ነገሮች ጥሩ አይመስሉም። ንፋሱ ወዴት አቅጣጫ እንደሆነ ለመተንበይ የሚቸግር ግን አይደለም። የሆነ መስመር ግልጽ እየሆነ የመጣ ይመስላል። አሰላልፍ ላይ ማን ከማን እንደቆመ ምልክት መታየት ጀምሯል። የወታደሩ ክፍልና በፌደራል መንግስት ላይ ሃይለማርያምን የሚመራው የህወሀት ቡድን ሚናቸውን ለመረዳት የሚያስችል ክስተቶችን ከሰሞኑ እየታዘብን ነው። በተለይም በሁለቱ ክልሎች (ኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ) መሃል ተነሳ የተባለው ውዝግብ ማን ከማን እንደተሰለፈ በብልጭታ ደረጃ የሚያሳይ ነገር አለው። የአባዱላ ገመዳ የስራ መልቀቂያና ለኢቢሲ የሰጡት መግለጫ ላይ ”ለጊዜው ሆድ ይፍጀው” ያሉበት ምክንያታቸው ይህንኑ ጥርጣሬአችንን የሚያጠናክር ነው። የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት የዛሬው ቆንጠጥ፡ መረር ያለው ማስጠንቀቂያም የሚያመላካተን አሰላልፉ ግልጽ እየሆነ መምጣቱን ነው።
ሁኔታዎች ሊቀያየሩ ቢችሉ የሚለውን ከግምት በማስገባት አሰላልፉን ለመግለጽ ያህል የህወሀት ጄነራሎች ከሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳንት ጎን ቆመዋል። ቀድሞውኑም ሶማሌ ክልልን በተለየ ሁኔታ የሚፈነጭበት የህወሀት ወታደራዊ አዛዦች ከአብዲ ኢሌ ጀርባ ሆነው ይሄን ሁሉ ትርምስ የሚፈጥሩ ለመሆናቸው በርካታ መረጃዎች ይወጣሉ። ዛሬ የኮሚኒኪሽን ጽ/ቤቱ ማስጠንቀቂያ የሚነግረን ቢኖር ሶማሌ ክልል በፌደራል መንግስቱ አልታዘዝም ማለቱን ነው። እነጄነራል አብረሃም ወልዴ(ኳርተር) የሶማሌ ክልል ስውር መሪዎች ናቸው። በክልሉ ስም የሚወጡ ማናቸውም መግለጪያዎች የሚጻፉት በእነዚህ የህወሀት ጀኤነራሎች ስለመሆኑ ከጥርጣሬ ያለፈ ጉዳይ ነው። አብዲ ኢሌ እንደፈለገው እንዲናገር፡ እንዲያስፈራራ፡ የጦርነት ነጋሪት እንዲጎስም የሚያደርጉትም እነሱ ናቸው። የጅምላ መፈናቀል በተከሰተበት ጊዜ የመከላከያ ሰራዊቱ ምንም እርምጃ አለመውሰዱ የአጋጣሚ ጉዳይ አልነበረም። ሁለቱ ክልሎች ብረት ተማዘው ሲገዳደሉ፡ መከላከያ ሰራዊቱ ማስቆም እየቻለ ያላደረገውም ”ህገመንግስቱ ስለማይፈቅድለት” የሚል ጅላጅል ምክንያት መስጠት የሰውን የማገናዘብ አቅም መፈታተን ነው። የኦሮሞው አክቲቪስት ገረሱ ቱፋ በፌስ ቡክ ገጹ እንዳስነበበን፡ ሁለት ከፍተኛ የኦህዴድ አመራሮች ከግድያ ሙከራ አምልጠዋል። የግድያ ሙከራውን አደረገ የተባለው ደግሞ መከላከያው ነው። እነጄነራል አብረሃም ወልዴ(ሳሞራ በበላይነት) የሚያዙት መከላከያ ማለት ነው።
የአባዱላ መልቀቅ የሚፈነጥቀው የእነሳሞራ ወታደራዊ ቡድን አይኑን ጭፍኖ እየሸመጠጠ ያለበትን መስመር ነው። አባዱላ ለጊዜው አልናገርም ብለዋል። ይህም የሆነ አንዳች ነገር እንዳለ ጠቋሚ ነው። አባዱላ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ስለመሆናቸው ይነገራል። ከእነሳሞራ ጋር ቢሆኑ ኖሮ ሆድ ይፍጀውን ትተው ምክንያታቸውን አፍረጥርጠው ይናገሩ ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ። ፌደራል መንግስቱ ጥርስ አልባ የሆነ ይመስላል። ወታደሩ ክፍል ስውር መንግስት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ምናልባት ግልበጣም ሊከሰት ይችላል። በዚሁ ከቀጠለ የግብጹ አልሲሲ እንዳደረገው እነሳሞራሞ መለዮአቸውን አውልቀው በሲቪል ቆብ አራት ኪሎ ቤተመንግስት ለመግባት የሚከለክለው ሃይል የለም። አንድ በቅርበት የማውቀው የቀድሞ የሰራዊቱ ከፍተኛ አዛዥ እንደነገረኝ የመንግስት ግልበጣ ሊከሰት የመቻሉ እድል ሰፊ ነው።
ህወሀቶች መቀሌ ላይ መሽገዋል። ስብሰባቸው ተራዝሟል። ትንፋሽ እንዳይሰማ አድርገው እያካሄዱት ካለው ስብሰባ ምን ሊሰማ እንደሚችል የሚታወቅ ነገር የለም። ሁለቱንም ጎራዎች የሚመሩት የህወሀት ሰዎች በአንድ አዳራሽ ውስጥ የሚያደርጉት ዝግ ምክክር ውጤቱ ይጠበቃል። በተለመደው የስኬት መግለጫ ታጅቦ አዲስ ነገር እንደሌለ ተደርጎ ቢነገረን እንኳን ልንቀበል የሚገባው ያልተነገረንን ነው። ህወሀት መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኑን ከመቀሌው ስብሰባ የምንሰማው አይሆንም። በመሃላቸው ንፋስ እንኳን እንዳልገባ እንጂ ሀገር ሊያጠፋ በሚያስችል መስመር ላይ መቆማቸውን ይነግሩናል ብለን አንጠብቅም።
ኢትዮጵያ አደጋ ላይ መሆኗ ግልጽ ነው። ህወሀት ከስግግብነትና በራዕይ አልባ ጉዞው ምክንያት ኢትዮጵያን ከገደል አፋፍ አስጠግቷታል። አንድ የፌደራሊዝ ምሁር እንዳሉት፡ የኢትዮጵያ ልጆች በክልል ታጥረው ከክልላቸው የተሻገረ ራዕይ እንዳይኖራቸው ተደረገው እንዲኖሩ የፈረደባቸው የህወሀት ስርዓት ጭንቅ ውስጥ ገብቷል። የወረወረው ሰይፍ ፊቱን አዙሮ እየተምዘገዘገ ወደራሱ ህወሀት እየገሰገሰ ነው። ዘ ኢኮኖሚስት በሰሞኑ ዘገባው እንዳተተው ፌደራሊዝሙ ከሽፏል። አሰላለፉ የሚያሳየውም ፌደራሊዝሙ ለኢትዮጵያ አንድነት ጠንቅ መሆኑን ነው። ህወሀት ለስልጣኑ በመስገብገብ የበተነው የጎሳ ፖለቲካን መቆጣጠርና መሰብሰብ አቅቶታል። እውቀት የነጠፈባቸው፡ ማስተዋል የራቃቸው፡ ትዕቢትና ድንቁርና ያፋፋቸው የህወሀት ጄነራሎች የደቀኑት አደጋም የሚመነጨው ከዚሁ የፌደራሊዝሙ ክሽፈት ነው።
መደማመጥ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ከተደቀነባት አደጋ ትላቀቅ ዘንድ ሀገራዊ ራዕይ ያለው መስመር ከምን ጊዜው በላይ ግድ ይላል። ክልሎች የየድርሻቸው ላይ መቸንከራቸውን ትተው የትልቋን ሀገራቸውን ጉዳይ በያገባኛል ስሜት መነጋገር አለባቸው። ህወሀት የገነባውን የልዩነት ግድግዳ ማፈራረስ ለኢትዮጵያ የጊዜው ወሳኝ መድሃኒት ነው። ለዘላቂውም ፈውስ ነው። በትንንሽ ድሎች የሚቦርቁ ወገኖች ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል። ህወሀቶች አስረዝመው በገመድ ለክተው በሰጡት ጊዚያዊ ደስታ መፈንደቁ የሚያወጣው ወደመቃብሩ እየገሰገሰ ላለው ህወሀት ብቻ ነው። በጥገናዊ ለውጥ የሚመጣ ድል የለም። ስርነቀል ለውጥ ያስፈልገናል። ስርነቀል ለውጡ ደግሞ በህወሀት መቃብር ላይ እውን የሚሆን ነው።