ደራሲ፤ ተስፋዬ መኮንን ባይለየኝ (ዶ/ር)
ቅኝት፤ መስፍን ማሞ ተሰማ
ቀዳሚ፤
እነሆ ከጣምራ ቁስል በፊት “ቀይ አንበሳ” ነበረ። እነሆም ስለ ‘ቀይ አንበሳ’ ‘በማንኪያ’ እናቀምሳለን። እንዲህ ብለን፤ አልኻንድሮ ዴል ባዬ ኩባዊ ነው። ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ለንደን፤ እንግሊዝ ውስጥ ነበር። በወቅቱ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ሀኪም ወርቅነህ ማርቲን (ደብሊው ማርቲን) በጋዜጣ ላይ ባወጡት ማስታወቂያ አነሳሽነት አምባሳደሩ ፊት በመቅረብ ለአትዮጵያ በፈቃደኝነት ለመዋጋት የሚፈልግ መሆኑን ይገልፃል። አምባሳደር ወርቅነህም ጠየቁት፤
“ከእኛ በኩል ሆነህ ለመታገል ስትል ነው ከአገርህ ድረስ የመጣኸው?”
“አይደለም። ከስፔን ገና መምጣቴ ነው። ወደ ኩባ ለመመለስ ነበር እቅዱ። ለውጪ አገር መኮንኖች በአቢሲኒያ ላይ የተቃጣውን ወረራ ለመዋጋት የቀረበውን ጥሪ አንብቤ ነው የመጣሁት። ይኸው ነው በቃ።”
“አንተ የኔን ምድር ታፈቅራታለህ?”
“በእርግጥ አላፈቅራትም። ግን በሀይልና በጉልበት አንድ ሀገር ይዞ የሚደርሰውን ግፍ በፍፁም እጠላለሁ። የእኔ ሀገር በጣም ትንሽ ናት። ለሀገር ምድር ሙሉ ነፃነትና ክብር ለሚደረግ ውጊያ እጅግ በጣም ደስ ይለኛል።”
አምባሳደር ማርቲን በሰጠሁዋቸው መልስ የረኩ ይመስላሉ። በውስጤ ያለውን ዘልቀው ለመመልከት በዝምታ አተኩረው የተመለከቱኝ ምንጊዜም ይታወሰኛል። ይላል አልኻንድሮ በታሪክ ትውስታው።
እነሆ ከዚህ በሁዋላ ከለንደን ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘው አልኻንድሮ ስለ ጉዞውና በጉዞው ስለገጠሙት ደግሞም በኢትዮጵያ ውስጥ በቆየበት ወቅት ያየውን፤ ያጋጠመውን፤ የሰማውንና እንዲሁም የአስራ አንድ ወራት የጦርነትና የተጋድሎ ታሪክ በሰፊው አውስቷል። አልኻንድሮ አዲስ አበባ ከቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ ጋር ከተገናኘና ከተወያየ በሁዋላ ለኢትዮጵያ የጦር ሚኒስትር ለራስ ሙሉጌታ ይገዙ አማካሪ በመሆን ወደ ሰሜን ዘመተ። እነሆም በኢትዮጵያና በህዝቧ ፍቅርም ተነደፈ። እንዲህም አለ፤ “ለአቢሲኒያ ህይወቴን እሰጣታለሁ እንጂ አልሸጥላትም።”
ለሻለቃ አልኻንድሮ ዴል ባዬ የኮሎኔልነት ማዕረግ የሰጡትና አርማውን የጫኑለት ቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ ሲሆኑ ይህም የሆነው በተፋፋመው ጦርነት ወቅት ኮረም ላይ ሲገናኙ ነበር። በግንኙነታቸው ወቅት የንጉሡን ቃል ሲገልፅ እንዲህ ብሏል፤
“ስላደረግኸው ሁሉ ውለታህን እግዚአብሄር ይክፈልህ። ለአገሬ ላደረግኸውና ለዋልከው ውለታ ልሰጥህ የምችለው አሁን የምሰጥህን ምሥጋናና እጄን ብቻ ነው” በማለት ንጉሡ ለስላሳ እጃቸውን ፈገግ በማለት ዘረጉልኝ። ትኩር ብለው እያዩ በመኩራራትና በሙሉ ልብ እንዲህ አሉኝ።
“ይሄ ነው እውቁ ‘ቀይ አንበሳ’ የአቢሲኒያው አንበሳ ፈረንጅ። ልክ እንደ ራሱ ምድር ለእኛ መሬት የተዋጋ የታገለ ‘ቀዩ አንበሳ’ ይሄ ነው።”
ኮሎኔል አልኻንድሮ በኢትዮጵያ ሠራዊት ውስጥ የሚታወቀው “ቀዩ አንበሳ” በሚል የቁልምጫና የጀግና መጠሪያ ነበር። በምድረ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያውያን ጎን ሆኖ ለነፃነት መዋጋት ማለት እንዴትና ምን ማለት እንደሆን ለነጩ ዓለም አንባቢ ሲገልፅ እንዲህ ይላል፤
የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት ከሌሎቹ ጦርነቶች ሁሉ ልዩ የሚያደርገው የኢትዮጵያውያን ውጊያ ፍርሃት ግዳጅ የማይታይበት ሁሉም ለክብሩ ለሀገሩ ሆ ብሎ በመነሳት ገድሉን፤ ጀግንነቱን፤ ጭካኔውን የሚያሳይበትና ስጋ ለስጋ የሚሞጫለፍበት ጦርነት መሆኑ ብቻ ነው። ከዚህ ህዝብ ጋር መቀላቀል ከፈለግህ እኔ የመጀመሪያ ተግባሬን ስፈፅም እንዳደረግሁት በውስጥህ ያለውን ነገር ሁሉ ርግፍ አድርገህ መተው አለብህ። ስልጡንነትህን በመተው ወደዃላ በመመለስ ብዙ እጅግ በጣም ሁዋላ ቀር ነገሮች ውስጥ መዘፈቅ፤ ፊት ለፊት ሞትን በፀጋ መቀበል፤ እተርፋለሁ ማለትንም ሙሉ ለሙሉ መተው፤ በህይወት ወደ ሌሎች ዘንድ ወደ ዘመዶችህ ያለመመለስህን ያለጥርጥር መቀበል ስላለብህ ይሄንን ጦርነት ልዩ ያደርገዋል። ከጠላት ጋር መጋፈጥን ማለቴ አይደለም። ከጫካና ከዱር ጋር መጋፈጥ፤ ከከፍተኛ የአካባቢው ለውጥ በአካባቢው ካሉት ለጤና ጠንቅ የሆኑና ለበሽታ በቀላሉ የሚያጋልጡህ ሁኔታዎችን አንድ ነጭ በቀላሉ ሊጋፈጣቸው ወይም ሊወጣቸው የማይችለውን ማለቴ ነው።
ትከሻችንን አደጋግፈን አብረን የመጣውን ጠላት ከምንዋጋው ሰዎች በነጭነትህ ምናልባት አደጋ ሊደርስብህ ይችላል ብለህ የሚኖረውን ስጋት ማለቴ ነው። የሚያበሩ ዓይኖቻቸውን አፍጥጠው አትኩረው ይመለከቱሃል። ትንሽ መዛነፍ፤ ከዓላማ መዘናጋት ወይም ማሳሳት እንዳይኖር በጥንቃቄ ይከታተሉሃል። ሲያጠቁ አብረህ ማጥቃት አለብህ። ከፊታቸው ይህን ወደር የሌለው የጀግንነት ውጊያ ለማመን በሚያስቸግርህ ሁኔታ ሞቱን አብረህ መጋፈጥ፤ ከጠላት በሚወርድብህ የቦንብ፤ የመድፍ፤ የጥይት ናዳ ጩኸት የወገንህን ሬሳ ሳይቀር እየረገጥክና በላዩ ላይ እየተረማመድክ ከደረትህ ጥቂት ሜትሮች የማትርቅ መሬትን በብዙ የወገኖችህ መስዋዕትነት ባንተ ቁጥጥር ስር ማድረግ፤ መጨረሻውን ወደማታውቀው ወደፊት መገስገስ። ድካም መውደቅ የለ። በመጨረሻም ደንዝዘህ ያለምንም ጥንቃቄ በዚያ ትርኢት ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ በመሆን ከወዲያኛው የጠላት ምሽግ ተስበህ ከጠላት ጋር መደባለቅ። ሳንጃ ለሳንጃ መሞሻለቅ። በመደምደሚያው ጣሊያኖች ባደረባቸው ፍርሃትና ባልጠበቁት አጋጣሚ አንደበታቸው ተዘግቶ ሰውነታቸው በድንጋጤ ገርጥቶ ታገኘዋለህ። ይህን ማለቴ ነው ባጠቃላይ አነጋገር።
ማንም በትክክል አይፅፈውም። እኔም ራሴ ብሆን በዚያ ውጊያ ያየሁትን መግለፅ አልችልም። ምንም እንኳን ተዋናይ ብሆንም የዚህን ጦርነትና የሚሰማህን ሰቆቃ፤ በጦርነቱም ያ ቁጡ የሆነ ዘር በማይረቡ በአረጁና ጊዜያቸው ባለፈባቸው የጦር መሳሪያዎች በዘመናዊ መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን፤ ከዓለም በአንደኛ ደረጃ ከተሰለፉ የአየር ሃይሎች አንዱ ያለውና መርዛማ የቦንብ ጭስ ከሚጠቀም ጦር ጋር ገጥሞ የተሸነፈበትን ውጊያ በትክክል መግለፅ አልችልም። በማለት ስለሁለተኛው የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት ምስክርነቱን አኑሯል፤ ኮሎኔል አልኻንድሮ ዴል ባዬ። (ሰረዝ እና ‘ሃይ ላይት’ የቃኚው)
‘ቀይ አንበሳ’ ከሰሜን ግንባር ሽንፈት በሁዋላ አዲስ አበባ በፋሽስቶች ቁጥጥር ስር ስትውል ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ በመጓዝ ጦርነቱን ከራስ እምሩ ሃይለ ሥላሴ ጋር ለመቀጠል ቢሞክርም የራስ እምሩ ጦር በከፍተኛ የፋሽስት ሰራዊትና ፋሽስት ባስታጠቃቸው አያሌ የአካባቢው ነዋሪዎች የተከበበና ከፊትና ከሁዋላ በመትረየስ በቦንብና በመርዝ ጋዝ እየተደበደበና እየተፈጀ ፍፁም ተስፋ አስቆራጭ የሆነ ሰቆቃ ውስጥ በመሆኑና በዚህም ሂደት በጣሊያኖች ቁጥጥር ስር ራሱም ከመውደቁ በፊት በጥቂት ታማኝ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ብርታት ከብዙ ፈተና በሁዋላ ወደ ሱዳን መዝለቅ ቻለ።
ከሱዳን ወደ ካይሮ ተሻግሮ የከበደ ልቡን እንደተሸከመ ወደ ሀገሩ ኩባ በመግባት በኢትዮጵያ ውስጥ ስላሳለፍው ጦርነት ታሪክ የሚያወሳ በአንድ መቶ ቅጂዎች ብቻ የተባዛ መፅሀፍ በ1929 ዓ/ም በስፓኒሽ ቋንቋ ተፅፎ ወጣ። ኩባ ለትምህርት በቆዩበት ወቅት ይህንን ታላቅ የታሪክ መዘክር ያነበቡት ኢትዮጵያዊ እጅግ ማራኪ በሆነ የቋንቋ ፍሰት ወደ አማርኛ በመመለስ እና “ቀይ አንበሳ” የሚል ርዕስ በመስጠት (ኦሪጅናል ርዕሱ አይደለም) በ1992 ዓ/ም ለባለ ታሪኩ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያቀረቡት ዶ/ር ተስፋዬ መኮንን ባይለየኝ ናቸው። ይህ ታላቅ መፅሀፍ ሶስት መቶ አስራ ሰባት (317) ገፆች አሉት።
እነሆ በኢትዮጵያዊነትህ መደራደር የማታስብና እንዲያውም ለመደራደር መነሳቱንም ‘ታቡ’ /አይታሰቤ/ አድርገህ በራስህ የምትተማመን፤ የቀደመው ታሪክህ እንደ ታሪክነቱ የእኔነቴ አካል ነው ብለህ (ከነህፀፁም) ታሪክነቱን የምትቀበል፤ በቀደሙት አብናቶችህ (አባት እናቶችህ) ገድል ሀገር የማቆምና ዳር ድንበር የመጠበቅ መስዋዕትነት የማትዘባበት ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከአድዋ ለጥቆ ሁለተኛው የነፃነት ወይም የቅኝ ተገዢነትን አሻፈረኝ ባይነት የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት እንደምን እንደነበር አበክረህ የማወቅ ግዴታም አለብህና የኮሎኔል አልኻንድሮ ዴል ባየህን “ቀይ አንበሳ” አንብብ። ለአቢሲኒያ የዘመተውን የቼኮዝሎቫኪያዊውን የጦርነቱ ተዋናይን የካፒቴን አዶልፍ ፓርለሳክን “የሀበሻ ጀብዱ” – ተጫኔ ጀንበሬ መኮንን – የተረጎሙትን አንብብ። አርበኛውና ደራሲው ክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ የተሳተፉበትንና ላንተ ትተውልህ ያለፉትን የዚያን ሰቆቃዊ ጦርነት ታሪክ “ትዝታ”ን አንብብ። በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ የተነሳውን የዚህን ዘመን የክፉ ሰዎች ወጀብ ተቋቁመህ በኩራት ለመራመድ ላንተነትህና ለታሪክ ባለቤትነትህ ክብርን ያጎናፅፍሃልና። ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትህም የፅናት ምርኩዝ፤ የብርሃንም መቅረዝ ይሰጥሃልና።
ተከታይ፤
እነሆ “ጣምራ ቁስል” በ2009 ዓ/ም በ285 ገፆች ተቀንብቦ በሀገረ አሜሪካ ታትሞ ‘ቀይ አንበሳ’ን ተከተለ። ጣምራ ቁስል የጦርነት ታሪክ ነው። ጣምራ ቁስል የፍቅር ታሪክ ነው። ጣምራ ቁስል የክህደት ታሪክ ነው። ጣምራ ቁስል የፅናት ታሪክ ነው። ጣምራ ቁስል የፍትህ እጦት ታሪክ ነው። ጣምራ ቁስል የኢትዮጵያን የህክምና ዶክተሮች ችሎታ ያገዘፈ ወይም የዘከረ ሥራ ነው። ጣምራ ቁስል ከ1983 ዓ/ም ወዲህ ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካና የማህበራዊ ህይወት በአሳዛኝና በአስከፊ ገፅታዎቹ ጭምር ታጅቦ የቀረበበት በእውነተኛ ታሪክ ላይ የቆመ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ታሪክ አካል ነው። ይህንን መፅሀፍ የምንቃኘውም በውስጡ ያሰናሰላቸው አያሌ የታሪኩ ሂደት ሰበዞች ስለኮረኮሩን በሀዘንም በትካዜም ድባብ ውስጥ መላልሰው ስለዶሉን አደባባይ ልናሰጣቸው ፈልገን ነው፤ ከታሪኩ መኻል ያሉ ታሪኮች በርካቶች ናቸውና። ሆኖም በሁሉም ሰበዞች ላይ እንቆዝም ዘንድ አንችልም! ግዙፉን ሥራ ለመፅሀፉ አንባቢ እንተዋለንና። እንዲህ ካልን በሁዋላ ራሳችን ‘በፈጠርናቸው’ ንዑሳን ርእሶች እነሆ የ‘ጣምራ ቁስል’ን ቅኝት እናስከትላለን።
ሥልተ-ትርክት
የ‘ጣምራ ቁስል’ ትርክት በሶስተኛ መደብ ነው። በዚህ ታሪክ ውስጥ የሚገኙት ገፀ ባህሪያት አሳሳል እና የትርክት (ናሬሽን) አወራረድ እጅግ የረቀቀ የልብወለድ ሥራ እስኪመስል ልብ አንጠልጣይነት (ሰስፔንስ) እና ጡዘት (ክላይማክስ) አለው። ትርክቱ ተጀምሮ እስከሚያበቃ ያለው የአወቃቀር ‘ሴራ’ (ፕሎት) ግሩም ነው፤ አንባቢ ከየት ወዴት እንደሚያመራ በቅጡ አይተነብይምና። የታሪኩ መቼቶች (መቼ እና የት) – ታይም ኤንድ ፕሌስ – በቀዳማዩ ተራኪ ‘ክንፈሚካኤል ዘ-ፉኛን ቢራ’ ብቻ ሳይሆን የዘ-ፉኛን ቢራ ትርክት ለአንባቢ ቀምሞ የተረከው ደራሲው ራሱ የቦታና የጊዜ ቀረፃው ላይ የጠለቀ እውቀት እንዳለው ታሪኩ በራሱ ያሳብቃል። ትርክቱ በምልሰት (ፍላሽባክ) ተያያዥ ጉዳዮችን ከዋናው ገፀ ባህሪም ሆነ ከታሪኩ ጋር እያቆላለፈ ሲተረትረው የአንባቢን የእውቀት አድማስ መማሱ ብቻ ሳይሆን ተያያዦቹ ትርክቶች በራሳቸው ታሪክ መሆናቸው ለመፅሀፉ ጡንቻ ሆነዋል።
ቃላት በከንቱ አለመተኮሳቸው ዒላማቸውን እንዲመቱ አድርጓቸዋል፤ የአሰካክ ፍሰታቸውም (ሊትራሪ ፍሎው) ሳይጎረብጥ እንዲተምም ተደርጓልና። የሁኔታዎችን፤ የቦታዎችንና የድርጊቶችን ሥዕላዊ ገለጣው የተዋጣለት ነው። ከሁሉም በላይ በህክምናው መስክ እጅግ የተወሳሰቡ ሂደቶችንና ዝርዝር ጉዳዮችን በማፍታታት በግልፅ ቋንቋ ለታዳሚው ሲያስተላልፍ ግሩም ችሎታ ታይቶበታል። ተራኪው ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ ባልተገኘባቸው ሰአቶችና ቦታዎች፤ የታሪክ ዕውነቶችና ክስተቶች ላይ ሁሉ ደራሲው ከተፍ እያለ ‘ማን ተራኪ ማን ደራሲ’ እንደሆን እስከጠፋብን ድረስ ታሪኩ ይንቆረቆራል። የክንፈሚካኤል ዘ-ፉኛን ቢራ ‘ቃል አቀባይ’ /ደራሲው/ ስለ ክንፈ እንዲህ ይላል፤
ክንፈሚካኤል ዘ-ፉኛን ቢራ ከልጅነት ጀምሮ ጓደኛዬ ነው። አብሮ አደጌ ነው፤ አብረንም ፊደል ቆጥረናል። ከቄስ ት/ቤት እስከ ከፍተኛ ትምህርት አብረን ዘልቀናል። በሥራ ዓለምም አብሮ የመስራት ዕድሉ ገጥሞናል። ክንፈሚካኤል በህይወት ዘመኑ የገጠመውን አስደሳችም ሆነ አሳዛኝ ሁኔታዎች በወረቀት ወይም በአእምሮው መዝግቦ ያስቀምጣል። ወይ ሊፅፈው ወይ ለሰው ሊተርከው። ከእነዚህ ከመዘገባቸው ታሪኮች አንዱን የነመራን (ስሙ ተለውጣል) ታሪክ በሰባት ተከታታይ ረጃጅም ምሽቶች አጫወተኝ። እኔም በእግዚአብሄር ፈቃድ በዚህ መልኩ አቅርቤዋለሁ።. . .
እንግዲህ እኛም ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ እና ደራሲው አንድም ሁለትም ናቸው ብለን ወደ ቀደመ ጉዳያችን እነሆ እንዘልቃለን።
ነመራ ገመቹ – ኢጆሌ ወለጋ ፤
በ1990ዎቹ መጀመሪያ እንዲህም ሆነ።
ዝንተ ዓለም የሰው ደም ካልተገበረለት ሰላም ላያድር ለሰይጣን ቃል የገባ በሚመስለው የሰሜኑ ድንበር ዳግም በጥይት ባሩድ ሲታጠን፤ በፈንጂ ሲደረማመስ፤ በመድፍ የላዩ ታች የታቹ ላይ ሲሆን ነመራ ተረጋግቶ መቀመጥ አልቻለም።
ነመራ ከቤቱ ደጃፍ ቆሞ ውስጡ ይብሰለሰላል። ‘እንዴት ሊሆን ይችላል? ነፋስ አይገባው የተባለው ፍቅር፤ በሰላም አብሮ ለመኖር መፍትሄው መገንጠል ነው ተብሎ ተለፍፎ ከበሮ ሲደለቅ፤ ቄጤማና ፈንዲሻ ሲነሰነስ ተከርሞ ለፀብ ተነሱ? ሊሆን አይችልም፤ ሀሰት ነው ወይም ድብቅ ዓላማ አለው!” ብሎ ራሱን ይነቀንቃል። እንደ ዳዊት ደጋሚ ያጉረመርማል።
‘ፍቅር ሲያልቅ አያምር’ ይላል ተረቱ፤ የአበው ትውፊቱ። አዎ ዕውነት ነው። በዚያን የ1990ዎቹ መጀመሪያ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት ተነሳ የመባሉ እንቢልታ ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ዱብ ዕዳ ነበር የሆነበት። እንደ ነመራ፤ ኢጆሌ ወለጋ ስሜት ሁሉ – በሀረርጌም በባሌም በአርሲም በሲዳማም በጋሙጎፋም በከፋም በኢሉባቡርም በወለጋም በሸዋም በጎጃምም በጎንደርም በወሎም ያለው ሁሉ ጆሮው የሚሰማውን ማመን አቅቶት ነበር – ሻዕቢያና ወያኔ – ‘እንዴት ሊጣሉ ቻሉ?’ በማለት። የሻዕቢያው ኢሳያስና የህወሃቱ መለስ በ1983 ዓ/ም ሰሜንና ደቡብ ባቆሙዋቸው በቀለኛና ዘረኛ “መንግሥታት” ኢትዮጵያን ተቀራምተው እንደ ተራበ ጅብ ሁለቱ ድርጅቶች ሆድ ዕቃዋን ይመዘብሯት ነበርና።
ከድፍን ኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የተጋዘውን ወርቅና ብር ተነቃቅሎ የተወሰደውን ማሽነሪ ወዘተርፈዎች ሁሉና ኤርትራ በቡና ምርት በአለም ገበያ አቅርቦት የመጀመሪያውን ረድፍ የያዘችበትን ያን የዘራፊዎችና የአስዘራፊዎች ዘመን ወደሁዋላ መለስ ብሎ ያስታውሷል። ቀጥተኛው የሻዕቢያ ዝርፊያ ቢገታም የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ /ህወሃት/ ዝርፊያ ግን ዛሬ ዘመን ተራቋል እንጂ አላባራም። እንመለስ ወደ ጣምራ ቁስል።
በ1990ዎቹ መጀመሪያ እንዲህም ሆነ።
የአፀፋው ጦርነት ነጋሪት ሲጎሰም፤ ተረስተው የነበሩ የሀገር ፍቅር ስሜት ቀስቃሽ ዜማዎች እየተፈለጉ ቀኑን ሙሉ በሬዲዮ ሲለቀቁ ቀናቶች አለፉ። የመቀሌው አይደር ት/ቤት በመለማመጃ አውሮፕላን በቦንብ ሲደበደብና የህፃናት ደም በሜዳው ሲፈስ የሚያሳየው ምስል በጋዜጣና በቴሌቪዥን ሲለቀቅ “እንዴት ሲደረግ እንዲህ አይነት ድፍረት!” ተባለ። ከአራቱም ማዕዘናት የህዝብ ማዕበል ይወድቅ ይነሳ ይገማሸር ጀመር። ጉዞ ወደ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ሆነ። ጣቢያዎቹም በአስር ሺዎችና በመቶ ሺዎች ወጣቶችና ጎልማሶች ተሞሉ። የነመራም ልብ በእልህና በቁጭት ከተንገበገቡት አንዷ ነበረች። “ይህንንማ እጄን አጣምሬ አላይም!” ሲል ለራሱ ቃል ገባ። ጨርቄን ማቄን ብሎ ነገር የለም። የሚወዳትን ሚስቱን ልጆቹን የደከሙ አባቱን ተሰናበተ።. . .ከበርካታ ጓደኞቹ ጋርም በአቅራቢያው በሚገኘው የዴዴሳ ማሰልጠኛ ገባ።
እነሆ ወጣቱ ነመራ ገመቹ – ኢጆሌ ወለጋ – ትግራይን ሊታደግ፤ የትግራይን ህዝብ ሊያድን ለትግራይ ህፃናት እርሱ ሊሞት (የራሱን ህፃናት ባዶ ቤት ጥሎ) እሱን ከመሳሰሉ ወይም የርሱን ህይወት ከሚጋሩ – በመቶ ሺህ ከሚቆጠሩት ከተከዜ በታች እስከ ሞያሌ ካሉት ኢትዮጵያውያን (ኦሮሞ አማራ ጉራጌ ከንባታ ሀረሪ ወላይታ አኙዋክ ኮንሶ አፋር ሶማሊ እና) ጋር ተቀላቅሎ ወደ እሳተ ገሞራው ምድር አቀና። ትግራይ ሀገሬ ናት ብሎ፤ ትግራውያን ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ናቸው ብሎ፤ ከድምሩ የተከዜ በታች ኢትዮጵያውያን ጋር ሆ! ብሎ ተመመ፤ ነመራ ገመቹ፤ እንደ ቀደምት አያቶቹ።
ስለ ትግራይ ህዝብና ስለ ትግራይ ምድር ስንትና ስንት ከተከዜ በታች ያለ ኢትዮጵያዊ በዘመናት ሂደት ህይወቱን ገብሯል? ህልቆ መሳፍርት የሌለው መስዋዕትነት የተከፈለው ግን ትግራይ የኢትዮጵያ ትግራውያንም ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብሎ ነበር፤ ከ1983ዓ/ም በፊት በነበረው ሀገራዊ የታሪክ ዕውነታ። ከዛ ወዲህ ባሳለፍነው ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ዘልቆ በሚገኘው የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር /ህወሃት/ አገዛዝ ጊዜስ?
በዘመነ አፓርታይድ በህወሃት አገዛዝ ያፈጠጠውን ሀቅ እነሆ እናፈርጣለን፤ ትግራይ የኢትዮጵያውያን አልሆነችም፤ ኢትዮጵያ ግን የትግራውያን ነች!! ይህንንም የፈጠረውና በመተግባር ላይ የተጋው የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር /ህወሃት/ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም። ባለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት የኢትዮጵያን ህዝብ ከትግራይ ያገለለውና ከትግራይ ህዝብ ጋር ባዕድ ያደረገው ህወሃትና ‘ናዚስት’ መሪዎቹ ናቸው። ትግራይ ከተከዜ በታች ለሚገኙት ኢትዮጵያውያን በሯን የዘጋችውም ከውስጧ በፈለቁት “ልጆቿ” እንጂ ስለትግራይ ለምዕተ ዓመታት በወደቁት ኢትዮጵያውያን የልጅ ልጆች አይደለም።
ትግራይ በሯን ለኢትዮጵያውያን (ከተከዜ ወዲህ ለሚገኙት) ብትቀረቅብም ከመላዋ ኢትዮጵያ ግን የሚገኘውን አንጡራ ሀብት ብቻ ሳይሆን በየክፍላተ ሀገራቱ የነበሩትን ታላላቅ ጀኔሬተሮችንና ፈብሪካዎችን ነቃቅላ፤ ቋሚና ተንቀሳቃሽ የሀገሪቷን ታላላቅ ንብረቶች አጓጉዛ ‘ትግራይ ትልማ፤ ሌላው ይድማ’ በሚል በቀለኛ ብዝበዛ ለሩብ ምዕተ ዓመት ያላባራ ዘረፋ ላይ የምትገኘው ከውስጧ በተወለዱ ህወሃታውያን ልጆቿ ነው። ወያኔ ከደቡብ እስከ ሰሜን ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የሚገኙ ለም መሬቶችን በመዝረፍና በማዘረፍ ለመቶ ዓመት ለባዕዳን /ለህንድ ለሳውዲ ለወዘተ/ በመቸብቸብ ብቻ ሳይሆን የራስ ዳሽንንም ተራራ በመስረቅ በቀድሞዋ ትግራይ ክልል ያጠቃለለ ኢትዮጵያን እመራለሁ እያለ ከኢትዮጵያ የሚሰርቅ ጉደኛ ጉግ ማንጉግ ራሱ የትግራይ ወያኔ/ህወሃት ነው። ህወሃትንም አቅፎና ደግፎ የያዘው ‘ወርቅ ህዝብ’ ብሎ ‘ናዚስቱ መለስ ዜናዊ’ በትግራይ አደባባይ ያወደሰው “የትግራይ ህዝብ” ነው። የአክሱም ሀውልት ለወላይታው ምኑ ነው? በማለት የተሳለቀውም የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር መሪ ራሱ ‘ናዚስቱ’ መለስ ነው።…
የኢትዮጵያ ህዝብ (ከተከዜ ወዲህ ያለው) ከትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር አገዛዝ ምን ተረፈው? ምንስ ጠብ አለለት? ‘ትግራይ’ ግን በኢትዮጵያ ትከሻና በአማራው ህዝብ ማንነት የተፈጥሮ ሀብትና በልጆቹ ደም ኪሳራ ወደ ‘ታላቋ ትግራይ ሪፑብሊክ’ እያመራች ነው!! ‘እነሆም ቤታቸውን በድቡሽት ላይ ይገነባሉ’ የተባለው ይፈፀም ዘንድ!! ይህን የማታምን ካለህ ነሀሴ 18/2009 ዓ/ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀኑ የ7 ሰዐት ዜናው ላይ ያቀረበውን ከትግራይ ተነስቶ በጎንደር ጀርባ ቁልቁል ቆርጦ እስከ ቤንሻንጉል ጉሙዝ የወረደውን የህወሃቷን አዲሲቷን ትግራይ ካርታ ረዥምና ሰፊ ኮሪደር /ወሽመጥ/ ተመልከት። የኢትዮጵያ ህዝብ በአንጡራ ላቡ ብቻ ሳይሆን ከቀን ገቢውም እየተገፈፈ የሚገነባው “የህዳሴ ግድብ”ም በአዲሲቷ ትግራይ ካርታ የተጠቃለለ ወይም የሚያጠቃልል ንድፍ ያለው መሆኑንም አስተውል። ኢቢሲ ዘግየት ብሎ በዚያው ቀን በድረገፁ (በቴሌቪዥን መስኮት አለመሆኑንም ልብ በል) ‘በስህተት የቀረበ ካርታ ነው’ በማለት ‘ይቅርታ’ መጠየቁንም አጢንና ከዚህ ሁሉ ድራማ ተነስተህ ለራስህ ጥያቄ ደርድር፤ ከፊት ለፊትህ የተቆለለው መልስ ሊያሳብድህ ቢችልም።
በትግራይና ከተከዜ በታች ባለው ሀገርና ህዝብ መካከል ልዩነት የለም የምትል ካለህ እንደራስ ዳሽን ከገዘፈው ዘርፈ ብዙ ልዩነት መኻል አንዲቷን ቋጥኝ ልዩነት እንካ፤ ቤተ መንግሥት የሌለው የኢትዮጵያ ህዝብ የፍቅር ንጉሥ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ኢትዮጵያ” በሚል የሰየመውን አልበም ለህዝብ በማቅረብ አዲሱን ዓመት 2010ን ከህዝብ ጋር ለመቀበል የሚለኒየም አዳራሽ ዝግጅት በአፓርታይዱ ህወሃት አገዛዝ ሲከለከልና የሒልተኑን ዝግጅት ደግሞ ወታደር በማሰማራት ሲታገድ ሰሜን በሚገኘው የህወሃት ሀገር /ትግራይ/ ለትግሪኛ ዘፋኟ ኤደን ገብረሥላሴ አልበም ምርቃት በትግራይ መንግሥት አማካይነት መቀሌ ላይ የተካሄደውን አስደማሚ ትዕይንት ተመልከት። በህወሃት አፓርታይዳዊ ቅኝ አገዛዝ ለመውደቅህ ዛሬም ድረስ ለማታምን ዓይን ካለህ አይተህ እመን! በውስጥህ የቀረ እንጥፍጣፊ ኢትዮጵያዊ ሀሞትና ሀገራዊ ሰብዕና ካለህም – ተቆጭ፤ ተበሳጭ፤ ተማረር፤ ተቆጣ፤ በቃኝ እንድትል በቃ በል! (* ተጨማሪ መረጃዎች በቅኝቱ መገባደጃ ይገኛሉ።)
እንዲህ ያለ አምባገነናዊነትንና የህዝብ ንቀትን (ከተከዜ በታች በሚኖረው ህዝብ ላይ) እስከዚህ ዘመን ድረስ (ከ1983ዓ/ም እስከ 2010 ዓ/ም) ያለገደብና ለከት የሚያካሂደው ህወሃትና መሪዎቹ ናቸው። ከአንድ ‘የሀገር መሪ’ የማይጠበቅ ህዝብን ከህዝብ ማቃቃርንና ልዩነትን ማራገብን ሲያበረታና ሲያናፍስ የኖረው ራሱ ህወሃትና መሪዎቹ ናቸው። ይህንን አሌ የሚል የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ካለ እርሱ ከዕውነት ጋር የተላተመ ልበ-ወያኔ ነው።
በትግራይ ምድር ከቅኝ ገዢዎችና ምንደኞቻቸው ጋር ስለ ትግራይ አጥንቱን የከሰከሰው ደሙን ያፈሰሰው የኢትዮጵያ ህዝብ (ከተከዜ በታች ያለው) በትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር /በህወሃት/ ተካደ እንጂ ‘አድዋን’ አልካደም!!! በህወሃት የታሪካዊቷ አክሱም ባለቤትነቱን ተካደ እንጂ አክሱምን አልካደም!! በደምና በአጥንቱ ባቆማት የገዛ ሀገሩ ኢትዮጵያ ‘የሀገር በቀል ኮሎኒያሊስቶች’ ምርኮኛ ሆነ እንጂ እስካሁን በትግራይ ወንበዴዎች ላይ የበቀል ነበልባላዊ አፀፋውን አልመለሰም። ጣልያንን የወቃ ክንድ ገና አልተነሳም። ወዮ ወደዚህ እየገፉት ለሚገኙት ወያኔዎች ሁሉ! እስካሁን በትዕግሥት የታጠፈው ክንድ የተነሳ ዕለት መጪውን ቁጣ ‘እግዚኦታም’ አይመልሰውምና!
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና መሰል ኢህአዴጋውያን መቀሌ ላይ ህወሃት ከበሮ እየከበረና ብር ሃይለማርያም ኮሌታ ላይ እየሰካ ቢያስጨፍራቸው፤ ብአዴናውያን ወኦህዴዳውያን ወዴህዴጋውያን የህወሃት ድራማ ተዋንያን በመሆናቸው እንጂ በኢትዮጵያዊነታቸው አይደለም። ኢትዮጵያን የሚሉ ኢትዮጵያውያንማ በመላው ሀገሪቱ በእስር ቤቶች ታጉረው የስቃይ ሙከራና መከራ ይካሄድባቸዋል፤ ከሀገር ተሰደዋል ወይም በሀገር ውስጥ በደመ ነፍስ ወጥተው የሚገቡትም በፀጥታና በአፋኝ ማፍያዎች ቁጥጥር ስር ናቸው። መሬት ላይ ያለው ዕውነት ይህና ይህ ብቻ ነው። በትግራይና ከተከዜ በታች በሚገኘው ኢትዮጵያዊ መካከል የተቆፈረው አፓርታይዳዊ ገደል በሁለቱ አካባቢ ህዝቦች መኻል እያስከተለ ያለው ጥልቅ መዘዝ የማያሳስበው የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ካለ ከጭምብሉ ይወጣ ዘንድና መላም ያፈላልግ ዘንድ ወቅቱ አሁን ነው። እነሆ ጆሮ ያለው ይስማ!!
እነሆ ሀቅ እንፅፋለን እነሆም ሀቅ እናወጣለን። እንደ ነመራ ገመቹ እንደ ቢሰጥ ታረቀኝ እንደ ከድር የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን ወደፊት ከትግራይ ምድር ለሚነሳ ጦርነት በሀገር ፍቅር ወኔ ተነሳስተው ትግራይን ለማዳን ስለ ትግራይ የሚያፈሱት ደም ስለ ትግራይ የሚከሰክሱት አጥንት ይኖራልን?! የህወሃት አፓርታይድ አገዛዝ ባስከተለው ሀገራዊ ቀውስና መዘዝ በዚህ ትውልድ ሥነ ልቡና ውስጥ ይህ እየሆነ ስለመሆኑ የማያስብና ይህም እንቅልፍ የማይነሳው የትግራይ ‘ሀገር ወዳድ’ ካለ ፀሀይ ከመጥለቋ በፊት ይንቃ፤ መሮጥም ይጀምር።
አንባቢ ሆይ ልብ በል! በእኛ በኩል ትግራይ የኢትዮጵያ የትግራይ ህዝብም ኢትዮጵያዊ አልነበረም/አይደለም አላልንም። በፃፍነውና ባልፃፍነው መካከል ያለውን ጥልቅ ተገንዘብ!! ህወሃትና ህወሃታውያን በፃፍነውና ባልፃፍነው መኻል የሚያስነሱት አዋራ እይታህን እንዳይጋርደው ተጠንቀቅ። እነሆ ቅኝታችን ይቀጥላል። ነመራ ገመቹ – ኢጆሌ ኦሮሞ – በተሰለፈበት በአሰብ ቡሬ ግንባር ጣምራ ቁስል በስፋት ካወረደው ታሪክ ቀጣዩን ነቅሰናል።
ነመራ በቡሬ ግንባር በተዋጋባቸው በእነኛ ስድስት ወራት ጠላት በሰነዘራቸው ሶስት መጠነ ሰፊ የማጥቃት ውጊያዎች እንዲሁም በመከላከልና መልሶ ማጥቃት አኩሪ ውጤት ካስመዘገቡት ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ሆነ።
በተለይም ጠላት ሶስተኛውን ዙር ጥቃት የሰነዘረባት ዕለት ለነመራ ልዩ ነበረች። ጥቃቱ ሲሰነዘር በአዛዡ በኮሎኔል ዳዲ ብሩ ትዕዛዝ ወደ አሰብ ከሚወስደው መንገድ በስተግራ ባለች ጉብታ ስር ሃምሳ ወታደሮችን እየመራ በቆረጣ ስልት ከጠላት ጀርባ ገብቶ ለወሬ ነጋሪ እንዳይተርፉ አድርጓቸዋል – ወደ ጠላትነት የተለወጡትን የትላንት ወንድሞቹን።
የነመራ ወኔ ልዩ ነበር፤ ተኝቶ መተኮስ ብሎ ነገር አይገባውም። እንደ ፍርሃትም ይቆጥረዋል። አንዳንዴ ቆሞ አንዳንዴ በርከክ ብሎ “ኢጆሌ ወለጋ!” እያለ መትረየሱን አንዷንዷው። የቀኝ ትከሻው የመትረየሱን ሰደፍ ተደግፎ ብቻውን እንደ ወሎ ዳንኪረኛ ሲርገበገብ ልዩ ትዕይንት ነበር።
የዚያን ዕለት ጦርነት በቀላሉ አልበረደም – በሁለቱም ወገን የፈላው የአንድ እናት ልጆች ደም ነበርና። ለአራት ሰዐታትም ምድር ቀውጢ ሆነች። ፈንጂው ዘነበ። ጥይቱ ተርከፈከፈ። ወጣቶችና አዛውንቶች ተረፈረፉ – በአጭር ከተቀጩ ረጃጅም ህልሞቻቸው ጋር። ቀስ በቀስም ከጠላት በኩል የሚመጣው የቀላልና የከባድ መሳሪያ ተኩሶች ነጠፉ፤ ፀጥታም ሆነ።
እነሆ በጣምራ ቁስል ከተተረኩት ዘግናኝ አውደ ውጊያዎች መኻል ለማሳያነት በነቀስነው (ወደፊትም ከሌሎች አውደ ውጊያዎች የተወሰኑ እንነቅሳለን) ጥቂት አንቀፅ እኒያ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችና አዛውንቶች ህይወት በአራት ሰዐታት መቅሰፍታዊ ውጊያ ከነህልሞቻቸውና ተስፋዎቻቸው ጋር መክነው ይታየናል – በእዝነ ህሊናችን። የባሩዱ ነጎድጓድ የባዙቃው ፍንዳታ የመትረየሱ መንጣጣት የጄቶቹ ማጓራትና የሚያወርዱት እቶን እሳተ ሲያበቃና የአእላፍ ወጣቶች ህይወት ሲያሸልብ – እነሆ በስፍራው ፀጥታም ሰፈነ – ይላል ተራኪው ዘፉኛን ቢራ።
አዎ ፀጥታው ያፍነናል። አዎ የእኒያ ሁሉ ወጣቶችና አባት ወታደሮች ሩቅ ህልም በአጭር ሲቀጭና ሲመክን ይታየናል። ወንድማችን አጎታችን አባታችን ጓደኛችን ጎረቤታችን ያንን – የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር አገዛዝን – የድረሱልኝ ጥሪ ተቀብለው ‘ለወገን ደራሽ ወገን ነው’ ብለው ወያኔ ብቻ የሚያስተዳድራትን ትግራይ ከመሰል አካሉና ከዓላማና ግብ ወንድሙ ከሻዕቢያ የበቀል መንጋጋ ለመታደግ የከፈሉት መሥዋዕትነት የማታ ማታ በሻዕቢያ ግማሽ አካል በህወሃታውያኑ በእነ መለስ ዜናዊ ድውይ ተልዕኮ ‘ሁሉ ከንቱ’ እንዲል መፅሀፉ እነሆ ፍሬ የለሽ ከንቱ መሥዋዕትነት ሆኗል። ብርቱውን ፀፀታችንን፤ እስከ ዛሬም ያልወጣልንን በሀገር ፍቅር መሥዋዕትነታችን ህወሃት የነገደብንን የቁጭት ረመጥ – ጣምራ ቁስል – የቀሰቀሰብንን በዚሁ እንግታና ደግሞ ወደ ሌላ የተዳፈነ ረመጥ አቀጣጣይ አውደ ውጊያ እና ትዕይንት እናዝግም ፤ እንዴ ፈርዶብናላ!!
ነመራ ቡሬ በገባ በሰባት ወሩ ኮሎኔል ዳዲ የሚመሩት ጦር ከበላይ በተሰጠ ትዕዛዝ ወደ ባድመ ግንባር እንዲንቀሳቀሱ ተነገራቸው – ነመራና ጓደኞቹን ያላስደሰተ ትዕዛዝ። እንደነሱ ፍላጎት ድንበር ተብሎ በርቀት የሚታየውን መስመር የለሽ መሬት በርግደው ቢሄዱ በወደዱ። ፍላጎታቸው የአሉላም ፈረስና የአሊሚራህ ግመል ቀይ ባህር ላይ ሲጠጡ ወይም አሁን 12 ኪ.ሜ. ሰርቀው 66 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የቸከሉትን ‘የኤርትራ መንግሥት ግዛት’ የሚለውን ምልክት ቢያንስ በንጉሡም ሆነ በደርጉ ጊዜ በነበረበት ቦታ 54 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ባለችው ሊሾ ጉድጓድ ውስጥ መልሶ መትከል ነበር። ነመራ በልቡ እያዘነ የቡሬን ምሽግ ለተተኪዎቹ አስረክቦ…ዳግም ዑራል መኪናው ላይ ተሳፈረ።
እነሆ ሸፍጥ፤ እነሆ ዳግም ክህደት! የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ሾፌር በቀለኛው መለስ ዜናዊና በአምሳያው የተፈጠረው የሻዕቢያው ኢሳይያስ አፈወርቂ በቤተሰባዊ ጠብ ትግራይ ላይ ቢራኮቱ ‘ሀገራዊ ስዕል ተነድፎለት’ – በኤርትራ ተወረርን – በሚል የተሰራው ፕሮፓጋንዳና እንቢልታ እውነት መስሎት ‘ትግራይን’ ሊታደግ የዘመተው የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ከ1983 ዓ/ም ጀምሮ ከተከዜ በታች ያደረሰበትን ሰቆቃና ሀገር ማፍረስ ረስቶት ሳይሆን “ይቅር’ ብሎና በደሙ ያጣውንም ሊያስተካክል/ሊያስመልስ ቡሬን ተሻግሮ አሰብ ሊዘልቅ ቢያኮበኩብ ጊዜ – መለስና ግብረበላዎቹ ተረብሸው የነኮሎኔል ዳዲን ጦር አነሱት፤ አሰብን ከመያዝ ኢላማው አጨናገፉት፤ ያን ሁሉ በቡሬ መስመር የተከፈለውን መስዋዕትነት አመከኑት፤ ደሙንም ደመ ከልብ አደረጉት። የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ግፍ መቆሚያ አልነበረውምና! ዛሬም ድረስ የለውምና! እንመለስ ወደ ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ ታሪካዊ ትርክት።
የኮሎኔል ዳዲ ጦር ባድመ በገባ በአስራ አንደኛ ወሩ፤ ሰኔ ወር መጀመሪያ በውድቅት ሌሊት የ”ዘመቻ ፀሀይ ግባት” መጠነ ሰፊ የማጥቃት ዘመቻውን በሶስት ግንባሮች ከፈተ፤ – ሲል ይጀምራል ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ በሰፊው የባድመ ግንባር ትረካው። በዚህ ግንባር ስለተካሄደው አሰቃቂ ጦርነትና እልቂት፤ በአውደ ውጊያው ላይ ስለወደቁት የኢትዮጵያ ልጆች የልበ ሙሉነትና የጀግንነት ውሎ፤ ስለ አዝማቹ ኮሎኔል ዳዲ ብሩ፤ ‘የደርግ ጦር” ብለው ሻዕቢያና ወያኔ የበተኑትን የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር በጭንቅና በፍርሃት ምጥ በተወጠረ ጊዜ “አድኑኝ” ለሚለው ጥሪው ‘የወገን ደራሽ’ ሆነው ስለተሰለፉት አየር ወለዶችና አዛዣቸው ብርጌዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያም (እኒህ ጄኔራል ማዕረጋቸውን በሽፍቶቹ አይደለም ያገኙት)፤ በቀውጢው ወቅት ወያኔ በባዶ ጉራው ‘ደርግን የገረሰሰ ብሶት የወለደው ሰራዊት’ የሚለው የሽፍቶች ስብስብ እንኳን ሊያድነው ከነመኖሩም በጠፋበት ሰዐት ከተከዜ በታች ያለው ሀይል ወደ ትግራይ ተምሞ በባድመ የከፈለውን የመስዋዕትነት ጣራ፤ ከወደቀበት ያንሰራራው የቀድሞው “የኢትዮጵያ አየር ሀይል” ስላደረገው አስደማሚና አኩሪ ጀብዱ…ለታሪክና ለትውልድ ሰነድ ይሆን ዘንድ መልካም አድርጎ ተርኮታል፤ ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ። የእኛ ተልዕኮ ቅኝት ነውና ዝርዝር ታሪኩን ለመፅሀፉ አንባቢ ትተን ለወፍ በረር ምልከታችን የነቀስናቸውን እናስከትላለንና እንግዲህ አንባቢ ሆይ በርታ!
የባድመ የጦር ቀጠና ለተከታታይ ሶስት ቀናት አልፎ አልፎ ከሚሰማው የቦንብ ፍንዳታና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ድምፅ በስተቀር ፀጥ ብሏል። የአዛዣቸው እንዲሁም የብዙ ወንድሞቻቸው ሞት ሀዘን ከአእምሯቸው ያልወጣው ነመራና ጓደኞቹ መሳሪያቸውን ወልውለው ጥይት አሟልተው ቀጣዩን ግዳጅ ይጠባበቃሉ።
ብዙም አልቆየ። ዳግም የመድፎች ላንቃዎች ተከፈቱ። ባዙቃው፤ መትረየሱ በተራሮቹ ላይ ያስካካ ጀመር። ግማሽ ቀን ከፈጀ እልህ አስጨራሽ ጦርነት በሁዋላ በአየር ሃይል ከፍተኛ ድብደባ ጠላት ወደመጣበት ማፈግፈግ ሲጀምር ሌ/ኮ ፍፁም ‘ዱካውን እየተከተልክ በለው። እጁን በሰላም የሰጠ ወይም ነጭ ባንዲራ ያውለበለበን ግን አትንካው’ የሚል ትዕዛዝ አስተላለፉ። ጦሩም የሚሸሸውን ጦር እየተከተለ ሲያርበደብድ ተቆርጦ የቀረ የጠላት ጦር ነመራንና ጓደኞቹን አላራምድ አላቸው። በዚህ ጊዜ ነው ያልተጠበቀው የሆነው። የወለጋው ጎበዝ፤ የቡሬ ጥይት ያልደፈረው ነመራ ድንገት በከፍተኛ ድምፅ “ኢጆሌ…” ብሎ ሳይጨርስ ከነበረበት ቦታ ቁልቁል ተሸበለለ። ከቀኝ እጁና እግሩ እንዲሁም ከሆዱ አካባቢ ደሙ ይንዠቀዠቅ ጀመር…
አዎ፤ ኢጆሌ ወላጋ – ነመራ ገመቹ – ትግራይን ሲታደግ ወደቀ፤ ግን አልሞተም። ከቡሬ እስከ ባድመ ያልተለዩት ሶስቱ ቆራጥ ተዋጊዎች ጓደኞቹ ነመራን ለማትረፍ ሲረባረቡ ቢሰጥ ታረቀኝ ነመራ ደረት ላይ አሸለበ። ተክላይና ከድር እግሮቹ ላይ ወድቀው እስከወዲያኛው አንቀላፉ። ህይወት ከጦርነቱም ለባሰ ሰቆቃ ያጨችው ነመራ ገመቹ በዑራል መኪና ተጭኖ ወደ ሌላኛው የሲኦል ምዕራፍ ይገባ ዘንድ ህይወቱ እንድትተርፍ ለህክምና ተወሰደ። በዚህ ፍትህና ግብ አልባ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ህይወታቸው ከነህልምቸው ተቀጥፏል። ወደር የሌለው የሀገር ንብረት ከስሯል።
የሻእቢያ ስም ሲነሳ የሚርበተበተው የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጨ ግንባር /ህወሃት/ ‘ብሶት የወለደውን የኢህአዴግ ሰራዊት’ ወይም ‘ተራራ ያንቀጠቀጠ’ የሚለውን ብኩን የጦር ስብስብ ይዞ ሻእቢያን በገጠመና ጀግንነቱ በታየ ነበር። ግን አልሞከረውም። ጉራ ብቻ!! ምክንያቱም ሻዕቢያ ህወሃትን አርባ ገርፎና ጫማውን አሰወልቆ ከትግራይ ምድር ያባርረው ነበርና! ይህንን አሳምሮ የሚያውቀው ግማሽ ኤርትራዊው መለስ ዜናዊ በውጊያ ሳይሆን ‘አውቆ’ የተሸነፈለትንና ‘የደርግ ሠራዊት’ ብሎ የበተነውን የኢትዮጵያን ሠራዊትና ‘መዳብ ወይ ነሀስ’ አድርጎ የሚቆጥረውን የተከዜ በታች የኢትዮጵያ ህዝብ ‘ሀገርህ በጠላት ተወራለችና ድረስ’ ሲል ተማፀነ። ‘ተራራ ያንቀጠቀጠ ትውልድ’ ብሎ ፉከራ የለ! ‘ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሠራዊት’ እያሉ እሽኮለሌ የለ – የግንቦት 20 ጀግኖች እያሉ ቱሪናፋ የለ – ድርሱልን ብቻ!! እባካችሁ ትግራይን አድኑልን ብቻ!!
እነሆ ‘ናዚስቱ’ መለስ የሚጠላውንና ለአመታት ያገደውን የሀገር ፍቅር ቅስቀሳን፤ የኢትዮጵያዊነትን እቶን የሚያፈነዳውን የአበውን የጀግንነትን ታሪክ ቀረርቶና ሽለላን በየመገናኛው ብዙሃን ቀኑን ሙሉ ይሰማ ዘንድ ከታገተበት አስለቀቀ። እነሆም የሀገር ጉዳይ መስሎት ሻዕቢያን ቀጥቶ ሌላው ቢቀር በግፍ ‘የተሸጠውን’ የአሰብ ወደብም አስመልሳለሁ ብሎ የተመመው የኢትዮጵያ ሠራዊትና ህዝብ በደምና በአጥንቱ ትግራይን ከሻዕቢያ በቀል አዳነ። አሰብን የማስመለስ ህልምና ዓላማው ግን መከነ።
የጨለማው ዘመን ገዢ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ያንን ሁሉ ውለታና መታደግ ክዶ ከድል በሁዋላ ከተከዜ መለስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በበታችነት የበቀል ስሜት ዘመተ። በፋሽስቱ ሙሶሎኒ ጥቁር ለባሽ ጨፍጫፊዎች አምሳል የፈጠረውንና ያሰየጠነውን በዋናነት ‘ከወርቅ ዘር’ ብቻ የተዋቀረውን ወደር የለሽ ጨከኙን አጋዚን ሠራዊት አሰማራ። እነሆ ትንሽነቱ እያባነነው ከተከዜ በታች ያለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዝብ ያዋርዳል፤ እናቶችን ማቅ ያስለብሳል፤ ወጣቶችን ለሰቆቃ ይዳርጋል፤ በየእስር ቤቶቹ ‘ከወርቅ ዘር’ ብቻ የተመለመሉ እርጉምና ጨካኝ ፍጡራንን አሰማርቶ ወንድ ከሴት ሳይሉ አውሬያዊ ርኩሰት እየፈፀሙ በሰው ልጅ ስቃይና ዋይታ ሲዝናኑ ውለው ሲዝናኑ ያድራሉ።
ለዚህ ሁሉ ግፍና ኢሰብዓዊነት በራሱ አምሳያ የፈለፈላቸው ታዛዦቹና አፋሽ አጎንባሾቹ የአማራው ብአዴን፤ የኦሮሞው ኦህዴድ፤ የደቡቡ ደህዴግ/ን/ ደግሞ እንደ ሶስት ጉልቻ ተሸክመውት ‘ካንተ በፊት ያስቀድመን’ እያሉ የግፉ ሁሉ ተባባሪ ሆነው ይገኛሉ። የትግራይ ነፃ አውጪ እንደ ሸንኮራ እየመጠጠ ሲጥላቸው እያዩም እግሩ ስር ከመንከባለልና ፍርፋሪ ከመቃረም አልታቀቡም። እኒህን ሶስት ጉልቻዎች ማሽመድመድና ማንኮታኮት ጊዜው የሚጠይቀው ዐቢይ ተልዕኮ ሆኗል። የጉልቻዎቹ መፍረስ የህወሃት ግብዐተ መሬት ዋዜማ ነውና።
በቀድሞ ዘመን የኖሩት አብናቶቻችን ለጣሊያን ያደሩ ምንደኞች እያስጠቁ ቢያስቸግሯቸው <ጠላትማ ምንግዜም ጠላት ነው/ አስቀድሞ ማጥፋት አሾክሿኪውን ነው> ብለው ነበር። እኛም በዘመናችን እንላለን፤ ወያኔማ ምንግዜም ጠላት ነው/ አስቀድሞ መምታት ሶስቱን ጉልቻ ነው። ወዮ ለናንተ! የተባለው ለእኒህ አከርካሪ የለሽ – ብአዴን ኦህዴድና ደህዴግ – አስጠቂዎች ሳይሆን ይቀራል? አዎ፤ ወዮ ለ እናንተ ሆድ አደሮች!!
ሶስቱን የህወሃት መቀመጫ ጉልቾች በዋናነት ጠቀስን እንጂ ወያኔ የሚያዘው የሶማሊያ ክልል ልዩ ፖሊስ የአጋዚ ሌላው ክንድ እየሆነ በመምጣቱ በብዙ የኦሮሞ ልጆች ህፃናት አረጋውያንና ሴቶች ሰቆቃና ደም እጁ እየተበከለ ይገኛል። የአጋዚው የሶማሊ ክንፍ ልዩ ሀይል ፍጅቱን የሚያካሂደው በኦሮሞና በሌሎች ብሄረሰቦች ላይም ነው።…ይህን ቅኝት በምናዘጋጅበት ወቅት በሐረርጌ የተለያዩ ወረዳዎች፤ በሜኢሶ በጭናቅሰንና በጉርሱም ፉኛን ቢራ ከተማ ላይ የህወሃት አጋዚ ክንፍ የሶማሌ ልዩ ሃይል ይፋ ጦርነት ከፍቶ አያሌ ሰላማዊ ህዝብ ፈጅቷል፤ አፈናቅሏል…ከዚህም በተጨማሪ ይኸው መቀመጫውን ጅጅጋ ባደረገው ወያኔያዊው አሊ አብዶ የሚመራው የሶማሊያ ዞን መንግሥት በአጋዚ ጄኔራሎች እየታዘዘና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እየታገዘ ጦርነቱን በማስፋፋት በባሌና በቦረና ዞኖች በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ እጅግ በርካታ ህዝብ ፈጅቷል። ይህ ሁሉ እልቂትና ውርጅብኝ በነሀሴ ወር 2009 ዓ/ም በኦሮሚያ የተካሄደውን የሶስት ቀናት ከቤት ያለመውጣት ሠላማዊ ህዝባዊ ተቃውሞ ለመበቀል ወያኔ የወሰደው አካይስታዊ እርምጃ ነው። (ተጨማሪ መረጃ በቅኝቱ መገባደጃ ላይ ይገኛል)
ግፈኛው ወያኔ የተማሩና አንቱ የተባሉ የሀገር አድባራትን – የሥርዐቱን ግፍ በመቃወማቸው ብቻ – እንደ ተራ ወንጀለኛ የፊጥኝ አስሮና መሳሪያ ደግኖ በአደባባይ በማሳየት የህዝብን ሞራል ለመስበር ይውተረተራል። (አብነት የፈለገ የዶ/ር መራራ ጉዲናን እና የከፍተኛ ትምህርት መምህሩን የበቀለ ገርባን እና የዶ/ር ፍቅሩ ማሩን የፍርድ ቤት ጉዞ ይመልከት)።
የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ‘የወርቅ ዘር ዜጎቹን’ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የበላይነት ‘ናዚስታዊ’ በሆነ ስሌት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ አንሰራፍቷል፤ ብዙዎቹም በፀጋ ተቀብለውታል – ‘ወርቅ ዘር ገዢነታቸውን’!! ወያኔ የሀገር ንብረት በገፍና በግፍ ይዘርፋል ያዘርፋል። ዕብሪትና መታበዩ ቅጥ አጥቷል። ይህ በላዔሰብ ድርጅት – ህወሃት – ለትውልድ የሚተላለፍ፤ ከሁሉምና ከምንም በላይ ግን የትግራይን ህዝብና ትግራይን ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚነጥልና የሚያፋጅ አሜኬላ ዘርቷል። የዘራው አሜኬላ ግን እራሱን ይወጋዋል። የትግራይ ህዝብ ሆይ፤ ስለመፃዒው ህልውናህና ስለልጆችህም ስትል ሰከን ብለህ አስብ!! ነገ ሌላ ቀን ነው። አንተ ደሴት ነህ። ውቅያኖሱ ሠላም አይደለም። ማዕበሉ እያስገመገመ ነው።…ልብ ያለው ልብ ይበል!!
ኮሎኔል ዳዲ ብሩ፤
ጣምራ ቁስል የዚያ “የደርግ ሠራዊት” ተብሎ ርኩስ የበቀልና የዘር ዓላማ ይዘው በተነሱት በሻዕቢያ በህወሃትና በኦነግ የተበተነውና መጠነ ሰፊ ግፍ የተፈፀመበት ሠራዊታችንም ታሪክ ነው። ያ! በምሥራቅ አፍሪካና ከዛም ወዲያ ባሉት ሀገራት በጥንካሬውና በብቃቱ የሚያስተማምን ሠራዊት የተባለለት በዓለም አቀፍ ፀረ ኢትዮጵያ የሻዕቢያ የህወሃትና የኦነግ አዛዦች በተቀነባበረ ሴራና ርብርብ (ደርግ ከሩሲያ ጋር ባለው ግንኙነትም ምክንያት) በውስጥ ምንደኞችና በውጪ ጠላቶች ርብርቦሽ ተገዝግዞና ተሸርሽሮ ከአውደ ውጊያው “በቃህ’ ተብሎና እሱም “በቃኝ” ብሎ መሳሪያውን ሲያስቀምጥ የደረሰበትን ውርደት እንግልትና ፍጅት ታሪክና ትውልድ መቼም ቢሆን የሚረሳው አይደለም።
ኢትዮጵያ ከ1920ዎቹ ጀምሮ ለስልሳ ዓመት ገደማ መጠነ ሰፊ ወጪ አውጥታበትና ደክማ በወታደራዊና አካዳሚያዊ ዕውቀት በታነፁና ለዚህም ተግባር በተደራጁ ወታደራዊ ተቋማት ስትገነባው የኖረችውን የአየር ሃይል፤ የባህር ሃይል፤ የምድር ጦርና የፖለስ ሠራዊትን – በአጭሩ ከመላው ሀገሪቱ ተውጣጥቶ የተገነባውን የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ነበር – በቀንደኛነት ሻዕቢያና ህወሃት በአጃቢነትና ተባባሪነት ደግሞ ኦነግ “የደርግ ሠራዊት” በሚል ፀረ ኢትዮጵያ ተልዕኮ በ1983 ዓ/ም የበተኑት። እኒህ እኩይ ድርጅቶች በሀገርና በወገን ላይ ያዘነቡት ፍዳና ያስከተሉት ጥፋት ተዘርዝሮ አያልቅምና ወደ ነቁጣችን እንመለስ።
እነሆ በአስራዘጠኝ ዘጠናዎቹ በቡሬና በባድመ መስመር በተካሄደው ውጊያ ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ የዚያ “የደርግ ሠራዊት” የተባለው ጦር አካለት ያደረጉትን የተለያዩ አስደናቂ ገድሎች ለቃል አቀባዩ /ደራሲው/ ተርኮለታል። ታሪካቸው ወኔን ያጋሽባል፤ ግለ ህይወታቸው ደግሞ በሀዘን ይጨብጣል፤ ውስጥን ይረብሻል። እነሆ እኛም የቅኝታችን ታዳሚ እኒህን ብርቅዬ የቀድሞ ሠራዊት ጀግኖቻችንን በክቡር ስራቸውና በማንረሳው መስዋዕትነታቸው ታውቃቸውና ትዘክራቸው ዘንዳ ጥቂት ነቅሰናልና ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራን እያመሰገንክ ተቀበለን።
በሰማይ ደግሞ ሚግ 23 እና ኤስ.ዩ 27 የጦር አውሮፕላኖች አፋቸውን እንደ ንብ አሹለው ከምድር የሚላተሙ ይመስል ቁልቁል እየተወረወሩና ሽቅብ እየከነፉ የቦንብ ዶፋቸውን አዘነቡት።
ሰማይን ተቆጣጥረው ሲፈልጉ ቀይ ባህር ሲሻቸው አሰብ ወደብ ላይ አንባርቀው ዳግም የቡሬ ምሽግ ላይ ድፍት ይሉ የነበሩት በ1983 ዓ/ም ወታደራዊው መንግሥት ሲወድቅ ዘብጥያ ተወርውረው የትም ተጥለው በጅምላ የተፈረደባቸው የሰማዩ ንስሮች ነበሩ።
ሆኖም የጭንቁ ቀን መጣ። እነኛ ባጎረሱት የተነከሱት የኢትዮጵያ ልጆች በባትሪ ከየቦታው ተፈልገው እንደገና የአገር ድንበር ለመጠበቅ ተመሙ። ምሽግ ደርማሽ እየተባሉ በሚጠሩት ሄሊኮፕተሮች ተኩሱን ሲያንጣጡት ጠላት ቁስለኞችን ሳያነሳ እግሬ አውጪኝ ይል ገባ።
አንባቢ ሆይ! ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ በተረከልን ውስጥ ፈጦ የሚታየን ያልተረከልንና ህሊናችን በደመ ነፍስ ወይም በስድስተኛው ህዋስ የሚነግረን ግዘፍ የነሳ የተበተነው የአየር ሃይላችን ህያው ታሪክ አለ። እዚያ ውስጥ ቃኚው ይገባ ዘንድ አቅም የለውም። ያ! በቡሬና በባድመ መስመር የተሰለፈው ከዘብጥያ /እስር ቤት/ የዘመተው የኢትዮጵያችንን አየር ሃይል ሠራዊት ብኩኑ የወያኔ ‘ብሶት የወለደው ሠራዊት’ም ሆነ ወይም ሻዕቢያ ያሰለፈው ሀይል ወይም ሁለቱን አጅቦ የገባው ኦነግ በ1983 ዓ/ም አዲስ አበባ የዘለቁት በውጊያ ብቃት አሸንፈውት እንዳልሆነ ይህ ትረካ በራሱ ምስክርነቱን ይሰጣል። ይህንን በዚሁ እናብቃ። ጣምራ ቁስል ስለ ኮሎኔል ዳዲ ብሩ የውጊያ ውሎና ግለ ታሪክ በስፋት አውርዷል።
በዚህ የኮሎኔል ዳዲ ታሪክ ውስጥ ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ አያሌ የኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ጀግኖችን አንስቷል። ከኢትዮጵያ ብርቅዬ ጄኔራሎች ለምሳሌ እነ ህወሃትና ሻዕቢያ የበተኑትን አየር ወለድ እንደገና አሰባስበው በባድመ ግንባር ምድር አንቀጥቃጭ ጀብድ ስላስፈፀሙት ብርጌዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም የውጊያ ውሎዎች፤ ከሰነበተው ታሪክ ደግሞ በሀረርጌ ከካራማራ ቀብሬደሃር ቆራሄ… ከሶማሊያ ወራሪ ጋር ስለተደረጉ ውጊያዎች፤ በኤርትራ ከረን ናቅፋ አቆርዳት… ስለነበረው አውደ ውጊያ ስለነጄኔራል አብዱላሂ፤ ስለነኮሎኔል አበበ፤ ስለነኮሎኔል አርአያ…ደግሞም ስለኮሎኔል ፍሬሰናይ። ኮሎኔል ፍሬሰናይ ከእኒህ ስማቸው ከተጠቀሰ አዛዦች ጋር ሐረር በታዋቂው ወታደራዊ አካዳሚ አብሮ የተማረ የሰባተኛ ዙር ምሩቅ ነው፤ ይላል ተራኪው። ክንፈሚካኤል ከተረከው ቀጣዩን ያቀርቧል፤
ኮሎኔል ፍሬሰናይ ከኮሎኔል ዳዲና ከኮሎኔል አበበ ጋር የሶማሊያን ጦር ጠራርጎ ለማስወጣት በፈፋም ወንዝ፤ በዳለቻና ካራማራ ተራራ ላይ በተደረጉት ወሳኝ ውጊያዎች እንደ ጭላዳ ዝንዠሮ አቀበቱን ቧጥጠው፤ በቀበሮ ጉድጓድ ተኝተው ወታደራዊ ብቃታቸውን ያስመሰከሩ ናቸው ይባልላቸዋል። በወጣትነታቸው ዘመን በሐረር አካዳሚ ስልጠና ወቅትም ከኮሎኔል ዳዲ ጋር ልዩ ቀረቤታ ነበራቸው። በሚያገኟት የእረፍት ጊዜም አብረው የቡቴን ቡና ቤቶችን አተራምሰዋል። የጀጎልን ግንብ እየዘለሉ አንደኛ መንገድን መጋላ ጉዶን ሸዋበርን ከቀመሮና ከአመቱላ ጋር ተናፍሰውበታል።…የሐረርን ሀለዋ ዘይቱናና ግሽጣም ተካፍለው በልተዋል።…
ኤርትራዊው ኮሎኔል ፍሬሰናይና ኮሎኔል ዳዲ ብሩ በቀይ ኮኮብ ዘመቻ ወቅትም ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው በኤርትራ በረሃዎች ከሻዕቢያ ጋር ተዋግተዋል፤ ሻዕቢያ ‘ነፃነት’ ከማወጁ አንድ ወር በፊት ድረስ አብረው ነበሩ። የሁለቱ ኮሎኔሎች ቤተሰቦች አበልጃሞችም ናቸው።
እነሆ ከስምንት ዓመት ከአራት ወር በሁዋላ ኮሎኔል ዳዲ እና ኮሎኔል ፍሬሰናይ የሁለት ተቃራኒ ጦር አዛዦች ሆነው ቡሬ ግንባር ላይ ተገናኙ። አንዱ በጣዕር ላይ ያለ ተማራኪ ሌላው ማራኪ ሆኖ። በአንድ ባንዲራ ስር ለአንዲት ሉዐላዊት ኢትዮጵያ የተዋደቁት ኮሎኔል ዳዲና ኮሎኔል ፍሬሰናይ በሁለት ባንዲራ ስር በሁለት ወገን ተሰልፈው ተላለቁ። ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ ስለኮሎኔል ፍሬሰናይ ባወጋበት በረዥሙ አሳዛኝ ትረካው ፍፃሜ ላይ እንዲህ ይላል፤
ኮሎኔል ዳዲ ጣር ላይ ያሉ ወዳጃቸውን ራስ ደባበሱ። አባት ልጁን እንደሚደባብስ። “ውድ ወንድሜ” አሉ ኮሎኔል ዳዲ፤ “እውነት እውነት እልሃለሁ አሁንም ወንድሜ ነህ”። ኮሎኔል ፍሬሰናይ ገፅታ ላይ ጭል ጭል የምትል ፈገግታ ብልጭ አለች። ጥረት የጠየቀች ፈገግታ። የስቃይን ግድግዳ ደርምሳ የወጣች ፈገግታ። ጠላትነትን የረሳች ፈገግታ። በረጅሙ ተነፈሱም። “እኔም የምወድህ ወንድሜ ነህ…” …ልትጨልም ያለችውን ፈዛዛ ፈገግታ ገፅታቸው ላይ ለማቆየት እየጣሩ ነበር…አበቃ! አከተመ! የአንድ ዘመን ፍፃሜ።
ያቺ የደም ምድርም በሚከብድ ዝምታ ተዋጠች – የዕልቂት መሃል ዝምታ።
እነሆ ይህ ልብ ሰባሪ ትዕይንት የሆነው በጦርነቱ አውድማ ላይ ነበር። በኤርትራና በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ የስንትና ስንት መቶ ሺዎች ወይም ሚሊዮኖች ልብ እኩይ አላማና ግብ ባነገቡት ሻዕቢያና ወያኔ ተግባር ተሰብሯል? ስንትና ስንት ቤት ፈርሷል? ስንትና ስንት ቤተሰብ ተጠፋፍቷል?…ሀገር ይቁጠረው። ቤት ይቁጠርው።
እንግዲህ አንባቢ ሆይ የውስጥህን ሀዘን አስታግሰው፤ ቅኝታችን ይቀጥላልና። ሀዘንህም ይጨምራልና። እነሆ ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ የተረከውንና በጣምራ ቁስል ውስጥ በበርካታ ገፆች የወረደውን የኮሎኔል ዳዲ ብሩን ሙሉዕ ታሪክ ከመፅሀፉ ትኮመኩም ዘንዳ እየጋበዝን ለንዑስ ርእሳችን መቀንበቢያ ይሆን ዘንድ ከባድመ ግንባር ደግሞ የሚከተለውን (ያለ ቃኚው ጣልቃ ገብነት) ነቅሰናልና ብርታቱን ይስጥሽ/ብርታቱን ይስጥህ።
ከባድመ በስተግራ የሰፈረው ጦር ምሽግ ደርምሶ ወደ ባድመ ገስግሶ የኢትዮጵያን ባንዲራ ሰቅሏል። የማረከውን ማርኮ የተረፈውን ወደመጣበት ወደ መንደፈራና ባሬንቱ አቅጣጫ አባሮታል። ከድሉ በሁዋላ የሞተን መቅበር የቆሰለን መሰብሰብ ሥራ ተጀመረ።
ኮሎኔል ዳዲ የመጨረሻዋ ጥቃት በተፈፀመባት አሳቻ ስፍራ አምርተው ሟቹን ከቁስለኛው እየለዩ የሚቀብሩትን ወታደሮቻቸውን ሲያበረታቱ ስሜታቸው ተረበሸ። በአንድ ጉድጓድ ሊቀበሩ ከተሰበሰቡት ከመቶ በላይ የጠላት አስከሬኖች በርከት ያሉ የሴቶች አስከሬኖች ያሉበት ስፍራ ሲያገኙ የሰውነታቸው ስርዐት ተዛባ፤ አንጀታቸው ተላወሰ፤ ልባቸው ነጠረ፤ ዓይኖቻቸው ዳርቻም ረጠባቸው – የሴት ልጅ አባት ናቸውና። ወታደሮቹ ሁሉንም ደራርበው ሲጨርሱ አፈር ከማልበሳቸው በፊት ከላይ ካሉት የአንዷ አስከሬን የኮሎኔሉን ስሜት ሳበው።
ማንነቷን መለየት አስቸጋሪ ነበር። …ዕድሜዋ በግምት 18-19 ይሆናል።…ካሉበት ሆነው ለረጅም ጊዜ አፍጥጠው ቀሩ።…ኮሎኔል ዳዲ በርከክ አሉ። በደም የተለወሰውን ልብሷን ገለጥ አድርገው ቀበቶዋ ላይ በቀኝ ጎኗ በኩል የተሰካውን ኮዳ መያዣ ሸራ ተመለከቱ። ሳምባዎቻቸው አመፁ። የልባቸው አድራሻ ለአፍታም ቢሆን ጠፋ። በሁለት እጆቻቸው ፊታቸውን ግጥም አድርገው ያዙ። ቀና ለማለት ያስቸገራቸው ይመስል በተንበረከኩባት ስፍራ ይበልጡን ሰመጡ።…በሬሳው የኮዳ መያዣ ሸራ ላይ በጥቁር ቀለም ‘ሰመሐር ዳዲ ብሩ’ የሚል ፅሁፍ ነበር።
ኮሎኔል ዳዲ ሽቅብ አንጋጠጡ። “ምነው ፈጣሪዬ ምን አደረግሁህ! ምን በደልኩህ?” ሲሉ ፈጣሪን ሞገቱት።…እንባቸው በሁለት ጉንጫቸው ይንዠቀዠቅ ነበር። ዙሪያቸውን ተመለከቱ። ምንም ያልሆኑትንና የነገና ተነገ ወዲያ ተረኞችን፤ የቆሰሉትንም የሞቱትንም ተመለከቱ።
በለሰለሰ የእሳቸው ባልሆነ ድምፅ መናገር ጀመሩ። “ድመቷ ፌጦ የሚረጫት አጥታ ልጆቿን በላች አሉ። እኔ ማለት ያቺ ድመት ነኝ። ዘመዶቼን ወዳጆቼን ሁሉ ጨረስኩ። ከእንግዲህ ምን ቀረኝ!… ሙሉ ዕድሜዬን ለዚህች አገር ስንከራተት ኖርኩኝ። ወለድኩኝ እንጂ አባት አልሆንኩኝም። አቅፌ ለማሳደግ አልታደልኩም። ጫካ ለጫካ ስሹለኮለክ፤ ከድንጋይ ድንጋይ ስዘል፤ ሽቅብና ቁልቁል ተራራና ጋራ ስቧጥጥ፤ የቀበሮ ጉድጓዷን ሳሎኔና መኝታ ቤቴ አድርጌ ስኖር አሻግሬ የተሻለ ጊዜ፤ የተሻለች አገር እያየሁ ነበር። አንድ ቀን ከጦርነት እልቂት ወጥተን ሁላችንም በፍቅር እንኖራለን የሚል ተስፋ ሰንቄ ነበር። አልሆነም ወዳጆቼ ያኔም አሁንም አልሆነም!…
“በንፁህ ልብ ኢትዮጵያን ባገለገልኩኝ ከእነጓደኞቼ ጨፍጫፊዎች እየተባልን ስንሰደብ ኖርን። እኔም ከዚያ ሁሉ መከራ በመውጣቴ እፎይ ብዬ ዘወትር የሰው ሬሳ ከመራመድ ያወጣኝን አምላክ ተመስገን ብዬ የምድር መከራዬን እየተቀበልኩኝ ስድብ እየጠጣሁ ስኖር ዳግም ለጦርነት ተጠራሁ። ያገር ጉዳይ ነውና፤ ቅር የተሰኘሁት በወንድሞቼ እንጂ በአገሬ አልነበረምና የሰቀልኩትን መለዮዬን እንደገና አጠለኩት፤ ፈረስ ኮቴዬን አነገብኩ። ጦርነቱ አብቅቶ ሰላም ሲሰፍን እንደሌሎቹ ወንድሞቼ ልጄን የማየት እድሉ ይገጥመኛል፤ የአብራኬን ክፋይ ልጄን፤ ስሜ ያልጠገብኳትን፤ አቅፌ ናፍቆቴን ያልተወጣሁባትን ልጄን ሰመሐር ዳዲን በዓይነ ሥጋ አያለሁ የሚል ተስፋ ሰንቄ ነበር።…
“…ግዴለም አሁንም ተስፋ አለኝ። በዓለማዊ ኑሮዬ ያላገኘሁዋትን ልጄን፤ የምወዳትን አንድ ልጄን ሰው ሰራሽ ድንበር በሌለበት፤ አሳሪና ታሳሪ፤ አባራሪና ተባራሪ በሌለበት የሰማይ ቤት አገኛት ይሆናል።…
“…ለውዷ ባለቤቴ ለሰመሐር እናት ለአፅበሀት እንደምወዳት ንገሩልኝ። በምድር ብንለያይም ይግባኝ በሌለበት፤ አድልዖ በሌለበት ፤ እኩይ ሀሳቦች በሌሉበት በሰፊው ሰማይ ቤት እንገናኛለን ብሏል በሉልኝ። በአንድ በኩል ባሏን ፤ በሌላ ደግሞ ልጇን አሳልፋ ስቃይዋን ለምታየው የጣምራ ቁስል ህመምተኛ ውዷ ባለቤቴ ብርታቱን ይስጥሽ ብሏል በሉልኝ።…እግዜር ፈቅዶ በግንባር የልቤን ባለመግለፄ በጣም እንዳዘንኩኝ ለህዝቤ ንገሩልኝ።
“በሁለቱም ወገን ያሉትን አባቶች ትውልዱን ምከሩ በሏቸው። ፍቅር ይንገሥ። ሰው ሰራሹ ድንበር ተጥሶ ወሰን የሌለው ፍቅር በሁሉም ላይ ይንገሥ። በሁለቱም በኩል ለሞቱት 70፤ 80፤ 100፤ 120 ሺህ ወንድማማቾች ለእያንዳንዱ ሰው አንድ ዘንባባና አንድ የቴምር ዛፍ ከምሥራቅ በኩል ከአሰብ ቀይ ባህር ዳርቻ፤ በአፋር ቡሬ ግንባር፤ በመሃል ዘላንበሳ ፆረና፤ እንዲሁም ባድመ፤ ሽራሮ፤ በምዕራብ እስከ ሱዳን ጠረፍ ድረስ በሰፊው ይተከል። አንዱ ቢደርቅ ሶስት እግር ይተካ። ከሁሉም በኩል ያሉ አገር ተረካቢዎች አትድረሱበት የሚባል ሰው ሰራሽ ድንበር እንዳይሆን። ትውልድ ያለፈውን ቁስል ረስቶ ፍቅርን ያለገደብ እንደ ውሃ የሚጠጣባት፤ እንቡጥ አበባ የሚቀጥፍበት ስፍራ አድርጉት።…ደጉን ቀን ያምጣላችሁ። ከልጄ፤ ከወንድሞቼ፤ ከወታደሮቼ እንዳትለዩኝ አደራ፤ እኔ ሩጫዬን ጨርሻለሁ!”
እነሆ አፍዝ አደንግዝ ያለበትን የኮሎኔል ዳዲን ኑዛዜ በቅርብ ርቀት ከሚሰሙት ወታደሮቻቸው መኻል ወዳጃቸው አስር አለቃ ነመራ ገመቹ በመጨረሻዋ ደቂቃ እንደ ነብር ቢወረወርባቸውም ሳተናው ኮሎኔል ዳዲ ብሩ ከመቅፅበት ሽጉጣቸውን ላጥ አድርገው አንዴ ብቻ ራሳቸው ላይ ተኮሱ። ከጭንቅላታቸው የተፈናጠረው ደም የነመራን ደረትና ፊት አለበሰው። የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ የኮሎኔል ዳዲ ብሩ ግዙፍ ሰውነት ተዝለፍልፎ በተቆፈረው ጉድጓድ ወደቀ – ከሰመሐር ዳዲ ብሩ አስከሬን በስተቀኝ።…ኮሎኔል ዳዲ ብሩ ጦር ሜዳ ኖረው ጦር ሜዳ አለፉ። የእሳቸው የታሪክ ድርሳን ተዘጋ። የአገር የታሪክ ድርሳን ግን ቀጠለ፤ ሲል ተርኳል ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ።
ደገፉ ጭኮ – ጉዱ ካሳ፤
አስር አለቃ ነመራ ገመቹ በቡሬ መስመር ታጋድሎ በባድመ ግንባር ቆስሎ አዲስ አበባ ህክምና ተደርጎለት በበርካታ የጦር ሜዳ ወዳጆቹና በአዛዡ ኮሎኔል ዳዲ ብሩ ታሪክና ህልፈት የተሰበረ ልቡንና የሚያነክስ እግሩን ይዞ ነቀምት ወለጋ ከሚያፈቅራት ባለቤቱ፤ ከልጆቹ ከዘመድ አዝማድና ከሚወደው ህዝብ መኻል በተቀላቀለ ጥቂት ቀናት ውስጥ በደረሰበት አሰቃቂ የነፍስ ማጥፋት ሂደት የተከሰተውን ዘግናኙንና ልብን ሰባሪውን የነመራን ህይወት ታሪክ ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ ለቃል አቀባዩ /ደራሲው/ ተርኳል። ጣምራ ቁስል የዚህን ትርክት አብላጫ ክፍል ይዟል። ይህ ቅኝት አስቀድሞ እንደገለፅነው ውሱን ነውና አንባቢ ጥሙን ማርካት የሚችለው ከምንጩ ሲቀዳ መሆኑን እያስታወስን ወደ ቅኝታችን እናቅና።
እዶሳ ዳባ ይባላል። የነመራ አብሮ አደግ የቅርብ ጓደኛውና ወዳጁም ነበር። ነመራ በሻዕቢያ ቦንብ ያለቁትን የትግራይ ህፃናት በቴሌቪዥን ተመልክቶ ስለ ሀገሩና ስለወገኑ ህልውና መሥዋዕት ለመሆን ዴዴሳ ማሰልጠኛ ሲገባ፤ ምላስ፤ ዕኩይነትና ‘ሁሉን እኔ/ሁሉም ለኔ’ ባይነት እንጂ ተግባር በሽታው የሆነው እዶሳ ዳባ ደግሞ ምላሱንና ትንሽነቱን ይዞ ኢህአዴግ እቅፍ ገባ። ወያኔ /ትግራዊ/ ባይሆንም ወያኔያዊ ሰብዕናን እና ግብርን ተላበሰ፤ በተፈጥሮውም ይህ ነበረውና።
የትንንሽ ሰዎች ስብስብ የሆነው ህወሃት/ኢህአዴግ አባላቱ በርኩስ ምግባርና ሰብዕናቸው የሚገዝፉበት ሆነ፤ ማንነታቸውን የሚያገኙበት መድረክ። ይህ አንዳች ግነት ያለበት ወይም ሸውራራ አመለካካት ወይም ጭፍን ጥላቻ የወለደው ድምዳሜ አይደለም፤ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ በዘለቀው የኢህአዴግ/ህወሃት አገዛዝ የአባላቱ ትንሽነት በአገዛዙ ግብና ተግባር ከዛን ዘመን እስከዚህ የታየና እየባሰ እንጂ ከቶም የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል መሻሻል ያልታየበት በመሆኑ የተደረሰበት ተፈጥራዊ አንደምታ እንጂ! ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ ስለ እዶሳ እንዲህ ይላል፤
የባኮ ከተማ ሰዎች እዶሳን ለስሙ ጓደኛ ይሁን እንጂ ልቡ በቅናት የተሞላ፤ ሲናገር ለስላሳ፤ በአፉ ጤፍ የሚቆላ፤ የማይጨበጥ፤ ስልጣን እንደ ሸሚዝ እየለዋወጠ የሚኖር የለየለት አምታች ነው ይሉታል። ተምሮ ዲግሪ ባይጭንም አገር ውስጥ ገቢ፤ ግብርና፤ ፖሊስ ጣቢያ፤ ፍርድ ቤት ፖስታና ስልክ ቤት ሠርቷል። የመሰረተ ልማት ሃላፊም ሆኖ ተሹሟል።
እኛም እንመሰክራለን። አዎ፤ እውነት ነው። ህወሃት ወኢህአዴግ ሁሉ ይህ የእዶሳ ባህሪ ባህሪያቸው፤ ይህ የእዶሳ ሰብዕና ሰብዕናቸው፤ ይህ የእዶሳ መታወቂያ መታወቂያቸው ነው እንላለን። ዘረኝነት፤ ክፋት፤ ዘራፊነት፤ ጉቦኝነት ወይም በቁልምጫው አጠራር ሙሰኝነት፤ ሁሉን አዋቂነት፤ ከሀዲነት፤ ግብረገብ አልባነት፤ እብሪት፤ ተሳዳቢነት፤ ጥራዝ ነጠቅነት፤ በሥልጣን መታበይ፤ አምባገነናዊነት እኒህና የክፋትና የኢሰብዓዊ ተግባራት መገለጫዎች ሁሉ ህወሃት/ኢህአዴግ እንደ ድርጅት የተላበሳቸው ባህሪያቱ ናቸው። ይህንን ሀቅ የማታምን ካለህ ከቁንጮ ህወሃት-አዊ ወኢህአዴግ-አዊ ጀምሮ እስከ ታች ያሉት ተግባርና ሰብዕና የአደባባይ ምሥጢር ነውና – አይንህን ክፈት፤ ጆሮህንም ኮርኩር። አሊያ ግን ‘አይን አላቸው አያዩም፤ ጆሮም አላቸው አይሰሙም’ የተባለው ላንተና ለመሰሎችህ መሆኑን ልብ በል። እንግዲህስ ‘ንግባዕኬ ሀበ ጥንተ ነገር’ እንዲሉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች እኛም ወደ ቀደመ ጉዳያችን እንመለስ።
እነሆም በነመራ ትክለ ቁመና፤ በህብረተሰቡና በተለይም በቆነጃጅት በነበረው ከፍተኛ ተወዳጅነትና ይህም የህይወቱ ፈርጥ የሆነችውን ውቢቷን ዲምቱን የእርሱ እንድትሆን ማስቻሉ፤ በህዝቡ ዘንዳ በነበረው ባህሪያዊ ተፈቃሪነት፤ በበአለት ቀናት በሚደረጉት ባህላዊ ፉክክሮች በሚያስገኘው ድሎች ለዘመናት ውስጡ ሲደማና ሲንጨረጨር የኖረው እዶሳ ዳባ – እነሆ በህይወት አጋጣሚ ህመሙን የሚታመምበትና የሚታከምበትን ዋሻ ህወሃት/ኢህአዴግን አገኘና ተቀላቀለ። በነመራ ታላቅ ሰብዕና ውስጡ ሲቃጠል የኖረው ትንሹ እዶሳ በጦር ሜዳ ያልሞተውን ነመራ እሱ ጣምራ ስለት ያለው የወለጋ ጦር በውድቅት ሌሊት አንገቱ ላይ ሰክቶ ሊገድለው ሞከረ።
እነሆም ከነቀምት እስከ አዲስ አበባ ጉድ ያሰኘውን ይህንን በነመራ አንገት የተሰካውን ዘግናኝ ጦር ለመንቀል በዶክተሮች የተካሄደውን ታላቅ ትንቅንቅ አንባቢ ትንፋሽ እስኪያጥረው በጣምራ ቁስል ተተርኳል። እነሆ በኦሮሞ አዛውንቶችና በህዝቡ የገዳ ባህል ወንጀለኛውን እዶሳን ለፍርድ ለማቆምም የተካሄደውን እልህ አስጨራሹንና በእዶሳ ኢህአዴግነት ያልተሳካውን ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ ለደራሲው በልብ ሰቃይ ገለፃ አውርዶለታል። ቃኚው በዚህ ሂደት ውስጥ ከአንባቢ ጋር ለማስተዋወቅ ‘ንዑስ ርዕስ’ የከፈተለት ደገፉ ጭኮ እዶሳን ወደ ፍትህ አደባባይ ለማምጣት የክስ ማመለክቻ ከፍቶና ጠበቃ ገዝቶ ጉዳዩን እንዲከታተል በአባ ገዳዎችና በህዝቡ የተወከለ፤ በዘመነ ህወሃት/ኢህአዴግ የተፈጠረ፤ ኢትዮጵያዊነቱን ከራሱ በላይ ከፍ አድርጎ ያውለበለበ የትንታጉ ትውልድ አካል – የዘመኑ ጉዱ ካሳ – ነው።
ደገፉ ሁለት ዓመት ከተማረበት ኮሌጅ ‘በኮሌጁ ውስጥ የስነምግባር ጉድለት አሳይተሃል’ በሚል ቀጭን ትዕዛዝ ለሁለት ዓመት ከትምህርት ገበታው እንዲባረር የተደረገ ወጣት ነው። ደገፉ ከአባ ገዳዎችና ከህዝቡ የተቀበለውን ሃለፊነት ለመወጣት የከሳሽና የክሱን ዝርዝር የያዘ ማመልከቻ አዘጋጅቶ ኢንስፔክተር ሮቢ ዘንድ ቀረበ። ስለ ኢንስፔክተሩ ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ እንዲህ ይላል፤
ኢንስፔክተር ሮቢ በደርጉ ዘመን የብሄራዊ ውትድርና ዘማች ነበር። ሰለክላካ አካባቢ በተደረገ መጠነኛ ውጊያ ተማረከ።…ኢንስፔክተሩ አስራ ሁለተኛ ክፍልን አጠናቋል። ትግርኛ፤ ኦሮምኛ፤ አማርኛና እንግሊዝኛ አቀላጥፎ ይናገራል። ከምርኮ በሁዋላም በአማርኛና ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ድርጅት ታቀፈ። በወለጋ በኩል ቡሬን ተሻግረው ‘ዘመቻ ቢሊሱማ ወልቂጡማ’ን ሲያውጁ ‘ሮቤል’ የሚለውን ስሙን ‘ሮቢ’ በሚል ለውጦ በቀላሉ ከአካባቢው ሰው ጋር ከተደባለቁት የፖሊስ ሠራዊት አባሎች አንዱ ነው።
ሮቢ ከአባቱ አቶ ዲንቄሳ ጉዲናና ከእናቱ ርግበ መሀሪ ጨርቆስ አካባቢ ተወልዶ ያደገ የከተማ ልጅ ነው።…የባኮ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ነቀምት ተወልደው ነቀምት ያደጉት ህይወታቸውን ሙሉ በፖሊስነት ያሳለፉት ሻምበል ኩምሳ መገርሳ ናቸው። ሆኖም ፈላጭ ቆራጩና ተሰሚነት ያለው ሮቢ ዲንቄሳ ነበር። ከቢሮ አቅም እንኳን ሰፊውና በዘመናዊ ሶፋዎች የተጨናነቀው የእሱ ቢሮ ነው።…
እንግዲህ ይህ ማለት ሮቢ ዲንቄሳ የዋሻው አባል ነው፤ የህወሃት/ኢህአዴግ። ይህ ዋሻ የሚያስገባውና የሚደብቀው እንደነ ሮቢ እንደነ እዶሳ ያለ ሰብዕና ያላቸውን ብቻ ነውና። ሮቢና እዶሳ በህወሃት የተፈለፈለው የኦህዴድ አባል መሆናቸው የሚያጠራጥር አይደለም። ሮቢ ዘራፊዎች፤ ዘረኞችና ፅንፈኞች፤ በቀለኞችና ትውልድን ታሪክንና አዛውንትን አዋራጆች በነደፉት ‘አብዮታዊ ዲሞክራሲ’ በሽታ የተጠመቀና ያበደ ኢህአዴጋዊ ወያኔ ነው። ለዚህም ነው እድሜና ልምድ የጠገቡት የባኮው ሻምበል ኩምሳ መገርሳ ወንበር እንጂ ሥልጣን የሌላቸው። እነሆ ይህን ያህል ስለ ዋሻውና ሮቢ ቁርኝት ከቆዘምን ይበቃናልና ወደ ቀደመ ጉዳያችን እንመለስ።
ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ ተማሪው ደገፉ ጭኮ የክስ ማመለከቻውን ይዞ ኢንስፔክተር ሮቢ ዘንድ ሲገባ የነበረውን ድባብና ፍልሚያ ለደራሲው በሰፊው ከተረከው ውስጥ ቀጣዩን ያቀርቧል።
“ስም ከነአያት ስላልተፃፈ የአያት ስም መግባት አለበት። አንተ የኮሌጅ ተማሪ ነህ፤ እንዴት ይሄ ይጠፋሃል፤ ተሜ!” አለ በፌዝ መልክ።…ደገፉ የማያውቀው ነገር ቢኖር ኢንስፔክተር ሮቢ እሱን በዐይነ ቁራኛ እንዲጠብቅ የተመደበ መሆኑን ነው።
“የእሷ ስም ዲምቱ ለታ ዋቅጅራ ይባላል። የእኔ ደግሞ ደገፉ ጭኮ ምንዳርዓለው ዘውዴ ዶሪ መኮንን ሀብቶም…”
“የተጠየቅኸውን ብቻ መልስ!…እንኳን የቅድመ አያትህንና ቀጣዩን ስም ጨምረህበት የአያትህ ስም ብቻ…” አለና አንጠልጥሎ ተወው።
“ይቅርታ ኢንስፔክተር ስሙን እኔ አላወጣሁትም”
“ስሰማቸው የሚለበልቡኝ ስሞች አሉ!” አለ ኢንስፔክተሩ። እነሆ አንባቢ ሆይ! ከዚህ ቅንጭብ ቃለ ምልልስ በምድረ ኢትዮጵያ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ዘልቆ በሚገኘው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ኢትዮጵያዊ በሰውነቱና በኢትዮጵያዊነቱ ሳይሆን በስሙና በአያት ስሙ የሚፈረጅበት፤ “በውዝፍ ዕዳ” የሚወነጀልበትና “የታሪክ ሂሳብ” የሚወራረድበት ዘግናኝ ማህበራዊ ሥርዐት እንደሰፈነ ወይም እንዳሰፈነ ታያለህ። እንቀጥል የክንፈሚካኤልን አስደናቂ ትረካ፤
“ብሄር የሚለውን ደግሞ ‘ኢትዮጵያዊ’ በቅንፍ ‘ሀበሻ’ ብለህ ነው የሞላኸው። አልገባህ እንደሆነ ዘርህን ማለት ነው። እ!…ዘርህ ምንድን ነው?”
“ግልፅ እንዲሆን ከመጀመሪያው ልጀምርልህ” አለ ደገፉ። “የዘር ግንዴ መሰረቱ አርዲ፤ ሰላምና ድንቅነሽ-ሉሲ የአዋሽን ወንዝ ተከትለው፤ ከጀግናው አልሚራህ አገር ነበር ኑሯቸውን የጀመሩት። በዘመናቸው የልደት ማረጋገጫ ስለሌለ ማምጣት አይቻልም። ነገር ግን የሰው ቅሪተ አካል ተመራማሪዎች እየቆፈሩ ያወጡትን የሁላችንንም የዘር ግንድ ማስረጃ ለማየት ጃማይካው፤ ጃፓኑ፤ እንግሊዙ፤ አሜሪካው በድፍኑ ምድረ ፈረንጅ በሙሉ እየጎረፈ የአቢሲኒያን ምድር እየተሳለመ ፎቶ ሲያነሳና ሲነሳ ነው የሚውለው።” ኢንስፔክተር ሮቢ በደገፉ ጤንነት ጥርጣሬ የገባው ይመስላል።…
“የኔ ዘሮችና ዘመዶች ምድረ ፈረንጅ ሀገሩ ሲመለስ ‘የሰው ዘር መገኛ የቅድመ አያቶቼን ቤት ኢትዮጵያን ጎብኝቼ፤ ወንድሞቼን አውቄ፤ በእጃቸው በልቼ፤ ሰው ወዳድነታቸውን፤ እንግዳ አክባሪነታቸውን አረጋግጬ መጣሁ። ፍቅር በምድር ላይ የነገሰባት፤ ክርስቲያን ከሙስሊሙ ተጋብቶ፤ ቤተክርስቲያን ከመስጊድ ጎን ለጎን አንፆ፤ ፈጣሪውን የሚያመሰግን ህዝብ፤ ስረ መሰረቴን አገኘሁ’ ብሎ መደሰቱን በየጋዜጣው የሚፅፍላቸው ናቸው።”…
“የቅርቦቹን ማወቅ ከፈለግህ ቅድም እስከ ሰባት ቤት ጠርቼ ሳልጨርስ አቋረጥከኝ እንጂ እዘረዝርልህ ነበር። በድፍኑ ግን ከጂንካ ኢቫንጋዲ መንደር፤ ጎንደር ከመቅደላ አፋፍ፤ ከሐረር ጅጅጋ ሜዳ፤ ከሸዋ በሰላሌና ፍቼ ደገም፤ ወሎ ከቦሩ ሜዳ፤ በከፋ ጅማ-አሰንዳቦ፤ በጎጃም ሉሟሜና ዋሸራ፤ በአርሲ-ነገሌ ቦረናና ባሌ፤ በኤርትራ አካለ ጉዟይ ማይ ወይኔ መንደር፤ እንዲሁም ከሸዋ አምቦ በወለጋ ነቀምት ደምቢዶሎ ያሉት የእኔ ዘሮች ናቸው።
“ባጭሩ የኢትዮጵያ ዋርካ የአባ ኬሎ ጋሮ ልጅ ጀግናው አርበኛ ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ አጎት ፊታውራሪ አባ ዶዬ ዋሚ ገሮ የጣሊያን ሶላቶ ብዙ ባንዳዎችን አስከትሎ የዘር መርዙን ሲዘራ ‘እኛ የመጣነው እናንተን ከአማራ ጭቆና ነፃ ልናወጣ ነው’ ብሎ ሲያባብላቸው መልሱን ለማሳየት አንድ ቁና ሠርገኛ ጤፍ አስመጥተው ‘ይህን ለቅመህ ነጩን ጤፍ ከጥቁሩ ወይም ከቀዩ አሁኑኑ ለይልኝ’ ብለው እንደማይቻል እንዳሳዩት ሁሉ እኔም እንደ ማኛው ጤፍ ጥርት ያልኩኝ ሳልሆን እንደ ሠርገኛው ጤፍ የተደበላለቅሁኝ ለመለየት ተቸግሬ የማስቸግር ሰው ነኝ። ለዚህም ነው እኔም ከእግር ጥፍሬ እስከ ራስ ፀጉሬ ድረስ እንደ አዙሪት ሽቅብ ቁልቁል እየተሽከረከረ የሚፈሰው ደሜ ድብልቅ ስለሆነ ኢትዮጵያዊ ድብልቅ ሁሉንም ነኝ ያልኩህ።”
ኢንስፔክተሩ ከወንበሩ ቀና አለና እንደማሾፍም እጆቹን ከፍ አድርጎ አጨበጨበ። “…እኛ ያስቸገረን እንዳንተ ዐይነቱ ሰባት ቤት፤ አሰር ቤት እያለ ተረት ተረት የሚያወራልን ሰው ነው። መፍትሄው በጣም ቀላል ነው።…ግዴለህም፤ ቀስ እያልክ ታየዋለህ፤ ወይም ታገኘዋለህ ብልህ ይሻላል መሰለኝ። እስካሁን የቀባጠርከው ዋጋ የለውም። የዘር ሀረግህ የሚቆጠረው በአባትህ ነው። አባትህ ጭኮ ከአምቦ ስለሆነ ብሄር ኦሮሞ ብዬ ሞልቼዋለሁ። ኦሮሞ ነህ ብያለሁ፤ ብያለሁ! አለቀ በቃ!”
“አልስማማም፤…አንተ የምትለው ራስህ ፈጥረህ አንተው ወስነህ የምትመድበው እኔን አይወክልም። ለመሆኑ በየትኛው ላቦራቶሪ ነው አሁን ያልከው መመዘኛ የሚረጋገጠው?”
“ላቦራቶሪ አያስፈልገውም። መመሪያ ይበቃዋል። ካስፈለገ ጣሊያን ሰራሽ ላቦራቶሪ ስላለ እንዳንተ ያሉትን ያልተዋጠላቸውን ሰዎች በደንብ መመርመር ይቻላል። ያኔ ሳትጠየቅ ታምናለህ። እና ባንተ መስፈርት የእኔ ዘመዶች በአባቴ በኩል ዲንቄሳ ከአምቦ፤ አሰፋ ከፍቼ፤ ተስፋሚካኤል ከመቀሌ፤ ተስፋጋብር ከአስመራ ተወለዱ። በእናቴ በኩል ደግሞ መሃሪ ከአድዋ፤ ባንትይወስን ከመኻል ሜዳ፤ ክንዴ ከጎንደር ወዘተ እያልኩ ልዘረዝር ነው! በጣም ቀላሉ የእኛ ቀመር ስለሆነ ዲንቄሳ ከአምቦ በሚለው መስፈርት መሰረት ኦሮሞ የሚለው ተስማምቶኛል። አንተም እወቅበት። ከጊዜው ጋር መራመድ ካልቻልክ እንደ ዳይኖሰር ከምድረ ገፅ ድምጥማጥህ ይጠፋል።”
አንባቢ ሆይ! ይህ አስደማሚ ምልልስ በምድረ ኢትዮጵያ የሚገኘውን የህወሃት/ኢህአዴግ ሥርዐተ አስተዳደር ፍንትውና ቅልብጭ አድርጎ አስቀምጦታል። ከሁሉም በላይ ግን ከዘር በፊት በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምንና ለታሪኩም ቀናዒ የሆነ እንደ ህወሃቱ ወኢህአዴጉ ኢንስፔክተር ሮቢ ዲንቄሳ አገላለፅና እምነት ከሆነ – ‘ከጊዜው ጋር መራመድ የማይችል ዘርን ያላስቀደመና ኢትዮጵያዊነት በሚለው ተረት የቆረበ እንደዳይኖሰር ከምድረ ገፅ /ከኢትዮጵያ ምድር/ ድምጥማጡ ይጠፋል’። ይህ የኢንስፔክተሩ ቀቢፀ ተስፋ ድንፋታና እብሪት በይፋና በአደባባይ በህወሃት ናዚስቶች ሲደነፋና ሲተገበር እነሆ ሩብ ምዕተ ዓመት አልፏል።
ነገር ግን ከዘር ፖለቲካ በፊት በኢትዮጵያዊነታቸውና በኢትዮጵያ ታሪክ የሚያምኑ በሥርዐቱ ውስጥ ያደጉ ትንታግ ወጣት ኢትዮጵያውያንን እንደዳይኖሰር ማጥፋት ከቶም አልቻሉም አይችሉምም። ይልቁንም የናዚስቶቹ መረን የጣሰ ግፍና ጭካኔ ኢትዮጵያዊነትን ይበልጥ እንደ እንጉዳይ እያፈካ ከህወሃት/ኢህአዴግ ጋር የሚደረገውንም ትግል ወደ ወሳኙ ምዕራፍ እያሸጋገረ አመጣው እንጂ! የአፋኞቹ ግፍና አፈና እስርና ወከባ ‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ”ና ሰዐት እላፊ ወላፈኑን ወጣት ትውልድ ለነፃነቱ ከመቆም አላገደውም። አብነት ካስፈለገም አምቦን ወሊሶን ባህርዳርን ጎንደርን እና ሌሎችንም ተመልከት። በመላው ሀገሪቱ ከተሞች – ከደቡብ እስከ ሰሜን – በተደጋጋሚ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የሥራ ማቆም አድማና ከቤት ያለመውጣት እምቢተኛ አመፅ ልብ በል!
መቶዎች ሲታሰሩ ሺዎችን እያፈሩ፤ የአጋዚ ጥይት መቶዎችን ሲገድል ሺዎች እየተተኩ እነሆ ከካቻምናው አምና ከአምናው ዘንድሮ የትግሉ ቋያ ስፋትና ግለት በርትቶ አራት ኪሎ መዳረሻ ላይ ነው። ‘ለሁሉም ጊዜ አለው’ ይላልና፤ እነሆ ጊዜው ተዳርሷል – ‘ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ’ የሚለው የቅዱስ መፅሀፍ ቃል ይፈፀም ዘንድ። አዎ፤ የቆመ የመሰለው አወዳደቁን አያውቅምና! …ይህንን በዚህ እንገታለን። እነሆ የትንታጎቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምልክት በሆነው በደገፉ ጭኮ ተከታይ ምላሽና በዋሻው አባል የወያኔው ኢንስፔክተር ሮቢ ዲንቄሳ መልስ ምት ንዑስ ርዕሳችንን እንሸብባለን።
“ስለ ምክርህ አመሰግናለሁ፤ ዋጋ የለውም እንጂ” አለ ደገፉ /ለኢንስፔክተሩ/። “ሁለት ፀጉር አውጥተው እንኳን እንደሚንገላቱት የተከበሩ አባቶች ባልሆንም ቢያንስ አጋጣሚ ሳገኝ ዕውነቱን እናገራለሁ።…ቢያንስ የተደፈነ ጆሮው የሚከፈት ወይም አዲስ ሰሚ ትውልድ አፈራለሁ ብዬ ስለማምን እንደ አበው ባልመጥንም የአቅሜን እለፈልፋለሁ። የዘር ነገር ለነሂትለርም አልበጃቸውም። ቋንቋ በአንድ አካባቢ ወይም ስፍራ የሚኖር ህዝብ መግባቢያ፤ ቀይ ጥቁር ሳይል ባህሉን ወጉን የሚገልፅበት፤ ታሪኩን ከትቦ ለትውልድ የሚያስተላልፍበት መሳሪያው እንጂ መከፋፈያው አጥሩ አይደለም። ይልቅ ከፋፍሎ የሚያራርቀንን ጣሊያን ሰራሹን ቋንቋ መሰረት አድርጎ የተገነባውን የዘር ግርግዳ እንደ ጀርመን ግንብ አፍርሰን ልክ እንደ ጥንቱ መሆን ነው።…”
ኢንስፔክተር በደገፉ ንግግር ከነበረው አስተሳሰብ ትንሽ እንኳን ፈቅ የማለት ምልክት አልታየበትም፤ ጭርሱን አመረረ። “በዚህ መርዘኛ ምላስህ አይደለም ከኮሌጅ ከሀገር መባረር ሲያንስህ ነው። የሚያዋጣው አንተን ከርቸሌ መወርወር ነው። ቀደም፤ ቀደም ማለት አብዝተሃል። ስማ፤ የተሰጠህ ነፃነት በማንኪያ እንጂ በአካፋ አይደለም። ብታስብበት ይሻልሃል። አለበለዚያ ከማሽላዎች መኻል አስቀድማ እንደዘረዘረችው ማሽላ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ ትሆናለህ።”
መቋጫ፤
እነሆ በሁለት መቶ ሰማኒያ አምስት ገፅ የተተረከውን ጣምራ ቁስል እኛ በጥቂት ገፆች አበራይተን ቃኝተናል ለማለት ከቶም አይዳዳንም፤ አፅመ ታሪኩን አቅርበናል እንጂ። ጣምራ ቁስል “የአመድ አፋሹ” ሠራዊታችን ተምሳሌ የሆኑት የኮሎኔል ዳዲ ብሩና ከመረብ ወዲያ የቀረችው ኤርትራዊት ባለቤታቸው ቁስል ብቻ አይደለም። ጣምራ ቁስል ተምሳሌነቱ የኢትዮጵያም ታሪክ ጭምር ነው። ጣምራ ቁስል የኢጆሌ ወለጋ – የአስር አለቃ ነመራ ገመቹ – ታሪክ ብቻ አይደለም።
እልፍ ኢትዮጵያውያን መሥዋዕትነትን የከፈሉበትና መሥዋዕትነታቸው በሸፍጠኞች መና የሆነበት ‘ሀገራዊ ክህደት’ በህወሃቱ ናዚስት መሪ መለስ ዜናዊ አመራር አልጀርስ ላይ የተፈፀመበት አሳዛኝ የታሪካችን አካልም እንጂ! ጣምራ ቁስል ስለሀገር ፍቅር በውጊያ የቆሰለው፤ በህይወት በመትረፉም አሰቃቂ የግድያ ሙከራ ተፈፅሞበት ፍትህ ያጣው የነመራ ገመቹ ታሪክ ብቻ አይደለም፤ የክፉ ሰዎች ሁሉ ዋሻ በሆነው ህወሃት/ኢህአዴግ ፍትህና ርትዕ ተነፍገው የሚማቅቁና የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ታሪክም ተምሳሌ እንጂ! ጣምራ ቁስል ግለሰባዊ ፤ ማህበረሰባዊና ሀገራዊ ታሪክ እንደ ሸማ ድርና ማግ ተወሳስበው የቀረቡበት የትላንቱ ታሪክ ከዛሬው ዕውነታ የተቆራኘበት የታሪክ መዘክርም ነው።
እነሆ ይህንን ታሪክ ለተረከው ክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ ገለታ ይግባው። እነሆ ደግሞ የክንፈሚካኤል ዘፉኛን ቢራ አብሮ አደግና ቃል አቀባዩ – ደራሲው – ተስፋዬ መኮንን ባይለየኝ (ዶ/ር) – በሰባት ተከታታይ ምሽቶች ወዳጃቸው የተረከላቸውን በፅሁፍ ከሽነው፤ በታሪክ ወንዝ አፍስሰው ለእኛ ስላደረሱን አክብሮታችንን ከልባዊ ምሥጋና ጋር ደርበን እናቀርባለን። በ”ቀይ አንበሳ” ነፍስያችን የቆዘመችውን፤ የታደሰችውንና፤ የጀገነችውን ያህል የ”ጣምራ ቁስል” ትረካም ለነፍስያችን የቀረበና እኛን ያሳየ እኛንም የሆነ እንደ እኛም የታመመ በመሆኑ የጨለማው ዘመን አገዛዝ ታሪካችን አካል አድርገን ተቀብለነዋል። አዎ! እኛም እንላለን፤ እነሆ የጣምራ ቁስል ትረካ አበቃ። የኢትዮጵያ ቁስል ታሪክ ግን እስከዚህ ዘመን ድረስ አላበቃም።
ኢትዮጵያ ሆይ! ስቃይሽ መቼና እንዴት ይሆን የሚያበቃው?!
****** ተ ፈ ፀ መ ******
ተፃፈ፤ መስከረም 2010 ዓ/ም (ሴፕቴምበር 2017)
ሲድኒ አውስትራሊያ
mmtessema@gmail.com
• ከጣምራ ቁስል በተነቀሱት ውስጥ የሚገኙት ሰረዞችና ጎልተው የወጡ ዐ/ነገሮች የቃኚው ትኩረት ናቸው።
• የሶማሊያን ልዩ ፖሊስ ወረራና ግድያን በተመለከተ የሚከተሉትን ዘገባዎች ተመልከት፤
• https://amharic.voanews.com/a/somali-oromia-region-conflict-9-12-2017/4025672.html
• https://www.youtube.com/watch?v=ZEt-NrveuKI
• https://www.youtube.com/watch?v=A01lHOnNXFo
• https://www.youtube.com/watch?v=kMeeKTsLclU
• ቀጥሎ የቀረበው ካርታ በ18/12/2009 ዓ/ም በኢቢሲ ዜና ላይ ቀርቦ የነበረው ነው።
በህወሃት አዲስ ካርታ ላይ ለተጨማሪ ማብራሪያ የሚከተለውን ዘገባ አድምጥ፤
ስለ ወጣቱ የህዝብ ፍቅር ንጉሥ ቴዲ አፍሮና ስለህወሃቷ ኤደን ገብረሥላሴ የሚከተለውን ተመልከት፤