/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ ከትናንት በስቲያ የተካሄደው የኬንያ ፕሬዚዳንሺያል ምርጫ ዋንኛ እጩ ተፎካካሪ በሆኑት ራይላ ኦዲንጋ ተቀባይነት አላገኘም። ምርጫው በኢንተርኔት በርባሪዎች(ጠላፊዎች) አማከካኝነት ወደ ዋናው የመረጃ ቋት በመግባት ውጤቱን አዛብተውታል። ይህም የተደረገው ምርጫው ሊካሄድ 9 ቀን ሲቀረው በተገደሉት የኮሚሽኑ የአይቲ ሀላፊ ክሪስ ማሳንዶ ስም ነው። ስለሆነም የተጭበረበረ የምርጫ ውጤት አልቀበልም ብለዋል። በዚህም ምክንያት እስካሁን ከ4 በላይ ዜጎች ህይወት ማለፉ ታውቋል።
በርዕሰ ከተመዋ ናይሮቢ ትናንት በአንዳንድ አካባቢዎች የተጀመረው ግጭት ዛሬም ቀጥሏል። የከተመዋ የንግድም ሆነ የማህበራዊ መሰተጋብሮች በእጅጉ ተወስነዋል።
በተለይ በምዕራብ ናይሮቢ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸውና የራይላ ኦዲንጋ ጠንካራ ይዞታ በሚባሉት “ኪቢራ” እና “ካንጓሬ” የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጠንካራ ነው። ጎልተው ከሚሰሙት መፈክሮች መካከል ራይላ ካልተመረጠ ሰላም የለም( No Raila, no peace)የሚለው ዋነኛው ነው። ሚስተር ኦዲንጋ የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን(IEBC) ከየምርጫ ጣቢያዎች የሚደርሱትን የመራጮችን ድምጽ ቀጥታ እንዳያስተላልፍም ጠይቀው ነበር።
የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚሽን በበኩሉ የምርጫው ውጤት በጠላፊዎች እጅ ይገባል ብለን አናምንም፤ነገር ግን ቅሬታዎችን ተቀብለን ማጣራት እናደርጋለን ባለው መሰረት ዛሬ 8 ሰዓት ላይ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫውም “ለመጥለፍ” መከራ ተደርጎ ከሽፏል፤ የምርጫ አመራር ስርዓታችን ደህንነቱ የተጠበቀና ምንም አይነት ውጫዊና ውስጣዊ ጣልቃ ገብነት የለበትም ብሏል።እስከ ሌሊቱ ስድት ሰዓት አጠቃላይ ውጤቱ ለኮሚሽኑ እንደሚደርሰውና ነገ ከሰዓት በሗላ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።
ምርጫውን የአሜሪካው የካርተር ማዕከል፣የአውሮፓ ህብረት፣የአፍሪካ ህብረት፣ኢጋድና የኬንያ የማህበረሰብ ተቋማት ታዝበውታል። ምርጫውም ነፃ፣ ትክክለኛና ፍትሃዊ እንደነበርም አስተያየታቸውን ሰተዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የነበሩት ጆን ኬሪ “ውጤት ማጣት ስሜቱን አውቀዋለሁ፣እኔም የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተሸንፋለሁ፤ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ነበሩኝ።ነገር ግን ወደ ፊት መሄድ ስላለብን ትቸዋለሁ።”በማለት ለተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ የሚመስል መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአውሮፓ ህብረትም ምርጫው ፍትሀዊ ነበር፡፤ ምርጫውን ለማጭበርበር የተደረገ አንድም ሙከራ አላየንም።ነገር ግን የቀረቡ ቅሬታዎች በአግባቡ እንዲጣሩ ጠይቋል። የፖለቲካ መሪዎችም ህዝቡ ተረጋግቶ የምርጫውን ውጤት እንዲጠባበቅ ጥሪ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩት ታቦ ኢምቤኪ የሚመራው የአፍሪካ ህብረት የታዛቢዎች ቡድንም ምርጫው ፍትሀዊ አንደነበረ ጠቅሶ፤ በርካታ የተበላሹ ድምጾች መኖራቸውን እንዳየ አብራርቷል።
የምርጫ ኮሚሽኑ 97 ፐርሰንት ያህሉን ውጤት በቀጥታ ስርጭት ይፋ ያደረገ ሲሆን እስካሁን ሁሩ ኬንያታ 54.2%
እንዲሁም ራይላ ኦዲንጋ 44.8% እየተከተሉ ነው።