አቶ አክሊሉ ወንድአፈረው፤ የኢትዮጵያ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) ሥራ ስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፤ በሸንጎው የፖለቲካና የጥናት ኮሚቴ “በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ተኮር የክልሎች አሸናሸንና ዕንድምታው” በሚል ርዕስ በተሰናዳው ጥናታዊ ሰነድ ላይ አቶ ካሣሁን ነገዎ በአውስትራሊያው የአማርኛ ራዲዮኑ ላቀረበለት ጥያቄዎች የሰጣቸውን መልሶች ያልሰማ እንዳለ እንዲሰማቸው ሐሳብ ላቅርብ።
ከውይይቱ እንደተረዳሁት፥ ጥናቱ የሚደገፍና የሚመሰገን ነው። ግን መደምደሚያውን ከሀገሪቱ ታሪክ ጋር አያይዞ በመደምደም ፈንታ ለሌላ ለአወዛጋቢ ጊዜ አስተላልፎታል።
ሁለት ጥያቄዎች አሉኝ። አንደኛው የተማሪዎቹ ንቅናቄ ባመጣብን “ብሔር፥ ብሔረ ሰብ” በሚለው አነጋገር ላይ የሚያተኩር ነው። ካሁን በፊት እንደተቸሁት፥ እነዚህ ቃላት የተፈጠሩት የኛን “ጎሳ፥ ነገድ” በመናቅ ስለ ሆነ ከፖለቲካ መዝገባ ቃላታችን አውጥተን መጣል አለብን። የራስን መናቅ ራስን መናቅ ነው። ራስን የሚንቅ ሕዝብ ሌሎችን አምላኪ ሆኖ ይቀራል።
ሁለተኛውም የምዕራባውያን ባህል ተጽዕኖ ባመጣብኝ ችግር ላይ የሚያተኩት ነው። ይኸውም “አገራችን ላይ የሚዘረጋው አስተዳደር አሐዳዊ ይሁን ወይስ ፌዴራዊ” የሚለው ጥያቄ ነው። አሐዳዊ ከሆነ ጎሳዎችና ነገዶች እንዴት ይስተናገዱ? ፌዴራዊ ከሆነ አገሪቱ እንዴት ትከፋፈል? እያልን እንተቻለን። ይኼ ትችት እኮ፥ ብናውቀውም ባናውቀውም፥ በታሪካችን ላይ የሚደረግ ዘመቻ ነው። ታሪካችን አገሪቱን ከፋፍሎ ለያንዳንዳቸው ክፍለ ሀገር ስም (አስተዳደርም) ሰጥቶታል። የሚከበር፥ የሚጠበቅ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ አስተዋጽዖ ነው። ክፍለ ሀገሮቹን እንዳሉ ጠብቆ አሐዳዊ ወይም ፌዴራዊ የዲሞክራሲ አስተዳደር ለመዘርጋት የማይቻልበት ምክንያት የለም።
ዋናው ነገር፥ ክፍለ ሀገሮቹ ራስ-ገዝና ለማእከላዊው መንግሥት ታዛዥ እንዲሆኑ መስማማት ነው። ሁለተኛው ዋና ነገር፥ ማንም ኢትዮጵያዊ ከማንኛውም ክፍለ ሀገር ለመኖር ምን ጊዜም መብቱ መሆኑን ማመን ነው። ይኸ “የነገድ (የዘረኝነት) መንግሥት መሥርተን የጎሳዎችን መብት እንጠብቃለን” የሚሉት አነጋገር፥ የጎሳዎችን መብት መጣስ ነው። ማንም ኢትዮጵያዊ ለማንም ኢትዮጵያዊ መብት የመስጠትና የመንፈግ መብት የለውም። ማን ከማን አንሶ! ማን ከማን በልጦ! የክፍለ ሀገሩን አስተዳደር የሚቀይሱ በክፍለ ሀገሩ ውስጥ ያሉት ሁሉ እንጂ የነገዶቹ የግል መብት አይደለም። የሚቀይሱትም እንደ ጎሳነታቸው ወይም እንደ ነገድነታቸው ሳይሆን፥ እንደ ገለሰብ የአካባቢው ዜግነታቸው ነው። የጎሳ ወይም የነገድ (ወይም የሃይማኖት) ማንነታቸው የግል ስለ ሆነ፥ ጎሳንና ነገድን (ሃይማኖትን) የሚገድ ጥያቄ ሲነሣ ጎሳዎችና ነገዶች ጉዳያቸውን ከመንግሥት አስተዳደር ውጪ ይነጋገሩበት።