ከጥቂት ዓመታት በፊት የአክስዮን ማኅበራት ጋጋታ የኢትዮጵያን ህዝብ አስጨንቀውት ነበር። የተለያዩ የስራ/የልማት ዘርፎችን በአክስዮን ማኅበራት ተግባራዊ ስራ መሙላት መቻል፤ ለዜጎች፣ ለማኅበሩ አባላትና ለሀገር ያለው ፋይዳ ቀላል አይደለም፤ ጥቅሙ የላቅ መሆኑ ይታወቃል።
ግን ማኅበራቶቹን ለማቋቋም አማልይ ቃላቶችን በመጠቀም ሲያደራጁ የነበሩ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች፤ በግል ጥቅም ማሳደድ ላይ ተጠምደው እንደነበረ በወቅቱ በጉዳዩ ዙሪያ ላይ ተከታታይ ዘገባዎችን (አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ፤ ‘ተጠየቅ’ በሚል አንድ ሥር ‘የአክስዮን ማኅበራት ጋጋታና አዲስ የምዝበራ ስልት’ በሚል ርዕስ የምርመራ ጋዜጠኝነትን በመጠቀም፤ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ሞግቶ በመጠየቅ) በመስራት አይቻለሁ።
በወቅቱ ትልቅ ቦታ ደርሰው እናያቸዋለን ብለን የጠበቅናቸው ማኅበራት እንዳልነበር ሆነው ሲፈርሱ አይተን አዝነናል። ከተቋም/ከህዝብ/ከሀገር ጥቅም በላይ የግል ጥቅም ሲቀድም (ያውም በማታለል) መጨረሻው ይሄ ነው።
ይህም ብቻ አይደለም፤ በዕቅድ ደረጃ “በዚህ ጊዜ ውስጥ ወደተግባራዊ ስራ እንገባለን፣ በዚህ ጊዜ ይህንን እናተርፋለን፣ …በዚህ ጊዜ የስራ ትርፉን ለአባላቶች እናከፋፍላለን …ወዘተ” ተብሎ በዋና አድራጆች ሲነገር የነበረው ቃል የውሃ ሽታ ሆኖም ታዝበናል። ከዕቅዳቸው በጣም ዝግይተውም ቢሆን በመከራ ወደስራ የገቡ አክስዮን ማኅበራት መኖራቸው ግን አይካድም፤ ይህም ያስደስታል። ጊዜ ገዝተውም አላስፈላጊ ተጨማሪ ወጪን በአባላት ላይ እንዲጨመር ያደረጉ፣ እንደዚያም ሆና ያልተሳካለቸው የአክስዮን ማኅበር አደራጆችም አይጠፉ።
በሌላ መንገድ፣ የህዝብን ገንዘብ መዝብረው ከሀገር ወጪ የወጡ፣ በሃገር ውስጥም አድራሻቸውን ሰውረው መኖር የጀመሩ አደራጆች እንደነበሩም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ግን ከዚያ ሁሉ የማስታወቂያ ጋጋታ በኋላ፤ ዛሬ ላይ ስንቱ አክስዮን ማኅበር ተሳክቶለት በስራ ላይ ይገኛል?! ስንቶቹስ አክስዮን ማኅበራት እንዳልነበረ ሆውነ የመፍረስ ታሪክ ሰለባ ሆኑ?! ስንቱስ ዜጋ አተርፋለሁ ብሎ ገንዘቡን ሱፍ በለበሱ በቀማኞች ተበላ?!
…እንደው ዛሬ በእጃችን ላይ ሚዲያ ቢኖር ኖሮ፤ አንድም በዚህ ዘርፍ ላይ ነበር የምርመራ ጋዜጠኝነት ሰርተን እውነተኛ መረጃን ለህዝብ ማቅረብ የሚያሻን፤ የሚገባን!
የዳበረ ሚዲያ ከሌለ፤ ሀገር የሌቦች መፈንጫ መሆኗ አይቀሬ ነው!