁም ማንቋሸሽ አድርሰውብኛል፡፡

6. ቀኑን ሙሉ በካቴና አስረው ከማዋላቸው በተጨማሪ ማታ ማታ በካቴና ታስሬ እንዳድር አድርገውኛል፡፡

7. በግዳጅ እነሱ የሚፈልጉትን ብቻ እንድናገር እያደረጉ በቪዲዮ ቀርጸውኛል፡፡

8. ምራቃቸውን ተፍተውብኛል፣ ጺሜን እየነጩ አሰቃይተውኛል፡፡

የተወለድሁት አዲስ አበባ ነው፡፡ የተማርሁትም እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ ከመታሰሬ በፊት በማስታወቂያ ስራ ተሰማርቼ ነበር፡፡ በፖለቲካ ተሳትፎዬ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ነበርሁ፡፡ ከስራ በሚተርፈኝ ጊዜዬ የህሊና እስረኞችን አዘውትሬ እጠይቅ ነበር፡፡ የሚደርስባቸውን በደል በቅርበት ታዝቤያለሁ፡፡ አሁን ላይ ደግሞ በራሴ ላይ እየደረሰ አየሁት፡፡ አሁን ቂሊንጦን አቃጥለሃል ተብዬ የቀረበብኝ ክስ አለ፡፡ ይህ ክስ የቀረበብኝ በቃጠሎው ወቅት ቂሊንጦ ባልነበርሁበት ሁኔታ ነው፤ ቃጠሎው ከመድረሱ ከሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ ወደ ዝዋይ እስር ቤት ተዛውሬ እዚያ በእስር ላይ ነበርሁ፡፡

LEAVE A REPLY