የፌደራል አቃቤ ህግ የአቶ በቀለ ገርባን የዋስትና ጥያቄ ተቃወመ

የፌደራል አቃቤ ህግ የአቶ በቀለ ገርባን የዋስትና ጥያቄ ተቃወመ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ የፌደራል አቃቤ ህግ በእነ ጉርሜሳ አያና የክስ መዝገብ በሽብር ተከሶ በብይን ክሱ ወደ ወንጀለኛ መቅጫ የተቀየረለትን የአቶ በቀለ ገርባን የዋስትና ጥያቄ ተቃውሟል፡፡ የፌደራል አቃቤ ህግ ዛሬ ሀምሌ 19/2009 ዓ.ም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት አቶ በቀለ ላቀረበው ጥያቄ በፅሁፍ በሰጠው መልስ አቶ በቀለ በብይን በወደቀለት የሽብር ክስ ዋስትና ተከልክሎ የነበር መሆኑን በመጥቀስ በዚህኛው ክስም ዋስትና እንዳይሰጠው ጠይቋል፡፡

‹‹ይህ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ማየት ሲጀምር በህግ አግባብ ተከሳሹን የዋስትና መብት ከልክሎ በማረሚያ ቤት ሆኖ ይህ ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ ጉዳዩን እንዲከታተል ትዕዛዝ ሰጥቶአል፡፡ ይህ ጉዳይ የመጨረሻ እልባት የሚያገኘው ደግሞ ውሳኔ ሲሰጥ ነው፡፡›› ያለው አቃቤ ህግ አሁን ተከሳሽ አንቀፅ ተቀይሮ ተከላከል መባሉ ለጉዳዩ እልባት አሰጥቷል የሚያስብል አይደለም ብሎአል፡፡ ‹‹በዚህም ምክያት የዋስትና ጉዳይ ላይ ይህ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሰጠበት ጉዳይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በድጋሜ ይህ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ ትዕዛዝ የሚሰጥበት ህጋዊ ምክንያት የለም›› ሲል መልስ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በወደቀው ክስ የሰጠውን ትዕዛዝ በተቀየረው አዲሱ ክስ የመሻር መብት የለውም የሚል ክርክርም አቅርቦአል፡፡

በተጨማሪም በብይን ውድቅ የተደረገው ክስ ዝርዝር ላይ አቶ በቀለ በውጭ ከሚገኙ የኦነግ አመራሮች ጋር ይገናኝ ነበር በሚል እና ዋስትና ቢፈቀድለት ከሀገር እንደሚወጣ በመጥቀስ የዋስትና መብቱ ተከልክሎ በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ጥያቄ አቅርል፡፡

የአቶ በቀለ ገርባ ጠበቆች አቶ በቀለ ቋሚ አድራሻ ያለውና ቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደሆነ፣ ክሱም ዋስትና እንደማያስከለክል፣ ተከላክሎ ጥፋተኛ ከተባለ እንኳን የተጠቀሰበት ድንጋጌ የሚያስቀጣው ቀላል እስር በመሆኑ ይህንም የታሰረው በመሆኑን በመጥቀስ ዋስትና ተፈቅዶለት በውጭ ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ለፍርድ ቤቱ አስተያየታቸውን ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን አስተያየት መርምሮ ለመበየን በሚልም ለሀምሌ 26/2009 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

LEAVE A REPLY