የታጨደው ሳር ድርቆሽ ነው የከብቶች መኖ በመሆን
በበሬ ጫንቃ ትሩፋት ጠግቦ አደር እንድንሆን፤
የሞተው የግጦሽ ሳር ነው ጮሌ ፈረስ አሳድጎ
የድል ብሥራት ያቀዳጀን ጀግና ተዋጊ አድርጎ፤
የበሬውን ቆዳ ከበሮ የበሬውን አንጀት ጅማት
የፈረሱን ሞት በደል የሸንበቆውን ያካል ስብራት፤
የእንስሳቱን ሞት ከእሳሩ ሞት ጋር ስናዋህደው
ከሞት ምንጭ ነው ለካስ የደስታ ጅረት የሚወርደው።
የሞተ በሬ አንጀት ነው፤የክራር ጅማት ሆኖ
ያሳለፍነውን ህይዎት ወደ ፊት አጠንጥኖ
መልሶ የሚያኖረን ያለፈውን ጊዜ ትዝታ
ሳናውቀው ለካስ ሞት ነው፤የሚለግሰን ደስታ።
የሞተ በሬ አንጀት ነው፤የክራር ጅማት ሆኖ
ልባችንን የሚያሸፍተው በቸበለው ቅኝት ፋኖ።
የሞተ በሬ ቆዳ ነው፤ከበሮ ሆኖ ተወጥሮ
ሲነረት ሲደበደብ ልዩ ቃና ድምጽ ፈጥሮ
ባጀቡት ዜማዎች ግነት ቅላጼውን አጉልቶ
መድረኩን ሲነቀንቀው ንዝረቱ ስሜት ነክቶ፤
የተሰበረው ሸንበቆ ነው፤አካሉ ተበሳስቶ
በጣት ላይ ትንፋሽ ጨምሮ፤የዋሽንት ድምጽ አፍልቆ
አእምሮን የሚያብከነክን የሰውን ቀልብ ሰርቆ
የሞተ ፈረስ ጭራ ነው፤የአዝማሪ ጥበብ ማሲንቆ
ደስታ የሚዘራብን ስሜታችንን ሰርቆ።
ከተገደለ እሳር፣ከተገደለ በሬ፣ ከተሰበረ ሸንበቆ
ከሞተ በሬ አንጀት፣ከሞተ ፈረስ ጭራ መረዋ ድምጽ ፈንጥቆ
ከሞተው ክርስቶስ ህይዎት፣የምህረት ፀበል ፈልቆ
የአዳምን ልጆች ሁሉ በደሙ ዋጅቶ ያፀዳው
ከሞት ምንጭ ነው ለካስ፣የሰው ደስታ የሚቀዳው።
መስከረም 2010
*መታሰቢያነቷ የሥነ ሃሳቡ ምንጭ ለሆነው ከያኒ እሱባለው ይታየው