/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ የኢትዮጵያ ሶማሊ ከልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሀመድ ዛሬ በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ እንደገለጹት፤ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት “የተባሉት” በአስቸኳይ ስልጣን እንዲለቁ ሲሉ ጠየቁ።
በአወዳይ መስከረም 2/2010 ዓ.ም በንጹሃን ሶማሌዎች ላይ የተደረገውን የግፍ ጭፍጨፋ ያቀነባበሩትና የመሩት አቶ ለማ መገርሳና የክልሉ ጨካኝ ፖሊሶቻቸው አማካኝነት ነው ብለዋል።
የኦሮሞና የሶማሊ ህዝብ በወንድማማችነት ለዘመናት አብሮ የኖረ ነው። የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ሙክታር ከድር በሀይል እንደተወገዱና አዲሱ የአቶ ለማ መገርሳ አስተዳድር ሲመጣ በእኛ ላይ የመሬት ወረራ ዘመቻ ፈጸሙብን በማለት ከሰዋል።
የሶማሊ ክልል ህዝብ ጫት በመግዛት የገቢ ምንጭ ቢሆናቸውም እነሱ ግን በፍቅር ፋንታ የወገኖቻችን አስከሬን ላኩልን ብለዋል።
መንግስታቸውም አቶ ለማ መገርሳ ከስልጣን እንዲለቁ፤ የፌዴራል መንግስቱ በአስቸኳይ ወንጀለኞችን አጣርቶ ተጠያቂ እንዲያደርግ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስቴር ሀይለማርያም ደሳለኝ ሁኔታውን በትክክለኛው መንገድ መቆጣጠር ካልቻሉ እርሳቸውም ከቦታ እንዲነሱ በማለት ጠይቀዋል።ህዝባቸው በፍርሃት ዝም እንደማይልና መብቱንም እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
አቶ አብዲ በመጨረሻም እጅግ አስገራሚ ጉዳይ ተናግረዋል። “በመጨረሻም ለትግራይ ህዝብና መሪዎቻቸው ላደረጉልን ያላወላወለ ድጋፍ ማመስገን እፈልጋለሁ።” በማለት ቋጭተዋል:፡