አቶ በቀለ ገርባ በዋስ እንዲፈቱ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ

አቶ በቀለ ገርባ በዋስ እንዲፈቱ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት በወንጀል ተከሰው ጉዳያቸው ሲታይ የነበረው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ባቀረቡት “የዋስትና የይግባኝ” ጥያቄ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታውን ከተመለከ በሗላ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ወጥተው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ በማለት ዛሬ ብይን ሰጠ። አቶ በቀለ ገርባ ያቀረቧቸው የመከላከያ ምስክሮች የማሰማት ሂደት እንደሚቀጥልም ፍ/ቤቱ በሰጠው ብይን አብሮ መጥቀሱም ታውቋል።

አቶ በቀለ ገርባ በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ ከተመሰረተባቸው የሽብር ወንጀል ነጻ ተብለው አንቀጽ ተቀይሮ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አንቀጽ 257 (ሀ) የተመለከተውን የህግ ክፍል መተላለፍ እንዲከላከሉ የተበየነባቸውና በከፍተኛ ፍ/ቤት የዋስትና መብታቸውን ተነፍገው “የዋስታና ይግባኝ” ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ 1ኛ ወንጀል ችሎትም የፌዴራል ፍርድ ቤት ዋስትና ለመነፈግ ምክንያት ናቸው የተባሉት “በዋስ ቢወጣ ህዝብን የማነሳሳት ወንጀል ሊፈጽም ይችላል የሚለውና ከሀገር ሊወጣና የዋስትና ግዴታውን አክብሮ ላይቀርብ ይችላል” የሚሉት ሁለት መከራከሪያዎች፤ አቶ በቀለ ከዚህ በፊትም ከሀገር ወጥተው የተመለሱ እንዲሁም በዋስ ቢወጡ የማነሳሳት ወንጀል ሊፈጽሙ ይችላሉ የሚለውም በማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ የዋስትና መብት ማግኘት እንዳስቻላቸው ታውቋል።

አቶ በቀለ ገርባ ከ2008 ዓ.ም ጀምረው በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን ዛሬ ከሰዓት በሗላ ከእስር ሊለቀቁ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

LEAVE A REPLY