የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እናት ማን ናቸው? /አቻምየለህ ታምሩ/

የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እናት ማን ናቸው? /አቻምየለህ ታምሩ/

የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን እናት በሚመለከት የተለያዩ ሰዎች የተለያዬ ነገር ሲናገሩ ይሰማል። የቁልቢው ልጅ ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ «አጤ ምኒልክ» በሚል ርዕስ አዘጋጅተው በ፲፱፻፹፬ ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ ገጽ 13 ላይ. . .

«ብዙ የታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚሉት ወይዘሮ እጅጋየሁ ውብና ከደህና ቤተሰብ መወለዳቸውን ይገልፃሉ። የአባታቸውን ስም ግን የሚገልጽ የለም። ለማ አድያሞ ይባላሉ። ይህም ሲተነትኑም አንዳንዶቹ ከጉራጌ አገር የተማረኩ ባሪያ ናቸው ይሏቸዋል። ባርያ ማለት በገንዘብ የሚሸጥ ብቻ ሣይሆን በጦርነት የሚማረክ ሁሉ ባርያ ይባላል። ይህ ሁሉ ይቅርና ዋናው ቁም ነገር ታሪክ መሥራት እንጂ ትውልድ አይደለም። ታላቁ ናፖሊዮን እንደዘመኑ አፃፃፍ ወደላይ የሚቆጠር ዘር አልነበረውምና ታሪኩን የሚጽፈው ፀሐፊ ቀርቦ «የትውልድ ታሪክዎን ከየት ልጀምር?» ቢለው «ያለፈውን ትተህ ከኔ ጀምር አለው እንደሚባለው ነው።» ሲሉ ጽፈዋል።

የዐፄ ምኒልክን እናት በሚመለከት ብዙ ሰው ሲጽፍ በአመዛኙ የሚጠቅሰው ወይንም የሚስማማው ከፍ ሲል የቀረበውን የደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞን ትርክት ዋቢ ያደርጋል። ሆኖም ግን ይህ ትርክት ትክክለኛ ታሪክ አይደለም። የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን እናት በሚመለከ ንጉሰ ነገስቱ በሕይወት ሳሉ የተመዘገበው እውነታ ከዚህ ቀጥሎ የሰፈረውን ይመስላል።

የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እናት ትክክለኛ ስም እጅጋየሁ ኃይሉ ነው። ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ እንደጻፈው ወይዘሮ እጅጋየሁ ኃይሉ ባርያ አይደሉም። ወይዘሮ እጅጋየሁ ኃይሉ የጎጃም ተወላጅ የጎዛምን ሰው ናቸው። ይህን ታሪክ የሚነግሩን በ1889 ዓ.ም. «የጎጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ» በሚል የመዘገቡት አለቃ ተክለ እየሱስ ዋቅጅራ ናቸው።

አለቃ ተክለ እየሱ ዋቅጅራ በ1860 ዓ.ም. በዛሬው ወለጋ ክፍለ ሀገር ሆሮ ጉድሩ ቅርብ ከሆነች አልባሳ በሚባል ስፍራ የተወለዱና በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የጎጃም አስተዳደር ዘመን በሰዓሊነትና በጸሓፊነት አገራቸውን ያገለገሉ ስመ ጥር ሊቅ ናቸው። «የጎጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ» በሚል ርዕስ ያሰናዱትን የትውልድ መድብል ለመጀመሪያ ጊዜ በ1889 ዓ.ም. ሲጠናቅቁ 11 ዓመታት የፈጀ መረጃ የማሰባሰብ ስራ ሰርተዋል።

አለቃ ትክለ እየሱስ የጻፉት የጎጃም ትውልድ መድበል ለህትመት የበቃው ረቂቁ ካዘጋጁት ከ114 ዓመታት በኋላ በ2003 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ አሳታሚነት በግርማ ጌታሁን አዘጋጅነት ነበር። አለቃ ተክለ እየሱ ዋቅጅራ ጽፈውት በግርማ ጌታሁ አዘጋጅተው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የታተመው የአለቃ መድበል ገጽ 73 ላይ እንደሚታየው የዳግማዊ ምኒልክ እናት ወይዘሮ እጅጋየሁ ኃይሉ ሲሆኑ የትውልድ ክፍለ ሀገራቸው ጎጃም ሲሆኑ ትውልዳቸው ከጎዛምን ነው።

አለቃ ተክሌ በጻፉት የጎጃም ትውልድ መድበል መሰረት የዳግማዊ ምኒልክ እናት ወይዘሮ እጅጋየሁ ኃይሉ የጎዛምን 3ኛ ትውልድ የሆነው የተከብጀን የልጅ ልጅ ልጅ ሲሆኑ የሚወለዱት ጎጃም ጎዛምን እነራታ፣ የብራጌ፣ ዳሊገውና የደረት አካባቢ ነው። በነገራችን ላይ እነዚህ የገጠር ቀበሌዎች ደብረ ማርቆስ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ የገበሬ ቀበሌ ማህበራት ናቸው።

የዳግማዊ ምኒልክን እናት ውበትና ቁንጅና በሚመለከት የቁልቢው ልጅ ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ «ወይዘሮ እጅጋየሁ ውብ ናቸው» ሲል የገለጸው ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ። ነፍሱን ይማረውና ድምጻዊ ተስፋዬ ወርቅነህ የወደዳት የጎጃም ቆንጆ «ስዕለ ማርያም» እንደምትመስል የዳሊገው ጊዮርጊሷን ቆንጆ «ዉቢቱ ጎጃሜ» በሚለው ዘፈኑ

አልጋ ላይ ስትጥይ ቀበቶ አስፈትተሽ፣

ማሩኝ ታሰኛለሽ ወንድ ልጅ አስተሽ፤ ሲል ይገልጻታል።

የሆነው ሆኖ የወይዘሮ እጅጋየሁ ኃይሉ ሙሉ የቤተሰብ ሀረግ እንደሚከተለው ነው። የጎጃም እነራታ፣ የብራጌ፣ ዳሊገውና የደረት አካባቢ ተወላጅ የሆኑት ተከበጀን ታላቅ ቤትን ወለዱ፤ ታላቅ ቤት ዮሐንስን ወለዱ፤ ዮሐንስ ማሮን ወለዱ፤ ማሮ ኃይሉን ወለዱ፤ ኃይሉ እጅጋየሁን ወለዱ፤ እጅጋየሁ ዳግማዊ ምኒልን ወለዱ።

ልብ በሉ ይህ ታሪክ የተመዘገበው ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በሕይወት እያሉ በ1889 ዓ.ም. ነው። ስለዚህ የዳግማዊ ምኒልክ እናት በተለምዶ እንደሚባለው እጅጋየሁ አድያሞ ሳይሆን እጅጋየሁ ኃይሉ ነው። የትውልድ ሀረጋቸውም ጎጃም ደብረ ማርቆስ ከተማ ዙሪያ ባሉ የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ነው።

LEAVE A REPLY