/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ የሁለቱ ክልሎች ግጭት ሰሞኑን እንደ አዲስ አገርሽቶ በርካታ ሰዎች ሲሞቱ ከ55 ሺህ በላይ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከሱማሊ ክልል በሀይል መፈናቀላቸው ታውቋል።
ከጅጅጋ ከተማ ብቻ 25 ሺህ ዜጎች ንብረታቸውን ተነጥቀው ተባረዋል። ቀሪዎቹ ከውጫ፣ ሽንሌ፣ ቀብሪ በያህና ሌሎች አካባቢዎች በመፈናቀል በድሬ ደዋ፣ ሀርና ጭናቅሰን ከተሞች በግዜዊነት ሰፍረዋል።
የሶማሊ ክልል ልዩ ሀይል ፖሊስ እየተባለ የሚጠራው የታጠቀ ሀይል በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ እያደረሰ የሚገኘውን ግድያ የአወዳይ ከተማ ነዋሪዎች ማክሰኞ እለት ለመቃወም በወጡበት ወቅት ከ28 እስከ 37 የሚሆኑ የሶማሌ ጎሳዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ከተገደሉ በሗላ ውጥረቱ ጫፍ እየረገጠ ይገኛል።
ጦርነቱ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች እንደቀጠለ ነው። ይህን ተከትሎ ከሶማሊ ክልል ተፈናቅለው ሀረር ከተማ የገቡት ተፈናቃዮች ዛሬ ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ በርካታ ሰዎች እንደሞቱ መረጃዎች እየተቆሙ ነው። በ26 ዓመታት ውስጥ ግጭቶች በየ ጊዜው የሚከሰት ቢሆንም የክልል መንግስታት ግን እንዲህ እንደ አሁኑ የኦሮሚያንና ሶማሊ ክልሎች የጎንዮሽ የጠነከረ የቃላት ጦርነት ሲገቡ ማየት ያልተለመደ ነው።