የምስራቅ ኢትዮጵያ የዛሬ ውሎ

የምስራቅ ኢትዮጵያ የዛሬ ውሎ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ በምስራቅ ኢትዮጵያ በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት ዛሬም የተለያዩ ኩነቶችን አስተናግዶ ውሏል።

በቆቦና ጨለቆ ከተሞች ሦስት ሰላም ባሶችና አንድ የነዳጅ መጫኛ ቦቲ መኪና መቃጠላቸው ተነግሯል። ከድሬ ዳዋ- ሐረርና ጅጅጋ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል። በባቢሌ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ የተደረገ ሲሆን በሰልፉ ላይ የኦሮሚያ ፖሊስ ሰልፈኛው ላይ መተኮሱን ሲገልጹ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ ሰልፉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንደተጠናቀቀ ዘግበዋል።

ከሳምንታት በላይ በዘለቀው የሁለቱ ወገኖች ግጭት በርካታ ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከ1500 በችላይ የኦሮሞ ተወላጆች ከሶማሌ ክልል ሸሽተው ወደ ሐረር ከተማ መግባታቸው ታውቋል። አንድ የመከላከያ ኦራል መኪና ከሶማሌ ክልል የሸሹ ኦሮሞችን ዛሬ ወደ ሐረር ከተማ ጭኖ ማምጣቱን እማኞች ለዶቸ ቬሌ አስረድተዋል።

“የኦነግ” አስተሳሰብ ባለቸው የኦሮሞ ተወላጆች ወደ ክልላችን ገብተው በህዝብ ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው፤ እኛም የመከላከል እርምጃ እየወሰድን ነው በማለት የሶማሌ ክልል የመንግስት ቃል አቀባይ ትናንት ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ አንድም የታጠቀ የኦነግ ወታደር በክልሉ እንደሌለ ገልጸው፤ በአቶ አብዲ ሙሐመድ የሚመራው የ“ልዩ ሀይል” ፖሊስ ወደ ኦሮሚያ ክልል በመግባት የክልላቸውን ባንዲራ እንደሰቀሉና በነዋሪውም ላይ ጥቃት እንደፈጸሙ ገልጸዋል።

እንዲህ አይነት ችግሮች ሲከሰቱ የፌዴራል መንግስቱ አልያም የፌዴሬሽን ም/ቤቱ የመፍታት ሀላፊነት ቢኖርበትም እስካሁን ምንም አለማለቱ ስርዓቱ ምን ያህል አላፊነት የጎደለው መሆኑን ያሳያል ተብሏል። በግጭቱ የሶሜሌ ልዩ ሀይል ፖሊስ መሪ ተዋናይ ሲሆን በክልሉ ፕሬዚዳንና በህወሓት ባለስልጣናት ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚደረግለትም አንዳንድ ወገኖች እየገለጹ ነው።

ባለፉት 26 ዓመታት በኢትዮጵያ የጎሳ ፌዴራሊዝም (የመንግስት አወቃቀር) ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ እንዲህ አይነት ግጭቶች በየጊዜው በሁሉም ክልሎች ይከሰታሉ። ዜጎች በዘራቸው ወይም በጎሳቸው ምክንያት የተለያየ በደል ሲደርስባቸው መቆየቱም የሚታወስ ነው። ችግሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና ከቁጥጥር እየወጣ መምጣቱን የሚገልጹ አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛል።

LEAVE A REPLY