አሁን በዚህች ሰዓት በሰላሌ(ኦሮሚያ) ከሚገኙ ከተሞች አንዷን ተጠልዬ እገኛለሁ። ተጋዳላይ መብራህቱ ገ/ሕይወት (ማለቴ ጓድ በረከት ስምዖን) ኦቦ አባዱላ ገመዳን ተከትሎ መልቀቂያ ባስገባ ማግስት ለቢሮ ሥራ ከፊንፊኔ ወጥቼ… መመለሻ አጥቼ ሰላሌ አደርሁ። “ባሰቡት ልክ አይውሉ፣ በተኮሱት ልክ አይጥሉ” ትል ነበር አያቴ። የወጣሁበት ሥራ ቀርቶ ሙሉ ቀን የኦሮሞን የጎዳና ላይ ተቃውሞ “ላይቭ” ስከታተል ውዬ… አሁን አልጋ ፈልጌ ጋደም ብያለሁ። ስመለከተው የዋልሁትን ትእይንተ ሕዝብ እንዴት ዘግቤ ለትረካም ለታሪክም እንደማበቃው እያሰብሁ ነው።
…
የጓድ በረከት ከኢህአዴግ መልቀቅ ከኦቦ አባዱላ መልቀቅ በእጅጉ ይርቃል – ይረቃልም። ሁለቱም የሕወሓት እጆች ነበሩ/ናቸው ካልን ያለ ጥርጥር ቀኝ እጅ የሚሆነው ክቡር አቶ በረከት ስምዖን ነው። ከመለስ ቀጥሎ ሊጠቀስ የሚችል የኢህአዴግ ፖለቲካ ዘዋሪ ነውም ይሉታል። “የስምዖን ልጅ… መለስ የሚተማመንበት ቀኝ እጁ” የሚሉት ብዙዎች ናቸው። የበረከት መልቀቅ ከአባዱላ መልቀቅ ይለያል። ኦቦ አባዱላ ከኢህአዴግ ወደ ኦህዴድ ሄደው “ለድርጅቴና ለሕዝቤ ክብር እታገላለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል። ጓድ በረከት ግን ከፌዴራል ለቀው ክልል ላይ የመጠጋት ዕድል ይኖራቸዋል ብዬ አላምንም። ኧረ እንዲያውም በብአዴን አመራሮች የመገፍተር ነገር ሳይደርስባቸው አልቀረም እየተባለ ነው። ባጭሩ ለወደፊቱ ለብአዴን እና ለአማራ ሕዝብ የሚታገል በረከት ስምዖን አይኖርም (ይመስለኛል)። የት ሊሄድ ይሆን? ከመለስ ኅልፈት በኋላ በረከት የሸሸው ኢህአዴግስ ምን ዓይነት ድርጅት ሆኖ ሊቀጥል ይሆን…???
…
በዛሬው ውሎዬ ብዙ ነገር ገጥሞኛል። አብረውኝ ከሸገር የወጡት ባልደረቦቼ አንዱን ሆቴል የሙጥኝ ብለው ዋሉ። እኔ ግን የመጣውን እቀበላለሁ እንጅ ሕዝብ አደባባይ በተሰጣባት ዕለት አልጋ ቤት አልውልም ብዬ ወጣሁላችሁ። ልክ እንደወጣሁ የብዙ ጎረምሶች ዓይን ማረፊያ ሆንሁ። ጠጉረ ልውጥነቴን መደበቅ እንዴት ልቻል? አብሬ መፎክር እንዳላሰማ ቋንቋ አልችል ነገር። ዳር ይጄ ስልኬን ደቅኜ ትእይንቱን መቅረጽ ጀመርሁ። በድንገት አንድ ጎረምሳ ከፊት ለፊቴ እጆቹን አጣምሮ ቆመና በኦሮሚፋ የሆነ ነገር አለኝ። ያለኝን ባልሰማውም ያው “እጅህን አጣምር” የሚል ትርጉም ሰጠሁትና አጣምሬ ተቃውሞውን ተቀላቀልሁ። ፈገግ ብሎ ተጠጋኝና ስልኬን ተቀበለኝ። ፎቶዎቼን ማየት ቀጠለ። ፈጣሪ ሲመክረኝ በጠዋቱ “ዳውንሎድ” ያደረግሁት ትልቅ የኦዳ ዛፍ ነበር። በተጨማሪም አማራና ኦሮሞ በስሮቻቸው የተሳሰሩባቸው ሁለት ትልልቅ ዋርካዎች ፎቶም ነበረኝ። ልጁ በደስታ አየኝና “አማራ ወንድማችን ነው። ምንም እንዳትፈራ” ብሎ በቀኝ እጁ ቀኝ እጄን ጨበጠኝ። የልብ ምቴ ተስተካለ።
…
ዛሬ የሥልጣን መልቀቂያ አስገባ የተባለው የኢህአዴግ ቀኝ እጅ አቶ በረከት በአንድ አጋጣሚ ቀኝ እጄን ጨብጦት ያውቃል 🙂 የጆርናሊዝም ሁለተኛ ዲግሪዬን ስማር “የሀገሪቱን የልማታዊ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ቲዮሪ እና ትግበራ” እንዲያብራራ ተጋብዞ በነበረበት አጋጣሚ ስድስት ኪሎ ግቢ ውስጥ።
(እውነት ለመናገር ሰውዬው የሚዲያና ተግባቦት ጽንሰ ሐሳቦችን ቀላል አይተነትናቸውም። መምህራንም ተማሪዎችም አጨብጭበንለታል። ያላነሳንለት ጥያቄ አልነበረም። በተረጋጋ መንፈስና በበቂ ማስረጃ ሲመልስ “ከኢህአዴግ ታጋዮች መካከልም እንዲህ ያለ ምሁር አለ እንዴ?” አስብሎናል። ችግሩ ጽንሰ ሐሳብ ብቻ ሆነ። በተግባር አላሳየንም። በዕለቱ “እንደ ኢቢሲ ጋዜጠኞች ልማታዊ ጆርናሊዝምን ያልተረዳና ለመንግሥት ሸክም የሆነ የለም” ሲል በጆሮዬ ሰምቼዋለሁ። ግን እኮ… ለረጅም ጊዜ የኢቢሲ የቦርድ ሰብሳቢ እርሱ ነበር። ለምን አላስተካከለውም? ወሬ ብቻ። የእርሱ “አንፃራዊ አዋቂነት” ማንን ጠቀመ? ምን አልባት ኢህአዴግን? አሁን ለምን ለቀቀ? የእርሱ መልቀቅ ወዴት ለመሄድ? በእውኑ እንደ አባዱላ ሕዝባዊ መሆን ይቻለዋልብ? ከየትኛው ሕዝብ ተጠግቶ? ጊዜ ይመልሰው።
…
የሰፊው ኦሮሞ ሕዝብ ፍርሃትን አክ እንትፍ ብሏል። ዛሬ የሰላሌ ከተሞች መንገዶች በሰልፈኞቹ ተሞልተው ነው የዋሉት። “ቻው! ቻው! ወያኔ” ፣ “ዳውን ዳውን ወያኔ” የሚሉት መፈክሮች ተደጋግመው ይደመጡ ነበር። ለማንኛውም መኪና “እጅን የማጣመሩን ተቃውሞ ምልክት” (ተሳፋሪዎቹም በሾፌሩም) ሳያሳይ ወደ ሸገርም ሆነ ወደ ጎንደር መንቀሳቀስ ክልክል ነበር። ይህንን መርህ የጣሱ መኪኖች ትናንትና ተቃጥለዋል አሉ። ሕዝቡና የክልሉ ፖሊስ ተስማምቷል። በአንጻሩ “ፓትሮል የሚያደርጉ” የመከላከያ አባላትን ሲያይ የሕዝቡ ቁጣ ይገነፍላል። መከላከያ አይቶ ሲሸሽ ያየሁት ሕዝብ የለም። ይልቁንስ መከላከያን የጫኑት መኪኖች በፍጥነት ሮጠው ከሕዝቡ ሲርቁ አይቻለሁ።
.
አሁን መሽቶ ሕዝቡ ከሙሉ ቀን ሰልፉ ለማረፍ ወደየቤቱ ገብቷል። ለመኪኖች የነጋላቸው ይመስላል። ተደብቀውበት ከዋሉበት እየወጡ በሁለቱም ቅጣጫ እየተግተለተሉ ነው። ፖሊስም በየመንገዱ አለ። ምሽቱ ሰላም ነው።