/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ፓትሪያርክ ብፁዕ ቅዱስ አቡነ ማቲያስ የአቡነ ጳውሎስ ሞትን ተከትሎ ስድስተኛው ፓትሪያርክ ናቸው። የኢትዮጵያ የአገዛዝ ስርዓት ቤተ-ክርስቲያኒቷን የፖለቲካ መናኸሪያ ባማድረጉና አቡነ ማትያስም እንደ አቡነ ጳውሎስ የፖለቲካው ቁማር በቀላሉ የማይረዱት በመሆኑ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ በየ ጊዜው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁሙ ነበር።
“Hara Tewahido ሐራ ተዋሕዶ” የተባለ ድህረ ገፅ የሚከተለውን አስነብቦናል።
“ፓትርያርኩ ከሓላፊነታቸው ለመልቀቅ በቃል ጠየቁ፤ ጫና ለማሳደር የታሰበ ስልት መኾኑ ተጠቆመ
• ከሥልጣን የመገለል ስጋት ባይኖራቸውም፣ ተገቢነታቸው ብርቱ ጥያቄ እየተነሣበት ነው፤
• “በአቅም ማነስ ያጡትን ተቀባይነት ለመመለስ፣ ከአማካሪዎቻቸው ጋራ የወጠኑት ነው፤”
• ለብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ምክር የሰጡት ምላሽ፣ ብዙዎችን ቢያሳዝንም ሊያግዷቸውም ዛቱ፤
• የተወነጀሉት ብፁዕነታቸው፣ በምልአተ ጉባኤ እና በሕግም እንደሚጠይቋቸው ተጠቆመ፤
• በሀ/ስብከታቸው ተቀባይነት ያጡት ብፁዕ አባ ማርቆስ፣በቦታቸው ለመተካት እየሠሩ ነው፤
† † †
ታማኝነታቸውና መንፈሳዊ አባትነታቸው ተቀባይነት እያጣ መምጣቱ በብርቱ አሳስቧቸዋል የተባሉት፣ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ “መሥራት አልቻልኩም፤” ሲሉ ከሓላፊነታቸው ለመልቀቅ፣ ለመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቃል ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰማ፡፡
ፓትርያርኩ ጥያቄውን ያቀረቡት፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ አውጭና ወሳኝ አካል ከኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ እና ከሥራ አስፈጻሚው የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደራዊ አካል ጋራ ያላቸው ግንኙነት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደገባ እየታየ ባለበት ወቅታዊ ኹኔታ ውስጥ ነው፡፡
“መፍትሔ ሊሰጠኝ ይገባል፤” በማለት በሓላፊነታቸው ለመቀጠል እንደተቸገሩ በቃል ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መናገራቸውንና በቅርቡም በጽሑፍ እንደሚያሳውቁ ነው፣ ምንጮች የጠቆሙት፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ የፓትርያርኩ ሢመትና ርደት ጉዳይ የሚወስነው ቅዱስ ሲኖዶስ ኾኖ ሳለ፣ ጥያቄያቸውን ለባለሥልጣናት ማቅረባቸው፣ በቅዱስ ሲኖዶስና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዘንድ በአስከፊ ኹኔታ እያጡ የመጡትን ተደማጭነትና ተቀባይነት በተጽዕኖ ለመመለስ፣ ከአማካሪዎቻቸው ጋራ የወጠኑት መኾኑን እንደሚያሳይ ተነግሯል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የመጀመሪያ ዓመታዊ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ፣ ከነገ በስቲያ፣ ጥቅምት 12 ቀን እንደሚጀመር እያወቁ፣ ከሓላፊነት ለመልቀቅ ጠይቀዋል፤ መባሉ ይህንኑ ጫና የማሳደር ስልታዊነቱን እንደሚያረጋግጥ ነው የተገለጸው፡፡
ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ በተያያዘ የሚያቀርቡት የእግድ አጀንዳ፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ አካላት(ቋሚ ሲኖዶስ እና ምልአተ ጉባኤ) ውድቅ መደረጉ፤ ቡድን ፈጥረው እየመከሩ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሚያስተላልፉት መመሪያ መሸራረፉ ሕመም እንደኾነባቸው ነው የተስተዋለው፡፡
የማኅበሩ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ሥርጭት፣ ከቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ውጭ እንዲታገድ ያስተላለፉት መመሪያ ተፈጻሚነት ሲያጣ፣ ከአጠቃላይ ጉባኤው 36ኛ ዓመታዊ ስብሰባ ተሳትፎ እንዲታገድ ወደ ማዘዝ ቢሸጋገሩም፣ እንዳሰቡት ሳይሳካላቸው ቀርቶ፣ በተፃራሪው፣ የማኅበሩ የማዕከልና የአህጉረ ስብከት ሥራዎች በጉልሕ እንዲስተጋቡ ምክንያት ኾኗል፡፡
በአጠቃላይ ጉባኤው መክፈቻ ምሽት፣ የማኅበሩ ተወካዮች እንዳይሳተፉ በማድረጋቸው፣ “የእኛን ሥልጣን ማወቅ አለባቸው፤ ሥልጣናችንን መረዳት አለባቸው፤” በማለት ከእነብፁዕ አባ ሩፋኤል፣ ብፁዕ አባ ማርቆስ እና ብፁዕ አባ ቶማስ ጋራ ውሎውን የገመገሙ ቢኾንም፤ በቀጣዩ ቀን፣ ማኅበሩ ከአህጉረ ስብከት ጋራ በመቀናጀት ያከናወናቸው ተግባራት በድምቀት እየተነገሩ በመዋላቸው፣ በጋራ መግለጫውና ቃለ ጉባኤው ላይ፣ የቴሌቭዥን ሥርጭቱ ሕገ ወጥ እንደኾነና እንዲዘጋ የሚጠይቅ አንቀጽ በጣልቃ እንዲገባ አርቃቂዎቹን አዝዘዋል፡፡ ሐሳቡን የተቃወሙ የአርቃቂ ኮሚቴው ሦስት አባላት፣ “የማኅበር ተላላኪዎች” ተብለው በሰብሳቢው የተዘለፉ ሲኾን፣ ሥርዋጹም በግድ እንዲገባና በድፍረት እንዲነበብ ተደርጓል፡፡
በአጠቃላይ ጉባኤው ያልተነሣ ጉዳይ በቃለ ጉባኤው የውሳኔ ሐሳብ ተብሎ መስፈሩ አግባብነት እንደሌለው ወዲያውኑ ከጉባኤተኛው ተቃውሞ የተሰማበትና በምክትል ሰብሳቢው ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁም ክፉኛ ቢተችም፣ ርእሰ መንበር የኾኑት ፓትርያርኩ ግን ሕገ ወጥነቱን ነው የተከላከሉት፡፡ ስሕተቶችን በፍጥነት እያረሙ፣ የአጠቃላይ ጉባኤውን ሒደት በጥብቅ እየተቆጣጠሩ፣ ማኅበሩን የማስወገዝና ሥልጣናቸውን የማግነን ምክራቸውን ያፈረሱባቸውን ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን፣ የመዝጊያ ንግግር እንዳደርግ ስለ ፈቀዱልኝ አመሰግናለሁ፤” በማለት በማጠቃለያ ቃለ ምዕዳናቸው በአሽሙር መናገራቸውም ተሰብሳቢዎችን ፈገግ አሰኝቷል፡፡
የቤቱን ፈገግታ ያከሰመው፣ የፓትርያርኩ ክብረ ነክ ንግግር ግን ወዲያው ነበር የተሰማው፡፡ “ተናግሮ አናጋሪ የትላንቱ ሰውዬ” ያሏቸውን ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን በመዝለፍ፣ ለአጠቃላይ ጉባኤውም ለመንበረ ፕትርክናውም ክብር በማይመጥን ንግግር፥ ደጋፊዎቻቸውን ሳይቀር አሳፍረዋል፡፡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በእጅጉ አዝነዋል፤ ቁጣቸውን በግልጽ ያሳዩም ነበሩ፡፡
ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል፣ ፓትርያርኩ በሚሰጧቸው ሕገ ወጥና ረብሕ የለሽ መመሪያዎች እንዲጠነቀቁ፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን አቅርበው ማነጋገርን እንዲያስቀድሙ ነበር ምሳሌያዊ ምክር የሰጡት፤ ቅዱስ ሲኖዶሱንም ያሳሰቡት፡፡ እንደተለመደው ግን፣ በዚያው ዕለት ማምሻውን፣ በተጠቀሱት ክፉ አማካሪዎች፣ ምሳሌያዊ ምክሩ በአሉታ እየተተነተነ የፓትርያርኩ ቁጣ እንዲጋጋም መደረጉ ተጠቅሷል፡፡
“አቡነ ፋኑኤል፣ በፈንጅና ጭስ መስለው የተናገሩትን [አማካሪዎቻቸው]ይዘው፣ ቅዱስነትዎ የሚጽፉት ደብዳቤ ከዚህ ግቢ ውጭ የማይሠራና አቅም የሌለው እንደኾነ፤ ምንም ቢጽፉ የትኛውም አካል የማያስፈጽመው ነው፤ ነገር ግን መነጋገርያ እየኾነ ብዙ ሰው እያደናገረ ነው፤ ብለው ተርጉመውላቸዋል፤ ይህም ሕመም ፈጥሮባቸው አድሯል፤”
ነውረኛ ንግግራቸው፣ በአጠቃላይ ጉባኤው ተሳታፊዎች ላይ የፈጠረውን ስሜት ቢያዩም፣ ይብሱኑ፣ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን ከሀገረ ስብከታቸው እንደሚያግዱ ነው የዛቱት፡፡ በሀገረ ስብከታቸው ተቀባይነት ያጡትና የመባረር ዕጣ የሚጠብቃቸው ብፁዕ አባ ማርቆስ፣ “ሀገረ ስብከቱን ለማኅበረ ቅዱሳን አሳልፎ ሰጥቶታል፤” እያሉ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን በማሳጣት በቦታቸው ለመተካት የፓትርያርኩን እልክ እየገፋፉ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡ “ምን ሲኖዶስ አለ፤ ሲኖዶስ እኛው ነን፤” በማለት ፓትርያርኩ፣ ሌሎችንም አባቶች እንዲያስተባብሩም እየወተወቱ ናቸው፡፡
ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በበኩላቸው፣ ለተሰነዘረባቸው ውንጀላ ፓትርያርኩን በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ደረጃና በሕግም እንደሚጠይቁ ነው፣ የተጠቆመው፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ርእሰ አበው እንደመኾናቸው መጠን፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው ለቤተ ክርስቲያኒቱ አጠቃላይ አመራር የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እንደተደነገገው፣ በቅዱስ ሲኖዶስ እያስወሰኑና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋራ እየተማከሩ መሥራት የሚጠበቅባቸው ቢኾንም፣ ከዚህ ውጭ እየመከሩ የሚከተሉት ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፍ አካሔድ፣ ታማኝነታቸውና መንፈሳዊ አባትነታቸው በካህናትና በምእመናን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጣ፤ በባለሥልጣናትም ዘንድ አቅመ ቢስ ተደርገው እንዲናቁ አድርጓቸዋል፡፡ የመንግሥት ሹማምንትን ባገኙ ቁጥር፣ “ማኅበሩን ዝጉልኝ” የሚለው የዘወትር ውትወታቸው በእጅጉ እንዳስናቃቸውና ተደማጭነት እንዳሳጣቸውም ተጠቁሟል፡፡
በቃል አሳውቀውታል፤ የተባለውና በቀጣይም በጽሑፍ እንደሚያቀርቡ የተጠቆመው ከሓላፊነት የመልቀቅ ጥያቄ መነሻዎች ባለሥልጣናቱን እያነጋገረ ነው፣ ተብሏል፡፡ ከሥልጣን ለመልቀቅ ፍላጎት እንዳላቸው ከማሳየት ይልቅ፣ ከመንግሥት ያጡትን ትኩረት ለመመለስ፤ በዚህም፣ በቀጣዩ ሰኞ በሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ጫና ፈጥረው ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም፣ ከእኩይ መካሪዎቻቸው ጋራ የወጠኑት ስልት ሊኾን እንደሚችል ተጠቁሟል፤ “ትቼላችሁ እሔዳለኹ፤” እያሉ ማንገራገራቸው ዐዲስ እንዳልኾነ በማስታወስ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ኾኖ የተሾመ አባት ከመዓርጉ የሚወርደው፡- ሃይማኖትን የሚያፋልስ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የማይጠብቅ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፍ ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ፤ በተሾመበት ቀን የፈጸመውን ቃለ መሐላ ካልጠበቀ፤ ታማኝነቱና መንፈሳዊ አባትነቱ ተቀባይነት ያጣ ከኾነና ይህም በተጨባጭ ተረጋግጦ በቅዱስ ሲኖዶስ ሲወሰን እንደኾነ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 33/1(ሀ)፣ (ለ) እና (ሐ) ተደንግጓል፡፡”