በዓይነቱ ከከርሞው በተለየ ታላቁዋ አሜሪካ ሰሞኑን ሀዘን ተቀምጣለች። አደባባይ ሙሉ ህዝብ እንደ በረት ከብት እያተራመሰ ከወደ ሰማይ ባራገፈው የጥይት ዝናም ካልጠበቀችው የጭካኔ ጎርፍ ውስጥ ከቱዋታል።
ይህ ሁሉ ሲሆን አሜሪካ ባንድ ወገን አስከሬንዋን እየለቀመች በሌላ፡ወገን ግን በገዳይና በሙዋቾች ትክክለኛ ስያሜ ላይ ሙግት ይዛለች። ይህ ሙግት ለኛ ለየዋህ አፍሪካውያን የዋዛ መስሎ ይታየናል ። አሜሪካ መሪር የዘመናት ሀዘን ቢደርስባትም ወንጀለኛውን “አሸባሪ “ ድርጊቱንም “አሸባሪነት” ለማለት እስካሁን በፍፁም አልደፈረችም። እንዲባልም ለሌላው አልፈቀደችም።
ለመሆኑ ስቴድየም ሙሉ ህዝብ አንደአልባሌ ተባይ አያሳደዱ በባሩድ የማንደድ ተግባር “አሸባሪነት” ካልተባለ በዚህ ዘመን ሌላ ምን ዓይነት ተግባር ነው “አሸባሪነት” ሊባል የሚችለው? ይህ የብዙዎች ጥያቄ ይመስለኛል። እዚህ ላይ የትርጉም ጠቅላይ ባለቤትነት ጥያቄና፡ ፖለቲካዊ ስሌቱ ብቻ ብዙ ሊያወያይ እንደሚችል ይገባኛል።
በበኩሌ በዚህ አጋጣሚ ላነሳው የፈለግሁት ነጥብ ግን ራሱ መጀመሪያ፡ ለ “ቃሉ “ ቦታና፡ ዋጋ፡ ሰጥቶ ከሀዘኑ ጎን ለጎን ሙግት መፍጠር የመቻሉን ምስጢር ነው። “ቃል“ ሀሳብን ይሸከማል። ፅንሰ ሀሳብ በረዥም ዘመናት ምርምር ፤ ልፋትና ኑሮ ውስጥ፡ በህዝብ ልቦና የሚሰርፅ የመግባቢያ፡ የመፈላሰፊያ በጠቅላላው የስልጣኔ የጋራ መሳሪያ ነው። ስለዚህ ቃል ሀሳብን የሚሸከም በውስጡም እምነትንና፡ እውቀትን ይዞ የግለሰብ ወይም የሀገር ማንነት ጭምር የሚገለጥበት የሰው ልጅ የረዥም ዘመን መኖርና መሰልጠን ትልቁ ምልክት ነው። የሰለጠኑ ሰዎችና፡ሀገሮች በፍትሀዊም ሆነ በፍርደ ገምድል መንገድ ግምባር ለግምባር ገጥመው ሲሙዋገቱ ቃልን ገምተው ቆጥበው ሲለዋወጡ የሚታዩት ዋጋውን/ፍቺውን በየስልጣኔያቸው ልክ ሰለሚሰፍሩት ነው። አሁን በደረስንበት ወቅት እንደአፍሪካውያን በተለይም እንደኛ እንደኢትዮጵያውያን “ቃል “ ሰብሉ ተለይቶት ማሳ፡ እንደቀረ ገለባ ሚዛኑ የቀለለ የማይሞቅ የማይቀዘቅዝ አንደባዶ ጣሳ የሚንኩዋኩዋበት ክፍለ ዓለም ያለ አይመስለኝም።
ከኛ ዘንድ “ቃል” ከፅንሰ ሀሳቡ ተፋትቱዋል። ከትርጉሙም ተለያይቱዋል። አሁን አሁን ንግግር የባዶ ቃል ድርት እንጂ የሀሳቦች ቅደም ተከተል ባለመሆኑ ዘንድሮ ለቃል ኪዳን የሚጉዋጉዋ በእርግማንም የሚደነግጥ ብዙ ሰው አይገኝም። ባጭሩ ቃል ምንዛሬው በአግባቡ ያልተተመነ ደረቅ ቼክ ሆኑዋል ማለት ይቻላል። መቆጠብ፤ መምረጥ ሀሳብና፡ ቃልን ማመጣጠን የማያሳስብ ጉዳይ ከሆነ ሰነበተ። ይህ ኪሳራ የአስተሳሰብና የዕውቀት ኪሳራ፡ ነው። ሌላ ቢቀር ለአሁንና፡ ለዛሬ እንኩዋን እርስ በርስ ባንድ ጉዳይ ላይ ፊት ለፊት ተግባብቶ ለመነጋገር ያለመቻላችን ዋነኛ ዕንቅፋት መሆኑ ነው የሚያሳዝነው።
አዚህ አገር እየኖረ ላለ ሰው ለዚህ ማስረጃ ማፈላለጉ ፌዝ ይመስለኛል። ቃል ያለፍቺ ፤ ቃል ያለሀሳብ ምጣኔ የሚነገርበት ቤትና መስሪያ ቤት መኖሩን እጠራጠራለሁ። ማስረጃ ግድነው ቢባል እንኩዋ ከመብዛቱ የተነሳ ቦታና፡ ጊዜም የማይበቃው ነው። በሁሉም የህይወት መስክ በተለይ በአለቃና፡ ሹመኛ ዘንድ ሀሳብን ወደ አቻ ቃልና፡ ፅንሰ አሳብ የመተርጎም ኪሳራ፡ገጥሞናል። (ያገራችን ሰው ሹመት ከእግዚሀር ነው ፤ ከሹመኛ የሚወጣም ቁዋንቁዋ ሁሉ ፡ያደባባይ ቁዋንቁዋ መስፈሪያ ነው ብሎ ስለሚያምን ክፉንም ደጉንም ከነምናምኑ ማስተጋባቱ አልቀረም ) እንዲሁ ላብነት ያህል አሸባሪነት የተባለው ቃል ራሱ አንዱ ነው። እሱ እንኩዋ፡ በብዙ ፖለቲካዊ ጉዋዙ የተነሳ፡ የብዙ ፖለቲከኞች ችግር ነው እንበል። አንድ ሰሞን “የመሬት ወረራ” የሚባል ቃል ኢትዮጵያዊ የመንግስት መስሪያ፡ ቤት በኢትዮጵያውያን በራሳቸው ላይ ካልተጠቀምኩ ሞቼ እገኛለሁ ሲል ሰማሁና ባደባባይ ጥቂት ልከራከር ሞክሬ ነበር። “የመሬት ወራራ” ውቅያኖስና፡ ተራራ፡ አቁዋርጠው ለመጡ በመልክም በተግባርም የማይመሳሰሉ ባዕዳን ለሚፈፅሙት አረመኔያዊ ተግባር የምንጠቀምበት የዚያ ድርጊትና መዘዙ ጥቅል ትርጉም መሆኑ እየታወቀ በገዛ ሀገሩ ላይ ቢጨንቀው በህገ ወጥ መንገድ እትብቱ የተቀበረበትን ምድር ሙጥኝ ልኑርበት ያለውን ያገሩን ዜጋ ከግራዚያኒ ወታደሮች እኩል “ወራሪ” የሚል ስያሜ መስጠት፤ እሱንም አርሙ ሲባል በኩራትና በግብዝነት መደጋገም የስልጣኔያችን ኪሳራ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። እንዲህ በግዴለሽነትና፡ በማናለብኝነት የምንሸጉራቸው አያሌ ቃላት እያደር በደመነፍሳችን ተንሰራፍተው መተሳሰሪያችንን እንደብል እየበሉ የሚያነትቡ ናቸው። በየአደባባዩ በየሸንጎውና፡በየሚዲያው የሚንኩዋኩት ባዶ “ቃላት” ልክና ቅጥ ከማጣቱ የተነሳ ያደባባይ ቁዋንቁዋ መስፈሪያም የሆኑ ይመስላል። እዚያማ ቃል ብቻ፡ ሳይሆን ሰዋስው ራሱ የተለወጠ ይመስላል። ቁዋንቁዋ በርግጥም ይለወጣል ይሻሻላል ነገር ግን ባዶውንና፡ራቁቱን መንኩዋኩዋቱ መለወጡንም መሻሻሉንም አያሳይም።ይልቁንም እንዳሻው የሚንኩዋኩዋ የባዶ ቃል ትርምስ እርሱ አንዳች ነጠላ ምልክት ይሆን እንደሁ እንጂ ሀሳብን የመሸከም ዐቅም አይኖረውም። ፍልስፍናንማ፡ በማን ዐቅሙ። እኛ ግን የሰውን ያህል እንመዝናለን። እኛም የራሳችን ስልጣኔ አለን የምንል የቃል ዋጋው እንደምን አልገባን አለ። አሜሪካም በዚህ መሪር ሀዘን መካከል ስለ ቃል ስትሙዋገት ዋጋው በስልጣኔ ሂሳብ መሰፈሩ አሁንም አልታየን ይሆን?