አገራዊ አሰባሳቢ ማንነት ቋንቋ (ብሔር) ወይስ ዜግነት? /አዲስ ጀምበር/

አገራዊ አሰባሳቢ ማንነት ቋንቋ (ብሔር) ወይስ ዜግነት? /አዲስ ጀምበር/

በአንድ ሀገር ውስጥ ተመሳሳይ ወይም የተለያየ ቋንቋ ፣ ባህልና ዕምነት ያለው የተወሰነ ሕዝብ ይኖራል። ሀገሩ የነዋሪው፣ ነዋሪውም የሀገሩ ባለቤትና ዜጋ ነው። የሰው መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በእኩልነት ሲረጋገጡ ሕዝብ አብሮ በጋራ ይኖራል። ሰው ከመብቱና ከነፃነቱ፣ ከእኩልነቱ እና ከፍትሐዊ ተጠቃሚነቱ በላይ የሚፈልገው ጉዳይ የለም።

ይህን መሠረታዊ የሰው ፍላጎት የሚያረጋግጥና የሚያስከብር ኢትዮጳያዊ ሀገራዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት በምን መነሻ፣ እሳቤ፣ ወይም ማንነት ላይ ተመስርቶ ይዋቀር፣ ይደራጅ፣ ይስራ የሚለው ጉዳይ ኢትዮጵያውያንን በስፋት እያነጋገረ ሲሆን፣ ቋንቋ (ብሔር) እና ዜግነት ጎልተው የወጡ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆነዋል። አማራጮች ጠቃሚ መማማሪያ የሚሆኑት ተዋንያን የምኞት ፖለቲካቸውን ትተው፣ በመረጃ እና በማስረጃ ላይ ተመስርተው፣ ከስሜት ውጭ ሆነው ፣ በእኩልነት እና በመከባበር በሰለጠነ መንገድ መነጋገር ሲችሉ ነው። ይህን ተስፋ በማድረግ የሁለቱን አማራጭ ሀገራዊ አሰባብሳቢነት አቋም፣ ዓላማ እና ግብ እንመልከት። የቋንቋ ሀገራዊ አሰባሳቢነት አቋም መነሻ ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች ሀገር ናት፣ ብሔረሰቦች የራሳቸው ባለቤት ሆነው ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድሩ፣ ብሔረሰቦች በመፈቃቀድ የቋንቋ ፌዴሬሽን መሥርተው አብረው ይኑሩ፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትም የቋንቋ ፌዴሬሽን ውጤት ሆነው ይቀጥላሉ የሚል ነው።

እውነት ነው ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔረሰቦች ሀገር ናት፣ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ለዘመናት የኖሩት የብሔረሰቦች አጥር ከልለው ፣ በየክልልላቸው ተወስነው ማዶ ለማዶ እየተያዩ ሳይሆን በፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ሥር በጋራ ያሳለፉት የመከራ እና የሰቆቃ ዘመናት፣ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እና ሉዐላዊነት ለማስከበር የከፈሉት የጋራ መሰዋትነት ፣ የህዝብ የሀገር ውስጥ ፍልሰት ወይንም እንቅስቃሴ፣ የርስ በርስ ጋብቻ፣ የቋንቋ እና የባህል መወራረስ፣ በጥቅሉ ሕዝብ በመካከሉ የመሠረታቸው ሰፊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች፣ ትሥሥር እና መስተጋብር በፈጠሩላቸው የጋራ ታሪክ ፣ ባህል  ሥነ ልቦናና ማንነት በአጠቃላይ በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ በዜግነት ተሰባስበው ክፉ እና ደጉን፣ ጭቆና እና በደልን በአንድነት ተጋርተው ነው። ይህን ሁኔታ ነው ቋንቋ ሀገራዊ አሰባሳቢ ማንነት ሆኖ ከ1983 ወዲህ ዜግነትን የተካው።

የቋንቋ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለማስቀጠል በማለት ኢትዮጵያን በብሔረሰቦች ክልል ሸነሸነ ፣ ብሔረሰቦችን በየክልልላቸው ወሰነ፣ ያአንድ ብሔረሰብ ክልል ለሌሎች ብሔረሰቦች ክልክል በመሆኑ ብሔረሰቦች ማዶ ለማዶ መተያየት ጀመሩ ፣ በድንበር እና መሬት ይገባኛል ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት ገቡ ፣ ኢትዮጵያ ወደ ብሔረሰቦች ክልል፣ ኢትዮጵያዊነት እና ዜግነት ወደብሔርነት ወረዱ፣ የግለሰብ መብት እና ነፃነት በየብሔረሰቡ ክልል ተገደበ ፣ እነዚህ ሁሉ የቋንቋ ፌዴሬሽን ትሩፋት ናቸው። በዚህ አጋጣሚ የቋንቋ አጠቃቀም (ፖሊሲ) እና የቋንቋ ፌዴሬሽን የተለያዩ መሆናቸው ግልፅ ሊሆን ይገባል። የቋንቋ ፌዴሬሽን መንግሥት የተዋቀረበት መሠረት ሲሆን፣ የቋንቋ አጠቃቀም ወይንም ፖሊሲ የእኩልነት እና የዲሞክራሲያዊነት ጉዳይ ነው።

በካናዳ ሁለት ቋንቋዎች፣ በስዊትስዘርላንድ ሦስት ቋንቋዎች በእኩልነት ደረጃ ኦፊሺያል (የሥራ)ቋንቋ በመደረጋቸው ካናዳ እና ስዊትስዘርላንድ የቋንቋ ፌዴሬሽን እንደሆኑ ፣ በቋንቋ ፌዴሬሽንም ዜጎች በነፃነት እና በእኩልነት አብረው መኖር እንደሚችሉ ለማሳየት የሚደረግ ሙከራ አለ። ዕውነታው ግን ካናዳም ሆነ ስዊትስዘርላንድ የቋንቋ ፌዴሬሽን አይደሉም። ካናዳ የክፍላተሀገራት እና የግዛቶች (Provincial and territorial administrative division)፣ ስዊትስዘርላንድ የካንቶኖች (Cantons are administrative and political sovereign states) ሕብረት (Union) ውጤቶች ናቸው። የሁለቱም ሀገር ህዝቦች በእኩልነት እና በነፃነት አብረው የሚኖሩት በብሔረሰብነታቸው ወይም በቋንቋቸው ሳይሆን በዜግነታቸው ነው ። ሌሎችም ፌደራል እና ኮንፌደራል መንግሥታት በተለያየ መመዘኛ (መልካዓ ምድር፣ ቋንቋ፣ አስተዳደር፣ ልማት፣ ደህንነት፣ ውጭ ግንኙነት …)ቅንጅት የተመሠረቱ የአስተዳደር እና የፖለቲካ መንግሥታት ህብረት ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። የዜግነት ሀገራዊ አሰባሳቢነት መሠረታዊ መነሻ ሀገር የማንም ሳይሆን የዜጎች ብቻ ናት፣ ዜግነት የግለሰብ እንጂ የድርጅት፣ የተቋም ፣ የቡድን፣ የማህበረሰብ ወይም የብሔረሰብ አይደለም፣ ዜጎች የየትኛውም ሥብሥብ እና ተቋም አባል ይሁኑ እንደ ዜጋ እኩል መብት እና ግዴታ ኖሯቸው በየትኛውም የአገራቸው ክፍል በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የመኖር፣ የመሥራት፣ ሐብት ንብረት የማፍራት፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት እና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸው ይከበራል፣ ይጠበቃል፣ በአጠቃላይ የግል፣ የዜግነት እና የወል መብት እና ነፃነት በእኩልነት እና ፍትሐዊነት ይከበራል የሚል ነው። የቋንቋ እና የዜግነት ሀገራዊ አሰባሳቢነት አቋም ፣ መነሻ እና መድረሻ በስፋት ታይተዋል ፣ የሁለቱም ዓላማ በአባባል ደረጃ ኢትዮጵያን እና ኢተዮጵያዊነትን ማስቀጠል ፣ ዜጎች በእኩልነት እና በነፃነት አብረው በጋራ እንዲኖሩ የሚያስችል ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት መመሥረት ነው ቢሉም መነሻ እርሾአቸው የተለያየ በመሆኑ ተመሣሣይ ውጤት ላይ መድረስ እንዳልቻሉ ግልጽ ሆኗል ። የቋንቋ ፌዴሬሽን መነሻው ልዩነት ሲሆን የፌዴሬሽኑ አባላትም የየራሳቸው ክልል/ሀገር ፣ ህገ መንግሥት ፣ ቋንቋ እና ባህል ያላቸው ስለሆነ፣ በመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ብለው እንሁን ያሉ፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የጋራ ማንነታችን ነው ለማለት ያልደፈሩ፣ በኢትዮጵያ አገራዊ ጣራ ውስጥ የኢትዮጵያ አካልነታቸውን ሳይቀበሉ በየአካባቢያቸው የተደራጁ፣ እንደልጅ በእናታቸው በኢትዮጵያ ዙሪያ መሰባሰብ ያልፈለጉ፣ ዜጎችን እንደ መንግሥታዊ ግዴታ ሳይሆን እንደ እንግዳ ተቀባይ የሚፈልጉትን የሚያስገቡ ያልፈለጉትን የሚያባርሩ፣ ኢትዮጵያዊነት እና ብሔርነት ጣምራ ዜግነት ሰጥተው ኢትዮጵያውያንን የባሕር ላይ ኩበት የአደረጉ በአጠቃላይ በልዩነት ላይ የብሔር መንግሥታት መሥርተው እንደተለያየ ሀገር መንግሥታት በጉርብትና የሚኖሩ በመካከላቸው ምንም ዓይነት የጋራነት አይኖርም፣ ቢኖርም ግጭት ነው። የብሔረሰቡ አባል የሆኑ ግለሰቦች በክልልላቸው እስካሉ ድረስ የመብት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይቸላሉ፣ ከክልልላቸው ሲወጡ ግን የህግ ማእቀብ ባይኖርም በርካታ የመብት እና የነፃነት ሳንካ ይገጥማቸዋል።

ነገሩን በበለጠ ለመረዳት ትግራይን በምሳሌነት ወስደን እንመልከት። የትግራይ ብሔራዊ ክልል የትግሬዎች መሆኗን በህገመንግሥታቸው አውጀዋል፣ በዚህ ክልል የሌሎች ብሔረሰቦች አባላት መኖር ቢችሉም የሚኖሩት እንደ ትግሬዎች እኩል ባለቤት ሆነው ሳይሆን በልዩነት የብሔር ማንነታቸውን (ኦሮሞ ፣ አማራ ፣ አፋር …) የሚለውን በግንባራቸው ለጥፈው ነው። ከዚህም የተነሳ የመብት እና የነፃነት ችግር ይደርስባቸዋል፣ የለም አይደርስባቸውም፣ ህግ እና ዲሞክራሲን በማሟላት መብት እና ነፃነታቸው በእኩልነት ይከበራል የሚል አነጋገር ይሰማል፣ ይህ አባባል እውነትማ ቢሆን አባይ ወልዱ ራያ ሔዶ ትግርኛ የማታውቁ ውጡ ባላለ ነበር፣ የቋንቋ ፌዴሬሽን መጀመሪያ የራያን ሕዝብ መሬት ነጠቀ፣ ቀጥሎም የራያን ህዝብ የተፈጥሮ ነፃነት፣ ህልውናና ማንነት ቀማ። ዶሮን እንቁላል ሳይሆን ድንጋይ አስታቅፎ ጫጩት መፈልፈል እንደማይቻል ሁሉ፣ የቋንቋ ፌዴሬሽንም የፈለገውን ህግ እና ዲሞክራሲ ቢታቀፍም ተፈጥሮው፣ እርሾው እና አስኳሉ ስለማይፈቅድለት እኩልነትን፣ አንድነትን እና የጋራነትን መፈልፈል አይችልም ፣ ይህ እቅፍ በዜግነት ላይ ለተመሠረተ መንግሥት ቢሆን ኖሮ እኩልነትን፣ ነፃነትን እና አንድነትን ለመፈልፈል ባልገደደ ነበር።

በመሠረቱ ልዩነት ክፍፍል ነው፣ ክፍፍልም ሽሚያን ፣ ሽሚያ ግጭትን ፣ ግጭት ደም መፋሰስን ያስከትላሉ ፣ ዛሬ በድንበር ግጭት የሚፈስው ደም ፣ ክልልላችሁ አይደለም ብሎ ማባረር ፣ የሐብት እና የንብረት ሽሚያ ፣ ብሔርነትን (መታወቂያ) በኪስ ይዞ መዞር ፣ የአንድ ብሔረሰብ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ የበላይነት ፣ የቋንቋ ፌዴሬሽን ወይም የልዩነት እርሾ ውጤቶች ናቸው ። የልዩነት እረሾን ምንም አይነት ህግ እና ዲሞክራሲ ወደ ሀገራዊ አሰባሳቢ ማንነት ሊመልሰው ስላማይችል አማራጩ የአቋም ለውጥ ማድረግ ወይም በቁርጡ ከነእጣ ፈንጣጣው መለያየት ነው ። የዜግነት አገራዊ አሰባሳቢነት ማንነት መነሻ ግለሰብ ሆኖ ዓላማው የዜጎችን መብት እና ነፃነት በእኩልነት ማስከበር እና ማስጠበቅ ነው ። ዜግነት መነሻው ሰው ነው ፣ ሰው ሁሉ በተፈጥሮው ነፃ እና እኩል ነው ፣ ሰው እኩልነቱን ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነቱን ፣ መብቱን እና ነፃነቱን ምን ግዜም ማጣት አይፈልግም ፣ መብቱ እና ነፃነቱ የተከበረለት ሰው ሁሉ እንደ ሕዝብ አብሮ መኖር አይቸግረውም ፣ የሰው የጋራ ባሕሪ እና ፍላጎት የሆነውን እኩል መብት እና ነፃነት ለማስከበር ዜግነት አመች ሀገራዊ አሰባሳቢ መድረክ ሆኗል ። ሰው እንደ ግለሰብ የግል መብቱ እና ነፃነቱ ፣ እንደዜጋ የጋራ የዜግነት መብቱ እና ነፃነቱ ፣ እንደ አባል የወል መብቱ እና ነፃነቱ በእኩልነት ስለሚከበርለት ከመብት ውጪ የሚሆን ዜጋ አይኖርም ማለት ነው። ያም ሆኖ ግን የሚነሱ የመብት እና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች የሉም ማለት አይቻልም፣ አሉ፣ በተለይም ለብሔረሰቦች መብት መከበር በቂ ትኩረት አይሰጥም የሚለው የጎላ ትችት ነው። እነዚህ ችግሮች የዜግነት አሰባሳቢነት ባህሪ፣ ወይም እርሾ የፈጠራቸው ሳይሆን በተለያዩ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚከሰቱ ናቸው።

መልካሙ ነገር ችግሮቹ ህግ እና ሥርዓትን በሟሟላት ፣አሰራር እና አፈፃፅምን በማሻሻል ፣ የህግ የበላይነትን በማጠናከር አቅምን በማሳደግ፣ ዲሞክራሲያዊ ባህልን በማዳበር ይፈታሉ። በዜግነት ላይ የተመሠረተ ፌደራል መንግሥት የብሔረሰብን መብት ለመፍታት አመቺ እና አስተማማኝ መድረክ ነው፣ በዚህ መድረክ ትንሽ እና ትልቅ፣ የሚከበር እና የማይከበር የሚባሉ ነፃነቶች እና መብቶች የሉም፣ ሁሉም በእኩልነት ይከበራሉ።

LEAVE A REPLY