ቢሾፍቱ ለጣና የጻፈው ደብዳቤ! !!! /‎መንግስቱ ዘገዩ/

ቢሾፍቱ ለጣና የጻፈው ደብዳቤ! !!! /‎መንግስቱ ዘገዩ/

አካም አካም ጣና ፤
ያማሮቹ ማተብ ፤ የአባይ ባልንጀራ ፤
በውሃህ ገመገም ፤
ጨለማ ምትገልጥ ፤ ህልም የምታጠራ ፤
የጎጃም ማርሸት ፤ ያባይ ዳር ወለላ ፤
አፌ ይጣፍጣል ፤
ወንድም አለም ብዬ ስምህን ስጠራ ።

ያልሰማሁ መስየ፤
እኔስ ሰምቻለሁ ፤
ከሚመላለሰው ከሳር ከቅጠሉ ፤
የክፉ ቀን ጓዴ ፣
ህመሜን ነግረውት ፤
መጥቶ ሳይጠይቀኝ ትለኛለህ አሉ ።

መቼስ ወንድም አለም ፤
ሁሉም በሽተኛ ፤
ሁሉም ህመምተኛ ፤
በሆነበት ጓዳ ፤ ትንፋሽ ይናፍቃል ፤
እግዚሃር ይማርህ ፤
የሚለው የሰው ቃል ፤ አድራሻው ይርቃል ።

ግን እንዲህም ሆኖ ፤
አዎን ወንድም አለም ፤
ጦቢያ ከምትባል ፤
ከኩሾች ምንጭ ስር ፤ የፈለቀ ውሃ ፤
በሴረኞች መሃል ፤
ጋንጩር እየዳሰ ፤
ሲጠብል ይኖራል ፤ የፍቅር አምሃ ።

እናም የናቴ ልጅ ፤
መልክህና መልኬ ፤
የተሳለበትን ፤
ያንን ንጹህ ውሃ ፤
በእበትና አዛባ ፤ እያደፈረሱ ፤
የወንዙን ዳር ዋርካ ፤
ምስክር እንዳይሆን ፤
በክፋት መጥረቢያ እየገነደሱ ፤
አጥርተህ እንዳታየኝ ፤
አጥርቼ እንዳላይህ ፤
በድፍርስ ውሃ ላይ ፤ ጭቃ እየከለሱ ፤
ስምህን ያጠፉት ፤
እነዚያ ጉንዳኖች ፤ ወደየት ደረሱ? ??
ዛሬማ ቀን ወጥቶ ፤
በድፍርሱ መሃል ፤
የጦቢያን ውብ አይኖች ፤
አሻግረው የሚያዬ ፍኖዎች ተነሱ ።

ጣናም እስካንኬኛ ፤
አባይ እስካንኬኛ ፤
ሰማዩም አፈሩም ገረቢያ ኬኛ ።
በሚል ውብ ዝማሬ ፤ እየተጫፈሩ ፤
የሰላሌ ልጆች ፤
ዳዋና ቆንጥሩን እየመነጠሩ ፤
ጣና ከሃይቁ ዳር ፤
ስለ ፍቅር ብለው ፤ ሺህ ፍቅር ገበሩ ።

አየህልኝ ጣና ፤
አሞታል ብለውኝ ፤
ሰምቼማ ነበር ፤ ከሁሉ አስቀድሜ ፤
ሳልመጣ የቀረሁ ፤
ግራ ቢገባኝ ነው ፤ጠንቶብኝ ህመሜ ።

ይኸው ወንድም አለም ፤
ሆራ መልከ ሰዲ ፤
አበባ ረግፎብኝ ፤ ከሃይቁ ገመገም ፤
እናላቅስሽ ብሎ ፤
ያልተንሰቀሰቀ ያላዘነ የለም ።

ካዘኔ ስነሳ ፤
እመጣለሁ ብዬ ፤ ወጥቼ ከቤቴ ፤
ይኸውልህ ዛሬ ፤
የልጄን ሙት አመት ፤
ካወጣሁ በሃላ ፤
ጣና ወንድሜ ጋር ፤
ልላቀስ መጣሁኝ ፤
እንደ ደጉ ዘመን ፤ እንደልጅነቴ ።

እናም ወንድም አለም ፤
ከውሃችን ገላ ፤
አይን የሚገደግድ አፈር እየረጩ ፤
አጥርተን እንዳናይ ፤
ያይናችንን ጭራ ፤
ዘግነው የጨረሱ ፣ በሜንጦ እየነጩ ።

ብካይ ትንቢታቸው ፤
የጦስ ንግርታቸው ፤
በጦቢያ መዶሻ ስለተወቀጠ ፤
ያመገሉት ቁጭት ፤
በፍቅር ወረንጦ ሙጀሌው ፈረጠ ።

ዛሬማ ዛሬማ ፤
እንደ ንስር ብሌን ፤
ካድማስ ባሻጋሪ ፤
ጨለማና ግፉን ፤ እየመነጠረ ፤
ሸርና ጭንገፋን ፤
ለይቶ የሚገፍ ፤
ባይኖቹ ብርሃን እየበረበረ፤
ይኸው በኛ ቀዬ ፤
ኢጆሌ ኦሮሞ ፤
ቢያን ኬኛ ብሎ ፤ ጣና ዳር አደረ ፤

ዛሬ በድፍርሱ ፤
በውሀው መልክ ላይ ፤
በዳበሳ ፍቅር ፣ ፊደል ለይተናል፤
የማይታየውን ፤
የብርሃን ቀለም ፤
በጨለማ መሃል ፤ ማየት ጀምረናል ።

ይህንን ብርሃን ፤
ከእጃችን ለማስጣል፤
በደረቀ መንፈስ ፤ ለሚንገዳገዱ ፤
በዲማው ጊወርጊስ ፤
ከጋንጩር ጋር ሲኦል መቀመቅ ይውረዱ ።
አሜን! !!!

By Mengistu zegeye

LEAVE A REPLY