እ.ጎ.አ በመስከረም 26፣ 1983 … ስታኒስላቭ ፔትሮቭ በሶቭየት ሕብረት የኒውክሌር ጥቃት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ማዕከል ውስጥ በሥራ ላይ ሳለ ድንገት በኮምፕዩተሩ ስክሪን ላይ አንድ አስደንጋጭ ነገር ተመለከተ፡፡ START የሚለው የኮምፕዩተሩ ትልቅ ቀይ ቁልፍ እያበራ አስፈሪ የማስጠንቀቂያ ድምፁ ክፍሉን ሞላው፡፡
አጠገቡ ያሉት ሁሉ ከመቀመጫቸው ዘለው ተነስተው አፈጠጡበት፡፡
አዎን፣ በእርግጥም የኮምፕዩተር ሥርዓቱ አሜሪካ ወደ ሶቭየት ሕብረት ሚሳዬል እንደተኮሰች እያሳየው ነው፡፡ የኮምፕዩተሩ ማስጠንቀቂያ የተሰማው 30 ያህል የኮምፕዩተሩን ስርዓት ቅጥልጥል ማጣሪያዎች አልፎ ነበር…
እና የኮምፕዩተሩን ማስጠንቀቂያ ይመን ወይስ ?
ስታኒስላቭ ፔትሮቭ ኮምፕዩተሩ ቢሳሳትስ ስል ተጠራጥሯል፡፡
ወዲያው ደግሞ ሌላ የማስጠንቀቂያ ደወል ተሰማ – ሌላ ሚሳዬል ከአሜሪካ ተተኩሶ ወደ ሶቭየት ሕብረት እየተምዘገዘገ ነው እያለው ነው ኮምፕዩተሩ… እንደ ገና ሌላ ማስጠንቀቂያ – እንደ ገና ሌላ – በአጠቃላይ 5 ሚሳዬሎች ወደ ሶቭየት ሕብረት እያመሩ መሆናቸውን ኮምፕዩተሩ እያስጠነቀቀው ነው፡፡
የሥራ ድርሻው በሚያዘው መሰረት ፔትሮቭ በሁለት ሶስት ደቂቃ ውስጥ አጠገቡ ያለውን ስልክ አንስቶ ጉዳዩ ለሚመለከተው የሶቭየት ከፍተኛ የጦር መኮንን ማሳወቅ ነበረበት፡፡
ከዚያም በመመሪያው መሰረት መልዕክቱ በፍጥነት የኬጂቢ ኃላፊ ለነበሩትና ለወቅቱ የሶቭየት ሕብረት መሪ ዩሪ አንድሮፖቭ ይደርሳል፡፡ አንድሮፖቭ ማድረግ የሚችሉት አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡
የተተኮሱትን ሚሳዬሎች ማክሸፍ አይቻልም – ስለዚህም እርሳቸውም የአፀፋ የኒውክሌር ሚሳዬል ወደ አሜሪካ ይተኩሳሉ… በዚህም አሜሪካ ሳታውቀው ትጠፋለች ወይም እሷም የአፀፋውን ወደ ሶቭየት ሕብረት ተኩሳ ሁለቱ ልዕለ ኃያላን ምናልባትም መላው ዓለም በኒውክለር ጦር መሳሪያ ይወድማል…
እንደብዙዎች ግምት ይህ ነበር የሚሆነው – ስታኒስላቭ ፔትሮቭ ግን የኮምፕዩተሩን ማስጠንቀ ቂያ አላመነውም፡፡ መግለፅ የማይችለው አንዳች ስሜቱ ምናልባት ኮምፕዩተሩ ተሳስቶ ቢሆንስ እያለው ነበር…
እናም ስልኩን ሳይደውል ቀረ…
በዚህም ቀዝቃዛው ጦርነት በተፋፋመበት በዛን አስከፊ ወቅት ምድራችን ካልታሰበ የኒውክሌር እልቂት ተረፈች፡፡
ያን ውሳኔውን አስመልክቶ ሲጠየቅ ፔትሮቭ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “በሁለት ሶስት ደቂቃዎች ውስጥ ሁሉን ነገር ተንትነህ አትችለውም፡፡ ስለዚህም ያለህ መሳሪያ ውስጥህን ማዳመጥ ነው፡፡ ሁለት ነገሮች ደግሞ አሉ … በመጀመሪያ ደረጃ የኒውክሌር ጥቃት ቢሰነዘር ከአንድ ቦታ ሳይሆን አሜሪካ ከሁሉም ማስወንጨፊያዎቿ ነበር የምትተኩሰው፡፡ እናም ደግሞ 5 ሚሳዬል ብቻ አትተኩስም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኮምፕዩተር ደደብ አይደለ እንዴ … እኛው ነን የፈጠርነው፤ ሊሳሳት ይችላል…”
ፔትሮቭ ኮምፕዩተሩ ተሳስቶ ይሆናል በሚል ስልኩን ሳይደውል የቆየባቸውን 23 ደቂቃዎች እንዴት ባለ ፍርሃት እና መርበድበድ እንዳሳለፈ ያስታውሳል፡፡
ምክንያቱም በትክክልም አሜሪካ ሚሳዬሎቹን ተኩሳ የኮምፕዩተሩም ማስጠንቀቂያ እውነት ቢሆን ኖሮ ሚሳዮሎቹ ሶቭየት ሕብረትን ለመምታት በዛ ቢባል 23 ደቂቃዎች ብቻ ይበቃቸው ነበር፡፡
በ77 ዓመቱ ሞስኮ ውስጥ ያረፈው ስታኒስላቭ ፔትሮቭ የዛን ወቅቱን ሁኔታ አስታውሶ ሲናገር፣ “ከ23 ደቂቃዎች በኋላ ምንም እንዳልተፈጠረ ተረዳሁ፡፡ ሚሳዬሎቹ ተተኩሰው ቢሆን ኖሮ በነዚህ ደቂቃዎች ውስጥ ይታወቅ ነበር፡፡ ታላቅ እፎይታ ነበር የተሰማኝ” ብሏል፡፡
በአንድ ወቅት በተደረገለት ቃለ መጠይቅ ላይ ደግሞ ፔትሮቭ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “የሚሳዬል ጥቃት እንደደረሰ የሚገልፅ መረጃ ደርሶኛል፡፡ ደውዬ ብናገር ኖሮ በእዝ ሰንሰለቱ ውስጥ ካሉት ውስጥ ማንም ሪፖርቴን የሚቃወም አልነበረም”
የኮምፕዩተሩን ማስጠንቀቂያ ያላመነው ፔትሮቭ ለበላይ ኃላፊዎቹ ከመናገር ይልቅ ወደ ጦር ኃይሉ ዋና መስሪያ ቤት ደውሎ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ስርዓቱ ተበላሽቷል ሲል አሳወቀ፡፡
የተናገረው ነገር ስህተት ቢሆን ኖሮ ሶቭየት ሕብረት ከምድረ ገፅ ጠፍታ ነበር…
ኋላ ላይ የተደረገ ምርመራ፣ የስህተቱ ምክንያት … የሶቭየት ሳተላይቶች ዳመና ላይ የተንፀባረቀን የፀሐይ ጨረር እንደ አህጉር አቋራጭ ሚሳዬል በመቁጠራቸው መሆኑ ታወቀ፡፡
ዓለምን በተለይም የወቅቱ ልዓለ ኃያላንን ከኒውክለር ጦርነት ጥፋት የታደጋቸው ስታኒስላቭ ፔትሮቭ የሞተው ከዛሬ 3 ወራት በፊት ግንቦት 10 ቀን ቢሆንም የዓለምችን ታላላቅ መገናኛ ብዙሃን ግን ወሬው የደረሳቸው ትላንት ነበር፡፡
የፔትሮቭን ታሪክ ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ይፋ ያደረገው ጀርመናዊው ፊልም ሰሪ ካርል ሹማይከር ጿግሜ 2፣ 2009 ዓ.ም ፔትሮቭን መልካም ልደት ሊለው ሲደውል የፔትሮቭ ልጅ አባቱ ግንቦት 10 ቀን መሞቱን ይነግረዋል፡፡
ወሬው በማህበራዊ ድረገፆች ሰዎች ሲቀባበሉት ከርመው እነሆ በትላንትናው ዕለት የዓለማችን ታላላቅ የመገናኛ ብዙሃን ጋር ሊደርስ በቃ…
የሞቱ ወሬ በሩሲያ ሚዲያዎች ያለመዘገቡ ሚስጥር ለብዙዎች እንግዳ ጉዳይ ነው፡፡
የምዕራቡ ዓለም፣ ፔትሮቭን፣ ከትልቅ ጥፋት አዳንከን በሚል በሽልማት ቢያንበሸብሸውም የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ባለሥልጣናት ግን የዛች ቀንን ክስተት ሌላው ቢቀር በቀን ውሎ መመዝገቢያ ላይ ለምን አላሰፈርክም በሚል ወቅሰውታል፡፡
የፔትሮቭ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው እ.ጎ.አ በ1998 የሶቭየት ሕብረት የሚሳዬል መካላከያ ስርዓት አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ባሳተሙት ግለ ታሪክ ነበር፡፡
ወዲያው የፔትሮቭ ዝና ገነነ፡፡
እ.ጎ.አ በ2006 “የዓለም ዜጎች ማሕበር” የተሰኘ ድርጅት በተባበሩት መንግሥታ የስብሰባ አዳራሽ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት፣ “ዓለምን ከኒውክሌር ጦርነት የታደጋት” በሚል አክብሮታል፡፡
በታሪኩ ላይ ተመርኩዞ በ2013 “The Man who Saved the World” የተሰኘ ዶክመንተሪ ፊልም የተሰራለት ፔትሮቨ በዛው ዓመት የተከበረው የድሬስደን የሰላም ሽልማት ተበርክቶለታል::