ሰማያዊ ፓርቲና መኢአድ፤ የኦሮሚያ – ሶማሌ ግጭትን፣ ማጣራታቸውን አስታወቁ

ሰማያዊ ፓርቲና መኢአድ፤ የኦሮሚያ – ሶማሌ ግጭትን፣ ማጣራታቸውን አስታወቁ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ ሰማያዊ ፓርቲ እና የመላ ኢትዮጵያዊያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢ የተፈጠረውን ግጭት፣ አጣሪ ኮሚቴ ልከው ማጣራታቸውን ያስታወቁ ሲሆን ግጭቱን ያባባሰው የአንድ ባለሀብት መገደል ነው ብለዋል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ በፓርቲዎቹ ሪፖርት ላይ አስተያየት መስጠት አልችልም ብሏል፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች የሁኔታውን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ አጣሪ ኮሚቴ ወደ ግጭቱ አካባቢ ልከው ጉዳዩን ማጣራታቸውን፣በዚህም ግጭቱ ወደ ከፋ ደረጃ እስኪሸጋገር ድረስ የፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ ገብተው የማረጋጋት ስራ አለመስራታቸውን ማረጋገጣቸውንም ሰሞኑን ባቀረቡት ሪፖርት አስታውቀዋል፡፡

ግጭቱ ከመስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በዋናነት የተባባሰበት ምክንያት በምስራቅ ሃረርጌ አወዳይ ከተማ፣አንድ የሶማሌ ተወላጅ ባለሀብት ላይ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ መሆኑን የጠቆመው አጣሪ ኮሚቴው፤ ይህን ተከትሎ በከተማዋ በተነሳው ብጥብጥም፣በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ቤታቸውን ማቃጠል፣ ንብረታቸውን መዝረፍና ግድያ መፈፀሙን ተረድቻለሁ ብሏል፡፡

በዚህ አላስፈላጊ ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች፤ በቂ ምግብና አልባሳት፣ እንዲሁም የመኝታ ፍራሽ እንደማያገኙ፣ በዚህም የተነሳ በባዶ መጋዘን በደረቅ ወለል ላይ እንደሚተኙ አጣሪ ኮሚቴው ማረጋገጡን የገለፁት ፓርቲዎቹ፤ በምግብና በንፁህ ውሃ እጥረት የተነሳ ህፃናት ለተቅማጥ በሽታ መዳረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡

መንግስት ለደረሰው ሰብአዊ ውድመት ተጠያቂ መሆኑን በመግለጫቸው ያስታወቁት ፓርቲዎቹ፤ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ለሞቱት ቤተሰቦች የሞራል ካሣ እንዲከፍልና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች፣ በአፋጣኝ መቋቋሚያ ሰጥቶ፣ ወደተረጋጋ ኑሮአቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊትም ግጭቱን በአስተማማኝ ደረጃ እንዲያስቆም በመጠየቅ፣ ለወደፊትም ይህ ዓይነቱ የዜጎችን መብት የሚጥስ ድርጊት እንዳይደገም ጥሪ አቅርበዋል – ፓርቲዎቹ፡፡

እያንዳንዱ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊና ዓለም አቀፍ ግብረሠናይ ድርጅቶች፣የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ለማቋቋም የበኩላቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን ያሉት ፓርቲዎቹ፤ በእነሱ በኩልም ድጋፍ የሚጠይቁ ደብዳቤዎችን ለተመረጡ አካላት ለማሰራጨት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለተጎጂዎች እርዳታ የሚሰባሰብበትን የባንክ ሂሳብ ቁጥርም በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል፡፡

ፓርቲዎቹ በግጭቱ ላይ አደረግነው ባሉት ማጣራት ላይ ተመስርተው ያወጡትን ሪፖርት በተመለከተ ከአዲስ አድማስ አስተያየት የተጠየቁት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፤ “ሪፖርቱ ባልደረሰን ሁኔታ የመንግስትን አቋም ለመግለፅ እቸገራለሁ” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ፤ የግጭቱን መንስኤና ጉዳት አስመልክቶ ያጠናቀረውን የምርመራ ሪፖርት በዚህ ወር ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን የፌደራል መንግስቱም በዋናነት ይሄን ሪፖርት እየተጠባበቀ መሆኑን በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡

LEAVE A REPLY