እንዴት በኬኒያ ሕግ ወይም ፍርድ ቤትና ዳኛ መንግሥትን ማዘዝ ቻለ?
ለምን እና እንዴት ሥልጣን ላይ ያለ አንድ የአፍሪካ መንግሥት አሸንፌአለሁ ብሎ የፈነጠዘበት ምርጫ በፍርድ ቤት ውድቅ ሲደረግበት አሜን ብሎ ተቀበለ?
የ54 ዓመት የነፃነት ዕድሜ ያላት ኬኒያ እንዴት ይህንን የመሰለ የሕግ የበላይነትን ማስፈን ቻለች?
ኬኒያ አፍንጫ ስር የምትገኘው ኢትዮጵያስ? የቆየው መንግሥታዊ ሥርዓት እንኳ ባይነሳ ከ122 ዓመት በፊት የነጭ ቅኝ ገዢን አንበርክካ ከራሷ አልፋ የጥቁር ሕዝብ የነፃነትና የጀግንነት ተምሳሌት የሆነች ሃገር ጭራሹን ሕዝቧ ነፃነት አጥቶ ወደ ባሪያ ፍንገላ ዘመን ተመልሶ ሰው እንደ እንሰሳ በሰንሰለት ተጣምሮ ታስሮ የሚሰቃይበት የጎሳ አፓርታይድ ሥርዓት የተንሰራፋባት ሃገር ሆና ቀረች?
እንዴት ኢትዮጵያ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንኳ ተገድለው ማንም ተጠያቂ የማይሆንባት ግፍና ጭቆና ጣራ የነካባት ኋላ ቀር ሃገር ሆነች?
መልስ
ኬኒያ
ዋና ነጥብ። የኬኒያ ሕዝብ ይከበራል፤ ይፈራል። ይህንን x 10 እናንብበው። የተከበረውም ለመብቱ በቁርጠኝነት በመታገሉና ከፍተኛ መስዋዕትነትን በመክፈሉ፤ አሁንም መብቱ ቢነካ ትግሉን መቀጠል የሚችል ጀግና ሕዝብ በመሆኑ ነው።
ይህ ስለሆነ ዳኞች ለመፍረድ ቻሉ።
ይህ ስለሆነ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሳይወድ በግድ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቀበለ። ፍርዱን አልቀበልም ቢል ከሕዝቡ የሚመጣበትን በሚገባ ያውቃልና።
ኢትዮጵያ
ዋና ነጥብ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ አገዛዝ የማይከበርና የማይፈራ ነው። ይህንን x 10 ጊዜ እናንብበው።
ወያኔ ለሥልጣን ከበቃበት ጊዜ ጀመሮ፤ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው የሕግ የበላይነትንና እኩልነትን ለማስፈን ታግለዋል፤ መስዋዕነትንም ከፍለዋል። ነገር ግን የወያኔን ግድያና እስር አልፎ የሄደ ትግል እስከ አሁን አልተካሄደም። ለዚህም ወያኔ በመግደልና በማሰር ትግልን እያኮላሸ ለዘለዓለም እንደሚገዛ ስለሚያውቀው የኢትዮጵያን ሕዝብ አይፈራም አያከብርም።
በኬኒያ ግን መንግሥት ስለገደለ የቆመ የነፃነት ትግል የለም በድርድር እንጂ። ለራሱና ለሃገሩ ነጻነትና እኩልነት የቆመ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህንን በትክክል ሊገነዘበው ይገባል!!
የወያኔ ተቋዋሚዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በወያኔ የሚዋረዱት፤ የሚታሰሩት፤ የሚሰቃዩትና የሚገደሉት የሚታገሉለት ሕዝብ የማይከበርና የማይፈራ ስለሆነ ነው። ምክንያቱም ታጋዮቹን ወያኔ ሲያስር የታገሉለት ሕዝብ እቤቱ ገብቶ ይተኛል እነሱ ይረሳሉ።
የኬኒያ ሕዝብ ግን የሕዝብ የተቃዋሚ መሪዎቹ ቢታሰሩበት ሃገሪቷ ትናወጣለች እንጂ እነሱን አሳስሮ ቤቱ ገብቶ አይተኛም። የሕዝብ መከበርና የመናቅ ውጤቱ ይህ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ በገዢዎችህ ዘንድ የሚያስከብርህና የሚያስፈራህ ትግል ካላደረግህ ዘለዓለም ባሪያ ሆነህ ትኖራለህ!! እቅጩን እወቀው።