“እኔ የተከሰስኩት ለምን አማራ ማንነት አቀረብክ ተብዬ ነው” ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ

“እኔ የተከሰስኩት ለምን አማራ ማንነት አቀረብክ ተብዬ ነው” ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ

በዓቃቤ ህግ ማስረጃ ላይ የቀረበ የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ መቃወሚያ

“እኔ የተከሰስኩት ለምን አማራ ማንነት አቀረብክ ተብዬ ነው……………እኔ እንድከሰስ ምክንያት የሆነው በህገ ወጥ መንገድ በግዴታ የተነጠቀው የወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ለመንግስት ለማቅረብ በህዝብ ተመርጨ የማንነት ጥያቄውን በህጋዊ መንገድ በህገ መንግስቱ መሰረት ይመለከተዋል ለተባለ የመንግስት አካል ሁሉ ሳቀርብ ጥያቄውን ለማፈን ሲባል ከመኖርያ ቤቴ በሌሊት ተከብቤ ጥቃት ሊፈፀምብኝ ሲል ራሴን በመከላከሌ ነው” ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ

ለአማራ ብሔራዊ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ጎንደር ምድብ ችሎት

ጎንደር

(ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ ከጎንደር ማረሚያ ቤት)

ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎች በሶስት ዘርፍ የሚከፈሉ ናቸው። እነሱም 1) ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ስልክ በመጥለፍ ተገኘ የተባለ ሪፖርት፣ 2) በአማራ ክልል ወደሙ የተባሉ ንብረቶች ዝርዝር እና ግምታቸውን የሚገልፅ ሪፖርት፣ 3) ምስክሮች በፖሊስ ሰጡት የተባለ ምስክርነት ሲሆን ምስክሮቹ በመሞታቸው የሰው ምስክሮች ከተሰሙ በኋላ በማስረጃነት የቀረበ ሰነድ ነው። እነዚህን ሰነዶች እንደቅደም ተከተላቸው በሚመለከተው ዝርዝር የህግ መስፈርት ተቃውሞዬን አቀርባለሁ።

1) ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተገኘ የተባለ ሰነድ:_ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ከስልክ ምልልስ ያገኘሁት ነው በሚል በእኔ እና በዚህ ክስ ውስጥ በሌሉ ሰዎች ላይ ሰፋ ያለ ሪፖርት አቅርቧል። ይሁን እንጅ ከእኔ በተቃራኒ ወገን የስልክ ንግግር አደረጉ የተባሉ ሰዎች ስልክ ቁጥር አለመጠቀሱና የድምፅ ማስረጃ አለመቅረቡ ሪፖርቱ ከስልክ ግንኙነት ያልተገኘ መሆኑን የሚያስረዳ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የማንም ሰው የግል ሕይወት በማንኛውም መልኩ በ3ኛ ወገን ጣልቃ ሊገባበት እንደማይችል በህገ መንግስቱ አንቀፅ 26 ከመደንገጉም በተጨማሪ በዓለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን አንቀፅ 17(1) እና (2) ስምምነት ተደርጎበታል።

የማንኛውም ሰው የግል ማንነት ወይም የቤተሰቡ ወይም የመኖርያ ቤቱ ወይንም በማንኛውም መልኩ የሚያስተላልፈው መልዕክት ( የሚያደርገው ግንኙነት) በዘፈቀደ ወይንም በህገ ወጥ መንገድ ጣልቃ አይገባበትም። ግላዊ ክብሩ አይደፈርም በሚል ተደንግጓል። ይህም የስልክ፣ የፖስታ እና ሌሎች ጠለፋዎችን የሚከለክል መሆኑን በግልፅ ያስረዳል። በተከታዩ ንዑስ ቁጥር ደግሞ መንግስት የተጣለበትን ግዴታ ይገልፃል።

ማንኛውም ሰው ከላይ የተጠቀሰው ጣልቃገብነት እንዳይፈፀምበት የህግ ጥበቃ ይደረግለታል። በማለት የመንግስትን ግዴታ የሚገልፅ ሲሆን በእኔ ላይ የተፈፀመው ግን ተቀራኒው ነው። ምክንያቱ ደግሞ መንግስት በግለሰቦች የግል ሚስጥር ውስጥ ገብቶ የቤተሰብ ሚስጥር ሲበረብር የነበር ስለመሆኑ ማስረጃውን ራሱ አቅርቧል።

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ይልቁንም ህገ መንግስቱ ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር ተጣጥሞ መተርጎም እንደሚገባው በአንቀፅ 13(2) ላይ አረጋግጣለች። በዚህም መሰረት በብሔራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተገኘ የተባለው ሪፖርት በራሱ እውነት ባይኖረውም እውነት ቢሆን ኖሮ እንኳን የግል ነፃነታችንን በመድፈር የተገኘ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።

2) በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀፅ 26(1) እና (2) የማንኛውም ሰው የግል ህይወት ማለትም ህይወቱ፣ ንብረቱ እና በማንኛውም የመገናኛ ዘዴ የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች ሊደፈሩ የማይገባ መሆኑን በአስገዳጅነት ከአረጋገጠ በኋላ በንዑስ ቁጥር 3 ላይ ደግሞ ለህዝብ ደህንነት ሲባል አገልግሎቱ ሊገደብ እንደሚችል ብቻ ይደነግጋል። ዐቃቤ ህግ በዚህ ክስ ያቀረበው ማስረጃ ግን ይህን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ በመጣስ የግል ህይወቴን የደህንነት ባለስልጣኖች ሲበረብሩት እንደነበር በመግለፅ ነው።

የስልክ፣ የፋክስ ወይንም ሌላው የኤሌክትሮኒክስ ግንኙነት በህዝብ ሰላምና ደህንነት ላይ አደጋ የሚያደርስ መስሎ በሚታይ ጊዜ አገልግሎቱን ማቋረጥ ወይንም መገደብ እንጅ የሰውን የግል ህይወት ገብቶ የግል ሚስጥራቸውን እንዲከታተል በህገ መንግስቱ አልተፈቀደም።

ይልቁንም የመንግስት ባለስልጣናት የማንኛውም የግል ህይወት እንዳይደፈር የመጠበቅ ግዴታ የተጣለባቸው መሆኑን በአስገዳጅነት ያረጋግጣል። በሌላ በኩል እኔ የተከሰስኩት ለምን የአማራ ማንነት አቀረብክ በሚል ብቻ ስለሆነ ከአሸባሪ ጋር ይገናኛል ተብሎ አስቀድሞ የተደረገ ክትትል አለመኖሩን ተገናኘህ የተባልኳቸው ስልክ ቁጥሮች አለመገለፃቸው ብቻ ሰነዱ በቅንብር እኔ ከታሰርኩ በኋላ የተዘጋጀ መሆኑን ከማስረዳቱ በተጨማሪ በስልክ ተገናኝታችኋል የተባሉት ሰዎች የግንቦት 7 አባል ስለመሆናቸው ሆነ አሸባሪ ስለመሆናቸው የቀረበ ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ ከአሸባሪ ጋር ተገናኝተሃል አያሰኝም።

በተደጋጋሚ የሚጠቀሱት እነ ሰረበ ጥሩነህ እና ደጀኔ ማሩ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ከመሰረቱ ስለመፈጠራቸውም አላውቃቸውም። እንደዚህ የሚባሉ ሰዎች ካሉም በህይወት ይኑሩ አይኑሩ ወይም የአሸባሪ ቡድን አባል ይሁኑ አይሁኑ የማላውቅ ከመሆኑም በተጨማሪ በሪፖርቱ የተጠቀሱትን ስዎች ስለመሆናቸው ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ እኔን ከአሸባሪ ቡድን ጋር ተገናኝቷል ለማሰኘት የሚያስችል ብቃት የለውም።

3) በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁቁጥር 652/2001 አንቀፅ 14 ህገ መንግስቱን በግልፅ በሚቃረን ሁኔታ የተደነገገ ቢሆንም ቢያንስ የግለሰቦችን የግል ሚስጥር የመበርበሩ ስራ ሊከናወን የሚችለው ግን ፍርድ ቤት በውሳኔ ሲፈቅድ ነው። ዐቃቤ ህግ ያቀረበው ከስልክ ጠለፋ ተገኘ የተባለው ማስረጃ ህገ መንግስቱንም ሆነ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን የሚቃረን ስለሆነ ከህግ ውጭ የተገኘ ማስረጃ የወንጀል ተግባር ማስረጃ መሆን እንደማይችል በህገ መንግስቱ በግልፅ ተመልክቷል። በዚህም መሰረት የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት መ/ ቤት ተገኘ የተባለው የሪፖርት ማስረጃ ህገ መንግስቱንም ሆነ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን በመጣስ በሌለ ነገር ላይ የተዘጋጀ በመሆኑ ተቀባይነት የሌውም እንዲባል እጠይቃለሁ።

4) ከብሔራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት የቀረበ ሪፖርት ታማኝነቱን በተመለከተ:_ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 23 ላይ የብሔራዊ መረጃ እና ደህነት አገልግሎት ፅ/ ቤት የሚያቀርበው ሪፖርት ታማኝ ማስረጃ ነው ተብሎ ተደንግጓል። በዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው ነፃ ዳኝነት ተቋም ተቋቁሟል ተብሎ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 78 የተደነገገውን እና በአንቀፅ 79 ደግሞ ዳኞች ከማንኛውም አካል ትዕዛዝ ነፃ ሆነው ይሰራሉ ተብሎ የተደነገገውን በግልፅ የሚጥስ ነው። ከነፃ ዳኝነት አንዱ እና የመጀመሪያው ዳኞች በችሎት ጠይቀው የተረዱትን እና የማስረጃ ምንጮችን ከስር መሰረቱ አይተው የተከራካሪ ወገኖችን ማስረጃዎች በእኩልነት መዝነው መወሰን ከቻሉ ብቻ ነው። በተጠቀሰው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀፅ 23 መግቢያ ላይ ከታች የተዘረዘሩትን መረጃዎች ዳኞች ታማኝ ናቸው ብለው እንዲቀበሉ የሚያስገድድ (ልዩ ተፅዕኖ) የሚፈጥር ህግ ሲሆን በንዑስ አንቀፅ (1) ላይ “የመረጃ ምንጭ ወይንም ወረጃው እንዴት እንደተገኘ ባይገለፅም በሽብርተኝነት ወንጀል የተዘጋጀ ሪፖርት ታማኝ ነው” በሚል የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በየትኛውም መንገድ ያዘጋጀው (የራሱ አቋምም ቢሆን) ሪፖርቱ ታማኝ ማስረጃ ነው ተብሎ ተደንግጓል። ይህ ማለት ደግሞ ዳኞች በራሳቸው ስልጣን ማስረጃን እንዳይመዝኑ የተመዘነ ማስረጃ አለላችሁ ተብለው የተገደዱበት ህግ ነው።

ይህ ድንጋጌ ህገ መንግስቱን ስለሚቃረን ተፈፃሚ የማይሆን ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የፍርድ ቤቶች በነፃነት፣ በህሊናቸው እና በህግ መሰረት የተከራካሪ ወገኖችን ማስረጃ አይተው እና ሰምተው የመመዘን ስልጣን እያላቸው ሌላ ተቋም “ማስረጃህን እኔ አዘጋጅቸልሃለሁ። ያዘጋጀሁልህን ሪፖርት ብቻ አምነህ ተቀበል።” የሚለውን ለህገ መንግስቱ ተቃራኒ የሆነ ድንጋጌ መሰረት አድርጎ በማስረጃነት የቀረበው ሪፖርት የዳኝነት ነፃነትን በግልፅ የሚቃረን እና የተከራካሪ ወገን መብትንም ፈፅሞ የሚጥስ በመሆኑ በህገ መንግስት የተሰጡ መብቶችን የሚጥስ ህግ ባጋጠመ ጊዜ ደግሞ ፍርድ ቤቶች በህገ መንግስቱ አንቀፅ 9(2) መሰረት ተፈፃሚ እንዳይሆን የማድረግ ህገ መንግስታዊ ስልጣን ስላላቸው በህግ አግባብ ያልተገኘውና ምንጩ ያልታወቀው የአንድ ተቋም ሪፖርት ፍርድ ቤቶች እንዲቀበሉ አይገደዱም።

ከሁሉም በፊት መከበር እና መፈፀም የሚገባው ህገ መንግስቱ ስለሆነ ፍርድ ቤቶች ” እኔ ያቀረብኩልህን ማስረጃ ብቻ አምነህ ተቀበል” በሚል ስሜት የተደነገገውን ህግ ተፈፃሚ እንዳይሆን ለማድረግ ግልፅ እና በቂ የህገ መንግስት ድጋፍ አላቸው። ይልቁንም ማንኛውም የመንግስት አካል ወይም ግለሰብ ህገ መንግስቱን የማስከበር ግዴታውን መወጣት ከሚችልባቸው አንዱና ዋነኛው ለህገ መንግስቱ ተቃራኒ የሆኑ ህጎችን ዋጋ እንዳይኖራቸው ወይም እንዳይፈፀሙ የማድረጉ ሀላፊነት እና ግዴታ የተጣለው በፍርድ ቤቶች ላይ ስለሆነ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተገኘ የተባለው ሪፖርት ከላይ በተጠቀሰው የህገ መንግስቱ ድንጋጌ መሰረት ውድቅ እንዲደረግ እጠይቃለሁ።

5) በአማራ ክልል ስለወደሙ ንብረቶች የቀረበውን ማስረጃ በተመለከተ:_ በአማራ ክልል ህዝብ እየደረሰበት የነበረውን ግፍ እና በደል በሰላማዊ መንገድ ለመግለፅ አደባባይ በወጣበት ወቅት የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች በወሰዱት እርምጃ የተበሳጨ ህዝብ በደም ፍላት በሰጠው አፀፋ በንብረት ካይ ጉዳት መድረሱን እስር ቤት ውስጥ ሆኜ ሰምቻለሁ። ይህ ግን ማንም ከማን ሳይሆን በህዝብ ቁጣ የተፈፀመ ተግባር ከመሆኑ በላይ ይልቁንም በክሱ እንደተገለፀው በአማራ ክልል ንብረት ወደመ የተባለው ከሀምሌ 11/2008 በኋላ ስለሆነ እኔ በህግ ጥላ ስር ሆኜ ንብረት ለማውደም እንደማልችል ማንም የሚረዳው ሆኖ ሳለ በእኔ ክሰ ላይ ማስረጃ ሆኖ መቅረቡ ህጋዊነት የለውም። ንብረት ስለመውደሙ ብቻ የቀረበው የሰነድ ማስረጃ እኔ ተከሳሽ መፈፀሜን የሚያስረዳ ባለመሆኑ እንዲሁም ይህ ድርጊት በበደል ምክንያት በተነሳ ግጭት የተፈፀመ እንጅ በሽብርተኝነት ተግባር የተፈፀመ አለመሆኑን የክሱ አቀራረብም ሆነ ከስልክ ጠለፋ ተገኘ የተባለው ሪፖርት በራሱ በግልፅ የሚያሳይ በመሆኑ በእኔ ላይ ማስረጃ ሆኖ መቅረቡ አግባብነት ስለሌለው የዐቃቤ ህግን ማስረጃ መሰረት አድርጎ ለሚሰጠው ብይን ከሽብር ወንጀል ጋር የሚያያይዘው ነገር ስለሌለ በማስረጃ ሚዛን ውስጥ ሊገባ አይገባውም ተብሎ ውድቅ እንዲደረግ እጠይቃለሁ።

6) ስለ ጦር መሳርያ የተሰጠው ማስረጃ በመከላከያ ማስረጃ የሚስተባበል ቢሆንም ያለኝን ህጋዊ ማስረጃ በማስታባበል መልኩ የቀረበው ማስረጃ ሌላ በህገ ወጥ መሳርያ እንደያዝኩ ተደርጎ የተፃፈው ማስረጃ ፍትህ ለማሳሳት የተሰጠ መሆኑን ሰነዱ በራሱ ያረጋግጣል። ሌሎች ከተለያዩ መ/ ቤቶች የተሰጡ ናቸው የተባሉ ማስረጃዎች እኔ የወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነቱን ለማስመለስ የሚያቀርበውን የመብት ጥያቄ በህጋዊ መንገድ ለማስፈፀም በሀላፊነት መቀበሌን እንጅ የሽብር ወንጀል መፈፀሜን የሚያሳይ አንድም ነገር ስለሌለው ሁሉም የሰነድ ማስረጃዎች እኔን ጥፋተኛ ሊያሰኙ የሚችሉ ባለመሆናቸው በሰነድ ማድረጃዎቹ ሚዛን እንድከላከል ብይን ሊያሰጡ አይችሉም። ከዚህ በተጨማሪ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀፅ 23 ላይ የተጠቀሱትን ማስረጃዎች ፍርድ ቤቶች እንዲቀበሉ የተደነገገው በህገ መንግስቱ አንቀፅ 79 የተሰጠውን የዳኝነት ነፃነት የሚፃረር በመሆኑ እና ህገ መንግስቱን የሚቃረኑ ህጎች፣ የአሰራር ልምዶች ወይም የባለስልጣናት ውሳኔዎች በተገኙ ጊዜ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 9(2) መሰረት ተፈፃሚ እንዳይሆኑ ለማድረግ ዳኞች ግዴታ የተጣለባቸው ስለሆነ የአዋጁ አንቀፅ 23 ሙሉ በሙሉ ተፈፃሚ እንዳይሆን በማድረግ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ተገኘ የተባለውን ያለ ደጋፊ ማስረጃ በአንድ ተቋም ፍላጎት ብቻ ተዘጋጅቶ የቀረበውን ሪፖርት ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዲደረግ እጠይቃለሁ።

7) የሞቱ ሰዎች ምስክርነትን በተመለከተ:_ ረዳት ኢንስፔክተር ፈንታየ አበበ እና ም/ኮ/ር ገ/ እግዚያብሄር ገ/ መድህን የተባሉ ሰዎች በፖሊስ ቀርበው የምስክርነት ቃል ከሰጡ በኋላ በሞት በመለየታቸው አስቀድመው የሰጡት የምስክርነት ቃል በማስረጃነት እንዲያዝለት ዐቃቤ ህግ አቅርቧል። ነገር ግን ይህ ማስረጃ በሚከተሉት ምክንያቶች ተቀባይነት የለውም።

7•1 በማስረጃነት የቀረበው ሰነድ ሞቱ በተባሉ ሰዎች የተሰጠ ቃል ስለመሆኑ ምንም አይነት ማስረጃ አልቀረበም። በተለይ ም/ኮ/ር ገ/ እግዚያብሄር ገ/ መድህን መስከረም 21 ቀን 2009 ዓም ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የምስክርነት ቃሉን እንደሰጠ የሚገልፅ ሲሆን ከ19 ቀናት በኋላ ጥቅምት 9 ቀን 2009 ረዳት ኢ/ር ፈንታየ አበበ ለአማራ ክልል ፖሊስ ሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የምስክርነት ቃል ሰጠ መባሉ የሚታመን አይደለም። በአንድ ወንጀል ሁለት የተለያየ ስልጣን ያላቸው ተቋማት ምርመራ ማጣራት አይችሉም። በሌላ በኩል የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራውን ከጀመረ በኋላ የአማራ ክልል ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ምርመራ ያደርጋል ተብሎ አይታሰብም። ም/ኮ/ር ገ/እግዚያብሄር ገ/ መድህን የተባሉት ምስክርነት ሰጡ ከተባለበት ቀን በኋላ ስለመሞታቸው፣ የት እና መቼ እንደሞቱ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አልቀረበም።

ከዚህ መረዳት የሚቻለው ለፖሊስ ሰጡት የተባለው የምስክርነት ቃል እውነትነት የሌለው መሆኑን ነው። ምስክርነቱ የም/ኮ/ር ገ/ እግዚያብሄር ገ/መድህን ነው ተብሎ የሚታመን ቢሆን ምስክሩ ያረጋገጡት ሰላማዊ ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ለማፈን በሌሊት ተዘጋጅተው መሄዳቸውን ብቻ ነው። በትክክል የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢኖር ኖሮ በህዝብ መሃል ህጋዊ ቢሮ ከፍተው ህጋዊ የማንነት ጥያቄ ለፌደሬሽን ምክር ቤት እና ለትግራይ ክልል መንግስት በማቅረብ ላይ ያሉ ሰላማዊ ሰዎችን በሌሊት ለመያዝ የጦርነት በሚመስል ሁኔታ ዝግጅት የሚያስደርግ ምክንያት አልነበረም። የምስክሩ ቃል ነው የተባለው እንደሚያስረዳው በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጁ እና የታጠቁ ሀይሎች ለሀምሌ 5/2008 ሌሊት 10 ሰዓት ላይ መመርያ ተቀብለው እንዲያዙ በተዘረዘሩ 6 ሰዎች ቤት ሌሊት 11ሰዓት ላይ ደርሰው የተከሳሽን ቤት ከበው መያዛቸውን እና ህግ ለማስከበር ሳይሆን ለጦርነት ተዘጋጅተው መሄዳቸውን የሚያሳይ ሲሆን በሌሊት ጦር የዘመተበት ሰው ደግሞ ራሱን ለመከላከል የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ የግድ ስለሆነ ባልታሰበ ሁኔታ በሌሊት ከተከሳሽ መኖሪያ ቤት በመሄድ ተከሳሽን እንድሸበር አደረጉ እንጅ ተከሳሽን በአሸባሪነት የሚያሳይ ምስክርነት አይደለም።

የምስክሮችን ቃል ለመግለፅ አሁን ጊዜው ባይሆንም በጠቅላላ የቀረበው የሰው ሆነ የሰነድ ማስረጃ የፀጥታ ሀይሎች ከህግ ውጭ በሌሊት ከተከሳሽ መኖርያ ቤት በመሄዳቸው ምክንያት የተፈጠረ ግጭት መኖሩን እንጅ ተከሳሽ በአሸባሪነት ተግባር መሰማራታቸውን አንድም የሚያሳይ ማስረጃ የለም። ግጭት እና አሸባሪነት ደግሞ ፈፅሞ የሚያገናኛቸው ባህሪ የለም። አሸባሪነት የፖለቲካ ፣ የሀይማኖት ወይም የአይዲኦሎጂ ዓላማ ይዞ ህይወትን ለማጥፋት፣ ንብረትን ለማውደም የሚደረግ ዝግጅትና ተግባር ሲሆን ግጭት ደግሞ አሁን እየታየ ባለው ክስ በግልፅ እንደታየው አንደኛው ወገን ከህግ ውጭ ሲንቀሳቀስ ሌላኛው ወገን መብቱን ለማስጠበቅ በሚያደርገው መልስ የሚፈጠር ድንገተኛ ሁኔታ ነው። አሁንም በእኔ ላይ በተደረገው ሴራ ግጭት መፈጠሩን እንጅ አሸባሪነትን አያሳይም።

7•2 የሞቱ ሰዎች የሰጡት ቃል በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችለው ወደ ሞት እየተቃረቡ ባሉበት ወቅት እውነት ይናገራሉ ተብሎ ስለሚታመን ብቻ ነው። አሁን በማስረጃነት የቀረበው ሰነድ ግን በህጉ አላማ መሰረት እውነት ለመናገር ታስቦ በኑዛዜ መልክ የተሰጠ ሳይሆን ሞቱ የተባሉት ሰዎች በሙሉ ጤንነት ወይንም ለሞት የሚያሰጋ ምክንያት በሌለበት ጊዜ ለመርማሪ ፖሊስ ሰጥተዋል የተባለ ቃል ነው። እውነታው ይህ ከሆነ ሟቾች ተከሳሽን ለመወንጀል ሆን ብለው እና አስበው የሰጡት ቃል ስለመሆኑ የድርጊቱ አፈፃፀም በራሱ ያረጋግጣል።

ሟቾች የተባሉት ሰዎች የምስክርነት ቃላቸውን ሲሰጡ ተከሳሽ በቦታው አልነበሩም። ወይም የተከሳሽ ጠበቆች እየሰሙ የተሰጠ ቃል አይደለም። ማንኛውም ሰው ክርክሩን በግልፅ የመስማት ህገ መንግስታዊ መብት ያለው ሲሆን ተከሳሽ ወይንም ጠበቃው በሌሉበት ተሰጠ የተባለ ምስክርነት በመስቀለኛ ጥያቄ ወይም በተለያዩ የማብራሪያ ጥያቄዎች ነጥሮ ያልወጣ በመሆኑ ማስረጃው ተቀባይነት የለውም።

ከላይ በዝርዝር እንደተገለፀው እኔ እንድከሰስ ምክንያት የሆነው በህገ ወጥ መንገድ በግዴታ የተነጠቀው የወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ለመንግስት ለማቅረብ በህዝብ ተመርጨ የማንነት ጥያቄውን በህጋዊ መንገድ በህገ መንግስቱ መሰረት ይመለከተዋል ለተባለ የመንግስት አካል ሁሉ ሳቀርብ ጥያቄውን ለማፈን ሲባል ከመኖርያ ቤቴ በሌሊት ተከብቤ ጥቃት ሊገፀምብኝ ሲል ራሴን በመከላከል እና የመንግስት ባለስልጣናት በሚፈፅሙት አስተዳደራዊ በደል ከህዝብ በቀረበ ተቃውሞ ግጭት መፈጠሩን ሰነዱ ከሚያሳይ በቀር እኔም ግጭት ከመፈጠሩ ውጭ አሸባሪ ከተባለ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ጋር ተገናኝቼ ስለማላውቅ በተለይ የአሸባሪ ቡድን አባል እየተባሉ የተጠቀሱት እነ ደጀኔ ማሩ፣ እነ ሰረበ ጥሩነህ የሚባሉ ሰዎች ስለመኖራቸው ወይንም የአሸባሪ ቡድን አባል ስለመሆናቸው ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ በጊዜያዊ ግጭት ወንጀል ሊባል የሚችል ድርጊት ተፈፅሞ ከሆነም በመደበኛው የወንጀለኛ ህግ ከሚያስከስስ በስተቀር አሸባሪነት ሊሆን አይችልም።

ስለዚህ በህጋዊ መንገድ የመረጠኝን ህዝብ ማንነት ለማረጋገጥ ሳደርግ የነበረውን ጥረት ክሱም ሆነ ማስረጃው በግልፅ የሚያሳይ ሲሆን የሰነድ ማስረጃዎቹ በተከሳሽ ላይ መቅረባቸው ፍፁም ከእኔ ተግባር ጋር የሚገናኙ ስላልሆኑ በብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ተገኘ የተባለው ሪፖርትም ከላይ በሰፊው እንደተገለፀው የሀገሪቱን ህገ መንግስት፣ የዓለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶችን ቃል ኪዳን ስምምነት እንዲሁም የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ራሱን በመጣስ የዜጎችን የግል ሚስጥር ለመበርበር ህገ መንግስቱን በመጣስ የተደነገገውን (የአዋጁን አንቀፅ 14) በመጣስ በህገ ወጥ መንገድ የተገኘ በመሆኑ ይህም በሪፖርት መልክ ከመቅረቡ ውጭ ሪፖርቱ የተዘጋጀበት የድምፅ ቅጅ ከሌለ ሪፖርቱን ያዘጋጀው የብሔራዊ ደህንነት አገልግሎት ፅ/ቤት አቋም ስለሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርዓት ቁጥር 146 መሰረት ስለምቃወማቸው በብይኑ ላይ በማንኛውም መለኪያ በማስረጃነት ተቆጥረው ለአሸባሪነት ወንጀል ሚዛን ውስጥ እንዳይገቡ በትህትና አመለክታለሁ!<sp

LEAVE A REPLY