መታወቂያ ላይ ” ብሔር” የሚለውን ለማስተካከል ረጅም ጉዞ የተጓዘው ያሬድ ሹመቴ

መታወቂያ ላይ ” ብሔር” የሚለውን ለማስተካከል ረጅም ጉዞ የተጓዘው ያሬድ ሹመቴ

“በህገ መንግስቱም ብሔሬ እንዲጠቀስ የሚያስገድድ አንቀፅ የለም። “

ከሶማሌ ክልሎች ግጭት ጋር ተያይዞ መታወቂያ ላይ ብሔር መስፈሩ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል። በተለይም መታወቂያ ላይ ያለ የብሔር ማንነት ሰዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል በሚልም ጉዳዩ መከራከሪያ ሆኗል።

ምንም እንኳን ብሔርን መታወቂያ ላይ መጥቀስ መንግሥት ከዘረጋው ማንነትን መሰረት ካደረገው ፌዴራሊዝም ጋር 26 ዓመታትን ቢያስቆጥርም አሁንም ጥያቄ የሚነሳበት ጉዳይ ሆኗል።

ከሚነሱት አከራካሪ ጉዳዮች ውስጥ ከተለያዩ ብሔሮች የተወለዱ ሰዎች አንድ ብሔር ብቻ እንዲመርጡ መገደዳቸው፤ የብሔር ማንነት አይገልፀንም የሚሉ፤ ብሔር የሚለው ቃል አንድን ማሕበረሰብን አይገልፅም የሚሉት ይገኙበታል። ከዚህ በተቃራኒው ብሔር ማንነትን የሚገልፅ በመሆኑ መታወቂያ ላይ እንዲካተት አጥብቀው የሚከራከሩም አሉ።

ብሔር መታወቂያ ላይ መካተቱን ከሚቃወሙት አንዱ የፊልም ባለሙያ የሆነው ያሬድ ሹመቴ ይህንን ለማስቄር ብዙ እርቀት ተጉዟል። “ብሔር ለሚለው ሀሳብ ለኔ ኢትዮጵያ የምትለው ትበቃኛለች።” በማለትም ይናገራል።

መጀመሪያ መታወቂያውን ሲያወጣ ብዙ ያላሰላሰለበት ያሬድ እንደ ብዙ ኢትዮጵያዊ በቅፅ በተሞላው መስፈርት መሰረት ነው መታወቂያ ያወጣው። ምንም እንኳን መታወቂያው ከወጣ ብዙ ዓመታት ቢያስቆጥርም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባንክ ቤት ብር ለማውጣት ወይም ለተለያዩ ጉዳዮች መታወቂያውን በሚጠቀምበት ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ይረበሽው እንደነበር ይናገራል ።

ከዛም ለማምለጥ የሥራ መታወቂያን፣ መንጃ ፍቃድን እንዲሁም ፓስፖርቱን መጠቀም ጀመረ። በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ሀገሪቱ ላይ ባለው ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭትና ውጥረቶች ጋር ተያይዞ የበለጠ መታወቂያው ላይ ብሔር ብሎ መስፈሩን ሊቀበለው አልቻለም። “በብሔር ምክንያት የወዳጆች ግንኙነት እየተበላሸ፤ ለብዙዎች በሰላም ከሚኖሩበት ቦታ ለመፈናቀል ምክንያት በመሆኑ አደገኛነቱ እየጎላ መጥቷል። ” በማለት የሚናገረው ያሬድ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ብሔርን መተው ለሚፈልጉ መነሳሳትን ሊፈጥር እንደሚችል ያስረዳል።
በተጨማሪም “ብሔር የሚለውን ቃል ሃገር የሚለውን ሀሳብ የሚገልፅ እንጂ የተለየ መለያ ነው ብዬ አላስብም።” በማለት የሚናገረው ያሬድ ለማጣቀሻም ያህል የቀድሞ ፅሁፎችን ይጠቅሳል። በኢትዮጵያ የህትመት ታሪክ ቀዳሚ ሥፍራን የሚይዙት ተስፋገብረ ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋን “ቡልጋ” የሚባል ብሔር የለም። በዚህም ትርጉሙ ቦታን ማሳያ ሆኖ ነው የተጠቀሰው ይላል።

“ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዚዳንት የሚለውን ቃል በአማርኛ ለመጠቀም ‘ርዕሰ-ብሔር’ እንለዋለን፤ ስለዚህ ብሔር የሚለው ለአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ወይም በአንድ ወንዝ ብቻ ተከልሎ ለሚኖር በአመለካከት አንድ ለሆነ ቡድን የሚሰጥ አይደለም። ” ይላል ያሬድ።

ብሔርን መሰረት ያደረጉ ቡድኖች መጠናከር የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን አዳክሟል ብሎ የሚያምነው ያሬድ፤ ኢትዮጵያዊነትን ከማቀንቀን ይልቅ ብሔር ላይ ማተኮር የበለጠ ጎልቷል ብሎ ያምናል። በተቃራኒው ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባለው ሃገር የሰሜኑን ባህል መሰረት ያደረገችና የሌሎችን ማህበረሰብ እምነት፣ ስርዓትና ወግን በመዋጥ እንዲሁም በመጨቆን የተመሰረተ በመሆኑ ኢትዮጵያዊ የሚባለውን ማንነት ጥያቄ ውስጥ ይከቱታል።

ከፍተኛ የሆነ የብሔር ጭቆና ነበር የሚሉት እንዳሉ ሆነው በኢትዮጵያ ውስጥ የመደብ ጭቆና እንጂ የብሔር ጭቆና አልነበረም የሚሉም አሉ። ሆኖም ግን ያሬድ እንደሚለው “ብሔራቸውን መጥቀስ ለሚፈልጉ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግራይ ተብሎ እንዲፃፍላቸው የሚፈልጉት ምርጫቸው ይተበቅ፤ ማንም ኢትዮጵያዊ ላይ ብሔር እንዳይፃፍ የሚል ጥያቄ የለኝም። ለኔ ግን የማይገልፀኝን ነገር፣ በህገ-መንግሥቱ የማልገደድበትን ማንነት ሊፃፍብኝ አይገባም። የኔም ጥያቄ ይመለስ መብቴ አይከልከል ነው እያልኩ ያለሁት። ” ይላል ያሬድ።

ብሔር የሚለውን ኢትዮጵያዊ እንዲባልለት ጉዳዩን ወደ ቀበሌ የወሰደውም ከስምንት ወራት በፊት ነው። መታወቂያው ላይ ብሔር በሚለው ቦታ ላይ ‘ኢትዮጵያዊ’ ተብሎ እንዲፃፍለት ጥያቄ ሲያቀርብ፤ የተሰጠው መልስ ግን ”ቅፁ ላይ ካለው ወይ ከአባትህ ወይ ከእናትህ ከአንዳቸው ብሔር መርጠህ መታወቂያ ይሰጥሀል እንጂ አንተ ላልከው መመሪያው አይፈቅድም። ” የሚል ነው።

ያቀረበው ጥያቄ በቀበሌው ተቀባይነት ባለማግኘቱ ወደ ወረዳው ሥራ አስፈፃሚ ተመርቷል። በማህበራዊ ድረ-ገፁ ላይ እንደፃፈው ብዙዎች ጉዳዩን እንዳልተረዱት ያስረዳ ሲሆን “ብሔርህ በእናትህ ተፅፎ ነው?” እና “ብሔር ሳይር እንዴት ዜጋ መሆን ይቻላል። ብሔር የግድ ነው።” የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡለት ሲሆን፤ መልሳቸው ግን ተመሳሳይ ነበር “መመሪያው አይፈቅድም!” የሚል ነው።

መመሪያውን የሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነቶችና የነዋሪዎች አገልግሎት ፅህፈት ቤት የተባለው ተቋም ነው። በነዋሪዎች መታወቂያ አሰጣጥ መሟላት ካለባቸው ጉዳዮች ውስጥ ከብሔር በተጨማሪ ሀይማኖት ቢጠቀስም እንደ አስገዳጅ ሁኔታ አልተካተተም።

ጉዳዩም ወደ ክፍለ-ከተማ ተመርቶ ብዙዎቹ በመገረምና በመሳቅ እንደተቀበሉት ያሬድ ይናገራል። ጥያቄያቸውም ተመሳሳይ ነው ለምን ብሔርህ እንዳይጠቀስ ፈለግክ? የእርሱ መልስም “በብሔር ስለማላምን ነው። ቤተሰቦቼም አንተ የዚህ ብሔር አባል ነህ ብለው ስላላሳደጉኝ፤ ስለብሔር ምንም አላውቅም። የማውቀው ኢትዮጵያዊ መሆኔን ብቻ ነው። በህገ-መንግሥቱም ብሔሬ እንዲጠቀስ የሚያስገድድ አንቀፅ የለም። ” የሚል መልስም ይሰጣል።

በመጨረሻም መመሪያው መሻር የሚቻለው በፍርድ ቤት ብቻ ስለሆነ፤ ፍርድ ቤት ሄዶ ብሔር የሚለው መታወቂያዬ ላይ አይስፈር በሚል እንዲያመለክት ነገሩት። ጉዳዩ በዚህ አላለቀም የክፍለ-ከተማው ፍርድ ቤት ወደ ሌላ ፍርድ ቤት ጉዳዩን መራው። በምላሹም ጥያቄውን እንደተረዱት ይህ “የመብት ጥያቄ ነው። ህገ-መንግሥታዊ መብት ነው የምትጠይቀው። ነገር ግን ይህ ጥያቄ በእኛ ደረጃ የሚታይ አይደለም። አንተ መፍትሔ የምታገኘው ፌደራል ፍርድ ቤት በመሔድ ነው። ” የሚል ነበር።
ፌደራል ፍርድ ቤት ባመራበትም ወቅት ያገኘው ምላሽ “ጥያቄህ መመሪያው እራሱ ህገ-መንግሥቱን ይፃረራል የሚል ስለሆነ መመሪያውን ያወጣው አካል ህገ-መንግሥቱን አላከበረም በሚል ለህገ-መንግሥት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማለትም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው ክስህን በማመልከቻ ማቅረብ ያለብህ። ” የሚል ነበር። ጉዳዩ አሁንም እልባት አላገኘም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ አቋርጦት የነበረ ሲሆን ክሱን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ እየተዘጋጀ ነው።

/ቢቢሲ/

LEAVE A REPLY