“ዱሮም ምንም አልነበረንም፤ አሁን ደግሞ ከምንም ምንም አጣን” ጋዜጠኛ ግርማዬነህ ማሞ

“ዱሮም ምንም አልነበረንም፤ አሁን ደግሞ ከምንም ምንም አጣን” ጋዜጠኛ ግርማዬነህ ማሞ

/አለምሰገድ ገብረኪዳን/

ትናንትና ነው ያየሁት ሆናም ትናንት አንድም ቃል መፃፍ አልቻልኩም፡፡
.ዛሬ ግን……የተሰማኝን መፃፍ አለብኝ፡፡
“አየህ!…ዱሮም ምንም አልነበረንም፡፡ አሁን ደግሞ ከምንም ምንም አጣን” አለኝ ሳግ እየተናነቀው፡፡ ከአንደበቱ የሚወጡት እያንዳንዱ ፊደላት በሳግ ይቆራረጣሉ፡፡ ወደ እግሮቹ የላካቸውን ዐይኖቹን ወደ እኔ ሲመልሳቸው ዐይኖቼን አሻሸሁ፡፡እንባ እንዳይቀድመኝ ከራሴ ጋር እየታገልኩ፣ ዐይኖቼን ቀ…ስ ብዬ ፊት ለፊቴ ወደተቀመጠው አናንያ ሶሪ ላክኋቸው፡፡
.
የአናንያ ዐይኖችም እምባ አቀርዝዘዋል፡፡ ከአናንናየ ጋር ፒያሣ የተገናኘነው ድንገት ነው፡፡ ሻይ ቡና ተባብለን ልንለያይ ስንል አሁን ቤት ነው የምትሄደው? ሲል ጠየቀኝ፡፡
“አይ አንድ የታመመ ጋዜጠኛ ወዳጄን ልጠይቅ ወደ ቀጨኔ ነው የምሄደው” አልኩት፡፡
“ኦ…… ትናንትና ሰለሞን ለማ እግሩ ተቆረጠ ብሎ የፃፈውን አንብቤአለሁ፡፡ ባክህ እኔም ልጠይቀው” አለኝ፡፡ ተያይዘን ወደ ጋዜጠኛ ግርማዬነህ ማሞ መኖሪያ ቤት ሄድን፡፡ ቀጨኔ ማዞሪያ የሚባለው አካባቢ ስንደርስ የግርማዬነህን ቤት እያጠያየቅን ሳለ ከአናንያ ጋር የሚተዋወቅ አንድ ወጣት አገኘን፡፡ ባለ ታክሲ ነው፡፡ ሰፈሩ ቢሆንም ግርማዬነህን አያውቀውም፡፡ ቢሆንም ቤቱን በማፈላለግ ተባበረን፡፡
.
ሶስታችንም አብረን ወደ ግርማዬነህ ቤት ገባን፡፡ ሳሎኑ ጨለምለም ያለመ ነው፡፡ እዚያ ጨለምለም ያለ ድባብ መሃል እጅግ የተጎሳቆለና ፊቱ ከጥቀርሻነት አልፎ ከሰል የመሰለው ግርማዬነህ ሳሎን ውስጥ (ሳሎን ከተባለ) የሚገኝ ረዘም ያለ ሶፋ ላይ ተቀምጧል፡፡ ዐይኔን ማመን አልቻልኩም፡፡ እጅግ በጣም ከስቷል፡፡ ያ ከአመታት በፊት የማውቀው፣ ያ ለ7 ዓመታት ያህል (ከ90 -97) አብሮኝ “ኢትኦጵ” ጋዜጣ እና መፅሔት ዝግጅት ክፍል የሰራው፣ ያ ሮጦ ሮጦ የማይታክተው፣ ያ የሙያ መምህሬ (አርአያዬ) ከምላቸው ሰዎች አንዱ የነበረው፣ ያ ብርቱ፣ ቁርጠኛና ትንታግ የነበረ ሰው … ከሰውነት ተራ ወጥቶ፣ “የሰው ያለህ” እያለ ሳገኘው….. በቃላት የማይገለፅ ህመም ውስጤን አተራመሰው፡፡
.
እናም በሃሳብ የኋሊት ነጎድኩኝ፡፡ ያኔ “ኢትኦጵ” ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በምንሰራ ጊዜ ግርማዬነህ ሮጦ የማይደክም ነበር፡፡ መረጃ አለ በተባለበት ሁሉ የማይታክት ቀልጣፋ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ እጅግ ንቁና ብርቱ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ ቢሮ ውስጥ አንዳች የውይይት ሃሳብ ከተነሳ እስከመጨረሻ ድረስ ሽንጡን ገትሮ የሚከራከር፣ ባመነበት ጉዳይ ወደኋላ የማይል ለማንም ለምንም የማይመለስ ነበር፡፡ በተለይ እሱ እና ሲሳይ_አጌና ክርክር ከጀመሩ ቢሮው ጦር ሜዳ ነበር የሚሆነው፡፡ የእሱና የሲሳይ ክርክር መቋጫ አልነበረውም፤ ከቢሮ ውጪ ሻይ ቡና ልንጠጣ ወጥተንም “ጦርነታቸውን” ይቀጥላሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ … የሆነ መረጃ አለ ከተባለ ተወርውሮ ወደ መረጃው ለመሄድ የሚቀድመው አልነበረም፡፡ …. አብዛኛውን ጊዜ ወደ ቢሮ ሲመጣም ሆነ ወደ ቤቱ ሲመለስ ትራንስፖርት አይጠቀምም ነበር፡፡ በእግር መሄድ ነበር የሚያዘወትረው፡፡ እኛ ታክሲ ለመያዝ ስንጣደፍ “ለምን በእግራችሁ አትሄዱም፤ ለጤንነትም ቢሆን ጥሩ ነው” ይለን ነበር፡፡ ይህ ሰው ነው ዛሬ አንድ እግሩን ታፋው ላይ ተቆርጦ የአልጋ ቁራኛ የሆነው፡፡
.
“እንዲህ አይነት ችግር ላይ መውደቅህን ሰርካለም ፋሲል ከአሜሪካ ፌስቡክ ላይ ያወጣችውን ፅሁፍ አንብቤ ነው፤ እዚሁ እያለሁ አለመስማቴ ይገርማል” አልኩት፡፡
.
“ሁላችንም እኮ እንደዛው ነን፤ አለን እንላለን እንጂ የለንም፡፡ …. ታውቃለህ፤ ህመሙ እግሬን ሲጀምረኝ እንደማስነከስ ነበር ያደረገኝ፡፡ ከሳምንት በኋላ ተወኝ፡፡ እንደገና ከ15 ቀን በኋላ ጀመረኝ፡፡ …. ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጣቶቴን ተከትሎ የእግሬ መዳፍ ቆሰለና ተሰነጣጠቀ፡፡ …. ሃኪም ቤት እንደሄድኩ ጉዴን ሰማሁ፡፡ … ብር ቢኖረኝ ከጉልበቴ በታች ነበር የምቆረጠው፡፡ 30 ሺ ብር ከየት ይምጣ፡፡ … ዱሮም ምንም አልነበረንም፤ አሁን ደግሞ ከምንም ምንም አጣን” አለ የተቆረጠውን እግሩን በእጁ እየዳበሰ፡፡
.
“ካልነበረን ምንም፤ ምንም አጣን …” ቃሉን በውስጤ እየደገምኩት ዐይኔን ወደ አናንያ ወረወርኩ፡፡ ዐይኖቹ እንባ እንዳቀረረ ነው፡፡
.
ከደቂቃዎች በኋላ ልንሰናበተው ስንል “አሁን ምን እንዲደረግልህ ትፈልጋለህ?” አልኩት፡፡ ለወጉ ያህል ጠየቅኩት እንጂ የማደርገው ነገር እንደሌለ ልቤ ያውቃል፡፡
.
“አሁን የምፈልገው …. በእግሬ ቆሜ ከቤቴ ወጣ ብዬ መመለስ ነው፡፡ … የምፈልገው እግሬን ነው፡፡ በእግሬ መቆም …..” አለኝ፡፡
.
አዘንኩ፡፡ ቤቱን ያሰየን ወጣት፤ አናንያ ሶሪ እና እኔ በሃዘኔታ ስሜት ተውጠን ተሰናብተነው ወጣን፡፡ ሶስታችንም ወደ ፒያሳ ስንመለስ መኪና ውስጥ ተቀምጠን ያስታወስነው ያወራነው አባባሉ አንድ ዓይነት መሆኑ ነው የሚገርመው፡፡
.
“.ዱሮም ምንም አልነበረንም፤ አሁን ደግሞ ከምንም ምንም አጣን”
.
እኛ (እኔና አናንያ )ጋዜጠኛ ግርማነህ ማሞን እዚያው አልጋው ላይ ትተነው ወጥተናል፡፡ እናንተ ወዳጆቼ ግን እንደማትተውት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እናም … የነበረው እግር እጅጉን የናፈቀውን ይህን ቀደምት የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኛ ባላችሁ አቅም ትረዱት ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

በስልክ ልትጠይቁት የምትፈልጉ በ 0911 12 25 29 ወይም በባለቤቱ በሽብሬ
ጥሩነህ በ09 20 00 74 16 ልታገኙት ትችላላችሁ፡፡

ግርማዬነህን ለመርዳት፡-
ወይዘሮ ሽብሬ ጥሩነህ ቡና ባንክ አዲሱ ገበያ ቅርንጫፍ
የአካውንት ቁጥር 1749501001155 በሚለው ይጠቀሙ

LEAVE A REPLY