የኬንያ ፖሊስ በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ናይሮቢ የደረሱ 60 ኢትዮጵያዊያንን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ትናንት አስታወቀ።እሁድ እለት ናይሮቢ መድረሳቸውን የገለጹት ስደተኞቹ በምስራቃዊ ናይሮቢ ካዮሌ በተባለ ሰፈር በአንድ ጠባብ ቤት ውስጥ በፖሊስ ተይዘዋል።ዳቦ ብቻ በመመገብና በአንድ ንጽህናው ባልተጠበቀ ሽንት ቤት በመጠቀም ጤንነታቸው አደጋ ላይ እንደነበረም ተገልጿል።
ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ለፖሊስ እንደገለጹት ናይሮቢ የተገኙት በደላሎች መንገድ መሪነት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር እንደሆነ አስረድተዋል።ደላሎቹም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የናይሮቢ ፖሊስ ኮማንድር ጃፌዝ ኮሚ ገልጸዋል። ስደተኞቹ እንግሊዝኛም ሆነ ኪስዋህሊ መናገር ስለማይችሉ መግባባት እንዳልተቻለ የገለጹት ኮማንደሩ ፍ/ቤት እንደሚቀርቡም አሳውቀዋል።ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ ቦታ 13 ኢትዮጵያዊያን ተይዘው ፍ/ቤት መቅረባቸው ይታወቃል።
ስደተኞች ላይ የሚሰሩ አለም አቀፍ ተቋማትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ለህገ-ወጥ ስደት መባባስ ድህነትና የመንግስታቱ የመብት እረገጣ ዋና ምክንያት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገልፃሉ።