/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ ከብዙ መጉላላት በኋላ ለዛሬ ነሃሴ 28/2009 ዓ.ም ቀጠሮ የተያዘለት የቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያ ሲዲ ምረቃ ስነስርዓት እንዳይካሄድ ተከለከለ፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች በከፍተኛ የመንግስት ተጸኖ ሚሊኒዩም አዳራሽን ጨምሮ ልዩ ልዩ የመሰብሰቢያ ቦታወች ውስጥ የምረቃ ስነስራቱ እንዳይካሄድ እገዳና ክልከላ ሲደረግበት የነበረው ይሄው አዲስ የሙዚቃ ስራ በስተመጨረሻ ከሂልተን ሆቴል ጋር በተደረገ ስምምነት ለዛሬ ቀጠሮ ተይዞለት እንደነበር የታወቃል፡፡
የምረቃ ስነስርዓቱ በተሳካ መልኩ እንዲከናወን ከፍተኛ ዝግጅት ከተደረገና እንግዶች ተጋብዘው የሙዚቃ መሳሪያወችና የዝግጅቱ እቃወች ወደ ሆቴሉ በመግባት ላይ እንዳሉ በታጣቂ ፖሊሶች እቃወቹ ወደ አዳራሽ መግባት እንደማይችሉ መከልከላቸውን ቴዲ አፍሮ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባወጣው የሃዘንና የይቅርታ መልእክቱ አስታውቋል፡፡
ቴዲ አፍሮ በዚሁ መልእክቱ ላይ በድርጊቱ ከልቡ ማዘኑንና ለእንግዶቹና አድናቂዎቹ ይቅርታን ከመጠየቁም በላይ ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም አዲስ አመትንና ዜጎች በእኩል አይን የሚታዩበት የፍትህ ዘመን እንዲሆን ተመኝቷል፡፡
ቴዲ አፍሮ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ የለቀቀው ሙሉ መለክት እንደሚከተለው ይነበባል፦
የተወደዳችሁ ወገኖች በቅድሚያ የከበረ ሰላምታችንን እያቀረብን በዛሬው ዕለት ነሐሴ 28 – 2009 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በደመቀ ሁኔታ ልናካሒድ የነበረው የ ” ኢትዮጵያ ” አልበም ምርቃት አስፈላጊው ዝግጅት ሁሉ ተጠናቆና ጥሪ ለተደረገላቸው ዕንግዶች የመግቢያ ወረቀት ታድሎ ካበቃ በኃላ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ጉድዩ ይመለከተኛል የሚለው የመንግስት አካል መረሃ ግብሩን ማካሔድ እንደማንችልና ፍቃድ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ዝግጅቱ እንዳይካሄድ መከልከሉን ለክብሯን ወገኖቻችን ስናሳውቅ የተሰማንን ከፍተኛ ሀዘን በመግለጽ ነው ።
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው ይህን ዝግጅት ለማካሄድ ፍቃድ መጠየቅ ማለት አንድ ዜጋ የሠርግ ወይም የልደት በዓሉን ለማክበር ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ከመንግስት ፍቃድ የመጠየቅን ያህል ስራ ላይ ውሎ የማያውቅ አሰራርና ከአገሪቱ የህግ አካሄድ ጋር የሚጣረስ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ለጊዜውም ቢሆን ሁኔታውን ለማስቀጠል ባደረግነው ሙከራ ምንም አይነት የሙዚቃ መሳሪያና ለዝግጅቱ አስፈላጊው የሆኑ ግብዕቶች በሙሉ ወደ ሆቴሉ እንዳይገቡና ከመኪና እንዳይወርዱ መለዮ በለበሱ የመንግስት ታጣቂዎች በመከልከላችን ያለውን ሁኔታ ለመቀበል ተገደናል ።
በተፈጠረው ሁኔታ ጥሪ ለተደረገላቸሁ ክብራን እንግዶቻችን እና ለመላው ውድ አድናቂዎቻችን ይህን ይቅርታ ያዘለ መልዕክታችንን ስናስተላልፍ መጪው አዲስ አመት የሰላምና የፍቅር ከምንም በላይ ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ልጆች በዕኩል ዓይን የሚታዩበት የፍትሕ ዘመን እንዲሆን በመመኝት ነው ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
ፍቅር ያሸንፋል
ቴዎድሮስ ካሳሁን ( ቴዲ አፍሮ )