/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ የተጠቀሱ ምስክሮች ስም ዝርዝር ለተከሳሾች ሊደርስ ይገባል፣ አይገባም በሚለው ክርክር ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጥበት በጠየቀው መሰረት የፌደሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩ የህገ መንግስት ትርጉም አያስፈልገውም የሚል መልስ ሰጥቶበታል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና ለተከሳሾች የምስክር ስም ዝርዝር እንዲሰጥ የሚፈቅደውን የህገ መንግስቱን አንቀፅ 20(4) በመጥቀስ የምስክር ስም ዝርዝር እንዲሰጣቸው ተቃውሞ ባቀረቡት መሰረት ፍርድ ቤቱ የመቃወሚያ ብይን ባሰማበት ወቅት ጉዳዩን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ልኮ የነበር ቢሆንም የፌደሬሽን ምክር ቤት የፀረ ሽብር አዋጁም ሆነ የምስክር ጥበቃ አዋጅ ከባድ ወንጀሎች ሲፈፀሙ የምስክሮችን ደህንነት ለመጠበቅ የወጡ ስለሆነ ከህገ መንግስቱ ጋር የማይጋጩ በመሆኑ ጉዳዩ ህገ መንግስታዊ ትርጉም አያስፈልገውም የሚል መልስ ሰጥቷል።
የከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የእነ ዶ/ር መረራ ጉዳይ ከባድ ወንጀል መሆኑን በመግለፅ የምስክሮች ዝርዝር እንዳይገለፅ ብይን ሰጥቶ ምስክርነቱ እንዲሰማ ለጥቅምት 24/2010 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ዶ/ር መረራ ጉዲና የእምነት ክደት ቃላቸውን እንዲሰጡ በጠየቀው መሰረት ዶ/ር መረራ የተጠቀሰውን ወንጀል ” አልፈፀምኩም! ጥፋተኛም አይደለሁም!” ሲሉ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል። የዶ/ር መረራ ጠበቆች የፌደሬሽን ምክር ቤት ትርጉም አያስፈልገውም ብሎ መልስ እና ፍርድ ቤቱም ብይን በሰጠበት ጉዳይ ላይ ብይን ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ገልፀዋል። ዶክተር መረራ ከታሰሩ አስራ አንድ ወራት ሆኗቸዋል።በሀገር ውስጥ በሚካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ ዶክተር መረራን ጨምሮ ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ እንዲፈቱ ህዝቡ እየጠየቀ እንደሚገኝ ይታወቃል።