አሜሪካ “Mixed race” (ቅይጥ ዘር) እያለች በዳታቤዟ መመዝገብ የጀመረ በጣም ዘግይታ ነበር። ከዚያ በፊት በደፈናው ነጭ፣ ጥቁር… እያለች ነበር የምትመዘግባቸው። በአስተሳሰብ ደረጃ ዛሬም ያው በቀድሞው መልኩ ነው የሚታሰበው። ታዲያ የነጭና ጥቁር ቅይጥ ሰዎች ሁሌም ጥቁር ተብለው ነው የሚታሰቡት። ከወላጆቻቸው በአንዳቸው ጥቁር የሆኑ ሰዎች ጥቁር ነው የሚባሉት። ከአራት አያቶቻቸው በአንዳቸው ብቻ ጥቁር የሆኑ ሰዎችም ጥቁር ነው የሚባሉት። ምክንያቱ ደግሞ ዘረኝነት ነው። ውኃ ላይ ትንሽም ይሁን ብዙ ቆሻሻ ከተጨመረበት ውኃው ቆሽሿል ነው የሚባለው። ልክ እንደዛ ነው የጥቁር ዘር የተቀየጠበት ነጭ ጥቁር የሚባለው። የነጩ ዘር በጥቁር ተበክሏል እንደማለት። ባራክ ኦባማ ጥሩ ምሳሌ ነው።
፩) እኔ የሆነ ነገር በጻፍኩ ቁጥር (ጽሑፉ ትክክልም ይሁን ይሳሳት) የዘውግ ቡድን ይፈለግልኛል፣ እንደታርጋ ይለጠፍብኛል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ጮክ ብሎ የሚሰማው ደግሞ “ግማሽ እንቶኔ፣ ግማሽ እንቶኔ” የሚለው አጠራር ነው። በዚህ መልኩ “ትንሽም ቢሆን እንቶኔ በዘር ሐረጉ ጠብ ካለ፣ በውስጠ ታዋቂነት ተቀባይነት ያለው የጅምላ ፍረጃ አስተሳሰብ ሰለባ ነው ማለት ነው” ለሚለው ክርክር መንገድ ይተዋሉ። ይህን አካሔድ ለመከላከል (“ራሴን ነጻ ለማውጣት”) ከኔ የሚጠበቀው እዚህ ወጥቼ የዘር ሐረጌን እየዘረዘርኩ እንዳስረዳ ነው። እምቢ፣ ዘር አልቆጥርም!
፪) “ስለዘውግ ማውራት አልፈልግም” የሚሉ ተቃዋሚዎችን (ቢያንስ በብዛት) የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር ቢኖር፣ ትግራዋዮችን ለማጥላላት እና የመሳሰሉትን ለማውራት ሲሆን ዘውግን አይጠየፉትም። ስለዘውግ ቡድኖች የፖለቲካ ንቅናቄ ማውራት እና ዘረኝነት የሚያገናኛቸው ነገር የለም። ጭራሹኑ አይወራ የሚሉ ካሉ ሊደብቁት የሚፈልጉት ነገር አለ ማለት ነው። “እኛን ተወን፣ እነእንቶኔን እና እነ እንቶኔን ስደብልን” የሚል አስቂኝም፣ አሳዛኝም አስተያየት ይደርሰኛል። አንደኛ፣ “እኛ” የተባሉትንም ይሁን “እነ እንቶኔ” የተባሉትን አልሳደብም። እስካሁን የጻፍኩት ውስጥ ይሔኛው ስድብ ነው የሚል የለም በጥቅሉ አንድ ሰው ተነስቶ የሆነ ቡድንን ወክሎ ተሰደብን ሲል፣ ሌላው ተከትሎ ሳያረጋግጥ ይንጫጫል። ሁለተኛ፣ ስለማንኛቸውም ቢሆን የምናገረው ሲኖረኝና መናገር እንዳለብኝ ሲሰማኝ እናገራለሁ እንጂ ቲፎዞ ለማፍራት ወይም ትችት እና ዘለፋ ሽሽት ርዕስ አልመርጥም፣ ስለእነቶኔ እና እንቶኔ በፈረቃ አልጽፍም። እምቢ፣ በትዕዛዝ አልጽፍም!
፫) ታስሮ መፈታት በአሉታዊ መንገድ እንደሚቀይር የማይጨበጥ ወሬ ይናፈሳል። አዎ፣ ታስሮ መፈታት ሽርሽር ደርሶ እንደመመለስ አይደለም። ፈታኝ ነው። ለዓላማ የታሰሩ ሰዎች የታሰሩለትን ዓላማ እስር ይመጥነው እንደሁ መጠየቃቸው አይቀርም። ሁሉንም ለመፈተሽ፣ ራስን ለመገምገም ዕድል ይሰጣል። ስለ ፍትሕ እና ትርጉሙ፣ እንዴት ሊገኝ እንደሚችል እና እንደማይችል ያመራምራል። ትላንትና ዛሬ፣ ዛሬና ነገ፣ ብሎም ትላንትና ነገ ያላቸውን ግንኙነት ያሳስባል። በቀረርቶና ሽለላ ለውጥ እንደማይመጣ፣ በማሸማቀቅና በማጥፋት ለውጥ (የለውጥ ጥያቄ) ተዳፍኖ እንደማይቀር ያስገነዝባል። እኔም በነዚህ ከባድ ንድፈ ሐሳቦች ተንጫለሁ። አውርቼባቸዋለሁ። አንብቤባቸዋለሁ። በርግጥ በተቃራኒው ቂምና በቀል ይዞ የሚወጣ ይኖራል። እኔን ግን ይህ አይወክለኝም፤ ስለ ፍትሕ፣ ስለሰብኣዊ ክብር፣ ስለ ትግል ያለኝ ተቆርቋሪነት እና ቁርጠኝነት ጨመረ እንጂ አልቀነሰም። ወንጀል ሠርቼ ታስሬ አላውቅም። የግፍ እስረኝነቴን ተረድተው “ይፈታ” ብለው የጮሁልኝን አመሰግናለሁ። እነርሱ የሚወዱትን የምወድ፣ የሚጠሉትን የምጠላ መስሏቸው ድምፃቸውን ላባከኑ ግን አዝናለሁ። ነገር ግን ከእስር ሲፈቱ አድማጮች መስማት የሚፈልጉትን እንደበቀቀን ሲያስተጋቡላቸው እያጀገኑ፣ በተቃራኒው የምር የሚሰማቸውን ሐቅ ለመናገር የደፈሩትን የሚዘልፉና የሚፈርጁ የነጻነት ፀሮች ናቸው። ገና ለገና “ታስረህ ሳለህ ጮኸንልሃልና እኛ መስማት የምንፈልገውን ብቻ ተናገር” የሚለኝን አልቀበልም። ይህ ማለት ለኔ የእስር ቤት ምርጫ እንደመስጠት ነው። ሊያፍኑኝ በሞከሩ ቁጥር የበለጠ እናገራለሁ እንጂ፣ እምቢ፣ አልሸማቀቅም!
፬) ከወጡልኝ ሥሞች መካካል “ዳግማዊ ዋለልኝ” የሚል ይገኝበታል። ስለኢትዮጵያ የብሔር ጥያቄ መጣጥፍ የጻፈው የ‘ያ ትውልድ’ ወጣት ዋለልኝ መኮንን ጋር እየመሰሉኝ መሆኑ ነው። ሥም አወጣጡ እሱ ከጻፈውም፣ ካልጻፈውም ጋር በተገናኘ ሁኔታ ነው። ዋለልኝን (በተለይም ወግ አጥባቂ ሆኖ አጭር ቀሚስ ይቅር ዓይነት ክርክር በማድረጉ) አላደንቀው ይሆናል። የብሔር ጥያቄ ላይ የጻፈውን ጽሑፍ ግን መቼም የሐፍረትና የማሸማቀቂያ ምንጭ አድርጌ አስቤው አላውቅም። በሱ ደረጃ ተቃራኒ መጣጥፍ የጻፈ ምሁር/ታጋይም የለም። እንዲያውም፣ ዋለልኝ ወሎዬ – አማራ ሆኖ፣ እኔ አለሁበት ሳይል ፍትሕን ብቻ መሠረት አድርጎ መሟገቱ ሊያስመሰግነው በተገባ ነበር። ይህ ዓይነቱ ትችት “የእንቶኔ ቡድን እነ አንቶኔን ብቻ ነው መደገፍ ያለበት” ከሚል የመጣ ነው። ስለዚህ ሥም አወጣጡ “የእንቶኔ ቡድን አባል ነህ፤ ለዚህ ቡድን ወግን” የሚል ነውና እምቢ፣ አልወግንም!
፭) “የወቅቱ ጠላታችን ወያኔና ወያኔ ብቻ ነው፤ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው” የሚል ጥቅል ምክር ተመክሬያለሁ። እኔ ግን በጠላት አላምንም። ኢትዮጵያ የአምባገነኖች አገር የሆነችውም ዛሬ በኢሕአዴግ አስተዳደር ብቻ አይደለም። አምባገነኖቻችን ከኛው የወጡ የኅብረተሰባችን ክፍሎች ናቸው። እኔ የምፈልገው ነጻነትና ዕኩልነት ከወዳጅነት ጋር ነው። እነዚህ የሚመጡት ሁላችንም እንደ ዜጋ ነጻነታችን ሲከበር፣ በፍትሕ ዓይን በዕኩል ስንታይ፣ እንዲሁም በወዳጅነት የምንከባበርባት አገር ስትፈጠር ነው። ወደዚህ የሚወስደን መንገድ ብዬ የማምነው በየቡድኑ አለቃና ምንዝር፣ ጠላትና ወዳጅ ተደራርገን የምንተያይበትን መንገድ ማኅበረሰባችን ላይ በመሥራት በመቅረፍ ነው ሕልሜ። የዛሬ ታጋዮች የነገ ባለድል/መንግሥት ሊሆኑ ይችላሉ። ተረኛ ጨቋይ፣ ተረኛ በላተኛ እየሸነገልኩ አላሳድግም። የለውጥ አማጪዎች የሚጠሉትን እንጂ የሚፈልጉትን ሳያውቁ ሲቀሩ አደገኛ ነው። ነገሩ ዶ/ር ነገደ ጎበዜ “መጀመሪያ ንጉሡ ይውረዱ እንጂ የሚመጣው ችግር የለም አልን፣ ቀጥሎ ደርግ ይውረድ እንጂ ችግር የለም አልን፣ አሁን ደግሞ ወያኔ ይውረድ እንጂ እያልን ነው” እንዳሉት ነው። ዋናው ትኩረቴ ዋናው ሥልጣን፣ መሣሪያ እና ኢኮኖሚውን የተቆጣጠረው አካል መሆን እንዳለበት ባይጠፋኝም የነገውን ባለተራ ኢፍትሐዊ አካሔድ በአጋርነት ሥም እምቢ፣ ኢፍትሐዊነትን አልደግፍም!
፮) “አውቀህ ያልጨረስከውን ነገር አትናገር” የሚል ተግሳፅም ደርሶኛል። ምክሩ መልካም ቢመስልም የሳንሱር ማድረጊያ የዋህ አካሔድ መሆኑንም አውቃለሁ። በምድር ላይ አውቆ የጨረሰ ሰው የለም። እርግጥ ነው ምንም ስለማያውቁት ነገር መናገር ተገቢ እንዳልሆነ (ወይም ግምት እንደሆነ ማሳወቅ እንደሚያስፈልግ) ይገባኛል። ነገር ግን እኔ የተናገርኩት ላለፉት ዐሥርት ዓመታት ደጋግሞ ሲነገር የነበረ ነገር ነው። ሲሆን ሲሆን ክፍተቴን በከፊል የሚሞላልኝ ተጨማሪ መረጃ ቢሰጠኝ መልካም ነበር። ሳይሆን ንቆ መተውም ያዋጣል። ዝም በል ማለትን ግን አልቀበልም። የሰው ልጅ እውቀትን እና ነጻነትን እየፈለገ ይኖራል እንጂ ጨርሶ አያውቅም፣ ጨርሶ ነጻ አይወጣም። እኔም በማይሆን ሰበብ ተሸንግዬ እምቢ፣ ዝም አልልም!
፯) እኔን ተአማኒነት ለማሳጣት በጣም ብዙ ስልቶች ተሞክረዋል። ማጥላላት (በተለይም በሕዝብ ተጠልተዋል ተብለው ከሚታሰቡ ቡድኖችና ሰዎች ጋር ሐሳቤን በማመሳሰል ወይም ግንኙነት እንዳለኝ በማስመሰልና የአንድ የኅብረተሰብ ክፍል ጠላት ነው በማለት)፣ ማጣጣል (በተቻለ መጠን እኔ የምናገረው ሁሉ የማይረባ ነገር እንደሆነ በቀልድም በቁምነገርም በማናናቅ)፣ በመጠምዘዝ (ያላልኩትን ነገር አለ በማለት)፣ እና በስድብ (በተለይም ሐሳቡ ውስጥ እውነት የታያቸው አስተያየት ከመስጠት በፍርሐት ተሸማቀው እንዲቀሩ በማድረግ) እና ወዘተ ናቸው። እኔ ግን ለነዚህ ዓይነቶቹ መልስ በመስጠት አላከብራቸውም። ይህ ደግሞ በኔ ብቻ የመጣ አይደለም። እዚሁ ፌስቡክ ላይ እንዳየነው፣ አገራቸውን ሲያገለግሉ የኖሩ ሽማግሌዎች ሳይቀሩ ሥነ ምግባር በማያውቁ ሰዎች ተዋርደዋል። በበኩሌ፣ የፈለገውን ያህል ያጥላሉኝ፣ ያጣጥሉኝ፣ ንግግሬን ይጠምዝዙ፣ ይስደቡኝ እንጂ ለእንዲህ ዓይነቶቹ የሐሳብ እና የውይይት ፀሮች (መሐይምነትን እና ጭቆናን ያበረታታሉና) እምቢ፣ አልንበረከክም!
በመጨረሻም በዚህ ሁሉ መሐል፣ በግርግሩ ሚዛን ሳይታለሉ፣ ከጽሑፉ ውስጥ ትክክል ወይም ስህተት የመሰላቸውን መርጠው እነርሱ ያላቸውን ሐሳብ ለመጨመር ወይም ለመሞገት ለተፍጨረጨሩት ሰዎች ያለኝ ክብር ግን ከክብር ሁሉ የላቀ ነው። ለአገራችን አዎንታዊ ለውጥ ተስፋ እንዳላጣ የሚያደርጉኝ እንደነዚህ ዓይነት ቀና ሰዎች መኖራቸው ነው። ከእልፍ ባለጌዎች ጩኸት ይልቅ የጥቂት ጨዋዎች ግርማ ያንበረክከኛል። እነርሱ ይናገሩ እንጂ እኔ ልቤን ከፍቼ አደምጣለሁ!