በአዲስ አበባ አዲስ በሚገነባው አደይ አበባ ስታዲየም ውስጥ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ የሰባት...

በአዲስ አበባ አዲስ በሚገነባው አደይ አበባ ስታዲየም ውስጥ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ የሰባት ሰዎችን ህይወት ቀጠፈ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ በአዲስ አበባ የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ ሳይት የሰራተኞች ማረፊያ ቤት ውስጥ የደረሰ የእሳት አደጋ የሰባት ሰዎችን ህይወት ሲያጠፋ በርካታ ሰዎች ላይ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

ግንባታው ሲጠናቀቅ የሀገሪቱ ትልቁ ስታዲየም ይሆናል በተባለው “አደይ አበባ ስታዲየም” በፈረጆች አቆጣጠር ነሐሴ 8/ 2017 ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ በሰራተኞች ማረፊያ ቤት የፈነዳው የጋዝ ሲሊንደር የቃጠሎው መንስኤ ነው ተብሏል።በቃጠሎውም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ከ12 በላይ ሰዎች በዳግማዊ ሚኒልክ ሆስፒታል፣ በዘውዲቱ መታሰቢያና በሌሎች ሆስፒታሎችም ህክምና እየተከታተሉ እንደሆነ አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል።

እጅና እግራቸው በእሳት የተቃጠሉ ሦስት ሰዎች በቂ ህክምና ሳያገኙ ከሆስፒታል እንደወጡም ለማወቅ ተችሏል።አብዛኛዎቹ የሞቱትም ሰዎች ከሻሸመኔና ወሎ የመጡ ሲሆኑ አስከሬናቸውም ወደየ በተሰቦቻቸው ተሸኝቷል። ለሟች ቤተሰቦችም ክስ እንዳያነሱ ለእያንዳንዳቸው 15000 ብር የስታዲየሙን ግንባታ የሚያካሂደው ቻይናዊው ድርጅት የነፍስ ዋጋ ከፍሏል።

ጉዳቱ ከደረሰ አንድ ወር እስኪሆነው ድረስ በመሀል አዲስ አበባ ሆኖ እያለ አለመሰማ መንግስትና የድርጅቱ ሀላፊዎች የደርጅቱን ጥቅምና ገጽታ ይጎዳል በማለት አፍነው በመያዛቸው ነው ሲሉ የጉዳቱ ሰለባዎች ተናግረዋል።አሁንም የድርጅቱ የስራ ሀላፊዎች አካባቢውን ለጉብኝት ክፍት አለማድረጋቸው ዘገባው አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የቻይና የንግድ ካምፓኒዎች ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ እያካሄዱ መሆኑ ይታወቃል።ይሁን እንጂ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በየጊዜው የተለያዩ ስሞታዎች ያሰማሉ።

ለአብነትም በድርጅቶቻቸው ለሚቀጠሩ ሰራተኞች በቂ ክፍያ አለመስጠት፤ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ማድረስ፤ ለሚያከናውኗቸው የኮንስትራክሽንና ሌሎች ተግባራት ደረጃቸውን የጠበቁ ስለማይሆኑ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የእራሳቸውን አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው የሚሉ ስሞታዎች በርካታ ናቸው።

LEAVE A REPLY