መሳሪያው የጣና ሃይቅን ከጥፋት ይታደጋል ተብሏል
/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ በጣና ሐይቅና በአባይ ወንዝ ላይ የተከሰተው እንቦጭ የተሰኘ አደገኛ አረም ማስወገድ የሚያስችል ማሽን በኢንጂነር ሙላት ባሳዝነው በባህር ዳር ተሰርቶ ለአገልግሎት መብቃቱ ታውቋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ሙያዊ እገዛ አድርጓል። ኢንጂነር ሙላት በሙያው የተለያዩ ማሽነሪዎችን ዲዛይን በማድረግ ለህዝብ ትራንስፓርትና ለዓሳ ማስገሪያ የሚውሉ ጀልባዎችን በመስራት ለገበያ ማቅረቡንም ተነገሯል።
ከጎንደር፣ ከወሎና ከሸዋ ወጣቶች በመደራጀት ጣናን ለመታደግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ። አረሙን በእጅ ነቀላ ለማስወገድ የአካባቢው ማህበረሰብ በየ 15 ቀኑ ዘመቻ ጀምሯል። ጣና የኢትዮጵያ ሀብት በመሆኑ የፌደራል መንግስትም ዝምታውን ሰብሮ በዘመቻው መሳተፍ እንደሚገባው የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ዋና ሀላፊ የሆኑት ዶክተር በላይነህ አየለ ጥሪ አቅርበዋል።
ጣና ሐይቅ ከ700 ሺህ ሄክታር በላይ ጠቅላላ ስፋት አለው። በዩኔስኮ ከተመዘገቡት የሰሜን ተራራ ብሄራዊ ፓርክ፤ የታችኛው ኦሞና አዋሽ ሸለቆ ቀጥሎ አራተኛው የተፈጥሮ አካባቢ ነው፡፡